ኢትዮጵያ ትሴብሕ ወትዜምር ግብፅ……
ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ማለደ ዋስይሁን
የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ እንደ ምሳሌ
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን ዕረፍት ተከትሎ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ስድስት ወራት ያህል ትኩረት የሰጠችው ተተኪ ፓትርያርኳን ለመምረጥ አስፈላጊውን ሁሉ መፈጸም ላይ ነበር፡፡ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወዲያ ውኑ ባደረገው ጉባኤ ለቤተ ክርስቲ ያኒቱ ዐቃቤ መንበር መሾም ሲሆን ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ዘቤሔይራ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው ተሰይ መዋል፡፡ ከዚያ ተከትሎ ግብፅ እግዚአብሔር ያዘዘውን ፓትርያርኳን ለማግኘት ተገቢ የምትለውን ቀኖናዊ እርምጃዎች ሁሉ መውሰዷን ቀጠለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የፓትርያርክ ምርጫ ሂደቱን ያከናወነችው እ.ኤ.አ በ1957 በወጣው ድንጋጌ መሠረት ነው፡፡
የመራጮች ሁኔታ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን የሚተካውን ፓትርያርክ ለመምረጥ ዕድል እንዲሰጣቸው የታሰቡት መራጮች ቁጥር ከ2594 ያላነሰ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ስማቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ እንዲመርጡ የታጩት 2405 ነበሩ፡፡ ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ በ1971 ዓ.ም ሲመረጡ የተሳትፎ ዕድል ተሰጥቷቸው የነበሩት መራጮች ቁጥር 1500 ነበር፡፡ ከዚያ አንጻር ሲታይ የአሁኑ የመራጮች ቁጥር በአንድ ሺሕ ያህል ብልጫ አለው፡፡ የዚህ ምክንያት በአርባ ዓመቱ የቅዱስነታቸው የአቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዘመን የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ዕድገትና መስፋፋት በማሳየቷ ከብዙ ከተቋቋሙ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት የተወከሉ መራጮች በመታከላቸው ነው፡፡
የእነዚህ መራጮችም ዝርዝር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር /እ.ኤ.አ/ ሐምሌ 23/ 2012 በሦስት የሀገሪቱ ጋዜጦች ይፋ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ምእመናን እንዲያገኙት ይፋ የተደረገ ሲሆን እስከ ነሐሴ 6 ድረስም ለመራጭነት በታጩት ሰዎች ማንነት ላይ የሚሰጡ አስተያየቶች ካሉ ለምርመራ እስከ ነሐሴ 6 ጊዜ ተሰጥቷል፡፡
በአጠቃላይ ሲታዩ 93 ጳጳሳት 18 ሜትሮፓሊታኖች፣ 34 መነኮሳት ተካተዋል፡፡ 1380 ምእመናን፣ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋዜጠኞች ኅብረት (Journalists’ Syndicate) አባል የሆኑ 21 ጋዜጠኞች፣ ከእነዚህ በተጨማሪም 4 የቀድሞና የአሁኑ የግብፅ ክርስቲያን የመንግሥት ሚንስትሮች፣ ክርስቲያን የፓርላማ አባላት፣ እና 27ቱ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት አባላት ተካተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 5 ተወካዮች፣ ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ደግሞ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ አባቶች ተወክለው እንደሚገኙ የወጣው ዝርዝር ያመለክታል፡፡
ከተካተቱት መራጮች 139 ሴቶች እና 29 ሴት መነኮሳት ይገኙበታል፡፡ በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታይቶ በማይታ ወቅ ሁኔታም ከመራጮቹ አንድ አምስተኛው መቀመጫቸው ከግብፅ ያልሆኑ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ሆነው ታይተዋል፡፡ በመራጮች ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ይዞ በትክክል ያሉና የሌሉትን እንዲከታተሉ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ /Morcos/ ዘሾብራ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ተሰይመዋል፡፡
አሁን ተግባራዊ የተደረገው የምርጫ አካሔድ ከዚህ ቀደም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ስድተኛና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ሲመረጡ ተግባራዊ የሆነ ነበር፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ሥራውን የጀመረው እ.ኤ.አ ጥቅምት 4 ቀን ነው፡፡ ሥራውንም የዐሥራ ሰባቱን ዕጩዎች ማንነት መለየት፣ ፋይልና መረጃዎችን አገላብጦ እስከ ኅዳር አጋማሽ ድረስ ለመራጮች ድምፅ አሰጣጥ የሚቀርቡትን ዕጩዎች ማቅረብ ነው፡፡
የጾምና የጸሎት ጊዜ
የምርጫው ሂደት ያለ፤ እግዚአብሔር ረድኤት አርኪ እንደማይሆን በማመን መደረግ የሚገባቸው መንፈሳዊ ተግባራት ሁሉ ተከናውነዋል፡፡ ዋናውም ጾም ጸሎት በመሆኑ እግዚአብሔር የምርጫውን ሂደት ሁሉ እንዲመራ እርሱን መማጸን የማይረሳ ተግባር ነበር፡፡ በዚያም መሠረት አርብ እና ረቡዕ በሚጾሙበት ሥርዓት የሚጾሙ ሦስት የጾም ጊዜያት ነበሩ፡፡
የመጀመሪያው በዕጩዎች ላይ የቀረቡ አስተያየቶችን ለመመርመርና ከሰባት እስከ አምስት የሚደርሱትን ለይቶ ለማውጣት ከሚከናወነው ተግባር በፊት የሚሆንና እ.ኤ.አ ከጥቅምት 1 እስከ 3 እንዲደረግ የታቀደውና የተከናወነው ነበር፡፡ ሁለተኛው የጾም ጊዜ ደግሞ ሦስቱን አባቶች በመራጮች ድምፅ ከሚለዩበት ጊዜ በፊት ከኅዳር 19 እስከ 21 እንዲደረግ የታቀደውና የተከናወነው ነበር፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የመሰዊያው ዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ከመከናወኑ በፊት ከኅዳር 26 እስከ 28 እንዲደረግ የታቀደውና የተከናወነው ነበር፡፡
ዐሥራ ሰባቱ ዕጩዎች
የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴው ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በተቀበሩበት ዋዲኤል ናትሮን በሚገኘው ቅዱስ ቢሾይ ገዳም በመጓዝ ወደ ምርጫው ሂደት የሚገቡ ዕጩዎችን ለመምረጥ ጥሯል፤ በዚያ በነበረው የሁለት ሳምንት ቆይታ ባዘጋጀው የምርጫ መሥፈርትም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ይገባቸዋል ያላቸውን ዐሥራ ሰባት ዕጩዎች በማዘጋጀት ያላቸውን የተለያዩ ጸጋና ክህሎቶች ሲመረምር ቆይቷል፡፡ ከዚያም ዕጩዎቹ ይፋ ከተደረጉ በኋላ በእነርሱ ላይ የሚቀርቡ አስተያየትና አቤቱታዎችን ሲቀበል ሲመረምር፣ ሲወስን ቆይቷል፡፡ እነዚህ የቅሬታና የተቃውሞ አስተያየቶች የሚቀርቡት ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲመርጡ ይፋ ካደረጋቸው መራጮች ብቻ ነበር፡፡
ለእነዚህም የተቃውሞ አቀራረቦች የዐሥራ አምስት ቀናት ጊዜ ተሰጥቷል፡፡ እነዚህም ቀናት ከጥቅምት 15 እስከ 30/2012 ያሉት ነበሩ፡፡ በግብፅ ውስጥ ካሉ ወገኖች የሚቀርቡ የተቃውሞ አስተያየቶች ለዕጩ አቅራቢ ኮሚቴው ጽሕፈት ቤት በግል በታሸገ ፖስታ እንዲቀርብ ታዟል፡፡ ከግብፅ ውጪ ካሉ ወገኖች ደግሞ በዲ ኤች ኤል ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ በቀጥታ እንዲቀርብ ታዞ ነበር፡፡ በፖስታ የሚቀርቡ ሁሉም መልእክቶች እ.ኤ.አ ከጥቅምት 30 በፊት መላካቸውን በላያቸው ያለው ማኅተም ማመላከት ይኖርበታል፡፡
ኮሚቴውም የቀረቡትን አስተያየቶች ለመመርመር ከጥቅምት 4 ጀምሮ እንዲያከናውን ዕቅድ የወጣለት ሲሆን ያለፉትን ዕጩዎችም በኅዳር ወር የመጀመሪያና ሁለተኛ ሳምንት ውስጥ ይፋ እንዲያደርግ ሆኗል፡፡ ከእነዚህም መካከል ከ5-7 የሚደርሱ ዕጩዎችን ለይቶ ለመራጮች የድምፅ አሰጣጥ ውሳኔ ያቀርባል፡፡
በዚያም አካሔድ መሠረት ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ የዐሥራ ሰባቱን ዕጩዎች ዝርዝር ይፋ አደረጉ፡፡ ከዕጩዎቹ ሰባቱ ጳጳሳት፣ ዐሥሩ ደግሞ መነኮሳት ነበሩ፡፡ ጳጳሳቱ የሚከ ተሉት ናቸው፡፡
-
ብፁዕ አቡነ ቢሾይ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊና የዳሜይታ ሜትሮፓሊታን አንዱ ሲሆኑ በምሕንድስና ሙያ የተመረቁ ናቸው፡፡
-
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የማኅበራዊ አገልግሎት ጉዳዮችን እንዲከታተሉ የተሰየሙ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ ሣልሳዊ ጸሐፊ ነበሩ፡፡ የሕክምና ትምህርትም የተከታተሉ ነበሩ፡፡
-
ብፁዕ አቡነ ቡትሮስ የብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ልዩ ጸሐፊ ነበሩ፡፡ በግብርና ሳይንስ ዲግሪያቸውን ያገኙ ናቸው፡፡
-
ብፁዕ አቡነ ታውድሮስ የኤል ቤሔርያ ጠቅላይ ጳጳስ የሆኑና በፋርማሲ ትምህርት ከአሌክሳ ንደርያ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስም አባል ናቸው፡፡
-
ብፁዕ አቡነ ራፋኤል የማእከላዊ ካይሮና ሄሊፓሊስ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ናቸው፡፡ የሕክምና ሳይንስ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
-
ብፁዕ አቡነ ባቭኖቲየስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የሳማልአውት እና የታሃኤል አሜኖ ጳጳስ ሲሆኑ የሕክምና ሳይንስ ምሩቅ ናቸው፡፡
-
ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሚላን ጳጳስና የምሕንድስና ሙያ ምሩቅ ናቸው፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ከዐሥራ ሰባቱ ዕጩዎች የጵጵስና መዓርግ ያላቸው ናቸው፡፡ የዐሥሩ መነኮሳትን ማንነት ስናይ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡
- አባ አንስታሲ በገዳም ያሉ መነኩሴ እና በንግድ ሥራ ሙያ ባለዲግሪ የሆኑ፣
- አባ ማክሲሞስ በገዳም ያሉ መነኩሴና በእርሻ ሙያ ዲግሪያቸውን ያገኙ፣ በሥዕላት ዕድሳትና ጥገና ሙያ የዲፕሎማም ባለቤት የሆኑ፣
- አባ ራፋኤል በገዳም የሚያገለግሉ መነኩሴና በሕግ ሙያ የተመረቁ፣
- አባ ቤጉል በገዳም የሚያገለግሉ መነኩሴና በሜካኒካል ምሕንድስና ዲግሪያቸውን ያገኙ፣
- አባ ሲኖዳ በገዳም የሚያገለግሉ መነኩሴ በሃይማኖት ጥናት ዲግሪያቸውን ያገኙ፤
- አባ ቢሾይ በገዳም የሚያገለግሉ መነኩሴና በግብርና ዲግሪያቸውን ያገኙ፤
- አባ ሳዊሪስ በገዳም የሚያገለግሉ መነኩሴና በሃይማኖት ጥናት ዲግሪ ያገኙ፣
- አባ ጳኩሚስ በገዳም የሚያገለግሉ በሳይንስ እና በትምህ ርት ሙያ ዲግሪ ያላቸው፤
- አባ ዳንኤል በገዳም የሚያገለግሉ በሳይንስ፣ በትምህርት፣ በኮፕቲክ ጥናት የዲግሪዎች ባለቤት የሆኑ፣
-
አባ ሴራፊም በገዳም የሚያገለግሉ በሳይንስ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡
በ1957 የወጣው ሕግ የሚያመለክተው ለፓትርያርክናት ዕጩ የሚቀርቡ አባቶች ዕድሜ ከአርባ የማያንስና ለዐሥራ አምስት ዓመታት በገዳማዊ ሕይወትና አገልግሎት ውስጥ ማለፍ እንደሚኖርባቸው ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ዕጩዎች ይህንን ያሟሉ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዐሥራ ሰባቱም እጩዎች ከዓለሙ ጋር ለመግባባትና ለመቅረብ የሚያስችሉ፣ ሀገራቸውንም ለማገልገል ማኅበራዊ አገልግሎቶችንና የበጐ አድራጐት ተግባራትን ማስፋፋት በሚችሉበት ሙያ ከ “ዘመናዊ” ትምህርት ቤቶች ተመርቀዋል፡፡ በገዳም አገልግሎት የተጉ፣ ምስክርነትም ያገኙ፣ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ሌላውም የሀገሪቱ ማኅበረሰብ ዕውቅና የሰጣቸውን ተግባራት ለማከናወን እንደሚጥሩ የሚታመንባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ሀገረ ስብከት ያላቸው ዕጩዎች በተለይም ሜትሮ ፓሊታን ቢሾይ ዘዳሜታ፣ ብፁዕ አቡነ ባቭኖቲያስ ዘሳማልአውት ወታሃኤል አሜዳ፣ እና ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ዘሚላን መታጨት አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡
የአስመራጭ ኮሚቴው የመለየት ሥራ
ኮሚቴው ካቀረባቸው ዐሥራ ሰባት ዕጩዎች ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ ዕጩዎችን አወዳድሮ መለየትና ለመራጮች ድምፅ አሰጣጥ ማቅረብ ይገባው ነበር፡፡ በመሆ ኑም ዐሥራ ሰባቱን ዕጩዎች ይፋ ከተደረጉ በኋላ በዕጩዎች ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን፣ አቤቱታዎችን፣ የተለያዩ ወገኖችን አ
ስተያየት በሃይማኖት ሚዛን መመርመር ወሳኙ ተግባር ነበር፡፡ በመለየት የሥራ ሂደት የጤንነት ሁኔታ፣ የዕድሜ ሁኔታ፣ በጽሑፍ ያቀረቧቸው ሥራዎች፣ መልካም ስማቸው፣ በማኀበረሰቡ ያላቸው ተቀባይነትና ታማኝነት፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የነበራቸው በጐ ተጽዕኖና የፈጸሟቸው ተግባራት፣ ነገሮችን የሚያዩበት ሚዛናዊነት፣ በተለያዩ መድረኮች ያደረጓቸው የተለያዩ ገለጻዎች ሁሉ ተመርምረዋል፡፡
እጅግ አድካሚ፣ ረጅም ሂደት የነበረው፣ የኮሚቴውን ታማኝነትና ኅብረት የሚጠይቅ፣ ግልጽነት የሰፈነበት፣ ከውስጥም ከውጪም ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁኔታዎች ከግምት ያስገባ የመለየት ሥራ ተከናውኗል፡፡ በዩናይትድ ኪንግደም የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጳጳስ እንደ ብፁዕ አቡነ አንጌሎስ ገለጻ መረጣው በተርታ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሥርዓት ብቻ የተካሔደ ሳይሆን የጋራ ጸሎትና በእግዚአብሔር ላይ ያለ እምነትን ቅድሚያ የሚሰጥ አካሔድ ነበር፡፡
ከዚህ ሂደት በኋላ አምስት ዕጩዎች መለየታቸውን ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ይፋ አደረጉ፡፡ ከእነዚህም ሁለቱ ጳጳሳት ሁለቱ መነኰሳት መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ አምስቱ ዕጩዎችም አባ ራፋኤል፣ ብፁዕ አቡነ ራፋኤል፣ ብፁዕ አቡነ ታውድሮስ፣ አባ ሴራፊም እና አባ ጳኩሚስ ዘአልሲሪያን ናቸው፡፡
በዚህ ሒደትም ሜትሮፓሊታን ቢሾይ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ፣ ብፁዕ አቡነ ቡትሮስን የመሳሰሉ የተጠበቁ ታላላቅ አባቶች በዝርዝር ውስጥ ተካተው አልተገኙም፡፡ ጊዜው ግብፅ ከነበረችበት ውጥረት አንጻር የኮፕቲክ ማኀበረሰቡን ፍላጐት በሀገር ጉዳዮች በብቃት ማስጠበቅ እንዲቻል የፓትርያርክ ምርጫው እንዲፋጠን ግፊት ይደረግ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በአገልግሎት፣ በአመራርም በግንኙነት ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ታላቅነት ከግብፅና ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ወዳጆች ሁሉ ይሰጣቸው የነበረው ከበሬታ የቀጣዩን ፓትርያርክ የመለየት የምርጫ ሒደት እጅግ በጥንቃቄ የተሞላና አሳሳቢ አድርጐት ቆይቷል፡፡
የምርጫው ክንውን
እ.ኤ.አ ከኅዳር 19-21 ቀን 2012 ለሦስት ቀናት ጾም የታወጀ ሲሆን ከዚያ በኋላ በ24/2012 መራጮች በአስመራጭ ኮሚቴው ከተለዩት ከአም ስቱ ዕጩዎች ሦስቱን ለመለየት ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ የመረጡትም እንዲመርጡ ተመዝግበው ከነበሩት 2405 መራጮች መካከል 2256ቱ ማለትም 93.3 /ዘጠና ሦስት ነጥብ ሦስት/ ፐርሰንቱ ነበሩ፡፡ የቀሩት በማጣራት ሂደትና በተለያዩ ምክንያቶች የቀሩ ናቸው፡፡
መራጮችም ከቀረቡላቸው አምስት ዕጩዎች ሦስቱን ብቻ የመምረጥ ሓላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በግብፅ ያሉ መራጮች በተቆረጠው ቀን በግል ተገኝተው እንዲመርጡ ታቅዶ ነበር፡፡ ከግብፅ ውጪ ያሉት ደግሞ ወደ ግብፅ ተጉዘው በቦታው ተገኝተው እንዲመርጡ፤ አስገዳጅ ሁኔታዎች ካጋጠሙ ግን ባሉበት አስቀድመው መምረጥ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተመልክቶ ነበር፡፡ የምርጫው ወረቀት በዕጩነት የቀረቡትን የአምስቱን አባቶች ስም የያዘ ነበር፡፡
ኅዳር 24 ከተከናወነው ምርጫ በኋላ በውጤቱ ለዕጣ ሥርዓቱ የሚቀ ርቡ አባቶች ተለይተዋል፡፡ አጠቃላይ ውጤቱም ሲታይ፡-
- ብፁዕ አቡነ ራፋኤል- 1980
- ብፁዕ አቡነ ታውድሮስ- 1623
- አባ ራፋኤል አቫ ሚና- 1530
- አባ ሴራፊም አል ሶሪያ-ኒ 680
- አባ ጳኩሚስ አል ሶሪያኒ- 305 ድምፅ አግኝተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ለዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱ ያለፉት አባቶች ከፍተኛ ድምፅ ያገኙት ሦስቱ ብፁዕ አቡነ ራፋኤል ብፁዕ አቡነ ታውድሮስና አባ ራፋኤል ነበሩ፡፡
ብፁዕ አቡነ ራፋኤል ከፍተኛውን ድምፅ ቁጥር ያገኙ ሲሆን ጠንካራ ሰብእና፣ ታላቅ ክብርና ዝና የነበራቸውና አወዛጋቢ ከሆኑ ነገሮች አንጻር አሉታዊ አስተያየት ያልተሰጠባቸው ነበሩ፡፡ በማእከላዊ ካይሮ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት ረዳት ጳጳስ ሆነው እያገለገሉ ያሉና በተለይ ከወጣቶች ጋርና ከወጣቶች ጉዳይ ጳጳስ ከሆኑት አቡነ ሙሳ ጋር ቅርበት
ያላቸው ነበሩ፡፡ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ ጋር ቅርበት ያላቸውና ቅድምና ያላቸው በመሆኑ “ተወዳጁ አባት” ተብለው ይጠራሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሰዎች ብቻ ሳይሆን የእግዚብሔርም ፈቃድ መኖር አለበትና ፍፃሜው በዕጣ አወጣጡ ሥርዓት ላይ ሆነ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታውድሮስ ዳግማዊ
እ.ኤ.አ በኅዳር 4/2012 በዕለተ እሑድ ከተደረገው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት በኋላ የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያ ርኳን ይፋ አድርጋለች፡፡ በዚህም መሠረት ለዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱ ተለይተው ከነበሩት ሦስቱ አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ታውድሮስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባት እንዲሆኑ መመ ረጣቸው ታውቋል፡፡
በዕለቱ እጅግ በርካታ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ የሆኑ ታዋቂ ሰዎች ባለሥልጣናት ከሕፃን እስከ አዋቂ ምእመናን በተገኙበት ካይሮ በሚገኘው ታላቁ የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ሥርዓተ ቅዳሴ ተከናውኗል፡፡ በቀጥታ በአልጀዚራ የአረብኛ ሥርዓተ ቅዳሴ የግብፅ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እርሱ ለቤተ ክርስቲያናቸው አባት አድርጐ እንዲሰጣቸው ጽኑ ተማጽኖ ላይ እንደነበሩ ከብፁዓን አባቶች ጀምሮ በሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ፊት ይነበብ የነበረው ስሜት ጠቋሚ ነበር፡፡
ሥርዓተ ቅዳሴውም እንዳበቃ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ወደ ዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱ መሸጋገራቸውን ግልጽ አደረጉ፡፡ ያንንም ተከትሎ ዐሥራ ሁለት ሕፃናት ወደ ብፁዓን አባቶች ቀርበው ጸሎት ተደረገላቸው፡፡ ከእነዚህም ለፓትርያርክነት የተመረጠውን አባት ዕጣ ለይቶ የሚያቀርበውን ሕፃን ከእነርሱም መካከል መለየት ይገባ ነበርና፡፡ ለሕፃናቱ ዕጣ ወጥቶላቸዋል፡፡ ለዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት የተመረጠው ሕፃን ቢሾይ ሆነና ወደ ዐቃቤ መንበሩ ቀረበ፡፡ በእርሳቸውም ጸሎት ከተደረገለት በኋላ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ በላዩ ቅዱሳት ሥዕላት በተሠራበት ጨርቅ የሕፃኑን ዐይኖች ሸፈኑ፡፡ ከዚያም ዕጣው ወዳለበት አቀረቡት፡፡ ታሽጎ በታቦተ ምስዋዕ ተቀምጦ ጸሎት ሲደረግበት ከነበረ የፕላስቲክ የዕጣ ጽዋ ውስጥ ለይቶ አን ዱን ዕጣ ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ አቀረበ፡፡ ያን በጥብቅ የታሸገ ዕጣ ፈትተው ፊት ለፊት ለሚጠባበቀው የግብፅ ሕዝበ ክርስቲያን ከፍ አድርገው አሳዩ “ታውድሮስ” ተብሎ በዓረብኛ ፊደላት የተጻፈው ስም በጉልህ ይታይ ነበር፡፡ በካቴድራሉ ያለው ሕዝብ የደስታ ጩኸት አስተጋባ፡፡ ዐቃቤ መንበሩ በጉልህ ድምፅ የምስጋና ቃልን በዜማ ማሰማት ቀጠሉ፡፡ ሁሉም የእርሳቸውን ተከትሎ የምስጋናውን ቃል መመለሱን ቀጠለ፡፡ በዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱ በሕፃን ቢሾይ ያልተነሡት ሁለት ዕጣዎች የያዙት ስም የቀሪዎቹ አባቶች መሆኑ ተረጋገጠ፡፡
ከዚያም የዓለም ሚዲያዎች ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ዋለ፡፡ ለአራት ዐሠርት ዓመታት ያህል የግብጽን ቤተ ክርስቲያን የመሯት የፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ ተተኪ ፓትርያርክ አባ ታውድሮስ መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ አባ ታዎድሮስ ከአባይ ዴልታ ሰሜናዊ ምዕራብ ላለው ለሰሜን ቤሄሪያ ግዛት ጠቅላይ ጳጳስ የነበሩና ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ለነበሩት አቡነ ጳኩሚስ ረድዕ የነበሩ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሉዐላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆነው የቅዱስ ሲኖዶሱም አባል ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1952 በማንሶራህ /Mansourah/ ልዩ ስሙ ዋኒሾቢባኪ ሱሌይማን /wagihsobhybakky Suleiman/በተባለው የግብጽ አካባቢ የተወለዱ ሲሆን አባታቸው የመስኖ መሐን ዲስ የነበሩ ሲሆን የወላጅ ቤተሰባቸው በልጅነታቸው ከማንሳራ ወደ ሾሃግ ከዚያም ወደ ዳማንሆር ተዘዋውረው ይኖሩ ነበር፡፡ አባ ታዎድሮስ ጵጵስና የተቀበሉት እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም ነው፡፡
አባ ታውድሮስ ከአሌክሳንደሪያ ዩኒቨርሲቲ በ1975 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በፋርማሲ ሙያ የመጀመሪያ ዲግሪ ያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሲንጋፖርና በዩናይትድ ኪንግደም የፋርማሲ ምህንድስና ሙያን በአግባቡ ያጠኑ ናቸው፡፡ በ1985 በእንግሊዝም የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባዘጋጀው ፊሎሺፕ ሠልጥነዋል፡፡ ከዚያም በዳማንሆር /Damanhour/ የአንድ የመድኀኒት ኩባንያ ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ በሌሎች በተለያዩ የግብፅ አካባቢዎች ባሉ የመድኀኒት ማምረቻ ኩባንያዎች በሓላፊነት ሠርተዋል፡፡ ስለዚህም ብቁ የአስተዳደር ችሎታ እንዳላቸው እየተጠቆመ ነው፡፡
አባ ታውድሮስ ለፖትርያርክነት ከታጩት አባቶች አንዱ ሆነው ወደ ዐሥራ ሰባቱ ዕጩዎች የገቡትም አሁን እስከ ፍጻሜው የእርሳቸው “ተወዳዳሪ” ሆነው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ራፋኤል ጠቁመዋቸው ነው፡፡ አባ ታውድሮስ በሕዝቡ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው በነበሩት በእኝሁ በአቡነ ራፋኤል እንደ ቅርብ ወንድም እና ባልንጀራ የሚታሰቡ ነበሩ፡፡ ከዚያም የተነሣ ለዚህ መዓርግ ሊበቁ እንደሚገባ አምነው የጠቆሟቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ ከአቡነ ራፋኤል ሌላ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ በቅርበት የሚያውቋቸውና የሚያከብሯቸውም ነበሩ፡፡ ታውድሮስ ውስብስብ የሆኑ የሥነ-መለኮት /theology/ ጉዳዮችን አብራርቶ በማቅረብ ጸጋቸውና ከወጣቶች ጋር በቅርበት በመሥራታቸው የታወቁ ናቸው፡፡
አባ ታውድሮስ በሀገር ውስጥ ባሉት ግብጻውያን ዘንድ ብዙ ቅርበትና ታዋቂነት ባይኖራቸውም በውጪ በስደት በሚኖሩ ግብጻውያን ክርስቲያኖች ዘንድ እጅግ ታዋቂና የተከበሩ መሆናቸው ይነገራል፡፡
በውጪ ባሉ አህጉረ ስብከቶች ያሉ አንዳንድ አባቶች “እርሳቸው ማለት የእግዚአብሔር ስጠታ ናቸው፤ ስለዚህ ተቀብለናቸዋል፤ ታውድሮስ /ቴዎድሮስ/ ማለትም ‹የእግዚብሔር ስጦታ› ማለት ነው! ስለእርሳቸው እግዚአብሔርን እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታውድሮስ መመረጣቸውን ተከትሎ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል፡፡ በተለይም በግብፅ ውስጥ እየተካሔደ ካለው ፖለቲካዊ ለውጥ ጋር በተያያዘ ቤተክርስቲያኒቱ ስለሚኖራት ሚና ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም ፖለቲካን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ “ቤተክርስቲ ያናችን በሀገር ደረጃ የምትጫወተው ሚና መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንጂ ፖለቲካዊ አይሆንም፤ ይህ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጠ ሚና ነው፡፡” ካሉ በኋላ አሁን በመረቀቅ ላይ ስላለው ሕገ መንግሥት በተጠየቁ ጊዜ ግን “ሕገ መንግሥቱ የሚጻፈው ከየትኛውም ሃይማኖት ወገንተኝነት በጸዳ መሆን ይገባዋል፤በሀገሪቱ ብዙኃን የሆኑትን ሙስሊሞችን ፍላጎት ብቻ የሚያስጠብቅ ማንኛውንም ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ ቤተ ክርስቲያን ትቃወማለች” ብለዋል፡፡ አሁን ያለውንም የግብጽ ፖለቲካ ከግምት አስገብተው ባደረባቸው ፍርሃት ምክን ያት ስለሚሰደዱ ኮፕቶች ተጠይቀው ሲመልሱ “ይህ የየግለሰቦቹ ውሳኔ ነው፤ ነገር ግን ግብጽ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኖረባት ውድ ሀገራችን ናት፡፡ መንግሥትም ለሙስሊሙም ለክርስቲያኑም ለዜጋ ውም ሁሉ እኩል ጥበቃ ሊሰጥ ይገባል፡፡” ማለታቸውን ተገልጿል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታውድሮስ ዳግማዊ /ካልዓይ/ በታላቅ ሥነ ሥርዓት ሲመተ ፓትርያርክ ተፈጽሞላቸው 118ኛው ፓትርያርክ ሆነው በመንበረ ማርቆስ እደሚቀመጡ ተገልጿል፡፡
አባ ታውድሮስ በዐረቡ ዓለም ሰፊ፤ ነገር ግን ንዑስ /minority/ የክርስቲያን ማኀበረሰብ የሆኑትን የግብጽ ክርስቲያኖችን ለመምራት የተመረጡበት ጊዜ የግብፅ ፓለቲካ በተጋጋለበትና ከፍተኛ ጥንቃቄና ንቃት በሚጠይቅበት ወቅት በመሆኑ የወሰዱት ሓላፊነት ከባድ መሆኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አመልክተዋል፡፡
ይህንን የአባ ታውድሮስን የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክና የእስክንድርያ ፖፕ ሆነው መመረጣቸውን በርካታ የግብፅ ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች በይሁንታ ተቀብለውታል፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ሚንስትሩን ሂሻም ካንዲልን የቀደማቸው አልነበረም፡፡ ለአዲሱ ተመራጭ ፓትርያርክ “እንኳን ደስ አለዎ” ብለዋል፡፡ የጦር ሠራዊቱ አባላትና መሪዎችም እንዲሁ መልካም የአመራር ዘመን ተመኝተውላቸዋል፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች ጠቅላይ መሪ ሞሐመድ ባዴ በተመሳሳይ መልካም የአስተዳደር ጊዜን ተመኝተዋል፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች ለነጻነትና ፍትኅ ፓርቲ /FJP/ በበኩሉ “ይህንን ምርጫ በበጎና በአድናቆት የምንመለከተው ነው፤ ከእኝህ ከአዲሱ የወንድሞቻችን የኮፕቶች መሪ ጋር ዲሞክራሲ፣ ፍትኅና እኩልነትን ለማስፋፋት አብረን እንሠራለን ሲል ያለውን በጎ አቀባበል አመልክቷል፡፡
ባለፈው ምርጫ ተወዳዳሪ ዕጩ የነበሩት ካሊድ አሊና አህመድ ሻፊቅም መልካም አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡ በተለይ አሕመድ ሻፊቅ “ያለፉት አባት ፖፕ ሺኖዳ የአመራር ጊዜ መልካም ትዝታዎችን ጥሎብን አል ፏል፤ ለአባ ታውድሮስም ስኬትን እመኛለሁ” ብለዋል፡፡ ታዋቂው የዓለም አቀፉ የኔኩሌር ኢነርጂ ተቆጣጣሪ ሞሐመድ አልባራዴ፣ የአረብ ሊጉ አሚር ሙሳ ተመሳሳይ አዎንታዊ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
አባ ታውድሮስ በምርጫው ከተለዩ በኋላ በዓለ ሢመቱ እስከሚፈጸም ዋዲ አል ናትሮን በሚገኘው በአባ ቢሾይ ገዳም ቆይተዋል፡፡ ከዚያም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታውድሮስ ዳግማዊ /ካልዓይ/ ኅዳር 18 2012 በታላቁ የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል በታላቅ ሥነ ሥርዓት ሲመተ ፓትርያርክ ተፈጽሞላቸው 118ኛው ፓትርያርክ ሆነው በመንበረ ማርቆስ መቀመጣቸው ተገልጿል፡፡
በዓለ ሢመቱም ሚትሮፖሊታን ጳኩሚስ በሚመሩት ሥርዓተ ጸሎት ተከናውኗል፡፡ ሥርዓቱ በሚያዘው መሠረትም ታውድሮስ የፖፑን አዲስ ሓላፊነቶችና የመሪነት ሚና የሚያመለክት ትልቅ ትእምርታዊ ቁልፍ ይዘው ሚትሮፖሊታኖችን፣ ጳጳሳትንና ብፁዓን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን ሁሉ ከኋላ አስከትለው ወደ ካቴድራሉ ገብተዋል፡፡
ታውድሮስ በአገልግሎት ጊዜ አዲስ ነጭ ልብሰ ተክህኖ /tonia/ ለብሰው ሥርዓተ ሢመቱ ተፈጽሞላቸዋል፡፡ የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ፖፑን ዐሥራ ሦስተኛ ሐዋርያ እንደሆኑ አድርጋ ታስባለችና የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሥዕል የታተመበት ወርቃማ ሞጣሂት ደርበዋል፡፡ ከዚያም የፖፑን አክሊል ደፍተው በመንበረ ማርቆስ ተቀምጠዋል፡፡ ከበዓለ ሢመቱም በኋላ ተሿሚው ፖፕ ከዋና ዋና በዓላት ቀናት በስተቀር ለአንድ ዓመት እንደሚጾሙ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህም ፖፑ “በእኩዮች መካከል በኩር” /the first among equals/ ሆኖ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ ሆነው ያገለግላሉ፡፡
ለበዓለ ሢመቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሂሻም ቃንዲል እና እርሳቸው የሚወክሏቸው ሌሎች ተጨማሪ ሚንስትሮችም ተጋብዘው ተገኝተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሙርሲ የመገኘታቸው ነገር ግን አጠራጣሪ ሆኖ የቆየ ሲሆን እንደታሰበውም ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡
ፓትርያርኳን ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ የሆኑና በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የሚመራ የልዑካን ቡድን በእዚያ የተገኘ ሲሆን በሥርዓተ ሢመቱም በቀጥታ ተሳትፎ እንደነበራቸው አልጀዚራ የአረብኛ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር በሰጠው ሽፋን የተገለጸ ሆኗል፡፡ የልዑካን ቡድኑ አባላት በዚያ መገኘታቸው ጠቃሚ የምርጫ ሥርዓቱን ተሞክሮዎች ማወቅና ማየት እንደሚያስችላቸው ይታመናል፡፡