ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ
ግንቦት ፲፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ፣ የዜማ ደራሲና ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ድንቅ ተጋድሎን ፈጽሞ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም የገባበት ዕለት ግንቦት ፲፩ የከበረች እንደመሆኗ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡
ቅዱስ ያሬድ የተወለደው ሚያዝያ ፭ ቀን በ፭፻፭ ዓ.ም በአክሱም ከተማ ነው፡፡ አባቱ አብዩድ ወይም ይስሐቅ ይባላል፤ እናቱ ደግሞ ክሪስቲና ወይም ታውክልያ ትባላለች። አባቱ የአክሱም ጽዮን ቄሰ ገበዝ ነበር፡፡ የሞተው ቅዱስ ያሬድ በተወለደ በሰባት ዓመቱ ነበር፡፡ ያሬድ ሰባት ዓመት ሲሆነው አባቱ ስለ ሞቱበት እናቱ ትምህርት ቤት ለማስገባት ወደ አጎቱ መምህር ጌዲዮን ጋር ወሰደችው፡፡ አባ ጌድዮንም በአክሱም ቤተ ቀጢን (ቤተ ጉባኤ) መምህር ነበሩ፡፡ ያሬድ ያኔ በትምህርቱ የሚያሳየው ውጤት ደካማ ስለነበር ከሌሎች ሕፃናት ጋር ሊወዳደር አልቻለም፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ያሬድ መዝሙረ ዳዊት በሚማርበት ጊዜ አጎቱ ይቆጣጠረው ነበር፡፡ ይህን መታገሥ ተስኖት ተስፋ ቆርጦ ከአክሱም ከተማ ወጥቶ ወደ እናቱ መንደር ማይኪራህ ወደ ምትባል ቦታ ሄዶ ተደበቀ፤ ያም ቦታ የቀዳማዊ ምኒልክ መቃብር ቦታ ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድም ወደ አንዲት ዛፍ ሥር ተጠግቶ ዐርፎ እያለ አንዲት ትል የዛፍ ፍሬ ለመብላት ዛፉ ላይ ለመውጣት ስድስት ጊዜ ሲወጣና ሲወርድ ከቆያ በኋላ በሰባተኛው ከዛፉ ላይ ወጥቶ የዛፉን ፍሬ ሲበላ አየ፡፡ ታደሰ ዓለማየሁ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ቅዱስ ያሬድ›› በሚለው መጽሐፉ ‹‹አንድ ትል የዛፉን ፍሬ ለመመገብ ፈልጎ ወደ ላይ እየወጣና እየወደቀ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በሰባተኛው ጊዜ ወጥቶ ፍሬዋን ሲመገብ አይቶ ቅዱስ ያሬድም ትሉ ተስፋ ሳይቆርጥ በከፍተኛ ትጋት ከዓላማው ሳይናወጥ ከብዙ ድካምና ጥረት በኃላ ያሰበው እንደተፈጸመለት ተመልክቶ ‹‹ሰውነቴ ሆይ ግርፋትን ለምን አትታገስም፤ መከራንስ ለምን አትቀበልም›› ብሎ ሰውነቱን ከገሰጸ በኃላ ወደ መምህሩ ተመልሶ ‹‹አባቴ ሆይ ይቅርታ አድርግልኝ እንደቀድሞ አስተምረኝ›› አለው፤ ትምህርቱንም ቀጠለ፤ ጥብብም ተገለጸለት፡፡
የቅዱስ ያሬድ የጥበብ መንገድ
ቅዱስ ያሬድ ወደ አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አዘውትሮ እየሄደ ጥበብና እውቀትን እንዲገልጽለት የጌታዬ እናቱ እመቤቴ ሆይ ዓይነ ልቦናዬን ያበራልኝ ዘንድ ለምኝልኝ›› እያለ ይጸልይ ነበር፡፡ ከዚያም በአንድ ቀን መቶ ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት፣ መኃልየ ነቢያት፣ መኃልይ መኃልየ ዘሰሎሞን እና ትርጓሜ መጻሕፍት ብሉያትና ሐዲሳትን አወቀ፡፡ በዚያ ዘመን ድምጹን ከፍ አድርጎ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ዜማ አልነበረም፤ ቀስ ብሎ እንደ ውርድ ንባብ እያዜሙ ያመሰግኑ ነበር እንጂ፡፡ እግዚአብሔርም በያሬድ ቃልና ከፍ ባለ ዜማ መመስገን በወደደ ጊዜ ኅዳር ፭ ቀን ፭፻፳፯ ዓ.ም በኤዶም ገነት በሥላሴ አምሳል ሦስት አእዋፍን ወደ እርሱ ላከ፤ እነሱም በግእዝ፣ በዕዝል እና በአራራይ ዜማ እንደዚሁ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ ሦስቱ አእዋፍ ቅዱስ ያሬድ በቆመበት ቦታ ፊት ለፊት በአየር ላይ ቆመው መንፈስ ቅዱስ በወፍ ተመስሎ ለቅዱስ ያሬድ ዜማ ሲገልጹለት ‹‹ብፁዕ ያሬድ ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዕት አጥባት እለ ሐፀናከ፤ የተመሰገንክና የተከበርክ ያሬድ ሆይ፥ አንተን የተሸከመች ማኀፀን የተመሰገነች ናት፤ አንተን ያሳደጉ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው›› አለችው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ወደ ሰማይ ተመልክቶ እናንተ በሰው አንደበት የምትናገሩ ወፎች ከወዴት መጣችሁ›› አላቸው? ከሦስቱ አንዲቱ እንዲህ ስትል ተናገረችው፤ ‹‹ከኤዶም ገነት ወደ አንተ ተልከን ሲሆን ይኸውም ከሃያ አራቱ ካህነት ሰማይ ማሕሌትን ትማር ዘንድ ልንነግርህ መጣን›› አሉት፡፡
ከዚያም ቅዱሳን መላእክት በዜማ ወደ ሚያመሰግኑባት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም በአካል ተነጠቀ፡፡ በዚያም መላእክት ሰማያውያንና ምድራውያን ደቂቀ አዳምን የፈጠረ እግዚአብሔርን በማኅሌት በቅኔ በከፍተኛ ድምጽ ያለማቋረጥ በመንበሩ ዙሪያ ሆነው ሲያመሰግኑት በሰማ ጊዜ ካለበት ስፍራ ተነሥቶ እነርሱ ወዳሉበት ቦታ ሊገባ ወደደ ነገር ግን አልተቻለውም፡፡ ከዚያም በኋላ እነዚያ አእዋፍት ወደ እርሱ ተመልሰው ያሬድ ሆይ ‹‹የሰማኸውን አስተውለኸዋል?›› ብለው ጠየቁት “አላስተዋልሁም” ብሎ መለሰላቸው፤ እንግዲያውስ ‹‹አዲሱን የእግዚአብሔርን ምስጋና ጥራ፤ እርሱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው›› አለችው፡፡ ቅዱስ ያሬድም “ማኅሌትን በዓይነቱ ልቤ መልካምን ነገር አውጥቶ ተናገረ” እያለ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ተማረ፡፡ ቅዱስ ያሬድም የመላእክት ሥርዓታቸውን ዐይቶ፣ ማኅሌታቸውን አጥንቶ ኅዳር ፮ ቀን ፭፻፳፯ ዓ.ም በጠዋት ሦስት ሰዓት ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል፡፡
የቅዱስ ያሬድ ዜማ
ከዚያም አክሱም ከተማ ወደ ምትገኝው ወደ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በዐውደ ምሕረቱ ቆሞ ድምጹን ከፍ አድርጎ “ሃሌ ሉያ ለአብ፣ ሃሌ ሉያ ለወልድ፣ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ ብሎ በልሳነ ግእዝ አዜመ፡፡ ይህም ማለት ዓለም ሳይፈጠር ለነበረና ዓለምን አሳልፎ ለዘለዓለም ለሚኖር ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድም ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፤ ከጽዮን አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ፤ ዳግመኛም ደብተራ ኦሪትን እንዴት አድርጎ መሥራት እንዳለበት ለሙሴ አሳየው ማለት ነው፡፡” ከሰማይ እንደተመለሰ ለመጀመሪያ ጊዜ ጣዕመ ዜማውን ያሰማበት ቦታ “ሙራደ ቃል” (የቃል መውረጃ) እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም ዜማው ከሰማይ የወረደ ለመሆኑ እውነተኛ ማስረጃ ነው፡፡ ይህችንም ዜማ “አርያም” አላት፡፡ ይህም ማለት ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘች ማለት ነው፡፡ ይህንንም ዜማ ከፍ አድርጎ በሚያሰማ /በሚያዜም/ ጊዜ ሰው፣ እንስሳና አዕዋፍ ሁሉ እርሱ ወዳለበት ቦታ ተሰብስበው ከጣዕሙ የተነሣ መንፈስን የሚያድሰውን ልቡናን የሚያስደስተውንና አጥንትን የሚያለመልመውን ሰማያዊን ዜማ ይሰማሉ፡፡
የቅዱስ ያሬድ የዜማ ዓይነቶች ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም ግእዝ፣ ዕዝልና አራራይ በመባል ይጠራሉ፡፡ ሦስቱም የዜማ ዓይነቶች ምን ጊዜም ሕያዋን ሆነው በቤተ ክርስቲያን ሰፊ የአገልግሎት ድርሻ አላቸው፡፡ ሦስቱም ዜማዎች መጽሐፍት ቅዱሳዊ ምሳሌና ትርጉም አላቸው፡፡ የዜማዎቹ ሦስትነት የምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌ ሲሆኑ ለአንድ አገልግሎት /ምስጋና/ መዋላቸው ደግሞ የሥላሴን አንድነት ያስረዳል፡፡
ግእዝ፡- ማለት በመጀመሪያ የተገኘ ማለት ነው፡፡ የቃሉ ትርጓሜም ‹‹ገአዘ›› ነጻ ወጣ ማለት ሲሆን በዜማነቱ ሲተረጎም ስልቱ የቀና ርቱዕ ቀጥ ያለ ጠንካራ ማለት ይሆናል፡፡ ምሳሌነቱም የአብ ሲሆን ከዜማው ጠንካራነት የተነሣ ሊቃንቱ ደረቅ ዜማ ብለውታል፡፡
ዕዝል፡- ከግእዝ ጋር ተደርቦ ወይም ታዝሎ የሚዜም ለስላሳ ዜማ ነው፤ ዕዝል ጽኑዕ ዜማ ማለት ሲሆን በወልድ ይመስላል፤ ምክንያቱም ወልድ ጽኑዕ መከራን ተቀብሏልና፡፡
አራራይ፡- የሚያራራ የሚያሳዝንና ልብን የሚመስጥ ቀጠን ያለ ዜማ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላል፡፡ ሐዋርያትን ከበዓለ ጰንጠቆስጤ /ከበዓለ ጰራቅሊጦስ/ በኋላ ያረጋጋ፣ ያጽናና እና ጥብዓት /ጽፍረት/ የሰጣቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ (ሐዋ.፪፥፩፣ዮሐ.፲፭፥፳፮)
በዚህም መሠረት በቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው ምስጋና በሙሉ በሦስቱ የዜማ ዓይነቶች ነው፤ ከዚህ የሚወጣ ዜማ ያለው ዝማሬ በቤተ ክርስቲያን የለም፤ ቢኖርም የቤተ ክርስቲያን አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው በቤተ ክርስቲያን መዝሙር የሚያቀርበው የቅዱስ ያሬድ የዜማ ምልክቶችና ዓይነቶች ተከትሎ ነው፤ ከሦስቱም የዜማ ዓይነቶች የወጣ ዜማ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሬድ ፭ የዜማ መጻሕፍትን ማለትም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬና መዋሥዕት ደረሰ፡፡ ከደረሳቸው የዜማ መጻሕፍትም ውስጥ ትልቁ ድጓ ነው፤ በሦስትም ይከፈላል፤ የዮሐንስ አስተምህሮና ፋሲካም ይባላሉ፡፡ በንባባት ብቻ ይቀደስባቸው የነበሩትን የ፲፬ቱ ቅዳሴያት ዜማ ባለቤት ቅዱስ ያሬድ ነው፤ ዝማሬም በ፭ ይከፈላል፤ ኅብስት፣ ጽዋዕ፣ መንፈስ፣ አኮቴትና ምሥጢር ይባላል፡፡
የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች
ድጓ፡- ድጓ ማለት ስብስብ ሲሆን ስያሜውን ያገኘበት ምክንያት የዓመቱ በዓላትና የሳምንታት መዝሙራት ተሰብሰበውና ተከማችተው ስለሚገኙ ነው፡፡ ድጓ ከብሉይ፣ ከሐዲስና ከአዋልድ መጻሕፍት ስለሚጠቅስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን፣ የመላእክትን፣ የነቢያትንና የሐዋርያትን፣ የጻድቃን የሰማዕታትን ክብር ይናገራልና፡፡
ጾመ ድጓ፡- በዐቢይ ጾም ወቅት በነግህ፣ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንዲሁም በሌሊት የሚዘመር መዝሙር ነው፡፡ አጠቃላይ መጽሐፉ ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ማርያምን፣ ነገረ ቅዱሳንን፣ ነገረ መላእክት፣ ነገረ ቤተ ክርስቲያን የሚዘከር እንዲሁም የጾምን፣ የጸሎትንና የምጽዋትን ጠቃሚነት የሚያስተምር ነው፡፡
ምዕራፍ፡- ምዕራፍ ማረፊያ ማለት ነው፤ የተደረሰውም በጠለምት ነው፡፡ የምዕራፍ መጽሐፍ ይዘት የዘወትርና የጾም ምዕራፍ ተብሎ በሁለት ክፍል የተከፈለ ሲሆን የዘወትር ምዕራፍ ዓመቱ ሳይጠብቅ በዓመቱ ውስጥ ባሉት ሳምንታትና በዓላት ወቅቱን እየጠበቀ በአገልግሎት ላይ የሚውል ነው፡፡ የጾም ምዕራፍ የሚባለው ደግሞ በጾመ ዐርባና በአንዳንድ የምሕላ ቀኖች የሚዘመር ነው፡፡
ዝማሬ፡- ዝማሬ ማለት ምስጋና ማለት ነው፡፡ ዝማሬንና መዋሥዕትን በደቡብ ጎንደር ዙር አባ በሚባል ቦታ ደርሶታል፡፡ የዝማሬ አገልግሎት በቅዳሴ ጊዜ ከድርገት በኋላ የሚቃኝ፣ የሚዜም፣ የሚዘመር፣ የጸሎተ ቅዳሴውን ዓላማ ተከትሎ የሚሄድ የአገልግሎት መጽሐፍ ነው፡፡
መዋሥዕት፡- አውሥአ መለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ምልልስ፣ ሰዋስወ ነፍስ›› ማለት ነው፡፡ ለአዕርጎ ነፍስ በፍትሐት ጊዜ የሚደርስ ነውና ያስ ይሁን ለሙት ድርሰት ደርሶ ማዘንን ከማን አግኝቶታል ቢሉ መልሱ ከነቢዩ ዳዊት የሚል ይሆናል፡፡
ቅዱስ ያሬድ ሰማያዊ ዜማ በሚያዜምበት ጊዜ ካህናቱ፣ ንጉሡና ምእመናን አዲስ ነገር ሆነባቸው፤ ከዚያም ‹‹እንዴት እንቀበለው? ምልክት ሳናገኝ ብለው›› ማሰብ ሲጀምሩ ንጉሡ አምላካችን ይግልጽልን ብለው ከታኅሣሥ አንድ ቀን እስከ እሑድ ድረስ ሕዝቡ ሱባኤ እንዲይዝ ዐወጁ፡፡ ከዚያም ከሰኞ ዕለት ጀምረው እስከ እሑድ አንድ ሱባኤና ምህላ ይዘው በየቀኑ የአክሱም ጽዮን ማርያምን ቤተ ክርስቲያን እየዞሩ ዐራት መቶ እግዚኦታና ዐርባ አንድ በእንተ ማርያም እያደረሱ ምህላውን አካሔዱ፡፡ በሰባተኛው ቀን እሑድ ምህላውን ጨርሰው ሲያሳርጉ ጌታ በዕለተ ዐርብ እንደተሰቀለ ሆኖ በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ ተገለጸ፡፡ ከዚህም አያይዞ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ዘበመስቀሉ ተቀነወ ወበነቢያት ተሰብከ መላእክት ወሊቃነ መላእክት ሰብሕዎ ኪያሁ ንሰብክ መድኅነ፤ በነቢያት ትንቢት የተነገረለትና በመስቀሉ ላይ የተቸነከረው ጌታ መላእክትና የመላእክት አለቆች አመሰገኑት፤ እኛም እርሱ መድኃኒት እንደሆነ እንናገራለን›› በማለት ነገረ መስቀሉን በማውሳት የወልድ ምሳሌ በሆነው በዕዝል ዜማ ዘመረ፡፡ በዚህ በተገለጸው ምስክርነት መሠረት ዜማው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ መሆኑ ታምኖ ከዚያን ዕለት ጀምሮ የቅዱስ ያሬድ ዜማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ መገልገያ ሆነ፡፡ (ያሬድ እና ዜማው ገጽ ፳፬)
ርእሰ ደብር ጥዑመ ልሳን ካሣ ቅዱስ ያሬድ ሙራደ ቃል በተባለ ቦታ ሆኖ ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲያዜም ንጉሡ ዓፄ ገብረ መስቀል ከእነ ሠራዊቶቻቸው ንግሥቲቱ ከእነ ደንገጡሮቿ፣ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ፣ ሊቃውንቱና ካህናቱ እየመጡ ያዳምጡ ነበር’’ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ያሬድ በግእዝ፣ በዕዝልና በዓራራይ ዜማ ዝማሜ እየደረሰ እያለ ንጉሡ ዓፄ ገብረ መስቀል ተገኝተው ነበር፡፡ በዜማው ተመስጦ ዓይን ዓይኑን እያዩ እንደ እርሱ እዘምማለሁ ብለው በያዙት የብረት ዘንግ ሳያውቁ ቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ቸከሉት፡፡ ሁለቱም በተመስጦ ስለነበሩ የሆነውን ነገር አላስተዋሉትም ነበር፡፡ ዜማው አብቅቶ ሁለቱም ከተመስጧቸዉ ሲነቁ የቅዱስ ያሬድ እግር ዘንጋቸው ተሰክቶበት ብዙ ደም ፈሶት ነበር፡፡ ንጉሡም ደንግጠው እጅግም አዝነው ‹‹ደምህን አፍስሻለሁና የምትፈልገውን ማንኛውንም ነገር ጠይቀኝ እሰጠሃለሁ›› ሲሉ ቃል ገቡለት፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹የምለምነው አንድ ነገር እርሱም እስካሁን እግዚአብሔር በፈቀደልኝ መሠረት በዚህ ከተማ ከእርሰዎ ጋር ቆይቻለሁ፤ ብዙ ደቀ መዛሙርትም ተክቼያለሁ፤ ከእንግዲህ በኋላ የቀረኝን ዘመን በጸሎትና በብሕትውና መኖር እንድችል ከከተማው ራቅ ወዳለ ቦታ ሔጄ ፈጣሪዬን ማገልገል እፈልጋለሁ›› ብሎ የንጉሡን ፈቃድ ጠየቀ፡፡
ዓፄ ገብረ መስቀልም የቅዱስ ያሬድን ቃል ሰማተው በዚያኑም በገቡለት ቃል መሠረት ፈቀዱለት፡፡ ከዚያም ጉዞውን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ሰሜን ተራሮች አደረገ፡፡ በዚያም አሁን በስሙ የታነጸዉ ቤተ ክርስቲያን ባለበት ቦታ ላይ በምናኔ ተወስኖ ፈጣሪዉን በብሕትዉና እያገለገለ ኖረ፡፡ ምናኔ ደብረ ሐዊ ከተባለዉ ተራራ ላይ ብዙ ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በጸለምት ዋሻ በአንዱ ግንቦት ፲፩ ቀን በ፭፻፸፩ ዓ.ም ተሠወረ፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተረዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፡- (ሰሎሞን ወንድሙ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ሕይወት፤ ፲፱፻፺፰ ገጽ ፲፭፤ ያሬድ እና ዜማው ገጽ ፳፫፣ ምዕራፍ)