አጠንተ መንበሩ!
ኀዳር ፳፫፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
አልፋና ኦሜጋ የሆነው አምላካችን ቅድመ ዓለም አስቀድሞ ሲለሠስ ሲቀደስ እንደኖረ ሁሉ ድኅረ ዓለም በፍጥረታቱ ሁሉ ሲመሰገን፣ ሲቀደስና ሲከበር ይኖራል፡፡ ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ የፈጠራቸው መላእክትና ሰውም ይህን ግብር የሚሠሩ ቀደምት ፍጥረታት ናቸው፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘእሑድ)
የአምላካችን እግዚአብሔር ምስጋና በሰማይና በምድር ነው፤ በዓለመ መላእክት ዘወትር “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ ከሚያመሰግኑት መላእክት መካከል “አጠንተ መንበሩ” ተብለው የሚጠሩት “ካህናተ ሰማይ” ይገኙበታል፡፡ በምድር ባለች ማኅደረ መለኮት የአምላክ ማደሪያ ቤተ ክርስቲያን ምድራዊ ካህናት በታቦቱ ፊት ማእጠንት እያጠኑ እንደሚያመሰግኑ ሁሉ፣ ቅዱሳን ሱራፌል ሃያ አራቱ ካህናትም የቅድስት ሥላሴን መንበር እያጠኑ ሳያቋርጡ ያመሰግናሉ፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስም ስለ እነርሱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ፦ ‘ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች’ እያለ ይጮኽ ነበር።›› (ኢሳ.፮፥፩-፭) ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ‹‹በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር›› ብሏል፡፡ (ራእይ ፬፥፬)
እነዚህ ቅዱሳን መላእክት ሱራፌል ሥጋ የሌላቸው ረቂቅ የእውነት ካህናት ናቸው፡፡ ከሰማያዊ ሠራዊት ሁሉ ከፍ ከፍም ይላሉ፡፡ የሰው ልጆችን ጸሎት፣ ምጽዋትንና ጽድቅን በልዑል እግዚአብሔር ፊት ያቀርባሉ፡፡ የሚጸለየውን ጸሎትና የሚሠዋውን መሥዋዕት በማእጠንታቸው እያሳርጉ ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ፤ አይሞቱም፤ አይለወጡም፡፡
በከበረች ኅዳር ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን የስማቸው ትርጓሜ ሱራፌል “አጠንተ መንበሩ ለልዑል፣ ኤልሻዳይ” የሆነ ካህናተ ሰማይ የበዓላቸው መታሰቢያ ነው፤ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ ቅዱስን መንበር ያጠኑበት ዕለት ነው፡፡
የቅዱሳን መላአክት ሱራፌል፣ የቅዱሱ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ጸሎት፣ አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ ከበዓሉ በረከት ይደርብን!
