አገልግሎቴን አከብራለሁ!

ክፍል ስምንት

መጋቢት ፳፭፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

፲.፰.የመዝገበ አእምሮው ዝግጅት ዳራ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ረጅም ታሪክ፣ ጥልቅ ዕውቀት፣ ድንቅ ጥበብና ሰፊ ባህል እንዳላት በእምነቱ ተከታዮችም፣ በሌሎችም ዘንድ ይታወቃል፡፡ ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን በረጅም ዘመን ታሪኳ በብርቱ ልጆቿ አርቆ አስተዋይነትና በተውህቦ እግዚአብሔር ያስተላለፈቻቸው በርካታ ዕውቀቶች ለትውልዱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ በሥነ መለኮት፣ በሥነ ትምህርት፣ በሥነ-ሕንጻ፣ በሥነ-ጥበብ (ሥነ-ሥዕል፣ ሥነ-ዜማ፣ ሥነ-ቅርጻ ቅርጽ) በሥነ-ከዋክብት፣ በሥነ- ቡና፣ በሥነ-ቅመማ ቅመም፣ በፍልስፍና፣ በሥነ ጽሑፍ ወዘተ. ዙሪያ ተጽፈውና ተደጉሰው የተላለፉ የቤተ ክርስቲያኗ የዕውቀት ሀብቶች በራሳቸው ከሚሰጧቸው ጠቀሜታዎች በተጨማሪ የዘመኑን ሥልጣኔ-ወለድ የዕውቀት መስኮችም ለማሳደግ በልዩ ልዩ መንገድ ሊያገለግሉ ይችላሉ።

የቤተ ክርስቲያን የዕውቀት ሀብቶች ለዛሬው ትውልድ የደረሱት እንደዘመኑ በቀላል መሣሪያ ተጽፈው፣ በዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ተደራጅተውና በሥርዐት ተጠብቀው አይደለም፡፡ አባቶችም ብራና ፍቀው፣ መቃ አዘጋጅተው፣ ቀለም በጥብጠው ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ግላዊ እሴቶችን በመጻፍ ለትውልድ ያስተላለፏቸው በብዙ ድካምና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ኾነው ነው፡ ፡ ብረት አቅልጠው፣ ወርቅ አንጥረው፣ እንጨት ጠርበው በብዙ ድካም በልዩ ልዩ ቅርጾች የሠሯቸው ንዋየ ቅዱሳት አገልግሎትና ትእምርታዊ ትርጉም ለትውልድ እንዳይተላለፍ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ጉዳቶች ተጋልጠው እንደ ነበር በርካታ የታሪክ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አባቶች በብዙ ድካም ባዘጋጇቸው መጻሕፍት፣ ንዋየ ቅድሳትና በሌሎችም የቤተ ክርስቲያኗ ሥራዎቻቸው ላይ ጉዳት ሲደቀን በየዋሻውና በየኮረብታው በጥንቃቄ ደብቀው ለትውልድ አስተላልፈዋቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ፣ በተለያዩ ጊዜያት መጻሕፍቱንና ንዋየ ቅዱሳቱን በኃይል ለመንጠቅና ለማጥፋት ከመጡ ጠላቶች ለመጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ዘመናትን አሻግረው አቆይተውልናል።

በብዙ ድካምና በከፍተኛ መሥዋዕትነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉት የቤተ ክርስቲያኒቱ የዕውቀት ሀብቶች በአግባቡ ተሰብስበው እና ተደራጅተው፣ በሥርዓት ተጠብቀው በዘመናዊ መንገድ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ አልተሠራም። ቤተ ክርስቲያን መድበለ-ጥበብ፣ መዘክረ ዕውቀት ብትሆንም መረጃዎቹ በዘመናዊ መንገድ ተደራጅተው ለምእመናን፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ተመራማሪዎች በቀላሉ ተደራሽ አልሆኑም፡፡ በዚህ በዘመነ መረጃ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውድ የዕውቀት ሀብቶች ዘመኑን በዋጀ መንገድ አልተሰነዱም።

የቤተ ክርስቲያን የዕውቀት ሀብቶች በሥርዓት ተሰንደው አለመቀመጣቸው ለምእመናን እና ለተመራማሪዎች በቀላሉ ተደራሽ እንዳይኾኑ አድርጓቸዋል። ይህም ምእመናን ስለቤተ ክርስቲያን ያላቸው ትክክለኛ ዕውቀት እንዳይጎለብት ከማድረጉም በላይ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለሚቀርቡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት አስተምህሮ ጋራ ለማይጣጣሙ ሰበካዎች እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ምርምራቸውን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ሰዎች በተገቢ መረጃዎች ማደስደገፍ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ትኩረታቸው በቀላሉ ተደራሽ በኾኑ የውጭ ሀገር የመረጃ ምንጮች ላይ ለማድረግ ተገደዋል።

ጥበቦቹ የሰዎችን አስተሳሰብና አመለካከት በመግራትና በማስተካከል በኩል መሪ ሚና እንዲጫወቱ፣ ወጣቱን ከጥፋት ለመጠበቅ፣ ለሃይማኖቱና ቀናኢ እንዲኾን፣ ለሀገር ልማት፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲተጋ፣ ጉልበት እንዳይሆን ለማድረግ የቤተ ክርስቲያኗን የዕውቀት ነብቶች/ጥበቦች በመዝገበ አእምሮ መሰነድ በቅርቡና በቀላሉ ተደራሽ እንዲኾኑ ለማድረግ ያስችላል፡፡ የመዝገበ አእምሮ ጽሑፎች በቤተ ክርስቲያኗ ነገረ ዕውቀቶች ላይ አጠቃላይ ዕወቀት/ሐሳብ የሚሰጡ፣ ዝርዝር መረጃዎች የሚገኙባቸውን ምንጮች የሚጠቁሙ በመሆኑ ለተጠቃሚዎች ችከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣሉ፡፡ ብዙ የዕውቀት ዘርፎች በአንድ ላይ ተሰብስበው መገኘታቸው ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚደረግን መረጃ ፍለጋ ቀላል ያደርገዋል፡፡

የመዝገበ አእምሮ ዝግጅት ከመጀመሩ በፊት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር አጥኚዎች የተወሰኑ የቤተ ክርስቲያንን የዕውቀት ሀብቶች ለመሰነድ ጥረቶች መደረጋቸውን የሚያስረዱ መረጃዎች አሉ። በአባቶች ብዙ ድካምና ጥረት ተሰንደው ከሚገኙት የቆዩ የቤተ ክርስቲያን የዕውቀት ሀብቶች መካከል መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሃይማኖተ አበውና ገድላት የሚሉት መጻሕፍት ይጠቀሳሉ፡፡ ስንክሳር “የመላእክትን ማዕርግና ሹመት የሚያስረዳ፣ የነቢያትንና የሐዋርያትን፣ የጻድቃንንና የሰማዕታትን፣ የደናግልንና የመነኮሳትን ምግባር፣ መከራና ዕረፍት ከዕለት እስካመት የሚነግር፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ የእመቤታችንን ዜና፣ የልጇንም በጎ ሥራ ሁሉ በሰፊው” የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ (ደስታ፣ ፲፱፻፷፪፤ ፲፩፻፺፬)

ሃይማኖተ አበውም “አበው አባቶች የአንጾኪያና የእስክንድሪያ፣ የጽርእ እንዲሁም ሊቃነ ጳጳሳት እና ሊቃውንት በየጊዜው የጻፉት የሃይማኖት ምዕላድ፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን አሟልቶ አስፍቶ የሚናገር በቅዳሴ ጊዜ የሚነበብ መልእክት” ያለው ነው (ደስታ፣ ፲፱፻፷፪፤ ፬፻፬)፡፡ እንደዚሁም ገድል የቅዱሳን መከራ፣ ጸጋ፣ ተጋድሎ የቀረበበት፣ “ገድለ አዳም፣ ገድለ አብርሃም፣ ገድለ ሐዋርያት” እያለ የሚናገር መጽሐፍ ነው፡፡ (ኪዳነ ወልድ ፣ ፲፱፻፵፰፤ ፫፻፩) በሌላ አገላለጽ፣ ገድል “ሰማዕታት ስለ ክርስቶስ እጅ እግራቸውን ለስለት፣ ዓይናቸውን ለፍላት ሰጥተው በሰውነታቸው የፈጸሙት መንፈሳዊ ትግልና ግድያ” የሚነግር ነው፡ ፡ ገድል “ጻድቃን የመዓልት ሐሩር፣ የሌሊት ቁር ታግሠው፣ ዳዋ ለብሰው፣ ደንጊያ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ያደረጉት ስግደት፣ ጾም፣ ጸሎት ትሩፋት፣ መልካም ሥራ ሁሉ” የሚቀርብበት ነው። (ደስታ፣ ፲፱፻፷፪፤ ፪፻፴፮)

ከዚህም ገድል የጻድቃን የሕይወት ታሪክ፣ ተጋድሎ፣ ተአምራት፣ ቃል ኪዳን፣ መልክዕ የሚቀርብበት፣ በርካታ ጉዳዮች የሚነሡበት በመኾኑ የመዝገበ አእምሮ ዓይነት ቅርጽና ይዘት አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ ስንክሳር፣ ሃይማኖተ አበውና ገድል በይዘታቸው በርካታ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ማካተታቸው በቅርጻቸውም በአንድ ላይ በርካታ መንፈሳዊ ጉዳዮች መያዛቸው ከመዝገበ አእምሮ ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡

በሃያኛውና በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመኖች በግለሰቦች የመዝገበ አእምሮ ዓይነት ቅርጽና ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ታትመዋል፡፡ ከመጻሕፍቱ መካከል የኅሩይ ወልደ ሥላሴ (፲፱፻፳፩፣ ፲፱፻፺፭) ዋዜማ እና ዜና ሐዋርያት (ጥሩ ምንጭ) ( ነቅዕ ንጹሕ ) ዝውእቱ ዜና ሐዋርያት ንጹሐን ፤ የማኅተመ ሥላሴ ወ/መስቀል (፲፱፻፷፪) ዝክረ ነገር ፤ የአድማሱ ጀንበሬ (1963) መጽሐፈ ቅኔ (ዝክረ ሊቃውንት ) ፣ የስርግው ሀብለ ሥላሴ (1981) የአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ፣ የዳንኤል ክብረት (1999) የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች፣ የከፍያለው መራሒ (2003፣2004፣2006 እና 2012)፣ ዝክረ ሊቃውንት ፣ የፋንታሁን እንግዳ (2000)፤ ታሪካዊ መዝገበ ሰብ እና የመርሻ አለኸኝ (2012) ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን የሚሉት ይጠቀሳሉ፡ ፡ ይኹን እንጂ፣ የእነዚህ ሥራዎች ትኩረት ቤተ ክርስቲያን ካሏት የዕውቀት ሀብቶች እጅግ ጥቂቶቹን ጉዳዮች የሚመለከቱ ወይም የሚያነሱ ናቸው። ጸሓፍቱ ለማሳካት የፈለጓቸውን ዓላማዎች ያሳኩ እንጂ የመዝገበ አእምሮን አገልግሎት የሚተኩ አይደሉም፡፡

በእንግሊዝኛ ከተሠሩት ሥራዎች መካከል Belaynesh Mikael – Stanislaw Chojnacki – Richard Pankhurst (eds.) (1975). The Dictionary of Ethiopian Biography. I [ Early Times to c. 1270 A.D. ] በሚል ርእስ የታተመው መጽሐፍ በግለሰቦች የሕይወት ታሪክ ላይ ትኩረት በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ እንደዚኹም፣ በጀርመን ሀገር በሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ይዘቱ በኢትዮጵያ ጥናት ላይ የተደረሰበትን ዕውቀት መሠረት ያደረገና በአብዛኛው በማኅበራዊ ሳይንስ ያተኮረ በዐምስት ቅጾች “ኢሳይክሎፔዲያ ኢትዮፒካ” በሚል መጠሪያ መዝገበ አእምሮ ተዘጋጅቶ ታትሟል፡፡ Uhlig, S. (ed.) (2003; 2005; 2007; 2010; and 2014) Encyclopedia Aethiopica በሚሉ ዐምስት ቅጾች ባሉት መዝገበ አእምሮ በርካታ የነገረ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች መካተታቸው ይታወቃል፡፡ በተጠቀሱት ሥራዎች የነገረ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይን ያወሱት እግረ መንገዳቸውን እንጂ ዋና ትኩረታቸው አድርገው አይደለም፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!