አገልግሎቴን አከብራለሁ!

ክፍል ሰባት

መጋቢት ፳፫፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ጥናትና ምርምር የማኅበሩ መዳረ

፲.፩. የቅዱሳት መጽሐፍት ጥናት

በ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ማኅበረ ቅዱሳን ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ጥናትና ምርምር ማእከል›› በመክፈት ቅዱሳት መጻሕፍትን ማስተዋወቅ እና ከሚደርስባቸው ልዩ ልዩ ጉዳዮች አደጋዎች ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላላፉ ማድረግ ያቋቋመው የአገልግሎት ክፍል ለዛሬው የጥናትና ምርምር ማእከል መመሥረት ምክንያት ነው። ይህ ክፍል በተሻለ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ተጠናክሮ ከኅዳር ወር ፳፻፩ ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል›› በሚል ስያሜ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የጥናትና ምርምር ማእከል በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ጥናትና ምርምር እንዲለመድ ምሁራንም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናት አንዲያዘጋጁ ለማደፋፈር ውጤቶቹንም ለተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አካላት እና ምእመናን በተለያዩ መንገዶች ለማድረስ እና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጥናት ለሚያደርጉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሐሳብ፣ የሞያና የገንዘብ ድጋፍ ለማበርከት የተቋቋመ ነው። ማእከሉ የውይይት መድረኮችን፣ ዓመታዊ የጥናት ጉባኤ እንዲሁም የምርምር መጽሔት ያዘጋጃል፤ የቤተ ክርስቲያንን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶችን ይቀርጻል፤ ይተገብራል፡፡

        ፲.፪.የጥናትና ምርምር ማእከል መመሥረት

ማኅበረ ቅዱሳን ለአገልግሎቱ ይዟቸው ከተነሣቸው ዓላማዎች መካከል አንዱ የጥናትና ምርምር ተግባር ነው። “በኦርቶዶሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችን በተለይ ምሁራንን ማበረታታትና በሚቻለው ሁሉ መርዳት፡፡››  በ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. የተመሠረተው የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናትና ምርምር በ ፳፻፩ ዓ.ም. ወደ ጥናትና ምርምር ማእከልነት አደገ፡፡ ማእከሉም ጥናቶች እንዲጠኑ በማማከር፣ በማሰልጠን እና  ቤተ መጻሕፍት በማደራጀት ለተመራማሪዎች ሁለገብ ድጋፍ አድርጓል። በጥናት የተደገፉ አቅጣጫዎችን ለማኅበሩ፣ ለቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ሰጪ እና አጋርና ተባባሪ አካላት ሰጥቷል።

፲.፫. የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔት ኅትመት

የጥናትና ምርምር ማእከሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥናት መጽሔትን እያዘጋጀ ያሳትማል። አንድ ተቋም የምርምር መጽሔት ወይም ጆርናል ማሳተም ከቻለ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ባህላዊ በሆኑ ርእሰ ጉዳዮች ላይ አማካሪ ቦርድና አርትኦት ኮሚቴ አባላትን በማዋቀር፣ የራሱ መመሪያና ፖሊሲ አውጥቶ፣ በከፍተኛ ጥራት በመስኩ በተመሠከረላቸው ባለሙያዎች አስገምግሞ በዲጂታልና በሐርድ ቅጅ በዓመት አንድ ጊዜ ያሳትማል፤ እስከ አሁንም ዘጠኝ ቅጾችን አሳትሟል፡፡ መጽሔቱ ብቸኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት ሲሆን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ  ትምህርት ሚኒስቴር ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ በግምገማ ላይ ይገኛል፡፡

                           ፲.፬. የጥናትና ምርምር ጉባኤዎች

ማእከሉ በየሁለት ወራት የሚቀርቡ ዝክረ በዓለ አድዋ እና ዓመታዊ የጥናት ጉባኤዎች፣ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጥናት መድረኮችና የምክክር ጉባኤዎችን አካሂዷል። ከ ፳፼ (ሁለት መቶ ሺህ) በላይ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተሳተፉባቸው ከ ፻ (መቶ) በላይ ጥናቶችና የምርምር ግኝቶች በመድረክ ቀርበዋል። ከአምስት ጊዜ በላይ ዓለም ዓለማቀፋዊ የቤተ ክርስቲያን የጥናት ጉባኤያት ተካሂደዋል፡፡

 ፲.፭.ብቸኛው የጥናትና ምርምር ቤተ መጻሕፍት

በቤተ ክርስቲያን አካባቢ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች የሚገኙበት ብዙም አማራጭ የሌለው የማኅበረ ቅዱሳን  የጥናትና ምርምር ቤተ መጽሐፍት በዋናው ማእከል ይገኛል፡፡ የቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎቱ በመረጃ በማደራጀት፤ ለተጠቃሚዎች የንባብ አገልግሎት ይሰጣል። የአገልግሎት ክፍሉን በቤተ ክርስቲያን ለሚደረጉ ጥናቶች ጠንካራ የመረጃ ምንጭ ለማድረግ የመረጃ ክምችቱን በማሳደግ እና በዘመናዊ መልኩ በማደራጀት ማለትም ዲጂታል ካታሎግ አሠርቶ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍቱን በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ የአገልግሎት ክፍሉ ሁለት መደበኛ አገልጋዮችና ኢ-መደበኛ አገልጋዮችን በመያዝ አገልግሎቱን ያከናውናል። በዚህም መሠረት ከሀገር ውጭና ከሀገር ውስጥ ባሰባሰባቸው የመረጃ ምንጮች ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች (በተለይ ለአጥኚዎች) አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በቀጣይም በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ውስጥ የታተሙ መጻሕፍትን በልዩ ሁኔታ አሰባስቦ ለሁሉም ተደራሽ ይሆን ዘንድ በዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ይሰጣል፡፡

፲.፯.ጥናትና ምርምር ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል ዘመናት የነበራትን፣ ያፈራችውንና ያስተላለፈችውን ነገረ ዕውቀት (ታሪክ፣ ጥበብ፣ ክህሎት) በዘርፉ ባለሙያዎች በማሳተፍ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ይተጋል፡፡  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የብዙ ጥበባት፣ ሀብትና ጸጋዎች ቤት በመሆኗ ይህን ክብር እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ የሆነ የአስተዳደርና ዓቃቤ ንዋይ አጥኚዎችን በባለሞያ ያማክራል፤ ያሠለጥናል፡፡

ሙያዊ አገልግሎት መስጠት ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት እና ከሌሎች የምርምር ተቋማት በጋራ መሥራት እንዳለበት ቀዳሚ ዕቅዱ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዙርያ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች እጅግ አነስተኛ ከመሆናቸውም በላይ በአንድ ዘርፍ (ታሪክና ቅርስ) ብቻ ያተኮሩ መሆናቸውን ተረድቶ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳው ዘንድ ጥናትና ምርምር ማእከሉን ወደ ተቋም አሳድጓል፡፡ ተቋሙም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተያያዥነት ባላቸው ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ባህላዊ በሆኑ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡

በዚህ ረገድ ለጥናትና ምርምር ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ርእስ ጉዳዩችን ለይቶ ለአጥኝዎች በመስጠት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶችን በማሰባሰብ ለአጥኚዎች የማማከር አገልግሎት በመስጠት ለወርኃዊና ዓመታዊ የጥናት ጉባኤዎች የሚቀርቡ ጥናቶችን አንዲያዘጋጁ በማድረግ እና ለመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች የድርሻውን አስተዋጽኦ አድርጓል። ተቋሙ ከፍተኛ የሰውና የገንዘብ ሀብት እንደሚያስፈልገው የታመነሲሆን አገልግሎቱን ከዚህ በላይ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ይቆየን!

                      ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!