አገልግሎቴን አከብራለሁ!

 

ክፍል አምስት

የካቲት ፯፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

፭.፬.በምሕንድስና ዘርፍ

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን እንዲሁም መንፈሳዊ ተቋማትን ለመገንባት ከሚቻልባቸው መሠረታዊ ተግባራቶች የምሕንድስና ሙያ ቀደምት ተጠቃሽ እንደመሆኑ በሀገራችን እንዲሁም በውጭ ሀገር ለሚገኙት የቤተ ክርስቲያናትና አድባራት ግንባትና መልሶ ማቋቋም ሥራ መሐንዲሶች እጅጉን ተፈላጊዎች ናቸው፡፡ በተለይም በሀገራችን ውስጥ ያሉ ቤተ ክርስቲያናት በጠላቶች ሥውር ደባና ጥቃት፣ ምዝበራ፣ ቃጠሎ እንዲሁም መራቆት የደረሳበቸው በመሆኑ እነዚህን ቤተ ክርስቲያናት መልሶ ለመንባትና አዳዲሶችን ለማነጽ በታቀደው ሥራ መሠረት የማኅበረ ቅዱሳን የምሕንድስና ባለሙያዎች ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

ማኅበሩ መደበኛ ያልሆኑ እስከ ፳ (ሃያ) የሚደርሱ በሲቪል፣ በአርክቴክቸራል፣ በኤሌክትሪካል፣ በሜካኒካል ምሕንድስና እና በሌሎችም የምሕንድስና ዘርፎች የተመረቁ ባለሙያዎች ተደራጅቶ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ቅዱሳት  መካናት እና ሌሎችንም ሙያዊ ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ከዋናው ማእከል ጋር በመቀናጀት ያጠናል፤ ይተገብራል፤ ክትትልም ያደርጋል፡፡ የስትራክቸራል፣ አርክቴክቸራል፣ ኤሌክትሪካልና ሳኒተሪ ዲዛይኖችን በተጠቃሚዎች ጥያቄ መሠረት ከማዘጋጀቱም ባሻገር ጥራታቸውን የጠበቁ ዲዛይኖችን ያዘጋጃል፡፡

ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጋር የተያያዙ ጥናቶችን ያጠናል፤ ለተዘጋጁ ዲዛይኖች ከተጠቃሚዎች (እንዲሠራላቸው ከጠየቁ) ቢያንስ ቋሚ ወጭን በመሸፈን መሠራቱን ያረጋግጣል፤ የሰርቬይንግ (የቅየሳ) ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ማኅበሩ የምሕንድስና ጥበብን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የኪነ ሕንጻ ጥበብ እና ዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማጣመር ሰፊ ሥራ እየሠራበት ይገኛል። በዚህ ዘርፍ የተከወኑ አገልግሎቶች ሰፊ ቢሆንም በምሕንድስና ዋና ክፍል የሚሠሩ የዲዛይን ዓይነቶች ክብ ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን (ቤተ ንጉሥ)፣ ሰቀላማ (ካቴድራል) ዲዛይን፣ የቤተልሔም ዲዛይን፣ የደወል ቤት ዲዛይን፣ የጠቅላላ አገልግሎት ሕንጻ፣ የትምህርት ቤት ሕንጻ፣ የመኖሪያ ቤት (መንበረ ጵጵስና) የእንግዳ ማረፊያ፣ የመሬት አቀማመጥ እና የቅየሳ ሥራ፣ የጤና ማእከል፣ ሁለገብ አዳራሽ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ሙዝየም በመገንባት አገልግሏል፡፡

በአርሲ ሀገረ ስብከት ሮቤ ወረዳ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያናት ሊሠራ የታሰበው አብነት ትምህርት ቤት፣ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የሚሠራው አብነት ትምህርት ቤት፣ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የሚሠራው አብነት ትምህርተ ቤት፣ በከንባታ ሀዲያ ሀገረ ስብከት የኤላ ጌሜዶ ቅዱስ አማኑኤል አዲስ የሚሠራው ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን፣ በጉራጌ ሀገረ ስብከት፣ ምሑር አክሊል ወረዳ አዲስ የሚሠራው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን፣ አዲስ የሚሠራው የአሶሳ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ዲዛይን፣ በኢሉባቡር ሀገረ ስብከት  በመቱ ከተማ የሚሠራው የገቢ ማስገኛ ሕንጻ፣ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በሞላሌ ከተማ የሚሠራው የእመጓ ቅዱስ ዑራኤል ገዳም የገቢ ማስገኛ ሕንጻ፣ በነቀምት ከተማ የሚሠራው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የገቢ ማስገኛ ሕንጻ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

፭.፭.በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በተቋማት የሥራ ሂደት ላይ ያለው ተጽእኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የማኅበሩንም ዓለማ በበለጠ ከግብ ለማድረስ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ማኅበሩ ከዚህ ቀደም በልዩ ልዩ ክፍል ተደራጅቶ የነበረውን የአይ.ሲ.ቲ የመረጃ እና መዛግብት አገልግሎት ወደ አንድ በማምጣት በማስተባበሪያነት ተደራጅቶ እና በሥሩ ክፍሎችን በማዋቀር አገልግሎቱን እንዲፈጽም ያደርጋል። በመሆኑም ማኅበረ ቅዱሳን የወንጌል አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ተደግፎ እንዲስፋፋ ዓላማው አድርጎ ለተለያዩ ማስተባበሪያዎች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት (አህጉረ ስብከት፣ ገዳማት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ መንፈሳዊ ተቋማት) እና መንፈሳዊ ማኅበራት አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ለእነዚህ መንፈሳዊ ተቋማት የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃናት ማስፋፊያና ማጎልበቻ ምክር አገልግሎትና ሥልጠና ይሰጣል፡፡

በዚህም መሠረት የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን በማበልጸግ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉ በርካታ ድረ ገጾችን አዘጋጅቶ በማቅረብ ለስብከተ ወንጌል ተደራሽነትና ለመንፈሳዊ አገልግሎት ጥንካሬ ለመጨመር ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ በመደበኛና በኢ-መደበኛ ዳታቤዝና ሲስተም ዴቨሎፕመንት ባለሙያ በሆኑ አገልጋዮች በመታገዝ ከተካተቱት ዋና ተግባራት በጥቅል ሲገለጽ የኮምፒዩተር ሲስተም እና የመረጃ ቋት ፍሎጎቶች ላይ ተስማሚ ቴክኖሎጂ በመጠቆም፣ በማበልጸግ እና ለብልሽቶች እንዲሁም ለጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሙያ አበርክቶ ስብከተ ወንጌልን ተደራሽ ከማድረግ አንጻርም ሥራን ለማጠንከር የሚረዳ የቴሌቭዥን ሥርጭት አገልግሎቱ ነው፡፡ የማኅበሩ አይ.ሲ.ቲ ማስተባበሪያ ይህን ተልእኮን በሚገባ ተወጥቷል፡፡

በመሠረተ ልማትና ድጋፍ አገልግሎት ሥር ደግሞ ማኅበሩ ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ለሚቀርቡ የአይ.ሲ.ቲ ብልሽቶችና ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ናቸው፡፡ ይህም የሚከወነው በመደበኛና በኢ-መደበኛ የሀርድዌርና ኔትዎርክ ጥገና ባለሙያ በሆኑ አገልጋዮች ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተይይዞ በጅማ ሀገረ ስብከት ምእመናን የሚመዘግብ የአገልግሎት መሣሪያ በድጎማ አበርክቷል፡፡

፭.፮.በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ

ማኅበራዊ አገልግሎት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንዱ ተልእኮ ነው፤ ማኅበራዊ ወንጌል ተብሎም ይጠራል። ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ዘርፍ ሰፊ አገልግሎት ሲሰጥ ኖሯል። ማኅበራዊ አገልግሎቶች በገንዘብና በዓይነት ድጋፍ በማሰባሰብ ድጋፎችም ለተሰበሰቡለት አገልግሎት እንዲውሉም አድርጓል፡፡

በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ቀውሶች የተነሣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለገጠማቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የአስቸኳይ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ድጋፎችን አድርጓል። በተለይ ከጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. ጀምሮ የመልሶ ማቋቋምና አስቸኳይ ድጋፍ ዐቢይ ኮሚቴ በማቋቋም፣ በተከታታይ በደረሱ ሃይማኖታዊ ጥቃቶችና ማኅበራዊ ቀውሶች ለተጎዱ አካላት ድጋፎችን ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በተለያዩ ክፍለ ሀገራት ለደረሰው የማኅበራዊ ሕይወት ቀውስን በመራዳት ለችግሩ መፍትሔ ይሆን ዘንድ ለተጎጂዎቹ ርዳታ ከሰጠባቸው አካባቢዎች ውስጥ ለአብነት ያህል የአጋርፋ ወረዳ አምቤንቱ ለ ፲፻፪፻፶፫ (አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ ሦስት) ተጎጅዎች እና አዳባ ለዐራት መቶ ዐርባ ተጎጅዎች የምግብና የጽዳት ዕቃዎች ድጋፍ ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊ ምሕረት ቅድስት ማርያምና ክርስቶስ ሳምራ ከዕውቀት ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ጋር በመሆን ቦታው ላይ በመገኘት ርዳታ ተሰጥቷል፡፡

የተጎዱትንም መልሶ ለማቋቋም ማኅበሩ የእነዚህን የአልባሳትና የገንዝብ እንዲሁም የሕክምና ርዳት ቡልቡላ ለ፳ (ሃያ) አባወራ፣ በኮፈሌና ቆሬ ወረዳ፣ በአዳባ ወረዳ ለ፻፳፰ (መቶ ሃያ ስምንት) አባወራዎች፣ በአጋርፋ ወረዳ ኦዳ ነገሌ ቀበሌ ለ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ተጎጅዎች፣ በኮፈሌ ወረዳ ለሚገኙ ወጣቶች፣ በዶዶላ ወረዳ ፮፻፸፭ (ስድስት መቶ ሰባ አምስት) አባወራዎች እና ፳፮ (ሃያ ስድስት) ተጎጅዎች፣ ከሻሸመኔና ከአሰበ ተፈሪ ተፈናቅለው አዲስ አበባ ለሚገኙ ሦስት እማወራዎች፣ ለዝዋይ ለዱግዳ፣ ለሔረሮ፣ ለሻሸመኔ ለአዋሾ እንዲሁም መጋቢት ፲-፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም አጣየና አካባቢው በነበረ ችግር ጉዳ ለደረሰባቸው ፲፮ (ዐሥራ ስድስት) ተጎጅዎች፣በትግራይ ክልል ለሚገኙ ችግር ለገጠማቸው ሕፃናት፣ በደሴና በአካባቢው ተፈናቅለው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በደባርቅና ጭና፣ ከሰሜን፣ ደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋን የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በማኅበሩ ተረድተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በኮፈሌ ወረዳ የሚገኙ ወጣቶች እንዲደራጁና መንፈሳዊ ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ የመጽሐፍትና የሻይ ክበብ እንዲኖራቸው የቁሳቁስ፣ በወሊሶ አካባቢ ጉዳት ለደረሰባቸዉ ፷፭ (ስድሳ አምስት) ቤቶች በሰዓሊተ ምሕረት ሰንበት ትምህርት ቤት ወሊሶ ማእከል ክትትል የጥገና ሥራ ተሠርቶ ተጎጂዎች ረድቷል፡፡ በአጠቃላይ ማኅበሩ በጐ አድራጊ አካላትን በማስተባበር በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ለዚህ አስቸኳይ ማኅበራዊ ድጋፍ ከ ፳፻፼ (ሃያ ሚሊዮን) ብር በላይ ወጭ አድርጎ ረድቷል።

ማኅበራዊ አገልግሎትን በተመለከተ ለምእመናን በልዩ ልዩ መንገዶች ግንዛቤ በመስጠት የማኅበራዊ አገልግሎት ተሳትፏቸውን ያሳድጋል:: ኦርቶዶክሳዊያን በማኅበራዊ አገልግሎት ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ስልት ቀይሶ ይተገብራል፤ የከፍተኛ ትምህረት ተቋማት ኦርቶዶክሳዊያን ተማሪዎች በማኅበራዊ፣ በሥራ ፈጠራና በኢኮኖሚ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚሆኑበትን ትምህርት ክፍል እንዲመርጡ የተለያዩ ግንዛቤ እና ሥልጠና ይሰጣል::

ይቆየን!