አገልግሎቴን አከብራለሁ!

ክፍል አራት

የካቲት ፮፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

፭. የዘመመውን የማቅናት፤ የፈረሰውን ቅጥር መገንባት

ማኅበረ ቅዱሳን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እንዲስፋፋና የአማንያኑ ቁጥር እንዲጨምር ለማድረግ ከሥር መሠረቱ በተለይም ሕፃናቱን በትምህርተ ሃይማኖትና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ኮትኩቶ ለማሳደግ የአብነተ ትምህርት ቤቶችን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ የማኅበሩ የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ከተዋቀረበት ዓመት ምሕረት ጀምሮ አብነት ትምህርት ቤቶች ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ቤቶችን ሲያፋፋ ነባሮቹን ደግሞ የማጠናከር ሥራ ሠርቷል፡፡ በዚህም የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ገዳማትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በሁለንተናዊ መልኩ የሚጠናከሩበትን መንገድ አመቻችቷል፡፡ ገዳማትም ራሳቸውን በኢኮኖሚና በልማት እንዲችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ተግባራዊ አድርጓል፡፡

የአብነት ትምህርት ቤቶች መገንባትና መስፋፋት ከገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች በሁለንተናዊ መልኩ ብቁ የሆኑና ዘመኑን የዋጁ አገልጋዮችን ለማፍራትም አስችሏል፡፡ ይህም በአንድ በኩል የምእመናንን ቁጥር ሲጨምር በሌላ መልኩ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የሚያጠናክሩ አገልጋዮችን አስገኝቷል፡፡  ከዚህም ጋር ተያይዞ  ማኅበሩ የገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ሉዐላዊነት ተጠብቆና ተጠናክሮ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በሁለንተናዊ መልኩ እድገት እንድታገኝ የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡ የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘብ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ እንዲያገለግል አስፈላጊውን ሁሉ ማመቻቸት፣ ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችን በተለይ ወጣት ምሁራንን ማበረታታና በሚቻለው ሁሉ መርዳትም ከማኅበሩ ዐበይት ተግባራት መካከል ናቸው፡፡

፭.፩. የአብነት ምንጩ እንዳይደርቅ

ከ፳ኛው (ሃያኛው) መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ በዓለማችን የተከሰተው የአምላክ የለም አስተሳሰብ ወደ ሀገራችን በመግባቱ ኅብረተሰቡ ለሃይማኖቱና ለገዳማት ለአብነት ትምህርት ቤቶች የነበረው ክብር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በተለይም ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ከጀመረበት ወቅት ለአብነት ትምህርት ቤቶች የተሰጣቸው ግምት አነስተኛ እየሆነ በመምጣቱ ትምህርት ቤቶቹ እየተዳከሙ መጥተዋል፡፡ ከዘመናዊው ትምህርት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ኀብረሰተቡ ልጆቻቸውን ወደ ጥንታዊው የአብነት ትምህርት ቤት መላክ እየተወ ‹‹የአብነት ተማሪው ካህን ወይም መርጌታ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኑን ያገለግላል፤ለሀገር ይጠቅማል›› የሚለው አመለካከት እየቀረ ነው፡፡ በተለይም በ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. የመሬት ላራሹ አዋጅ ምክንያት ገዳማትና አድባራት ይተዳደሩበት የነበረው መሬት በመወረሱ መነኰሳት መተዳዳሪያ አጥተዋል፡፡

ገዳማት አንድነታቸውን አጥተው ወደቁሪትነት ተቀይረዋል፡፡ በእነዚህ ቅዱሳን ቦታዎች የሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው የሶሻሊስት ርእዮተ ዓለም ኅብረተሰቡ ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች ያለውን በጐ አመለካከት እንዲሸረሸር የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ከ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. ጀምሮ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ትምህርት ቤቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለከፋ ችግር እየተጋለጡ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ ጉባኤያት ወንበራቸው ታጥፈዋል፡፡ ሊቃውንቱም ዕውቀታቸውን ሳያስተላልፉ ተተኪ ሳይኖራቸው ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ባሉትም ጥቂት ትምህርት ቤቶች የሚገኙት ተማሪዎችም ቢሆኑ የዕለት ጉርስ ፍለጋ ትምህርት እያቋረጡ ለከተማ ስደትና እንግልት ይዳረጋሉ፡፡

በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ የሚገኙ ምእመናን በሚያጋጥማቸው ሰው ሠራሽ ተፈጥሮአዊ አደጋ ምክንያት ኑሮአቸው እየከበደ እንዲሁም የአመለካከት ለውጥ በመምጣቱ አብነት ተማሪው ቀደም ሲል እንደነበረው ‹‹በእንተ ስማ ለማርያም›› ብሎ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስም በመጥራት ቁራሽ እንጀራ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖበታል፡፡ በዚህም በትምህርት ቤት ከሚገኙ ተማሪዎች ከዐሥር ተማሪዎች መካከል ሰባቱ ምንም ዓይነት ቀለብ የሌላቸው ናቸው፤ ብዙዎቹ የአብነት ተማሪዎች ኑሮን አሸንፎ ለመማር ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ከተማ በመሰደድ በጉልበት ሥራ ይሠማራሉ፡፡

በማስተማር ላይ የሚገኙ መምህራን በቋሚነት የሚተዳደሩበት የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ የሚያገኙበት ሁኔታ እየጠበበ መጥቷል፡፡ ቋሚ እና በቂ የገቢ ምንጭ ወይንም ደመወዝ የላቸውም፡፡ ለመምህራን የሚደረገው ድጋፍ በወር በአማካይ እስከ ፶ (ሃምሳ) ብር ብቻ ነው፡፡ መምህራንና ተማሪዎቻቸው በቂ ምግብ እና አልባሳት ስለማያገኙ ለተለያዩ በሽታዎችና ለእርዛት የተጋለጡ ናቸው፡፡ የትምህርቱ ባሕርይ በቃል የሚጠና ሲሆን ተማሪዎቹ ከፍተኛ የመጻሕፍት ችግር አለባቸው፡፡ ቀደም ሲል የተገነቡት ጉባኤ ቤቶች በእርጅና ምክንያት ፈራርሰው ተማሪዎቹ ለፀሐይ እና ለዝናብ ተጋልጠዋል፡፡ ተማሪዎቹ ለማደሪያ ጎጆቸው ክዳን የሚሆን ሣር ስለማያገኙ የማደሪያ ቤት ችግር በስፋት ይታያል፡፡

በአብነት ትምህርት ቤቶቹ በሰፊው ይሰጥ የነበረው የመጻሕፍት ትርጓሜ እና ሐዋርያዊ ተልእኮ ትምህርት እየተዳከመ ትምህርቱ በአብዛኛው ዜማ ትምህርት ላይ ብቻ እያተኮረ መጥቷል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አብዛኛዎቹ በደቡብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ከአገልጋይ ካህናት እጥረት የተነሣ ለምእመኑ በቂ አገልግሎት በመስጠት አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡

በየትኛውም የዓለም ክፍል ለተማሪ እና ለትምህርት ቤት ድጋፍ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ በእርግጥ የሚደረገው ድጋፍ በተናጠል ሳይሆን በአብዛኛው በተቀናጀ ሁኔታ መዋቅራዊ አሠራርን የተከተለ ነው፡፡ ስለዚህም ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በማድረግ አባላቱና ምእመናን በጋራና በተቀናጀ ሁኔታ በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚታዩትን ችግሮች በሂደት ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ የሚያስችል የአብነት ትምህርት ቤቶች ማቋቋሚያ መርሐ ግብር በከ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ነድፏል፡፡ መርሐ ግብሩ ላይ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና የአብነት መምህራን መክረውበት ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

ጥንታዊ የሆኑ የአብነት ትምህርት ቤቶች ያለባቸውን የጉባኤና የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ የተማሪዎች ማደሪያ ቤት፣ ጉባኤ ቤት፣ የመመገቢያ አዳራሸ፣ የገላ መታጠቢያና መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት በዘመናዊ መልክ እንዲደራጁ ሲደረግ በጠረፋማና አብነት ትምህርት ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ደግሞ አዳዲስ እና አዳሪ የሆኑ አብነት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም በየአካባቢው በሚነገሩ ቋንቋዎች ጭምር ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ካህናትን ለማፍራት ተችሏል፡፡ በዚህ ረገድ ማኅበሩ በማሳያነት የሠራቸው ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አስገኝተዋል ማለት ይቻላል፡፡

በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የቀለብ ችግር በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍና ተማሪዎቹን ለማበረታታት ከምእመናን እና ማኅበራት ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ማኅበረ ቅዱሳን በአሁኑ ሰዓት በሁሉም አህጉረ ስብከቶች በሚገኙ ከመቶ በላይ መምህራን እና ከ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ  በላይ ተማሪዎች ከስድስት ሚለዮን ብር በላይ ዓመታዊ የገንዘብ ድጎማ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

፭.፪.የትሩፋት ምድር ገዳማት እንዳይፈቱ

በገዳማት ላይ የተከሰተው ችግር ሰፊና ሥር የሰደደ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ማኅበሩ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ምእመናኑ ይህንኑ ተገንዝበው የመፍትሔው ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ በተለይ ከ፲፱፻፺፫ ዓ.ም. ጀምሮ እነዚህን ቅዱሳት መካናት እና ገዳማት እንዲጠናከሩ የሚያደርጉ አንዳንዶቹንም መልሶ በማቋቋም ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን በተለያዩ አህጉረ ስብከቶች አከናውኗል፡፡ በገቢ ማስገኛነት ተግባራዊ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች ዓይነት የሚወሰነውም የችግሩን ስፋት፣ ገዳማት ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል የገቢ ሁኔታ እና መሠረተ ልማቶችን ከግንዛቤ በማስገባት ነው፡፡

በማኅበሩ የሚደረገው ድጋፍ የማኅበሩን እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን አቅም ያገናዘበ በመሆኑ ተጠቃሚዎች በቅደም ተከተል መወሰን ያስፈልጋል፡፡የችግሩ ስፋት፣ በችግሩ ተጠቂ የሆኑ መነኰሳት ቁጥር በሌሎች አካላት የሚደረግ ድጋፍ፣ መነኰሳት በልማት ለመሳተፍ ያላቸው ፍላጎት፣ የገዳማቱ ጥንታዊነትና ታሪካዊነት፣ የቅርሶች ሁኔታ፣ የገዳም ሥርዓት ከሆነው በአንድነት ኑሮ ለመኖር ያላቸው ፍላጎት እንዲሁም ገዳማቱ የሚገኙበት አካባቢ ያሉ ምእመናን ገዳማትን ለመደገፍ ያላቸው አቅምና ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ ገዳማቱን አብነት ትምህርት ቤቶችን ለመምረጥ የሚወሰዱ መስፈርቶች ናቸው፡፡

፭.፪.፩.የተመዘገቡ ዋና ዋና ለውጦች

በጐ አድራጊ ምእመናንና ማኅበራት ከተናጠልና ጊዜያዊ ድጋፍ ይልቅ የተቀናጀ ዘላቂ ልማት ላይ በማተኮራቸው ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በሆኑባቸው ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች የሚከተሉትን ለውጦች ለማየት ተችሏል፡፡

በገዳማት የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት ለመለወጥ ያላቸው የተነሣሽነትና ቁርጠኝነት መጨመር ለሌሎች አርአያ መሆን ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በልበሊት ኢየሱስ ገዳም፣ ባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ አቃቂ አባ ሳሙኤል ገዳም በገዳማት መተዳደሪያ ማግኘት በመቻሉ መናንያን በገዳማቸው ጸንተው የመኖር ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡ ለምሳሌ፡- ከሣቴ ብርሃን አቡነ ሰላማ ገዳም፣ ጉንዳጉንዶ ቅድስት ማርያም ገዳም፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም በውኃ እጥረት ይቸገሩ የነበሩት ገዳማት ችግር በመቅረፍ የመናንያን ቁጥር መጨመር አቡነ ቶማስ ዘሃይዳ ገዳም፣ ምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ ደብረ ሃሌ ሉያ አቡነ ሣሙኤል ገዳም ተማሪ በማጣት ተስፋ ይቆርጡ የነበሩ መምህራን ተማሪ በማግኘት ትምህርታቸው ዋጋ የተሰጠው መሆኑን በመረዳት ተስፋቸው ለምልሞ ተጠናክረዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ዋሸራ ደብረ ምዕራፍ፣ ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሰለልኩላ ቅዱስ ሚካኤል የአብነት ትምህርት ቤቶች የተሻለና ምቹ የመማሪያ ሁኔታ በመፈጠሩ ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል፡፡

ቅድስት ቤተልሔም የድጓ ትምህርት ቤት፣ ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ መጽሐፍት ትምህርት ቤት በአብነት ትምህርት ቤቶች በሚደረገው ድጋፍም የካህናት እጥረት ያለባቸው ጠረፋማ አካባቢዎች አገልጋይ ማግኘት ከቻሉት መካከል ናቸው፡፡ የአብነት መምህራንና ተማሪዎች ከአብነት ትምህርቱ በተጨማሪ በስብከተ ወንጌልና በተጨማሪ ሥልጠናዎች ለመሳተፍ ያላቸው ፍላጎት ማደግና ለተለያዩ ክህሎት ተሳታፊ መሆን በዚህም በአገልግሎት የሚተጉ ካህናት ማግኘት ዋና ዋናዎቹ የተመዘገቡ ለውጦች ናቸው፡፡

፭.፪.፪.የማኅበሩ አሻራዎች በአብያተ ክርስቲያናት ሕንጻ ግንባታ

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን ሁሉ መሰብሰቢያችን በመሆኗ ቅድስት ቤታችንን ልናንጽና ልንጠብቅ እንደሚገባ ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ሲል አስተምሮናል፡ ‹‹ቤቴንም ሥሩ፡፡›› የእግዚአብሔር ቤት ቅድስናው ተጠብቆና ሥርዓቱ ሳይፋለስ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት ቅድስት ቤቱን በአምሳለ ግብሩ ተምሳሌት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን እናንጻለን፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን የመገንባት ወይም የማስገንባት ሥራን የማካነወን ተልእኮ ማኅበረ ቅዱሳን ሥራዬ ብሎ የያዘው ተግዳሮት ነው፡፡ ማኅበሩ ለምእመናንና ለአብያተ ክርስቲያናት የሙያ አገልግሎት እንዲሰጥ ዕቅድና ስትራቴጂ በማውጣት በተለይም በገጠር ያሉ አብያተ ቤተ ክርስቲያናትንና ሕንጻ ግንባት ያንጻል፤ ያሳንጻል፡፡ (ሐጌ.፩፥፰)

ቤተ ክርስቲያን የብዙ ሙያዎችን አገልግሎት እንድታገኝ እና ባለቤት እንድትሆን ለማድረግና፣ ሙያዊ አገልግሎቱ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲፈጸም ሙያዊ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቅርስ አጠባበቅና ቱሪዝም የሚኖረውን አገልግሎት ያስተባብራል፤ ለሚመለከታቸው አካላት በቅርስ አጠባበቅና ቱሪዝም ዙሪያ ሥልጠናና ግንዛቤ ይሠጣል፤ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ያሉ ሙያዊ ዘርፎች (መዋቅራት) እንዲጠናከሩ ሥልት ቀይሶ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ሌሎች ኦርቶዶክሳዊያን በሙያቸው ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል የሚያስችላቸውን አሠራር አዘጋጅቶ ያቀርባል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን እና ከምእመናን የሚጠየቁ የሕንጻ ዲዛይኖች ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ በማዘጋጀት ሠርቶ ያስረክባል፡፡  ከአብያተ ክርስቲያናትና ኦርቶዶክሳውያን የሚጠየቁ የፕሮጀክት ቀረጻ ጥያቄዎችን ያስተናግዳል::

፭.፪.፫.ማኅበረ ቅዱሳን በሙያና ማኅበራዊ አገልግሎት ያከናወናቸው ተግባራት

ማኅበረ ቅዱሳን መንፈሳዊ አገልግሎቱን ተደራሽ ከሚያደርግባቸው መንገዶች መካከል ሙያዊና ማኅበዊ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በሙያ (በዕውቀት)፣ በጉልበት፣ በገንዘብ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የሚተጉ አባላትን አፍርቷል። በመተዳደሪያ ደንቡም ከተጠቀሱ ዓላማዎች መካከልም አንዱ ‹‹የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘቡ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ እንዲያገለግል አስፈላጊውን ሁሉ ማመቻቸት›› በመሆኑ አገልግሎታችን ለማከናወን በሥሩ ባሉት የአገልግሎት ዋና ክፍላትን አስተባብሮ ዋና ዋና የተልእኮ ዘርፎችን በተለያዩ የሙያ መስኮች ለአገልግሎት እገዛ ሊያደርጉ የሚችሉ ዝርዝር ማኑዋሎችን በማዘጋጀት ኦርቶዶክሳውያን እጓለ ምውታን ተቋማትን እንዲመሠርቱ ይሠራል፡፡ የተመሠረቱትም ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ የኦርቶዶክሳዊያንን ምጣኔ ሀብት ትሥሥር መፍጠር የሚያስችሉ ሥልቶችን ይቀይሳል፤ ተግባራዊም ያደርጋል። ኦርቶዶክሳዊያን በምጣኔ ሀብት እራሳቸውን እንዲችሉ የተለያዩ ሥልቶችን አዘጋጅቶ ያቀርባል፡፡ በኦርቶዶክሳውያን የተቋቋሙ የበጎ አድራጊ ድርጅቶችን (አረጋውያን መጦሪያ፣ ሕፃናት ማሳደጊያ) ልዩ ልዩ ሞያዊ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

፭.፫.በሕክምና ዘርፍ

ጤና ለሰዎች መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ የጤና እክል ከመንፈሳዊ ሕይወታችን የሚያስተጎጉልና ከዚያም አልፎ ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳርግ መሆኑን በቅርብ በምናውቃቸው ወንድሞቻችንና እህቶችን የተመለከትነው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎች በየጊዜው በተለያዩ በሽታዎች ተጠቅተው በሕክምና እጦት ሲሠቃዩና ለሞት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቱ እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት የሚሠሩ አገልጋዮችና ምእመናን በጾምና በጸሎት እንዲሁም በክርስቲያናዊ ምግባር እንዲተጉ እጅጉን አስፈላጊ ከሆነው መሠረታዊ ነገር የጤናችን መጠበቅ ስለመሆኑ አያከራክርም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለባት የገንዝብና የሞያ አቅም ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ የበኩሏን ጥረት እያደረገች እንደመሆኑ መጠን ማኅበሩም በዚህ ረገድ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በማስብ ባሉት የመደበኛና ኢ-መደበኛ አገልጋዮች በየከተሞች ባሉ የሕክምና ማእካላት ውስጥ በመሠማራት በሙያዎቸው የሕክምና አገልግሎት አንዲሰጡ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳውያን የሕክምና ባለሙያዎች በጤናው ዘርፍ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚሆኑበትን ሥልት ቀይሶ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ በተጓዳኝም በቤተ ክርስቲያን መዋቅር የጤና ዘርፍ እንዲጠናከር ስልት ነድፎ አስፈላጊውንም እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አገልጋዮቿ የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። በጤና ዘርፉም ቤተ ክርስቲያን ተጠቃሚ እንድትሆን ሥልታዊ እቅድ አዘጋጅቶ ይሠራል፡፡

ይቆየን!