አዳዲስ አማንያን እየተበተኑ መኾናቸው ተነገረ፡፡

ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ወንጌል ባልተዳረሰባቸው ፳፫ ገጠርና ጠረፋማ አህጉረ ስብከት ላይ ትኩረት አድርጎ ከአህጉረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነቶች፣ ከማእከላትና ወረዳ ማእከላት ጋር በመተባበር አዳዲስ አማንያንን በማስጠመቅ ላይ የሚገኘው በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር በ፳፻፰ ዓ.ም የአገልግሎት ዘመን ዐሥራ አንድ ሺሕ አማንያንን ለማስጠመቅ ዐቅዶ ቢነሣም በእግዚአብሔር ቸርነት ከሃያ ሺሕ በላይ አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

0005

የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብሩ አስተባባሪ አቶ ጌትነት ወርቁ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጹት በቅርቡ ሰኔ ፲፪ እና ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በዳራማሎ ወረዳ ቤተ ክህነት በሌፌ እና በጐጌ ቀበሌዎች በተደረገው የጥምቀት መርሐ ግብር በሌፌ ሁለት ሺሕ ሰባ፤ በጐጌ ደግሞ ሰባት መቶ ሃያ አምስት በድምሩ ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ዘጠና አምስት ሰዎች የሥላሴ ልጅነትን አግኝተዋል፡፡

ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብሩ በአምስት አካባቢዎች ማለትም በግልገል በለስ፣ ያቤሎ፣ ጂንካ፣ ዐርባ ምንጭና ከፋ የጥምቀት አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ የሚገኝ ሲኾን፣ የሰኔውን ወር ጨምሮ በአራት አመታት ውስጥ በእነዚህ ቦታዎች ስድሳ ዘጠኝ ሺህ አዳዲስ አማንያንን በማስተማር እንዲጠመቁ አድርጓል፡፡

0003
ኾኖም ግን የበጀት ማነስ፣ በአካባቢው ቋንቋ የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌልና ካህናት እጥረት፣ እንደዚሁም ምእመናኑ ከተጠመቁ በኋላ ትምህርተ ወንጌል የሚያገኙበት፣ ልጆቻቸዉን ክርስትና የሚያስነሡበትና ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት ቤተ ክርስቲያን በቅርብ አለመኖር የሥላሴ ልጅነትን ያገኙት ምእመናን እንዲበተኑና በመናፍቃን እንዲነጠቁ እያደረጋቸው መኾኑን አስተባባሪው አቶ ጌትነት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በላይ ቍጥር ያላቸው አማንያንን ለማስጠመቅና ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይበልጥ ለማስፋፋት ይቻል ዘንድ መላው ሕዝበ ክርስቲያን ከማኅበሩ ጎን በመቆም የድርሻቸዉን አስተዋጽዖ ቢያበረክቱ የበለጠ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የገለጹት አቶ ጌትነት ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያው የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አዘጋጅቶ እየሠራ መኾኑን ጠቅሰው ለፕሮጀክቶቹ መሳካትም የበጎ አድራጊ ምእመናን ድጋፍ እንዳይለየን ሲሉ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡

በመጨረሻም መርሐ ግብሩን በገንዘብ መደገፍ የሚፈልጉ ምእመናን፣ ለማኅበረ ቅዱሳን ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር በአዋሽ ባንክ ሒሳብ ቍጥር 0130 4024 2244 00 ገቢ በማድረግ እንዲተባበሩ ጠቁመው በተጨማሪም በስልክ ቍጥር 0913 57 48 15 /0911 63 95 52 ስልክ ቢደዉሉ ስለ መርሐ ግብሩ የበለጠ መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡