‹‹አትስረቅ›› (ዘፀ.፳፥፲፭)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ኅዳር ፳፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? እየበረታችሁ ነውን? የመንፈቀ ዓመቱ (የዓመቱ ግማሽ) የትምህርተ ዘመን ሊጠናቀቅ የቀሩት ጥቂት ሳምንታት ናቸው፡፡ ለመሆኑ ምን ያህል ዕውቀት አገኛችሁ? ትናንት የማታውቁት አሁን አዲስ የተጨመረላችሁ ዕውቀት ምንድን ነው? ይህን ራሳችሁን መጠየቅ አለባችሁ? መማራችሁ ከክፍል ወደ ክፍል ለመሸጋገር ብቻ ሳይሆን ባላችሁ ግንዛቤ ላይ ሌላ ዕውቀት ለመጨመር ነውና በርቱ! መማራችሁ ለተሻለ ሕይወት፣ ዛሬን ከትላንትና፣ ነገን ደግሞ ከዛሬ የተሻለ ሆኖ እንድታገኙት ሊሆን ይገባል፡፡ መልካም! ለዛሬ የምንማረው ከዐሥርቱ ትእዛዛት መካከል አንድ ስለሆነው ‹‹አትስረቅ›› ስለሚለው የእግዚአብሔር ሕግ ነው!
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አምላካችን እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ከሰጠው (ከነገረው) ዐሥርቱ ትእዛዛት አንዱ ‹‹አትስረቅ›› ይላል፡፡ ሕዝቡ ታማኝ እንዲሆን፣ የእርሱ ያልሆነውን ነገር እንዳይነካ፣ አንዱ የአንዱን ሰው ንብረት እንዳይወስድ መተማመን እንዲኖር ያዘዘው ትእዛዝ ነው፡፡
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ስርቆት ማለት ምን ማለት መሰላችሁ? ያለ ባለቤቱ ፈቃድ የሰዎችን ንብረት መውሰድ እንዲሁም የራስ ያልሆነን ማንኛውንም ነገር መንካት ነው፡፡ ስርቆት ሰውን ከሚያረክሱት ኃጢአቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሰዎች ወደ ስርቆት የሚገቡት ቸግሯቸው ሊሆን ይችላል! ወይም ደግሞ በልማድ ምንም ነገር ሳያጡ የሰው የሆነ ነገር እያማራቸው በምቀኝኘትም ሊሆን ይችላል።፡ ታዲያ ምንም ይሁን ምን የራስ ያልሆነን መንካት ወይም መውሰድ የእግዚአብሔርን ሕግ መጣስ ነውና በምንም ምክንያት የእኛ ያልሆነውን መንካት የለብንም፤ ቢቸግረን እንኳ አስፈቅደን (ጠይቀን) ልንወስድ ይጋባል እንጂ ሰርቀን መውሰድ የለብንም፡፡
ውድ የእግአብሔር ልጆች! ስርቆት የሚፈጸመው በተለያየ መንገድ ነው፡፡ በጉልበት (በኃይል) ቀምቶ በመውሰድ! ጉልበተኛ የሆነ ሰው የእርሱ ያልሆነውን የሰዎችን ንብረት አስፈራርቶ ቢወስድ ይህ ስርቆት ነው፡፡ ሕገ እግዚአብሔርንም መጣስ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ልጆች! ስርቆት የሚፈጸመው በማታለልና በመዋሸት የራስ ያልሆነን ነገር በመውሰድ ነው፤ እንዲሁም ደግሞ ባለቤቱ ሳያውቅ ተደብቆ ሳያስፈቅድ ቢወስድ ይህም ስርቆት ነው፡፡ ስለዚህ በምንም ምክንያት የእኛ ያልሆነውን ነገር ሁሉ መንካት፣ አታለን፣ ተደብቀን አልያም ቀምተን መውሰድ የለብንም፡፡ ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ምን አልባት ወድቆ እንኳ የምናገኘውን ማንኛውም ነገር ለምሳሌ በትምህርት ቤት እርሳስ፣ እስክርቢቶ፣ መጽሐፍ፣ ላጲስ፣ መቅረጫ እነዚህን የመሳሰሉት ሁሉ ተማሪዎች ረስተው አልያም ወድቆባቸው ብናገኝ ልንመልስላቸው ይገባል፡፡ እነርሱን ባናገኝም ለኃላፊዎች በመስጠት እንዲመለስላቸው ማድረግ ይገባል እንጂ ለራሳችን ወስደን ልንጠቀምበት አይገባም፤ ምክንያቱም የእኛ ያልሆነውን መውሰድ ስርቆት ነውና፡፡ ሁል ጊዜ በሁሉ ቦታ ታማኝ ልንሆን ያስፈልጋል፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! መስረቅ ከእግዚአብሔር መንግሥት ይለያል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከላቸው መልእክቱ ‹‹ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ…የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም..›› ብላል፡፡ (፩ኛቆሮ.፮፥፲) ልጆች! ታዳጊዎች እንደ መሆናችን መጠን ብዙ ነገር ሊያምረን ይችላል! ሆኖም ግን እኛ የሌለን ባልንጀሮቻችን ያላቸውን ነገሮች ስናይ የራሳችን ለማድረግ ብለን መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡ በቤት ውስጥ ወላጅ ሳያውቅና ሳናስፈቅድ ወስደን ለራሳችን የምንጠቀማቸው ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይህ ግን ሊታረም ይገባል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ከለመደብን የሰዎችንና የእኛ ያልሆነውን መመኘት እንለምድና ወደ ስርቆት ልንገባ ስለምንችል በሕይወታችን የእኛ ባልሆነው ነገር ላይ ሁሉ የሰዎችን ፈቃድ ሳናገኝ ንብረታቸውን መንካት የለብንም፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በመጽሐፍ ቅዱስ የብዙ ታማኝ አባቶችንና እናቶችን ታሪክ ላይ ተጽፎ እንደምንናገኘው በመታመናቸውና የሰው ገንዘብ ባለመንካታቸው እግዚአብሔር አክብሯቸዋል፤ ለበለጠ ታላቅ ኃላፊነትም መርጧቸዋል፡፡ የሰውን ገንዘቡ የሚሰርቁ ደግሞ ተቀጥተዋል፡፡ ለምሳሌ ብንመለከት በመጽሐፈ ኢያሱ ላይ አንድ ታሪክ አለ፤ አካን የተባለ ሰው የእርሱ ያልሆነውን ሰረቀና በቤቱ ደበቀ፤ እግዚአብሔር አትንኩ ብሎ ለሕዝቡ የነገረውን ትእዛዝ ተላለፈና ወሰደ፤ በዚህን ጊዜ እስራኤላውያን መከራ ገጠማቸው፤ በጠላቶቻው ተሸነፉ፡፡ ከዚያም መስፍኑ ኢያሱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ለኢያሱ መከራ የገጠማችሁ ከመካከላቸው የሰረቀ ሰው ስላለ መሆኑን ነገረው፡፡ ከዚያም ልጆች! ኢያሱ ፈልጎ ያንን የሰረቀ ሰው አገኘውና አስቀጣው፡፡ እግዚአብሔርም እስራኤላውያንን ከመከራ ጠበቃቸው፤ ጠላቶቻቸውን ድል አደረጉ፡፡ (ኢያ.፯፥፩ እስከ መጨረሻው) ልጆች! የስርቆትን ከባድነት አያችሁ? ስለዚህ ስርቆትን መጠየፍ አለብን፡፡ እኛ ታዳጊዎች ነገ አድገን ታላቅ ኃላፊነት ላይ የምንሾም ስለሆነ ከልጅነታችን ጀምሮ ስርቆትን ከሕይወታችን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡
ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እስከዛሬ ስርቆት ሳይመስለን የሰዎችን ንብረት ስንወስድ ከነበረ ከአሁን በኋላ ታማኞች ልንሆን ይገባናል! መማራችንና ማወቃችን ሰዎችን ልንደግፍና ልንረዳበት ነውና የእኛ ያልሆነውን በመውሰድ ሰዎችን ልናስከፋና ልናሳዝን አይገባም፡፡ የሚያስፈልገን ነገር ካለ ለወላጆቻችን፣ ለታላላቅ ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችንና መምህራኖቻችን በመንገር እንዲያሟሉልን መጠየቅ አለብን እንጂ ተደብቀን የእኛ ያልሆነውን መውሰድ የለብንም፡፡
ልጆች ለዛሬ ይብቃን! ትምህርቱን ተረድታችሁ እንደምትተገብሩት ተስፋችን ነው! ለሚቀጥለው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስከምንገናኝ ድረስ ሰላም ሰንብቱ!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!