“አትሮንስ” የመጻሕፍት ውይይት መርሐ ግብር ሊጀመር ነው

 ጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. 

በእንዳለ ደምስስ

books 26ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መጻሕፍት የንባብ ባሕልን ለማዳበር በየደረጃው ከሚሠራቸው ተግባራት በተጨማሪ “አትሮንስ” የተሰኘ በመጻሕፍት ላይ የሚደረግ የውይይት መርሐ ግብር ኅዳር 1 ቀን 2006 ዓ. ም. በማኅበሩ ኤዲቶሪያል ቦርድ አስተባባሪነት ይጀመራል፡፡

ንባብ ዕውቀትን ለማዳበር፤ አስተሳሰብን ለማስፋት፤ ሚዛናዊ ብያኔን ለመሥጠት፤ የአባቶችን ሕይወትና ትምህርት ለማወቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጸው የኤዲቶሪያል ቦርድ ክፍል፤ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ማንበብ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኛ መንገድን የሚጠርግና ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን በመገንዘብ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

የመርሐ ግብሩ ዋነኛ ዓላማም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱ የነገረ ሃይማኖት፤ የታሪክና የአስተዳደር መጻሕፍትን ማስተዋወቅ፤ የመንፈሳዊ መጻሕፍት የንባብ ባሕልን ማዳበር፤ በንባብ ባሕል ላይ የላቀ ልምድ ያላቸውን ሊቃውንት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ማድረግ፤ በመንፈሳዊ መጻሕፍት ላይ የውይይት ባሕልን ማሳደግና የልምድ ልውውጥን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ የተዘጋጀ መርሐ ግብር መሆኑን ከማኅበሩ ኤዲቶሪል ቦርድ ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

መርሐ ግብሩ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል በኤዲቶሪያል ቦርድ የመጻሕፍት አርትዖት ክፍል ሥር ራሱን የቻለ ማስተባበሪያ ሆኖ እንደሚደራጅ የተገለጸ ሲሆን ዕቅድና ሪፖርት፤ አስፈላጊው በጀትም እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡

“አትሮንስ” የመጻሕፍት ውይይት መርሐ ግብር ወር በገባ በመጀመሪያው እሑድ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡00 ሰዓት በማኅበሩ ሕንፃ ላይ በየወሩ እንደሚዘጋጅ ክፍሉ አስታውቋል፡፡ ኅዳር 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በሚካሄደው መርሐ ግብርም “የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” የተሰኘውና በረዳት ፕሮፌሰር ሉሌ መላኩ የተጻፈው መጽሐፍ ውይይት ይካሄድበታል፡፡

ምእመናን በተጠቀሰው ቀን፤ ሰዓትና ቦታ በመገኘት መርሐ ግብሩን መከታተል እንደሚችሉም የማኅበረ ቅዱሳን የኤዲቶሪያል ቦርድ ክፍል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡