አባቶቻችን ለዕርቅ አርአያ በመሆናቸው ዘመኑን ዋጅተዋል

 

ማስታረቅና ማስማማት ከሰላም መሪ የሚገኝ አርአያነት ያለው ተግባር ነው ይቅር ማለትም እንደዚሁ፡፡ በዓለም ላይ ተቈጥረው የማያልቁ ጦርነቶች ቢካሔዱም ለጊዜው የተሸነፈ የመሰለው ጊዜ እስከሚያገኝ አድፍጦ እንዲቆይ ማድረግ ቻለ እንጂ አማናዊ ሰላም ማምጣት አልቻለም፡፡ አንዱ ሌላውን ሲወር፣ አንዱ ሌላውን ሲያስገብር ኖሯል፡፡ አባቶቻችን ዘመኑን ሲዋጁ የኖሩት ዕርቅ በማድረግ የተለያዩትን በማስማማት ነው፡፡

የጦርነት ውጤቱ ቂምና በቀል ሲሆን የዕርቅ ውጤቱ ሰላም ነው፡፡ ቂምና በቀል የሚያመጣው ዕርቅና ሰላም መፍጠር ብቻ መሆኑን መንፈሳውያንም ሥጋውያንም መጻሕፍት ያስተምራሉ፡፡ በዚህ ምድር የሚያስተዳድሩ መንግሥታት ሳይቀር ከጥል ምንም ጥቅም እንደማያገኙ እየተረዱት መጥተዋል፡፡ የሃይማኖት ሰዎች ደግሞ ሰላም መፍጠር ከአምላካቸው የተቀበሉት በመሆኑ በተግባር ሲፈጽሙት ኖረዋል፡፡ ክርስቲያኖች ከአምላካቸው የተቀበሉት ይቅር ማለትን በተለያዩት መካከል አንድነት፣ በተጣሉት መካከል ሰላም መፍጠርን አባቶቻችን ዕርቅ መፈጸማቸው ለቤተ ክርስቲያን ያለውን በቊዔት በቃላት ገልጦ መጨረስ አይቻልም፡፡ ዓለምን መዋጀት የቻሉትና ንግግራቸው ተቀባይነት ሲያገኝ የኖረው ሰላማውያን፣ ይቅር ባዮች፣ የትሕትና ሰዎች በመሆናቸው ነው፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር በድለነው ሳለ ይቅር ያለን እኛም የበደሉንን ይቅር ብለን አርአያውን ለመከተል እንድንችል ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመውን ለሌሎች ማስተማር እና በተግባር መግለጥ ከአባቶች የሚጠበቅ በመሆኑ አሁን የተፈጸመውም መልካም ነው፡፡ የምንናገረው ፍሬ የሚያፈራው ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ትሕትና፣ ስለ ይቅር ባይነት የምናስተምረውን በተግባር መግለጥ ስንችል ነው፡፡ የያዝነው እውነት፣ የተናገርነው ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ስለ ባልንጀራ ድካም ብሎ መተው፣ ዝቅ ብሎ በትሕትና ለሰላም መገኘት አርአያ መሆን ከሃይማኖት ሰው የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ይህን የምንለው ሃይማኖታችን የተመሠረተው በፍቅርና በትሕትና በመሆኑ አሁን የተፈጸመው ዕርቅም የወንጌሉ ቃል በተግባር መፈጸሙን ያሳያል ብለን ስለምናምን ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ግማሽ መንገድ በመሔድ የሚጠበቅባቸውን መፈጸማቸው ወደ ፊት የሚከሠት ነገርም በትሕትና ይሸነፋል፡፡ በዚህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን ትጠቀማለች፡፡

ዘመኑ የሚጠይቀው ከአምላካችን የተቀበልነውንና ቀደምት አባቶቻችን ያስተማሩንን በተግባር በመግለጥ ሰላማዊነታችንንና የሰላም ምንጭ የሆነ ሃይማኖት ያለን መሆናችንን ለማስመስከር ሰላማችን ዘላቂነት እንዲኖረው የሚያደርግ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ሌሎችን ይቅር ለማለት ትሕትና ያስፈልጋልና፡፡ ይቅር በማለታችን ሀገር ሰላም ታገኛለች፡፡ ይህም በተግባር መታየት ጀምሯል፡፡ በዚህ ተግባራችንም በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ እንከበራለን፤ ታሪክም በመልካም ሲያነሣን ይኖራል፡፡ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ዓለም የምታስታውሰው መልካም የሠሩትን ነውና፡፡

የእምነት አባቶች ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓለ ብለው በድፍረት መናገርና የተሳሳተውን መገሠጽ የሚችሉት የበደላቸውን ይቅር ሲሉ፣ እግዚአብሔርን የበደለውን ከእግዚአብሔር ሲያስታርቁ ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ እምነት ያለውም የሌለውም የሚናገሩትን ይሰማል፤ አድርግ ያሉትን ያደርጋል፡፡ ይህም ባይሆን ምክንያት እናሳጣዋለን፡፡ ከእምነት የወጣሁት እንዲህ ስለሆነ ነው እንዳይል ያደርጋል፡፡ ሰሞኑን አሜሪካና ኢትዮጵያ የሚገኙ አባቶች ዕርቅ በመፈጸማቸውም ከርትዕት ሃይማኖት ወጥተው የነበሩ ይመለሳሉ፡፡ በእምነትም ይጠናሉ፡፡

ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት በተፈጠረ ታሪካዊ ክሥተት በአባቶች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ አለመግባባቱ የሃይማኖት ልዩነት ባለመሆኑም አባቶቻችን ተወያይተው ለመስማማት በቅተዋል፡፡ ሰማይ ተቀደደ ቢለው ሽማግሌ ይሰፋዋል አለ እየተባለ የሚጠቀሰው የአበው ንግግር መፍትሔ የሌለው ችግር፣ ዕርቅ የማይፈታው ልዩነት አለመኖሩን ያሳያል፡፡ የተጣሉ ሲታረቁ፣ የታሠሩት ሲፈቱ፣ የተለያዩ አንድ ሲሆኑ እየተመለከትን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገርም ለቤተ ክርስቲያንም ታላቅ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በተደጋጋሚ ልዑክ እየላከች ዕርቁ ተግባራዊ እንዲሆን ስታደርግ ቆይታ ጊዜው ሲደርስ ዛሬ እውን ሆኖ አየን፡፡

የቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋ ሰላምን ማብሠር፣ ለተጨነቁት መፍትሔ መስጠት፣ የተለያዩትን አንድ ማድረግ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ሆኖ ተከታቹን የዓለም ብርሃን ያስባላቸው ሰላማውያን፣ ይቅር ባዮች፣ ለሌላው ሲሉ ራሳቸውን ሳይቀር አሳልፈው የሚሰጡ በመሆናቸው ነው፡፡ ታላቁ ቴዎዶስዮስ አሠርቶት የነበረውን ሐውልት ሕዝበ ክርስቲያኑ በብስጭት ባፈረሰው ጊዜ ንጉሡን በምክርም በተግሣጽም ይቅር እንዲል ያደረገው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡ ይህም ንጉሡም የሚመራውን ሕዝብ ጨፍጭፎ በታሪክ እንዳይወቀስ፣ ቅዱሱም በደል ሲፈጸም ፈርቶ ዝም አለ ተብሎ እንዳይተች አድርጎታል፡፡

ቂርቆስና ኢየሉጣ ከእሳት በወጡበት በብሥራተ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል የመታሰቢያ ዕለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድ ሆነዋል፡፡ በዚህም የምእመናን ተስፋ ለምልሟል፡፡ የጥል ግድግዳ ፈርሷል፡፡ ይህ ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር የተፈጸመበት ዕለት ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ የደስታ ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጋት ጥይቱን የጨረሰበት፣ ዝናሩን አራግፎ ባዶ እጁን የቀረበት ነው፡፡ ዕለቱ የሰይጣን ጥርሱ የረገፈበትና የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ለዓለም የተገለጠበት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን የደስታ ቀን ነው፡፡

ለዚህ ዕለት ደርሶ የተገኘውን ዕርቅ አይቶ የማይደሰት ቢኖር ዲያብሎስ ብቻ ነው፡፡ ዕርቁ እውን እንዲሆን መለያየት እንዲወገድ፤ የተፈጠረው ክፍተት መፍትሔ እንዲያገኝ ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ዕርቁ እውን እንዲሆን በቅን ልቡና የተቀበላችሁ ሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮቻችን የፈረሰውን አንድነት በዘመነ ፕትርክናችሁ ለመጠገን፤ የተለያየውን አንድ ለማድረግ፤ የሻከረውን ለማለስለስ ያበቃችሁ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ አባቶቻችንን ለዕርቅ ያበቋቸውን ምክንያቶች እንደሚከለው እናቀርባለን፡፡

  1. ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ቅድሚያ መስጠታቸው፡- የሃይማኖት አባት በእግዚአብሔርና በምእመናን መካከል የሚገኝ ድልድይ ነው፡፡ አባቶች የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሕዝበ ክርስቲያን የሚያደርሱ፣ የሕዝቡን ጸሎትና ይቅርታ ጠያቂነት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ናቸው፡፡ በደል ሲፈጸምም ምህላ ይዘው፣ መሥዋዕት አቅርበው ለአባቶቻችን ስለገባህላቸው ቃል ኪዳን ብለህ ይቅር በለን በማለት ለምነው ይቅርታ ያሰጣሉ፡፡ ይህ ተግባርም ያላመኑትን ስቦ በማምጣት የድኅነት ተካፋይ፣ እንዲሆኑ ከሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ሲያደርግ ኖሯር፡፡ አሁን የተፈጠረው ሰላምም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማጠናከርም ያግዛል፡፡

የሃይማኖት አባት ተቀዳሚ ተልእኮ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ ነው፡፡ በክርስቶስ ደም የተዋጀች ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃን ስትሆን ኖራለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን የአባቶችን ተልእኮ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠበቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከእኔ በኋላ ለመንጋይቱ የማይራሩ ነጣቂዎች ተኲላዎች እንደሚመጡ እኔ አውቃለሁ” (ሐዋ. ፳፥፳፰-፳፱) በማለት ገልጦታል፡፡ ከዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተዋጀችውና የተመሠረተችው እስከ ሞት ድረስ በወደዳት በክርስቶስ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ተጠብቃ የኖረችውና ወደፊትም እስከ ምጽአት የምትኖረው በግብር አምላካቸውን በሚመስሉ፣ አሠረፍኖቱን በተከተሉ አባቶች መሆኑን ሐዋርያው ነግሮናል፡፡ አባቶች ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ፣ ምእመናንን ለመከባከብ ሓላፊነት የሰጣቸው እግዚአብሔር መሆኑንም ያስገነዝባል፡፡

አባቶች ሌላውን እንዲጠብቁ ሓላፊነት ሲሰጣቸው ራሳቸውን በመጠበቅ፣ ለሌላው እንቅፋት ላለመሆን በመጠንቀቅ፣ ምእመናንን ነጣቂ እንዳይወስዳቸው ንቁ ሆነው እንዲጠብቁ በማሳሰብ ነው፡፡ ዕርቅ ለማድረግ የተሰለፉ አባቶችም ይህንን ሁሉ በማሰብ የፈጸሙት፣ ሓላፊነተቻውን ለመወጣትና ከተጠያቂነት ነፃ ለመሆን ያከናወኑት መልካም ተግባር ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ለምእመናን ሕይወት መጨነቅ ይህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ለምእመናን ነውና፡፡ የካህናትንና የአባቶችን ግንኙነት ነቢዩ “ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍህን ታድናለህ” (ሕዝ. ፴፫፥፱) በማለት ገልጦታል፡፡ አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ቅድሚያ በመስጠታቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ቅዱሳን ፓትርያኮች በዘመናቸው ሰላም መፈጸሙ እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወዳቸው ማስገንዘቢያ ነው፡፡

  1. ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዘመኑ የሚጠይቀውን መፍትሔ መስጠታቸው፡- ቅድስት ቤት ክርስቲያን የምትመራው በቀኖና ነው፡፡ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ የምእመናን መጠበቅ፣ የዶግማ መጠበቅ ነው፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመው የተጣሰውን ቀኖና እንዴት መፍተሔ እናብጅለት የሚለው በመሆኑ ከሁለቱም ወገን ለዕርቅ የተመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መፍትሔ ሰጥተዋል፡፡ ወደፊት በአንድ ላይ እየተወያዩ ለሌሎች ችግሮችም መፍትሔ እንደሚሰጡ ማመን ይገባል፡፡ የአንጾኪያ፣ የቊስጥንጥንያ፣ የግብፅ አብያተ ክርስቲያናት ችግር በገጠማቸው ጊዜ መፍትሔ እንደሰጡት ቤተ ክርስቲያናችንም ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ሰጥታለች፡፡ እንኳን እግዚአብሔርን የያዙ አባቶቻችን እምነት የሌላቸውም በሕገ ተፈጥሮ ተመራምረውና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ዕውቀት ተጠቅመው ሰውን ከሰው ያስታርቃሉ፡፡ ሽማግሌዎች ሰውን ከሰው ካስታረቁ፣ በመገዳደል የሚፈላለጉትን ደም ካደረቁ የሃይማኖት አባቶች ከዚያ በላይ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከተፈጠረው ችግር የበለጠ ቤተ ክርስቲያንን የጎዳትና ምእመናንን ያለያያቸው ለችግሩ ያለን አመለካከት ነበር፡፡ ይህ አሁን ተወግዷል፡፡

ለዕርቀ ሰላሙ የተወከሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደፊት መከናወን ስላለበት ጉዳይ እንዲህ ብለዋል፡- “ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት የተነሣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃለች። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እንደ ተፈጸመ በልኡካኑ ታምኖበታል። ስለሆነም ለአለፉት ዘመናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር በመጠበቅና በማስጠበቅ በውጭም ሆነ በውስጥ በአገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉና ከጊዜው ጋራ አብሮ ባለመሔዱ፣ ስለተፈጸመው ጥፋትና ለዘመናት በቤተ ክርስቲያኒቱ መለያየት የተነሣ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ያለፉትንም ሆነ ዛሬ ላይ ያሉትን በጋራ ይቅርታ እንዲጠይቅ የልኡካኑ ጉባኤ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።

ስለሆነም ከሁለቱም ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ ያለፈው የቀኖና ጥሰት ስሕተት ለወደፊቱ እንዳይደገም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሉዓላዊነት ተጠብቆና ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረገ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲዘጋጅ የልኡካኑ ጉባኤ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።”

  1. ለምእመናን ሕይወት መጨነቃቸው፡- ለምእመን ሕይወት መጨነቅ የአባቶች ተግባር ነው፡፡ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፣ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ የሚጠቀሱት ለምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ለኑሮዋቸውም የሚጨቁ ስለነበሩ ቤተ ክርስቲያን በመልካም ታነሣቸዋለች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የደሀ ጠበቃ የተባለው ንግሥት አውዶክሶያ የድሀይቱን ርስት በቀማቻት ጊዜ እንድትመልስላት ደጋግሞ መክሯታል፡፡ ንግሥቲቱ አልመልስም ባለች ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ከምእመናን ኅብረት አውግዞ ለይቷታል፡፡ በዚህም የድሀ ጠበቃ ተብሏል፤ ለምእመናን ሕይወት የሚነጨቅ መሆኑንም በተግባር ገልጧል፡፡ ለምእመናን ሕይወትም ለአባቶች ታዛዥነትንም አጣምሮ መያዝ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲለመልም ትሩፋታችን ፍሬ እንዲያፈራ ያደርጋል፡፡

የአባት ተግባር ለመንጋው መንፈሳዊ ሕይወት መጠንከር ነቅቶ ማገልገል በመንጋው ሕይወት መዛል ላለመጠየቅ ሓላፊነትን መወጣት ነው፡፡ አባቶች ሹመት ሲመጣባቸው በገድል ላይ ገድል፣ በትሩፋት ላይ ትሩፋት የሚጨምሩት ለሌላው እንቅፋት ላለመሆንና እነሱ በፈጸሙት ጥቂት ስሕተት ምእመናን ተሰነካክለው ከሃይማኖት እንዳይወጡ በማሳብ ነው፡፡ ሹመትን የሚሸሹትም በሌሎች ውድቀት ተጠያቂ ላለመሆን ነው፡፡ እግዚአብሔር ካላስገደዳቸውና ምእመናን ካላለቀሱባቸው ሹመቱን በጅ ብለው አይቀበሉም፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ሹመቱ ኃላፊ የእነሱ ዓላማ ግን ዘለዓለማዊ በመሆኑ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ መርጧቸው ምእመናንን ለመጠበቅ በተሾሙበት ተጠያቂ ላለመሆን ምክንያት መፍጠር ዘለዓለማዊውን በጊዜያዊው መለወጥ መሆኑን ስለተረዱት ነው፡፡ አባቶች ለምእመናን ሕይወት የሚጨነቁ ከሆነም ምእመናንም አብረው ይሰደዳሉ፡፡ ወደ እግዚአብሔር አልቅሰው ለመንበራቸው እንዲበቁ ያደርጋሉ፡፡

የዕርቁ ተግባራዊ መሆን ሌትም ቀንም በጸሎት እግዚአብሔርን ሲለምኑ ለኖሩ ወደፊትም ለሚለምኑ ገዳማውያንም ተስፋ የሚሰጥ ለጸሎታቸው እግዚአብሔር መፍትሔ መስጠቱን ማረጋገጫ ነው፡፡ ገዳማውያን አባቶች እግዚአብሔር ለሀገራችንም ለቤተ ክርስቲያናችንም ምሕረት እንዲያወርድ ይለምናሉ፡፡ በአባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት መፍትሔ እንዲያገኝ ኢትዮጵያም አሜሪካም ለሚገኙ አባቶች የጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡

“እስከ ዛሬ ችግሩ ባለመፈታቱ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ስላሳሰበንና ለትውልዱም መለያየትን አውርሰን እኛም እናንተም የታሪክ ተወቃሽ ከመሆንና በእግዚአብሔር ዘንድም ዋጋ የሚያሳጣ ሥራ ይዘን መቅረብ ስለሌለብን ይህ ጉዳይ በበረሃ በወደቁና በዝጉሐን ገዳማውያን አባቶች ተመክሮበት፣ ታምኖበትና ተጸልዮበት የተላከ መልእክት ስለሆነ እስከ አሁን የተደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው የምንመኘው አንድነት አማናዊ ሆኖ ለማየት እንችል ዘንድ በዚህ መንገድ ላይ የሚያጋጥሙ ማናቸውንም መሰናክሎች ሁሉ አልፋችሁና አሸንፋችሁ የምንናፍቀውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ታሳዩን ዘንድ የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን ሥልጣን በሰጣችሁና ዓለሙን በደሙ በዋጃት በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ስም እንዲሁም ገዳማትን በመሠረቷቸው በታላላቆቹ አባቶቻችን በአቡነ አረጋዊ፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዓ፣ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ በአቡነ ዜና ማርቆስ፣ በአቡነ ሳሙኤል፣ በአቡነ ያሳይ፣ በአቡነ ዐምደ ሥላሴ፣ በአቡነ ዘዮሐንስ፣ በአቡነ ኂሩተ አምላክ፣ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንዲሁም ስማቸውን ባልጠራናቸው በሌሎችም ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ስም ተማጽኗችንን እናቀርባለን” በማለት ተማጽነው ነበር፡፡ ከእንግዲህ ሰላም እንዲፈጠር ላደረገው እግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባሉ፡፡

  1. ዘመኑን መዋጀታቸው፡- እስከ አሁን የሚለያዩን እንጂ አንድ የሚያደርጉን፣ የሚጣሉን እንጂ የሚያስታርቁን ምክንያቶች ጥቂት ነበሩ፡፡ አሁን ሁኔታዎች በመለወጣቸው አባቶቻችንም ዘመኑን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ተጠቅመውታል፡፡ ይህንንም ጊዜ መጠቀምና ጽኑ መሠረት ገንብቶ ማለፍ ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን ተረድተዋል፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃ ቆይታ ነበር፡፡ ፈተናውን እንደ መልካም አጋጣሚ ከተመለከትነውና ለወደፊቱ ጽኑ መሠረት ካስቀመጥን ተዳክሞ የነበረው ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲጠናከር፣ ወደፊት ለሚመጣውም ትውልድ ማስተማሪያ ሊሆን የሚችል ሥራ መሥራት ያስችላል፡፡ ዘመኑን ተጠቅመን ሥራ ከሠራንበት እንደምንመሰገን ሐዋርያው “እንዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ፡፡

ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት፡፡ ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ” (ኤፌ. ፭፥፲፭-፲፯) በማለት ምክሮናል፡፡ የሃይማኖት ሰው ትላንት የተከናወነውን፣ ዛሬ በመተግበር ላይ ያለውን፣ ነገ ሊፈጸም የሚገባውን መረዳት ይቻለዋል፡፡ ለዚህ ነው ከስንት ሺሕ ዘመን በፊት የተነገረው ልክ ዛሬ የተፈጸመ ያህል ችግራችንን ሲፈታ ሕይወታችንን ሲያንጽ የሚገኘው፡፡ አባቶቻችንም በዚህ ሁሉ ነገር በፍጥነት በሚለዋወጥበት ዘመን ትውልዱ እንዲረጋጋ፣ ከቤተ ክርስቲያን የራቀው እንዲቀርብ የሚያደርግ ሥራ መሥራት ችለዋል፡፡ የተጀመረው ፍጻሜ እንዲያገኝ እግዚአብሔር ይርዳን እንላለን፡፡

  1. በታሪክ ከመወቀስ ራሳቸውን ነፃ በማውጣታቸው፡- በየዘመናቱ የተፈጸሙትን እያነሣን ተዋንያን የነበሩትን የምንተቸውም የምናመሰግነውም ለጥፋቱም ለልማቱም ተጠያቂ ስለነበሩ ነው፡፡ አባቶች መልካም እየሠሩ ቢወቀሱ ክብር ይሆናቸዋል፡፡ ለጥፋት ተባባሪ ከሆኑ ግን የሠሩት ተገለጠ እንጂ ሐሜት ደረሰባቸው፣ ተወቀሱ አያሰኝም፡፡ ለጊዜያዊ ጥቅም፣ ነገ ለሚያልፍ ሹመት ታሪክም እግዚአብሔርም እንዲወቅሳቸው ራሳቸውን ያደከሙ በታሪክ ተከሥተው አልፈዋል፡፡ በዘመኑ የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው ዕርቅ ለመፈጸም ሀገር ውስጥ ያሉ አባቶች ያስተላለፉት መግለጫ መልካም ነው፡፡ ውጭ ያሉትም ለዕርቅ የተወከሉትን አባቶች የተቀበሉበት መንገድ ከእስከ አሁኑ የተለየና ምእመናንን ያስደሰተ ነው፡፡ ይህም አባቶቻችን ዘመኑን እየቀደሙት መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ የተጀመረው ከዳር እንዲደርስና የልዩነት አጥር እንዲፈርስ አድርጓል፡፡ በትሕትና ከቀረብንና እግዚአብሔርን ካስቀደምን የማይፈታ ችግር አለመኖሩንም አሳይቷል፡፡

አባቶቻችን እንኳን የእምነት ልዩነት ለሌላቸው በእምነት የሚለዩትንም በፍቅር ስበው የቤተ ክርስቲያን አካል ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ ይህ የአባቶች ተግባር እስከ ምጽአት የሚቀጥል ነው፡፡ አንድን መነናዊ ወደ ክርስትና ስለመለሰው አንድ አባት የተጻፈውን በተግባር መፈጸም ዜና አበው የተሰኘው መጽሐፍ “በግብፅ ውሰጥ በበረሃ የሚኖር አንድ ቅዱስ ሰው ነበር፡፡ ከእርሱ ርቆ ደግሞ መነናዊ የሆነ (የማኒ እምነት ተከታይ) እነሱ ካህን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ይህ ሰው ከመሰሎቹ አንዱን ሊጠይቅ ሲሔድ ኦርቶዶክሳዊው ቅዱስ ከሚኖርበት ቦታ ላይ ሲደርስ መሸበት፡፡ ሆኖም መነናዊ መሆኑ እንደሚታወቅ ስላወቀ ወደዚህ ኦርቶዶክሳዊ አባት ብሔድ አይቀበለኝም በማለት በጣም ተጨነቀ፡፡ ሆኖም ምንም አማራጭ ስላልነበረው ሔደና አንኳኳ፡፡ አረጋዊውም አባት በሩን ከፈተለት፡፡ እርሱም ማንነቱን አወቀው፡፡ ደስ ብሎት በፍቅር ተቀበለው፡፡ ምግብ ከሰጠው በኋላ አስተኛው፡፡

መነናዊውም ሰው ሌሊት ይህን ሁኔታ ሲያሰላስል አደረና ስለ እኔ ምንም ያልጠረጠረው እንዴት ዓይነት ሰው ቢሆን ነው? በእውነት ይህ ሰው የእግዚአብሔር ሰው ነው አለ፡፡ ሲነጋም ከእግሩ ላይ ወድቆ ከአሁን በኋላ እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ አለው፡፡ ከእርሱም ጋር ኖረ” በማለት ያስነብበናል፡፡ ይህ አባት ላለማስገባት የሚያግዘውን በመጥቀስ መከልከል ይችል ነበር፡፡ ብርሃን መሆንን መረጠና መነናዊውን ወደ በዓቱ አስገባው፡፡ መነናዊውም በብርሃኑ ተማርኮ ከብርሃኑ ጋር ኖረ፡፡ በዘመናችን መፈጸም የሚያስፈልገውም እንዲህ ዓይነት የብርሃን ሥራ ነው፡፡ ዘመኑን መዋጀት፣ የተማሩትን በሕይወት መግለጥ ማለትም ይህ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አባቶቻችን ያደርጉትም መልካም ነው፡፡ የምእመናን ተስፋ እንደለመለመ ማሳያ ነው፡፡

  1. መለያየት ለመናፍቃን በር እንደሚከፍት በመረዳታቸው፡- መለያየት የሚጠቅመው ለሰይጣን ብቻ አይደለም፡፡ የግብር ልጆቹ፣ የዓላማ አስፈጻሚዎቹ ለሆኑትም ጭምር እንጂ፡፡ ያልተባለውን የተባለ እያስመሰሉ፣ ያልተነገረውን ተነገረ እያሉ የአባቶችን ልብ ሊያሻክሩ፣ ልዩነቱን ሊያሰፉ ይችሉ የነበሩ መናፍቃን ከእንግዲህ ዐርፈው ይቀመጣሉ፡፡ አባቶቻችን በመስማማታቸው የሰይጣንም የመናፍቃንም ቅስም ተሰብሯል፡፡ ለአባቶች ያሰቡ፣ ለቤተ ክርስቲያን የተቆረቆሩ እየመሰሉ ምዕራባውያን የጫኗቸውን በቤተ ክርስቲያን ላይ ለማራገፍ ሲሞክሩ ነበር፡፡ ልዩነቱም ለጥፋት ተልእኳቸው ሲያግዛቸው ነበር፡፡ ምእመናን በማይጠቅም ጉዳይ ጊዜያቸውን እንዲያባክኑ፣ አባቶች በአንድ ላይ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ተግባር እንዳይፈጽሙ ዕንቅፋት ሲፈጥሩ ቢቆዩም አሁን እንቅፋቷ ተወግዷል፡፡ ለወደፊቱም አባቶቻችን እየተመካከሩ ምእመናን በእምነት እንዲጸኑ፣ ያላመኑት እንዲያምኑ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ከእስከ አሁኑ የበለጠ ያጠናክሩታል ብለን እናመንለን፡፡

ዕርቁ በመፈጸሙ ምክንያት አጥተዋል፡፡ አባቶች በፍቅር ተገናኝተው አብረው ጸሎት በማድረጋቸው ለልዩነት ምክንያት የሆነው ሰይጣን አፍሯል፡፡ የሰይጣን ዓይን የሚጠፋው ክንፉ የሚሰበረው አባ ጊዮርጊስ እንዳለው በጸሎትና በፍቅር ነው፡፡ ጸሎት መራጃ ነውና የጠላትን ወገብ ይሰብረዋል፡፡ ጸሎትም ጦር ነውና ዓይኑን ይወጋዋል፡፡ የአባቶች አንድ መሆን ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ደስታ ሲሆን ለጠላት ግን ኀዘን ነው፡፡ በየዋህነት ከቤተ ክርስቲያን የወጡትን ለመመለስ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ከእንግዲህ መንገዱ ምቹ ይሆናል፡፡ አሜሪካም ኢትዮጵያም የሚገኙ አባቶች ይህን ሁሉ አስበው ለዕርቁ ተግባራዊ መሆን የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡ የወደፊቱ አገልግሎት እንዲቃና ምእመናን በጸሎት፣ ሊቃውንት በምከር ሊያግዙ ይገባል እንላለን፡፡ የተጀመረው ለፍጻሜ እንዲደርስ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ረድኤት አይለየን፡፡

ምንጭ-ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከነሐሴ 1-15ቀን 2010ዓ.ም