አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
ጻድቁ አቡነ እስትንፋስ ክርስቶስ የስማቸው ትርጓሜ ‹‹የክርስቶስ፣ የአብ፣ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ›› ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊታቸው ላይ እፍ ብሎ ጸጋውን፣ በረከቱን ስላሳደረባቸው በዚህ ስም ይጠራሉ፡፡ የጻድቁ፣ አባታቸው መልአከ ምክሩ፤ እናታቸው ወለተ ማርያም ይባላሉ፡፡ የትውልድ ቦታቸው በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ዳውንት ዐወን ዓባይ የተባለ አካባቢ ነው፡፡ የተፀነሱት ሚያዝያ ፰፤ የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ ፰ ቀን ነው፡፡
በተወለዱ ዕለት በእግራቸው ቆመው ሦስት ጊዜ ‹‹ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ›› በማለት እግዚአብሔርን አመሰግነዋል፡፡ የሕፃናትን አንደበት ለሚያናግሩ፣ ለሥላሴ እና ለእመቤታችን እንደዚሁም ለክርስቶስ መስቀል ዘጠኝ ጊዜ ሰግደዋል፡፡ በልጅነታቸው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትለጽላቸው ነበር፡፡ ያደጉትም የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃቸው ነው፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜም የመጻሕፍት ዂሉ ርእስ የሚኾን ፊደልንና የሐዋርያው ዮሐንስን መልእክት ደብረ ድባ በሚባል ቦታ ከመምህር ኪራኮስ ተምረዋል፡፡ የሐዋርያትን ሥራ፣ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት፣ የዳዊትን መዝሙር፣ እንደዚሁም ትርጓሜ መጻሕፍትን ተምረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በዘመኑ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የዲቁና መዓርግ ተቀበሉ፡፡ ከዚያም በሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም መነኰሱ፡፡ ከዚያም ወደ ሕንጻ ደብረ ድባ ሔደው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት፣ የገዳማት አለቃ፣ የመነኮሳት አባት ከሚኾን ከአባ ሙሴ መዓርገ ቅስና፣ ቍምስና እና ኤጲስ ቆጶስነት በቅደም ተከተል ተቀብለዋል፡፡
አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ፣ ዐቢይ ጾምን ዐርባ ሌሊትና ዐርባ ቀን እኽልን ውኃ ሳይቀምሱ ይጾሙ ነበር፡፡ እግሮቻቸው እስኪያብጡ ድረስ ቆመው ይጸልዩ ነበር፡፡ ለሽፋሽፍቶቻቸውም ዕረፍትን አይሰጡአቸውም ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ገዳም ሲሔዱ ወደ ገዳሙ ለመግባት ሐይቁን የሚያሻግራቸው ቢያጡ ተንበርክከው ሲጸልዩ በቅዱስ ሚካኤል እጅ ደንገል (ታንኳ) ቀርቦላቸው ሐይቁን ተሻግረዋል፡፡ ዘጠኝ ዓመት ዓባይ ባሕር ውስጥ በራሳቸው ተዘቅዝቀው በመቆም ለኢትዮጵያ ሲጸልዩ ከቆዩ በኋላ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሳቸው መጥቶ ‹‹ከመነኮሳት ዂሉ ብልጫ ያለህ ወዳጄ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ፥ ኢትዮጵያን ምሬልሃለሁና ከዚህ ባሕር ውጣ›› ብሏቸዋል፡፡ ከዚያም ማረፊያቸው ወደ ኾነች ዳውንት (ደብረ አስጋጅ) በመመለስ ዐሥራ ሰባት ገዳማትን መሥርተዋል፡፡
ወደ ደብረ ዳሞ በሔዱ ጊዜም በትእምርተ መስቀል አማትበው ያለ ገመድ ከደብረ ዳሞ ተራራ ላይ በመውጣት ከአቡነ አረጋዊ ጋር (ከተሰወሩበት ቦት መጥተው) ተገናኝተዋል፡፡
በየገዳማቱ ሲዘዋወሩ ከሞላ ውኃ በደረሱ ጊዜ በመስቀል ምልክት አማትበው በእግራቸው እንደ ደረቅ መሬት እየረገጡ ይሻገሩ ነበር፡፡ አምስት አንበሶችና አምስት ነብሮች ይከተሏቸው ነበር፤ እነዚያም አንበሶችና ነብሮች የሚመገቡትን ባጡ ጊዜ ድንጋዩን ባርከው ሥጋ ያደረጉላቸው ነበር እነሱም ያንን ይመገቡ ነበር፡፡
የትግራይን አድባራትና ገዳማትን ለመጐብኘት ወደ ቅዱስ ያሬድ ደብር ሲደርሱ እመቤታችን ከቅዱስ ያሬድ (ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ) እና ከልጅዋ ጋር ወደ እርሳቸው መጥታ ብዙ ተአምራትን አድርጋላቸዋለች፤ ከቅዱስ ያሬድም ተምረዋል፤ ቡራኬ ተቀብለዋል፡፡
የጻድቁ የዕረፍታቸው ቀን በደረሰ ጊዜ እንደ ነጋሪት ቃልና እንደ ነጎድጓድ ያለ ድምፅ በሰማይ ተሰማ፤ እንደ ፀሐይ እና እንደ ጨረቃ እንደ ከዋክብት የሚያበሩ የተለያዩ መብራቶች ታዩ፡፡ መሬትም አራት ጊዜ ተንቀጠቀጠች፡፡ ተራሮችና ኮረብቶች እጅግ ተነዋወጡ፡፡ ነፍሳቸው ከሥጋቸው በምትለይበት ሰዓት እንደ መብረቅ የሚጮኽ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ተሰማ፡፡ ያን ጊዜ ሰው ዂሉ፣ እንስሳት፣ አራዊት፣ ዛፎችና ቅጠሎች፣ ተራሮች፣ ኮረብቶች፣ ወፎችም በየወገናቸው አለቀሱ፡፡ ፀሐይና ጨረቃ ጨለሙ፤ ከዋክብትም ረገፉ፡፡
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በታላቅ ግርማ፣ በአንድነትና በሦስትነት እየተመሰገኑ መጡ፡፡ ኪሩቤል፣ ሱራፌል ከነማዕጥንታቸው፣ ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት፣ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ዐሥራ አምስቱ ነቢያት፣ ሰማዕታት ከቅዱስ እስጢፋኖስ እስከ ተፈጻሜተ ሰማዕት ሊቀ ጳጳስ ዼጥሮስ ድረስ ያሉት፣ ቅዱሳን መነኮሳት ከአባታቸው ከእንጦንስ ጋር መጡ፡፡ የሰማዕታት እናታቸው፣ የመነኮሳትና የደናግል አክሊላቸው፣ ክብራቸው፣ መመኪያቸው፣ የሐዋርያት ስብከታቸው፣ የነቢያት ትንቢታቸው፣ የመላእክት እኅታቸው፣ የኃጥኣን ተስፋቸው፣ የፍጥረት ሁሉ አማላጃቸው፣ የምሕረት እናት፣ ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደናግላንን አስከትላ መጣች፡፡
ጻድቁ አባታችን ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ለዚህ ክብር ያበቃቸውን እግዚአብሔርን አመስግነው በሰላም ዐረፉ፡፡ ዕረፍታቸውም ሚያዚያ ዘጠኝ ቀን ሲኾን፣ ያረፉበት ቦታም ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ዳውንት ከተማ ደብረ አስጋጅ ገዳም ነው፡፡
አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከተቀበሉት ቃል ኪዳን ጥቂቱ
- ዝክራቸውን የዘከረ፣ መታሰቢያቸውን ያደረገ፣ ስማቸውን የጠራ፣ ገድላቸውን የጻፈ፣ ያጻፈ፣ ያነበበ፣ የተረጐመ፣ የሰማ፤ በፍጹም ልቡና ‹‹አምላከ እስትንፋሰ ክርስቶስ (የእስትንፋሰ ክርስቶስ አምላክ) ኀጢአቴን ይቅር በለኝ›› ብሎ የጸለየ ስሙ በሕይወት መጽሐፍ ይጻፍለታል፡፡
- ለቤተ ክርስቲያናቸው መባዕ፣ ስንዴ፣ ዘይት፣ ዕጣን፣ ጧፍ የሰጠ ኀጢአቱ ይደመሰስለታል፤ በገነት፣ በመንግሥተ ሰማያት በደስታ ይኖራል፡፡
- በስማቸው የተራቆተውን ያለበሰ፣ የተራበውን ያበላ፣ ያዘነውን ያረጋጋ፣ በመታሰበያቸው ዕለት ለአገልግሎት የሚፈለገውን መልካሙን ነገር ያደረገ ኀጢአቱ ይሰረይለታል፡፡
- በየዓመቱ ሚያዚያ ፱ ቀን እና በየወሩ የዕረፍታቸውን መታሰቢያ በዓል ያከበረ፣ ዝክራቸውን የዘከረ ሰማያዊ ክብር ያገኛል፡፡ በስማቸው የጽዋ ማኅበር የሚጠጡ ሰዎች ቢኖሩ በመካከላቸው የጻድቁ አምላክ ይገኛል፡፡
- ዝክራቸውን የዘከሩ፣ መታሰቢያቸውን ያደረጉ፣ በስማቸው የተማጸኑ፣ በገድላቸው የተሻሹ፣ በጠበላቸው የተጠመቁና የጠጡ መካኖች ልጅ ይወልዳሉ፡፡
- ችግር ደርሶበት ስማቸውን የጠራ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በስማቸው የሰየመ፣ በበዓላቸው ቀን ቁራሽ እንጀራና ቀዝቃዛ ውኃ ለነዳያን የሰጠ ኀጢአቱ ይሰረይለታል፡፡
ጻድቁ በሕይወተ ሥጋ እያሉ ካደረጉአቸው ተአምራት መካከል ከፊሉ
- ከደቀ መዝሙራቸው ከልብሰ ክርስቶስ ጋር በጎዳና ሲሔዱ የደረቀ የሰው አጥንት አግኝተው ፈጽሞ ወደ እግዚአብሔር ሲለምኑ ያን ጊዜ በጸሎታቸው ኃይል ያ የሞተውና የደረቀው አጥንት ነፍስ ዘርቶ ተነሥቷል፡፡
- የቀትር ጋኔን ለክፏት ልቧን ሰውሮአት የአገኘችውን ሰው እና እንስሳ በጥርሷ ትነክስ የነበረች አንዲት ሴት ሕመሟ ጸንቶባት ሞታ ሰዎች ሊቀብሯት ሲሉ የእስትንፋሰ ክርስቶስን መስቀልና መታጠቂያውን በአስከሬኑ ላይ ሲያስቀምጡት በእግዚአብሔር ኃይል ተነሥታለች፡፡
- አባታችን እስትንፋሰ ክርስቶስ በብርሃን ሠረገላ ወደ ሰማይ ሲያርጉ ዓይኑ የጠፋ፣ እግሮቹ ልምሾ የኾኑ ሰው ዐይቷቸው ‹‹አባቴ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ፥ በጸሎትዎ ፈውሱኝ›› ብሎ ተማጸናቸው፡፡ አባታችን እስትንፋሰ ክርስቶስም ያንን ሰው አዝነውለት በእጃቸው ያለውን መሐረብ ወረወሩለት፡፡ በዚያን ጊዜ ልምሾ የነበሩ እግሮቹ ዳኑ፤ ዓይኑም በራለት፡፡
- ስንዴ ዘርተው፣ ወይን፣ ጽድንም፣ ወይራን፣ ግራርንም ተክለው በአንዲት ቀን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ስንዴውን ለመሥዋዕት፣ ወይኑን ለቍርባን ዕለቱን በተአምራት አድርሰዋቸዋል፡፡
ካረፉ በኋላ (በዐጸደ ነፍስ) ካደረጉአቸው ተአምራት መካከል ጥቂቶቹ
- በልጃቸው ዐይነ ሥውር መኾን ተጨንቀው የነበሩ አንዲት እናት እስትንፋሰ ክርስቶስ ልጃቸውን ቢፈውሱላቸው እንደሚመነኵሱ ስእለት ተስለው ጠበሉን ሲያስጠምቁት የልጃቸው ዐይኑ በራለት፡፡ ኾኖም ግን ተስለው የነበረውን ምንኵስና እንዳያደርጉ ዘመዶቻቸው ስለ ከለከሏቸው ልጃቸው ተመልሶ ዐይነ ሥውር ኾኗል፡፡
- ወለተ ማርያም የተባሉ እናት ትዳር መሥርተው ለዐሥራ ሁለት ዓመታት ልጅ ሳይወልዱ ሲኖሩ የጻድቁን ገድል አዝለው በስማቸው ስም ቢማጸኑ ልጅ ለመውለድ በቅተዋል፡፡ ሊበተን የነበረውም ትዳራቸውም ተቃንቶላቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጻድቁ አማላጅነት ከጡት ካንሰር በሽታ እንደ ተፈወሱ፣ ጤንነታቸው እንደ ተመለሰላቸው እኒህ እናት ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
- የጻድቁ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስን በዓል ይዘክሩ የነበሩ ሰዎች ላም አካለ ጎደሎ ጥጃ ትወልዳለች፡፡ ከቤተሰቡ መካከል በእምነቷ ጠንካራ የነበረችው እኅታቸው ጥጃዋን በእስትንፋሰ ክርስቶስ ገድል ብታሻት በእግሯ ቆማ ሔዳለች፡፡ የእናቷንም ጡት ተንቀሳቅሳ ለመጥባት ችላለች፡፡
- ለአምስት ዓመታት ሆዱ አብጦ የነበረ አንድ ዲያቆን የጻድቁ ገድል የተደገመበትን ጠበል ሲጠጣ ከሕመሙ ተፈውሷል፡፡
ምንጭ፡- ገድለ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
በአቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ስም እየተማጸኑ በገድላቸው በመጸለይና ሰውነታቸውን በማሻሸት፣ እንደዚሁም በገዳማቸው በሚገኘው በጠበላቸው በመጠመቅ፣ በእምነታቸው በመቀባት ብዙ ምእመናን አሁንም ከሕመማቸው እየተፈወሱ ናቸው፡፡ የጻድቁ ገዳም (ደብረ አስጋጅ) በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ዳውንት ከተማ አካባቢ ይገኛል፡፡
በረከት ለመቀበል ወደ ገዳሙ ለመሔድ ከወልድያ እስከ ዳውንት በመኪና የስምንት ሰዓታት መንገድ ይወስዳል፡፡ ከዳውንት ከተማ ወደ ገዳሙ አቅራቢያ የሚያደርሱ አነስተኛ ተሸከርካሪዎችም ይገኛሉ፡፡ ወደ ገዳሙ ለመግባት ለጠነከሩ የአንድ ሰዓት ያህል የእግር ጕዞ ይኖረዋል፡፡ የጻድቁ በዓለ ዕረፍት በሚከበርበት ዕለት (ሚያዝያ ዘጠኝ ቀን) ከወልድያ እስከ ገዳሙ የሚያደርሱ መጓጓዣዎች ስለሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ ገዳሙ በመሔድ ከበረከቱ ተሳታፊ እንዲኾኑ ገዳሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
የጻድቁ ጸሎታቸው፣ በረከታቸውና አማላጅነታቸው ከዂላችን ጋር ይኹን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡