አማናዊ ብርሃን
ታኅሣሥ ፲፫፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
እውነተኛው ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ከገቡበት የኃጢአት ባርነትና የጨለማ ዓለም ለማውጣት ወደዚህች ምድር እንደመጣ፣ መከራን ተቀብሎ፣ በመስቀል ተስቅሎ፣ ሞቶ፣ ተነሥቶ ነጻ እንዳወጣን ቅዱሳኑ ነቢያት ሰብከዋል፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌውን ነገረ ድኅነትን በሚገባ አስተምረዋል፡፡
ከድንቁርና ወደ ፍጹም ዕውቀት ያደረሰን፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ያወጣን፣ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋገረን ጌታ እርሱ ዓለም ብርሃን ነው፡፡ “አነ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም” እንዲል፡፡ (ዮሐ.፰፥፲፪) ነቢያትም ጌታን በብርሃን እየመሰሉ ሥጋዌውን ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ብርሃን ለጻድቃን፥ ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ።” (መዝ.፺፯፥፲፩) በመጽሐፈ ኢሳይያስም ደግሞ “ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ” ተብሎ ተጽፏል፡፡ (ኢሳይያስ ፵፱፥፮)
መጽሐፈ መዝገበ ታሪክ የጌታን ብርሃንነት እንዲህ አስፍሮታል፡፡ “ብርሃንም ቢባል እንደ ፀሐይ እንደ ጨረቃ ብርሃን ጠፈር ደፈር የሚከልክለው መዓልትና ሌሊት የሚፈራርቀው አይደለም፡፡ የማይጠፋ የማይለወጥ አማናዊ ብርሃን ነው እንጂ፤” (ገጽ ፻፮) ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደገለጸው “እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።” (፩ኛ ዮሐ. ፩፥፭) ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህን ለመዘከር ከታኅሣሥ ፲፬ እስከ ፳ ድረስ ያለውን ወቅት “ብርሃን” ብላ ሰይማዋለች፡፡
ብርሃን የሆነው አምላካችንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች፣ በችግር መከራ ተጨንቃ፣ በነፋሱ ውዥንብር ከግራ ቀኝ እየተማታች፣ በምድር መናወጥ እየተንቀጠቀች፣ በጎርፍ እየሰጠመች፣ በእሳት ውእያት እየተለበለበች ወደ ድቅድቅ ጨለማ ከተለወጠችው ዓለም ያውጣን፤ አሜን!!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር!
