አማኑኤል- እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ
መምህር ሰሎሞን ጥጋቡ
ጥቅምት ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹እነሆ ድንግል በድንግልና ትጸንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› በማለት ትንቢት እንደተናገረው የተስፋው ቃል ይፈጸም ዘንድ በዘመነ ሥጋዌ እግዚአብሔር ወልድ ከንጽሕተ ንጹሐን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ እንደሚወለድ መልአኩ እንዲህ ሲል አበሠራት፤ ‹‹እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ስሙንም አማኑኤል ትይለዋለች፤ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው።›› (ኢሳ.፯፥፲፬፣ማቴ.፩፥፳፫)
አማኑኤል ‹አማነ› እና ‹ኤል› ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ስም ነው፤ ትርጓሜውም የአምላክ ሰላም፣ የእግዚአብሔር እርቅ፣ የጌታ አንድነት ማለት ነው። አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ደግሞ ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ የተዋሐደ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር እንደኛ የሆነ ማለት ነው።
አዳም ዕፀ በለስን በልቶ የሞት ፍርድ በተፈረደበት ጊዜ በምድር በኃዘን ስለኖረና አምላኩ እግዚአብሔርን ለረጅም ዓመታት ስለተማጸነው በርኅራኄው ወደ ቀድሞ ቦታው እንዲመልሰው በሰጠው ተስፋ ከልጅ ልጁ ተወለዶ አዳነው፡፡ በዚያችም በተከበረች ቀን ትንቢቱ ተፍጽሞ አምላካችን ከእኛ ጋር ሆነ፡፡
አምላክ ሰው የሆነለት የሰው ልጅ ኃጢአት ተፍቆ ነበር፡፡ ስለዚህ ከኃጢአት ርቀን በስሙ ተቀድስን እንድኖር የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ የሰው ልጅ ሕይወት ይቀደሳል ማለት ነው፡፡ ሰው ደግሞ መልካም ከሆነ ሁል ጊዜ እግዚአብሔር አይለየውም፡፡
ሰዎች በሕይወት ዘመናችን ችግርና መከራ ሲጸናብንና ፈተናችን ሲበዛ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ ማሰብ ያዳግተናል፤ እንዲያውም ጨርሶ እንደተወንም እናስባለን፡፡ ሆኖም ግን ፈጣሪያችን ሁሉን የሚያደርገው በምክንያት በመሆኑ ፈተናችን ለበጎ እንደሆነ በማሰብ ጸንተን መጓዝ ያስፈልጋል፡፡
በተለይም በዚህ ጊዜ ችግራችን በዝቶ፣ የእርሱ በርሱ ጦርነት ብሶና የኮሮና ወረርሽኙ ተስፋፍቶ ብዙዎችን እየጨረሰ ባለበት ወቅት እኛ ክርስቲያኖች በሃይማኖት ልንጸናና ልንበረታ ይገባል እንጂ ችግራችንን እያገዘፍን አምላካችንን የምናማርር ከሆነ መፍትሔ አናገኝም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍጥረቱን በሙሉ የማይረሳ አምላክ ስለሆነ ከሁላችንንም ጋር ይኖራል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው እርሱን የሚያስደስት ሥራ በመሥራት በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ በሕገ እግዚአብሔር አምልኮትን በመፈጸም፣ ለአምላካችን በመገዛትና ትእዛዛቱን በመፈጸም በጽናት መኖር ነው፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር አይለየን፤ አሜን፡፡