‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› (ዮሐ.፭፥፩–፱)
መምህር አብርሃም በዕውቀቱ
መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
በኢየሩሳሌም ቤተ ሳይዳ ወደ ምትባል አንዲት መጠመቂያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልዩ ልዩ ደዌያት የተያዙ ብዙ ሕሙማንን መፈወሱ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚወሳበት የዐቢይ ጾም ዐራተኛው ሳምንት ‹መፃጉዕ› ነው፡፡ በተለይም ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ የነበረው አንድ በሽተኛ ሰው በጌታችን ቃል ተፈውሶና አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ መሄዱ በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቧል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዐራተኛው እሑድ ሳምንት ወደ ቤተ ሳይዳ መጠመቂያ ወርዶ አንካሶችን አቀና፤ ለምጻሞችን አነፃ፤ እውራንን አበራ፤ በሌሎችም ልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን በጣም ብዙ ሕሙማንን ፈወሰ፡፡ ሕሙማኑ በመጠመቂያው የተሰበሰቡት ድኅነትን ፍለጋ ነበር፡፡
ዛሬ ደዌ የጸናበት በሽታ የበረታበት ከበሽታው ለመዳንና ከሕማሙ ለመፈወስ ወደ ጠበል እንደሚሄድ በዘመነ ብሉይ የእግዚአብሔር መልአክ በሳምንት አንድ ቀን ወደዚያች መጠመቂያ ገብቶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ ወደ መጠመቂያይቱ የገባ ከማናቸውም ከለበት ደዌ ሁሉ ይድን ይፈወስ ነበር፡፡ ዕለቷም ቀደሚት ሰንበት (ሰንበተ አይሁድ) ነበረች፡፡ ፈውስ መሰጠቱ በአባቶቻችን ዘመን ነበር እንጂ በእኛስ ዘመን እግዚአብሔር ትቶናል እንዳይሉ ነው፡፡ በውኃው ተጠምቆ የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ መሆኑ ደግሞ በዘመነ ብሉይ ፍጹም ድኅነት አለመኖሩን ያጠይቃል፡፡
ፍጹም ድኅነት የተገኘው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በልዩ ልዩ ደዌያት ተይዘው በቤተ ሳይዳ ተኝተው የውኃውን መናወጥ ከሚጠባበቁ ሕሙማን መካከል በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ፣ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በዚያ የተኛ፣ ደዌው የጸናበት፣ አስተማሚ ጠያቂ ዘመድ የሌለው አንድ ሰው አገኘ፡፡ ከደዌው ጽናት የተነሣም ‹መፃጉዕ› ተባለ፡፡ መፃጉዕ ማለት ‹ሕሙም፤ ድውይ› ማለት ነው፡፡ ሳምንቱም ‹መፃጉዕ› ተብሎ በእርሱ ተሰይሟል፡፡ ጌታችንም ወደ እርሱም ቀርቦ ‹‹ልትድን ትወደለህን?›› ብሎ በሽተኛውን ጠየቀው፡፡ መጠየቁ ሰውየው መዳን እንደሚፈልግ ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን ‹‹በዕለተ ዓርብ ፈውሰኝ ሳልል ፈውሶኛል›› ብሎ የሚመሠክርበት ነውና አስፈቅዶ ለማዳን ጠየቀው፡፡ አንድም በድኅነት ውስጥ ሰው የራሱ ሱታፌ እንዳለው ለማስተማር ነው፡፡
ድውዩም ‹‹ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል›› ብሎ መለሰለት። ቸሩ አምላካችንም ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› አለው። መፃዕጉም ጉልበቴን ቁርጩምጩሚቴን ሳይል ጉልበቱ ጸንቶ ተነሣ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ፈርሳውያን ግን ‹‹በሰንበት አልጋህን ተሸክመህ መሄድ እትችልም፤ ፈውስም በሰንበት መሆን የለበትም›› ብለው ተቆጡ፡፡ (ዮሐ.፭፥ ፩-፱)
አይሁድም ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?›› ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሠውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ ‹‹እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ›› አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ ‹‹አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ›› አላቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ ‹‹ሰንበትን የሚሽር ነው›› በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን ‹‹አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል›› በማለት ነው እንጂ፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሣቸው÷ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም›› ብሎ አስተማራቸው፡፡ (ዮሐ.፭፥ ፩-፳፬)
እኛም ባለን አቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሠሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማጉረስ፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ፣ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው መልካም ተግባራት ናቸው፡፡ እንደ ጸሓፍት ፋርሳውያን እግዚአብሔር በቸርነቱ የጎበኛቸውን አንቃወም፡፡ መልካም በተደረገላቸው፣ በለስ በቀናቸውና ገመድ ባማረ ሥፍራ በወደቀችላቸው አንቅና፡፡ በወንድሞቻችን ደስታ እንደሰት፤ በኀዘናቸውም እናጽናናቸው፡፡ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ለተያዙትን እንጸልይላቸው፤ በደዌ ነፍስ (በኃጢአት) የወደቁትን አንሥተን ወደ መጠመቂያይቱ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንጨምራቸው፤ ብቸንነት ተሰምቶአቸው ወገን ዘመድ ሰው የለንም ለሚሉት ሰው ሆነን ከጎናቸው በመገኘት የተኙበትን የችግር አልጋ ተሸክመው እንዲሄዱ እንርዳቸው፡፡
የማይቆረቁር ምቹ አልጋ ሕገ እግዚአብሔር ነውና ምቾተ ነፍስና ሰላመ አእምሮ አጥተው በችግር ሕመም የሚሠቃዩትን ሁሉ ‹‹አልጋችሁ ሕገ እግዚአብሔርን በመከተል ልቡናችሁ ተሸክማችሁ ሂዱ›› እንበላቸው፡፡
የቤተ ክርስቲያን ልማቷ በሰው ልብ ላይ ነውና በተግባራችን፣ አነጋገራችን፣ በአኗኗራችን ለሰዎች ቀናውን መንገድ ማሳየትና በድከማቸው ሁሉ ማገዝ እንደሚገባ በዚህ ሳምንት የምናስተላልፈው መልእክት ነው፡፡