ኒቆዲሞስ

መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

የአይሁድ አለቆች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ምልክት አሳየን›› እያሉ ይፈታተኑት በነበረበት ወቅት ጌታችን ስለ ሞቱና ትንሣኤው በምሳሌ ቢያስተምራቸውም እነርሱ ግን አልገባቸውም፡፡ የእጆቹ ተአምራቱ የታመሙትን ሲፈውስ ደግሞ ‹‹ሕጋችን ተሻረ›› ይሉ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ድንቅ ሥራ የአይሁድ አለቆች ክርስቶስን ለመክሰስ በሚፈልጉበት ጊዜ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ ግን እንደ ባልንጀሮቹ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይቃወም በሌሊት ወደ እርሱ ዘንድ እየሔደ ወንጌልን ይማር ነበር፡፡

ጌታችን ኢየሱስም በነፍስ የታመሙትን በቃሉ፣ በሥጋ የታመሙትን በተአምራቱ ሲፈውስ ኒቆዲሞስ ሰምቶና ተመልክቶ በመምህርነቱ ሳይታበይ፤ አለቅነቱን መመኪያ ሳያደርግ፤ በልቦናው የተሳለውን እውነትን ማግኘት ፈለገ፤ ከጌታውና ከመምህሩ ከክርስቶስ ዘንድ በሌሊት ይገሰግስም ነበር፡፡ (ዮሐ. ፫፥፩) ምስክርነቱን እንዲህ ሲል መስጠትም ጀመረ፤‹‹መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና፡፡›› (ዮሐ.፱፥፳፬፤ ሐዋ.፲፥፴፰)

ይህን ምስክርነት በሚሰጥበት ጊዜም ጎዶሎን የሚሞላ፤ ካለማወቅ ወደ ፍጹም ዕውቀት  የሚያደርስ፤ ከምድራዊ ዕውቀት ወደ ሰማያዊው ምሥጢር የሚያሸጋግር አምላክ  ‹‹ዳግመኛ  ያልተወለደ  የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም፤›› በማለት የአይሁድ መምህር ለሆነው ኒቆዲሞስ አስተማረው፤ ሆኖም ምሥጢሩ አልተገለጠለትም ነበርና  ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኀፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?›› በማለት ለጌታ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፮፤ ፩ኛ ጴጥ.፩፥፳፫) ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና፤›› (ኤፌ. ፭፥፳፮) ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ቢያስረዳውም ምሥጢሩ ሊገለጥለት ግን አልቻለም ነበር፡፡ ‹‹እንደምን ይቻላል?›› በማለትም ጌታን ጠይቋል፡፡

አበ ብዙኃን አብርሃም ከአምላኩ ሞገስን አግኝቶ የሰዶምና ገሞራ ጥፋት እንዳይደርስ ለመማለድ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር እንደ ነበረ፤ ኒቆዲሞስም አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምሥጢር ከአምላኩ በጠየቀ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ‹‹አንተ የእስራኤል መምህራቸው ሆነህ ሳለ ይህን ነገር አታውቅምን? በምድር ያለውን ስንነግራችሁ ካላመናችሁ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም…ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀላል፡፡ ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዲጠፋ አይደለም…፤›› እያለ ሰው በመብል ምክንያት የአምላኩን ትእዛዝ አፍርሶ ከእግዚአብሔር ቢለይም የሰው ልጅ ያጣውን ልጅነት ለመመለስ፣ ስመ ክርስትናን፣ ሀብተ ወልድን ለመስጠት ጌታችን መምጣቱን አስረዳው፡፡ (ዮሐ. ፫፥፲፬) ይህን የክርስቶስን የማዳን ሥራና በሥጋ መገለጥም ‹‹ሐወጽከኒ  ሌሊተ  ወፈተንኮ  ለልብየ አመከርከኒ  ወኢተረከ ዐመፃ በላዕሌየ ከመ  ኢይንብብ  አፉየ  ግብረ  እጓለ  እመሕያው፤  ልቤን  ፈተንከው፡፡ በሌሊትም  ጐበኘኸኝ፤  ፈተንከኝም፡፡ ምንም  አላገኘህብኝም፡፡ የሰውን  ሥራ  አፌ  እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፤›› (መዝ. ፲፮፥፫) በማለት ቅዱስ ዳዊት ከኒቆዲሞስ ሕይወት ጋር በማዛመድ አመሥጥሮታል፡፡

በሌሊት ከአምላኩ ተምሮ ምሥጢሩ የተገለጸለት ኒቆዲሞስ ቀድሞ በአደባባይ ሔዶ መማርን ቢፈራም ምሥጢሩ ሲገለጽለት ግን አይሁድ ጌታችንን በሰቀሉት ዕለት ፍርኃት ርቆለታል፤ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ ለመቅበርም በቃ፡፡  ‹‹ወአልቦ  ፍርኃት  ውስተ  ተፋቅሮትነ፤ ፍጹም ፍቅር ፍርኃትን አውጥቶ ይጥላል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ (ማቴ. ፳፯፥፶፰፤ ፩ኛ ዮሐ. ፬፥፲፰)፡፡

በዘመነ ሥጋዌ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምደር መምጣትና መሲሕ መባል ያልተቀበሉት በርካታ እስራኤላዊያን እርሱን እስከመስቀል እንደደረሱ ወንጌል አስተምሮናል፡፡ ሆኖም በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው  ከተከተሉት ፈሪሳውያን አንዱ ኒቆዲሞስ ለታላቅ ክብር የበቃ ሰው ሆኗል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን  ታላቅ ሰው ለመዘከር የዐቢይን ጾም ሰባተኛ እሑድ በስሙ ሰይማ ታከብረዋለች፤ ተከታዮቿ ምእመናንም የእርሱን አሠረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፤››(ማር.፲፮፥፮) በማለት በሰጠን ቃል ኪዳን መሠረት በአምላክነቱ አምነን የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ ይፍቀድልን፤ ለኒቆዲሞስ ምሥጢሩን እንደ ገለጸ ለእኛም ይግለጽልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር