ኒቆዲሞስ

ሚያዚያ 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

እግዚአብሔር “ጾምን ቀድሱ ጉባኤውንም ዐውጁ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ሰብስቡ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ በጽዮን መለከት ንፉ ጾምንም ቀድሱ” በማለት ዐውጀን መጾም ያለብንን ጾም እንድንፆም በነብዩ ኢዩኤል ነግሮናል፡፡ ኢዩ.1፥14፣ 2፥15

እግዚአብሔር ሙሴን በእሥራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማኅፀንን የሚከፍት በኲርን ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ በማለቱ /ዘጸ.13፥12 ከሰው፣ ከዕለታትት ተለይተው የተቀደሱ ነበሩ፡፡ አጽዋማትም በዐዋጅ ተለይተው ይጾማሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም፡- የዐብይ ጾም ይገኛል፡፡

ዐብይ ጾም ዐብይነቱ ነብያት፣ ሐዋርያት፣ ቅዱሳን የጾሙት ጾም ሳይሆን የጠፋውን የሰውን ልጅ ለመፈለግ፣ የሞተውን አዳምን ለማስነሣት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም የመጣው ወልደ አብ ወልደ ማርያም በመብል የተጀመረውን የሞት መንገድ ለማጥፋት በጾም ስለጀመረው ነው፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ያደረጋቸውን የድኅነት ጉዞና ድንቅ ድንቅ ተአምራት ዋጋ የተከፈለባቸው በመሆናቸው አባቶቻችን በሠሩልን ሥርዓት መሰረት በዐብይ ጾም ወራት ዘወረደ ብለን ጀምረን ትንሣኤ ብለን አስከምናከብርበት ድረስ ያሉትን ሰንበታት ለሰው ልጆች የተከፈለልንን ዋጋ እያሰብን እንማረዋለን፣ አንዘምራለን፣ እንጸልያለን፡፡ ከነዚህ ሰንበታት በ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደግሞ ኒቆዲሞስ ተብሎ ተሰይሞ ይከበራል፡፡

ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ በነበረው በኒቆዲሞስ የተሰየመ ሰንበት ነው፡፡ የአይሁድ አለቆች አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ምልክት አሳየን” እያሉ ይፈታተኑት ነበር፡፡ ስለሞቱና ትንሣኤው በምሳሌ ቢነግራቸው አልገባቸውም፡፡ ሲያስተምር ብዙዎች ያምኑ ነበር፡፡ ለአይሁድ አለቆች ግን ጭንቅ ነበር፤ የታመሙ ሲፈወሱ ሕጋችን ተሻረ ይሉ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ተአምራትና ትምህርት የአይሁድ አለቆች ክርስቶስን ለመክሰስ በሚፈልጉበት ወቅት ከአይሁድ አለቆች አንዱ ኒቆዲሞስ በቀን እንዳያደርገው አይሁድን ፈርቶ አንድም ጊዜ አላደርሰው ብሎ እንደ አይሁድ አለቆች ኢየሱስን መቃወሙን ትቶ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሄደ፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነፍስ የታመሙትን በቃሉ በሥጋ የታመሙትን በተአምራቱ ሲፈውስ፤ ኒቆዲሞስ ሰምቶና ተመልክቶ “መምህር ነኝ” ብሎ በመምህርነቱ ሳይኮራ አለቅነቱን መመኪያ ሳያደርግ፡፡ በልቦናው የተሳለውን እውነትን የመፈለግ ስሜት አንግቦ ጌታው መምህሩ ዘንድ በሌሊት ገሠገሠ ዮሐ.3÷1

ደርሶም ምስክርነቱን እንዲህ ሲል መስጠት ጀመረ “መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና” ዮሐ.9÷24፣ የሐዋ.ሥራ 10÷38 በማለት መመስከር ሲጀምር ጎዶሎን የሚሞላ፡፡ አላዋቂነት በአዋቂነት የሚለውጥ፡፡ ከምድራዊ እውቀት ወደ ሰማያዊ ምስጢር የሚያሸጋግር አምላክ፡፡ “ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” ዮሐ.3÷6 1ጴጥ.1÷23 በማለት የአይሁድ መምህር ለሆነው ኒቆዲሞስ ቢያስተምረው ስለዳግመኛ መወለድ ከመጽሐፍ ቢያገኘውም ምስጢሩ አልተገለጠለትምና “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” በማለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

“እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዝአበሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ኤፌ.5÷26 ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ በማለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያስረዳው ምስጢሩ ከአቅሙ በላይ የሆነበት ኒቆዲሞስ እንደምን ይቻላል? በማለት ጠይቋል፡፡ አበ ብዙኀን አብርሃም ከአምላኩ ሞገስን አግኝቶ፤  የሰዶምና ገሞራ ጥፋት እንዳይደርስ እያማለደ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር እንደ ነበረ፤ ኒቆዲሞስም አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምስጢር አምላኩን የመጠየቅ ዕድል በማግኘቱ ሲጠይቅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ ግን ይህን ነገር አታውቅምን? በምድር ያለውን ስንነግራቸው ካላመናችሁ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም ….፡፡ሙሴ ምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀላል፡፡ ያመኑበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዲጠፉ አይደለም…..” ዮሐ.3÷14፡፡ እያለ ለድኅነተ ዓለም እንደ መጣ ሰው በመብል፣ አምላኩን ከድቶ ልጅነቱን ትቶ ከእግዚአብሔር ቢለይም የሰው ልጅ ያጣውን ልጅነት ለመመለስ ስመ ግብርና ሀብተ ወልድን ለመስጠት መምጣቱን አስረዳው፡፡ “ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረከ በዓመፃ በላዕሌየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው፡፡ ልቤን ፈተንከው በሌሊትም ጎበኘኸኝ ፈተንከኝም ምንም አላገኘህብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው” መዝ.16÷3 እንዳለ ቅዱስ ዳዊት ምስጢረ ሥጋዌን የድኅነት ምስጢር ገልጾለታል፡፡

በሌሊት ከአምላኩ ተምሮ ምስጢሩ የተገለጸለት ኒቆዲሞስ ፍርሃት ርቆለት ቀድሞ በአደባባይ ሄዶ መማርን የፈራ ምስጢሩ ሲገለጽለት አይሁድ በሰቀሉት ዕለት ሳይፈራ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ ለመቅበር በቃ “ወአልቦ ፍርሃት ውስተ ተፋቅሮትነ፡፡ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል ማቴ.27÷58፣ 1ዮሐ.4÷18 እንዲል፡፡

ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል ማር.16÷16፡፡ ባለው አማናዊ ቃል ኪዳን መሠረት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አምላክነቱ አምነን  ለመንግሥቱ ዜጋ እንድንሆን ለኒቆዲሞስ ምስጢሩን ጥበቡን የገለጸ አምላክ ለኛም ይግለጽልን፡፡