ኒቆዲሞስ – የክርስቲያኖች ፊደል
መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የምሥራቹን ቃል ሲያውጅ እስራኤላውያን የተቀበሉት በተደበላለቀ ስሜት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ለብዙ ዘመናት በባርነት ሲገዙ ስለ ነበር ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻ የሚያወጣቸው መሲሕ ይፈልጋሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለብዙ ዘመናት በባርነት ቀንበር ስለ ደከሙ ተስፋ በመቁረጥ ተዳክመው ነበር፡፡ መሲሕ ቢመጣ እንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ፣ ሠራዊት አስከትሎ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው የክርስቶስን መሲሕነት ያልተቀበሉት፡፡ አብዛኛው እስራኤላዊ የክርስቶስን መሲሕነት ቢጠራጠርና ባይቀበለውም፣ በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው የተከተሉትም ነበሩ፡፡ ለዚህም ትልቅ ማሳያ የሚኾነን ከፈሪሳውያን ወገን የኾነው ኒቆዲሞስ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን ታላቅ ሰው ለማዘከር የዐቢይን ጾም ሰባተኛ እሑድ በስሙ ሰይማ ታከብረዋለች፡፡ ተከታዮቿ ምእመናንም የእርሱን አሠረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም፡፡
ኒቆዲሞስ ማነው?
ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ነው (ዮሐ. ፫፥፩)
የእስራኤላውያን ለብዙ ዘመን በባርነት መኖር የሕዝቡን የአኗኗር ኹኔታ ቀይሮታል፡፡ በግዞት ጊዜ ከአሕዛብ የቀሰሟቸው አጉል ትምህርቶች በእምነትም በአስተሳሰብም እጅግ እንዲለያዩና እንዲራራቁ ምክንያት ኾነዋል፡፡ አይሁዳውያን፣ ሳምራውያን፤ ከአይሁዳውያንም ሰዱቃውያን፣ ጸሐፍት፣ ፈሪሳውያን፣ ወዘተ. ተብለው እንዲከፋፈሉ ከዚህም እጅግ ወርደው ገሊላዊ፣ ናዝራዊ እንዲባባሉ ያበቃቸው ከአሕዛብ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ፈር አለማስያዛቸው ነበር፡፡
ከአይሁድ ቡድኖች መካከል ፈሪሳውያን ሕግን በማጥበቅ ሕዝቡን የሚያስመርሩ፤ ቀሚሳቸውን በማስረዘም እነርሱ የማይፈጽሙትን ሕግ በሕዝብ ላይ የሚጭኑ፤ ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ‹‹አባታችን አብርሃም ነው›› እያሉ የሚመጻደቁ፤ የአባታቸው የአብርሃምን ሥራ ግን የማይፈጽሙ የአይሁድ ቡድን ክፍሎች ናቸው (ዮሐ. ፰፥፴፱)፡፡ ኒቆዲሞስም ራሱን ከዚህ ሕዝብ ለይቶ በፍጹም ልቡ ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ፈሪሳዊ ነው፡፡ ቀድሞ አባታችን አብርሃምን ‹‹ከቤተሰብህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሒድ›› ያለው አምላክ ኒቆዲሞስን ከፈሪሳውያን ለይቶ ጠራው (ዘፍ. ፲፪)፡፡
ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ነው (ዮሐ. ፫፥፩)
ሮማውያን ሕዝቡን የሚያስተዳድሩት ከላይ ያለውን ሥልጣን ተቆናጠው ታች ያለውን ሕዝብ ባህላቸውን በሚያውቅ፣ ቋንቋቸውን በሚጠነቅቅ አይሁዳዊ ምስለኔ ያስገዙ ነበር፡፡ አውሮፓውያንም አፍሪካን ለመቀራመት የተጠቀሙበት ስልት ይህን ዓይነት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ምንም እንኳ ፈሪሳዊ ቢኾን አለቃ እንዲኾን በሮማውያን የተሾመ ባለ ሥልጣን ነው፡፡
ኒቆዲሞስ መምህረ እስራኤል ነው (ዮሐ. ፫፥፭)
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ምሥጢረ ጥምቀትን በገለጸለት ጊዜ ሲደናገር አይቶ «አንተ የእስራኤል መምህር ስትኾን ይህን አታውቅምን?» ብሎታል፡፡ ይህ ጥያቄ የሚጠቁመን ኒቆዲሞስ አለቅነትን ከመምህርነት የያዘ፤ በአይሁዳውያን ዘንድ የታፈረና የተከበረ ሰው እንደ ነበረ ነው፡፡ መምህር ቢኾንም ‹‹የሚቀረኝ ያላወቅሁት፣ ያልጠነቀቅሁት ብዙ ነገር አለ›› በማለት የመምህርነቱን ካባ አውልቆ፣ የተማሪነትን ዳባ ለብሶ ከክርስቶስ ሊማር መጣ፡፡
ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ነው (ዮሐ. ፫፥፯)
አንዳንዴ ሳያውቁ አወቅን ሳይማሩ እናስተምር የሚሉ ደፋር መምህራን አይጠፉም፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ከዚህ በተለየ አለቅነትን ከመምህርነት፣ መምህርነትን ከምሁርነት አስተባብሮ የያዘ፤ ዕውቀትን ከትሕትና፣ ምሁርነትን ከመንፈሳዊነት ጋር አስማምቶ የኖረ ሰው ነበር፡፡ የኦሪት ምሁር መኾኑን የሚጠቁመን ደግሞ ከካህናት አለቆች ጋር ያደረገው ክርክር ነው፡፡
ኒቆዲሞስ ምን አደረገ?
ለምሥጢረ ጥምቀት መገለጥ ምክንያት ኾነ
የአይሁድ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀኑ እንደ ደረሰ ለሐዋርያቱ ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ እንደ ሰውነቱ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል ሕዝቡን ቀንና ሌሊት በትምህርትና በተአምራት ያገለግል ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት ነው ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችን የመጣው፡፡ በፊቱ ቀርቦም «መምህር ሆይ» ብሎ የእርሱን አላዋቂነት፣ የክርስቶስን ማእምረ ኅቡዓትነት (የተሰወረን አዋቂነት) መሰከረ፡፡ ጌታችንም አመጣጡ ከልብ መኾኑን አውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን (ዳግም ልደትን) ገለጸለት፡፡ ምሥጢሩም የኦሪት ምሁር ለነበረው ኒቆዲሞስ ለጆሮ የከበደ፣ ለመቀበል የሚቸግር ኾነበት፡፡ የከበደውን የሚያቀል፣ የጠበበውን የሚያሰፋ አምላክ ምሥጢሩ ለኒቆዲሞስ እንደ ከበደው ስላወቀ ቀለል አደረገለት፡፡ ዳግም ልደት ከእናት ማኅፀን ሳይኾን ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ እንደ ኾነ አብራራለት፡፡
አዋቂ ነን የሚሉትን አሳፈራቸው
ወቅቱ የአይሁድ የፋሲካ በዓል የቀረበበት፤ ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ እንደ ሙሴም ሕግም ሊያስፈርዱበት የተቻኮሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ጌታችን የሙሴ ፈጣሪ መኾኑን አላወቁምና፡፡ የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ በሚመካከሩበት ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የኾነ ታላቅ ሰው ነው – ኒቆዲሞስ፡፡
ጌታን ለመገነዝ በቃ (ዮሐ. ፲፱፥፴፰)
ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ከዮሐንስ በቀር ሲበታተኑ፣ በዘጠኝ ሰዓት ቀራንዮ ላይ የነበረው ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ኾኖ የክርስቶስን ስጋ ከአለቆች ለምኖ የገነዘው፤ ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ ነበር፡፡
ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?
አትሕቶ ርእስ (ራስን ዝቅ ማድረግ)
ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ፣ የዕውቀት እና የሥልጣን ደረጃ ራሳችንን ከፍ ከፍ አድርገን የመማር አቅም ያጣን፤ ቁጭ ብሎ መማር ለደረጃችን የማይመጥን የሚመስለን ስንቶቻችን እንኾን? በአንድ ወቅት አባ መቃርስ ከሕፃናት እንቆቅልሽ ለመማር ቁጭ እንዳሉ፣ በእንቆቅልሹም ልባቸው ተነክቶ እያነቡ ወደ በዐታቸው እንደ ተመለሱ እያወቅን እኛ ግን ከአባቶች የመማር አቅም አጣን፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ አለቃ፣ መምህረ እስራኤል፣ ምሁረ ኦሪት ቢኾንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ሥር ቁጭ አለ፡፡ ሕዝብን ከመምራትና ከማስተማር ይልቅ ቁጭ ብሎ መማር ምንኛ መታደል ነው!
ጌታችንም በትምህርቱ «ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች፤ ከእርሷም አይወሰድባትም» ያለው ስለዚህ አይደል? (ሉቃ. ፲፥፵፪)፡፡ በቅዱስ ወንጌል ላይ በተደጋጋሚ የምናገኘው የፈሪሳውያንን ግብዝነትና የጌታችንን ተግሣፅ ነው፡፡ ትሑት የሚያሰኘው ሳያውቁ አውቃለሁ ማለት ሳይኾን፣ እያወቁ አላውቅም ማለት ነው፡፡ ሳይማሩ ተምሬያለሁ ማለት ሳይኾን ተምረውም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ ከፈሪሳዊው ይልቅ የቀራጩ ጸሎት ተቀባይነትን ማግኘቱም ለዚህ አንዱ ማስረጃ ነው (ሉቃ. ፲፰፥፲፩-፲፮)፡፡
ጎደሎን ማወቅ
በአብዛኞቻችን ዘንድ የሚታየውና ክርስትናችንን፣ አገልግሎታችንን እና ቤተ ክርስትያናችንን እየተፈታተነ ያለው ችግር ጎደሎዎቻችንን አለማወቃችንና ምሉዕ እንደ ኾነን ማሰባችን ነው፡፡ ነገር ግን ምንም እንዳልኾኑ አውቆ ራስን ለክርስቶስ እና ለቤተ ክርስቲያኑ አሳልፎ መስጠት ምንኛ መታደል ነው! ኒቆዲሞስ ያለውን ሳይኾን ያጣውን፤ የሞላለትን ሳይኾን የጎደለውን ፍለጋ ወደ ክርስቶስ መጣ፡፡ ዕውቀት ብቻውን ምሉዕ አያደርግም፡፡ አለቅነትም ቢኾን ገደብ አለው፡፡ ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት እንጅ ምሁረ ሐዲስ አይደለም፤ መምህረ እስራኤል ዘሥጋ እንጅ መምህረ እስራኤል ዘነፍስ አይደለም፡፡ የሕይወቱን ክፍተት ሊሞላ የሚችል አንድ ክርስቶስ ብቻ ነውና ኒቆዲሞስ ጉድለቱን አምኖ ጎደሎውን ሊያስሞላ ወደ ክርስቶስ መጣ፡፡ ‹‹የሚጎድለኝ ምንድን ነው?›› ብሎ እንደ ጠየቀው እንደዚያ ሰው ጎደሎን ማመን ምንኛ ታላቅ ነገር ነው!
አልዕሎ ልቡና (ልቡናንን ከፍ ማድረግ)
ኒቆዲሞስ ይዞ የመጣው ሥጋዊ ሕዋሳቱን ነበር፡፡ ጌታችን ግን አመጣጡ ለመልካም እንደ ኾነ አውቆ ለሥጋዊ ዕውቀት እጅግ የሚከብደውን ምሥጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ መጀመሪያ ይህን ምሥጢር ለመቀበል አልተቻለውም ነበር፡፡ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ምሥጢሩን ፍንትው አድርጎ ሲያብራራለት ግን ልቡናው ምሥጢሩን ለመቀበል ተዘጋጀ፡፡ ምሥጢራትን ለመቀበል ልቡናን ከፍ ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡ የእምነታች መሠረት በሥጋ ዓይን ማየት፣ በሥጋ ጆሮ መስማት፣ በሥጋ እጅ መዳሰስ ብቻ ከኾነ እምነታችን ልክ እንደ እንቧይ ካብ ኾነ ማለት ነው፡፡ ትቂት የፈተና ነፋስ ሲነፍስበት፣ ጠቂት የመከራ ተፅዕኖ ሲደርስበት መፈራረስ፣ መናድ ይጀምራል፡፡ ኒቆዲሞስም ምሥጢሩ መጀመሪያ ቢከብደውም ቅሉ በኋላ ልቡናውን ወደ ሰማያዊው ምሥጢር ከፍ ስላደረገ ምሥጢሩን በቀላሉ ተረዳ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ሲፈታተኗትና እየተፈታተኗት ያሉ አካላት በሙሉ የስሕተታቸው ምንጭ እንደ ግያዝ ከአካባቢያቸውና ከምናየው አካል (ቁሳዊ ዓለም) ውጭ መመልከት አለመቻል ነው (፪ኛ ነገ. ፮፥፲፯)፡፡ ለዚህም ነው ካህኑ በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ የቍርባኑ ምሥጢር እንዲገለጽልን «አልዕሉ አልባቢክሙ፤ ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ» የሚሉን፡፡
ስምዐ ጽድቅ (የእውነት ምስክር) መኾን
ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም» በማለት እንደ ተናገረው (፪ኛ ቆሮ. ፲፫፥፰)፣ ቤተ ክርስቲያን በሰማዕትነት የምትዘክራቸው ቅዱሳን በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡትን አባቶች እና እናቶችን ነው፡፡ በፍርኀትና በሐፍረት፣ በይሉኝታና በሐዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም፡፡ ኒቆዲሞስ ያለ ፍርኀትና ያለ ሐፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ በመሪዎችና በታላላቅ ባለ ሥልጣናት ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ዐቢይ ቁም ነገር ነው (ሉቃ. ፲፪፥፫-፭)፡፡
ትግሃ ሌሊት (በሌሊት ለአገልግሎት መትጋት)
እንደ ሌሊት ለመንፈሳዊ ሕሊና፣ ለተመስጦ የሚመች ጊዜ የለም፡፡ ቀን ለሥጋ ሲራወጥ የነበረ አካልና መንፈስ ሌሊቱን ለነፍስ በመገዛት ሥጋውን ማድከም አለበት፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀኑን በቅዳሴ፤ ሌሊቱን ደግሞ በማኅሌት፣ በሰዓታት፣ በኪዳን እግዚአብሔርን ስታምሰግን የምታድረው፡፡ ‹‹ሌሊትስ ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው›› እንዳለ ቅዱስ ማር ይስሐቅ፡፡ ጌታችንም ሐዋርያቱን ‹‹ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ›› ብሏቸዋል (ማቴ. ፳፮፥፵፩)፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያን እንደ ኒቆዲሞስ ለኪዳን፣ ለማኅሌት፣ ለጸሎት በሌሊት የሚገሰግስ ምእመንን ትፈልጋለች፡፡
እስከ መጨረሻ መጽናት
ክርስትና ለጀመሩት ሳይኾን ለጨረሱት፤ ለወጠኑት ሳይኾን ለፈጸሙት የድል አክሊል የምትሰጥ መንገድ ናት፡፡ ስለዚህም የመሮጫ መሙ ጠበበን፤ ሩጫው ረዘመብን ብለው ከመስመሯ ለሚወጡ ዴማሶች ቦታ የላትም (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፲)፡፡ ጌታችንን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ሺሕ ሕዝብ ቢከተለውም እስከ መስቀሉ አብረውት የነበሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የተወሰነው ሕዝብ ቀድሞም የተከተለው ለምግበ ሥጋ ነበርና ቀራንዮ ላይ አልተገኘም፡፡ ቀራንዮ ላይ ምግበ ነፍስ እንጅ ምግበ ሥጋ የለምና፡፡ ሌሎችም አይሁድን ከመፍራታቸው የተነሣ ከመስቀሉ ሥር አልተገኙም፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ክርስቶስ በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው በለየበት ሰዓት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ኾኖ የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከመስቀል አውርዶ፣ ገነዞ በሐዲስ መቃብር ለመቅበር ታድሏል፡፡
በዚህ የመከራ ሰዓት ከዮሐንስና ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ውጭ ማንም በሥፍራው አልነበረም፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር የተገኙት የቁርጥ ቀን ልጆች ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ናቸው፡፡ ይህም ኒቆዲሞስ ፈተናውን ዅሉ ተቋቁሞ እስከ መጨረሻው ለመጽናቱ ምስክር ነው፡፡ በክርስትና ሕይወታችን በምቹ ጊዜ የምናገለግል፣ ፈተና ሲመጣ ግን ጨርቃችን (አገልግሎታችንን) ጥለን የምንሮጥ፣ ሰበብ አስባብ ፈልገን የምናፈገፍግ ብዙዎች ነን (ማር. ፲፬፥፲፭)፡፡ ዕውቀት፣ ሀብት እና ጊዜ ጣኦት ኾኖበት ከመሃል መንገድ የቀረውን፤ ሩጫውን ያቋረጠውን፤ ከቤተ ክርስቲያ አገልግሎት የራቀውን ክርስቲያን ቈጥረን አንጨርሰውም፡፡ ጌታችን በትምህርቱ «ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል» (ማቴ.፳፬፥፲፫) በማለት የድኅነት ተስፋ ሰጥቶናልና ዅላችንም እንደ ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው በሃይማኖታችን ልንጸና ይገባናል፡፡
በአጠቃላይ ከኒቆዲሞስ ሕይወት ብዙ ቁም ነገሮችን እንማራለን፡፡ የኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ መምጣት ለምሥጢረ ጥምቀት ትምህርት መገለጥ ምክንያት እንደ ኾነ ዅሉ፣ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን በቅዳሴው፣ በኪዳኑ፣ በሰዓታቱ፣ በማኅሌቱ ብንሳተፍ ረቂቅ የኾነው ሰማያዊ ምሥጢር ፍንትው ብሎ ይገለጥልናል፡፡ እንደ ኒቆዲሞስ ራሳችንን ዝቅ አድርገን በምሥጢራት በመሳተፍ ለታላቅ ክብር እንበቃ ዘንድ የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡