ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – የመጨረሻ ክፍል
በዲ/ን ታደለ ፈንታው
መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
‹‹ኢየሱስም መለሰ፤ እንዲህ ሲል፡- እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም››
ጌታ ይህንን እውነት ዝቅ አድርጎ እንዳይመለከተው በማሰብ አስቀድሞ የተናገረውን ነገር ደገመለት፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል አዎ አይደለም ከሚለው አፍአዊ ነገር በዘለለ መልስን የሚጠይቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ ከመረዳት አቅሙ በላይ ቢኾንም ጌታ እንደ ገና መወለድ ትምህርቱ ላይ ጠንከር ብሎ ሔዷል፡፡ ያለዚህ ልደት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየትም ለመግባትም የሚያስችል መንገድ የለም፡፡ ሰው ከውኃና ከመንፈስ መወለድ አለበት ይላል፡፡ ስለምን ውኃን ይጠቀማል? ውስጣዊ የመንፈስ መታጠብን ለማመልከት ነው (ሕዝ. ፴፮፥፳፭፤ ፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፩፤ ቲቶ. ፫፥፭)፡፡ ይህ ውስጣዊ የመንፈስ መታጠብ በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጸም ነው፡፡ እርሱ ብቻ ያጥባል ያነጻል ውስጣዊ ልባችንን አዲስ ያደርጋል፡፡ ጌታ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን በመቀየር በሰርጉ ቤት ለነበሩ ዕድምተኞች ደስታን እንደ ሰጠ በመንፈሱ የሰጠው ውጫዊ የሰውነት መታጠብ አይደለም፡፡
ይህ ውኃ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ ይጠጣ በማለት ለሳምራዊቷ ሴት የነገራት የሕይወት ውኃ ነው፡፡ በያዕቆብ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለው ውኃ አይነት አይደለም ያዕቆብ፣ ልጆቹና፣ ከብቶቹ የጠጡት ውኃ የሚያረካው የሥጋን ጥማት ነው፡፡ ጌታችን የሚሰጠን ውኃ ግን የነፍስን ጥማት የሚያረካ ነው፡፡ አዲሱ ልደት በውኃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ እየተባለ መፈጸሙ ሞትን የመቀበልና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመቀበር ምልክት ነው፡፡ ከእርሱ ጋር እንነሣ ዘንድ የግድ ያስፈልገናልና፡፡ ‹‹እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፡፡ ከሞቱ ጋር አንድ እንኾን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡
ከውኃና ከመንፈስ መወለድ የአሮጌውን ሰው መሞትና የአዲሱን ሰው ትንሣኤ ይጠይቃል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የኾነውን አዲስ ሕይወትም መቀበል ነው፡፡ እርሱም የትንሣኤ መንፈስ ነው፡፡ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር የሚያደርገንን አዲሱን ሰው የመፍጠር ሒደት ነው፡፡ በፈጣሪያችን መልክ የተፈጠረውን አዲስ ሰው መመልከት ነው፡፡ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምነው መስቀሉን ሊሸከሙ የሚወዱ ወገኖች በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ አለባቸው፡፡ ‹‹የጌታ ቃል ትርጕም ለኒቆዲሞስ ምንድን ነው?›› ብሎ ለሚጠይቅ ምላሹ ‹‹ጌታ ከሥጋ ትውልድ ወጣ ብሎ መንፈሳዊውን ትውልድ እንዲያስብ ሳበው›› የሚል ነው፡፡
ጌታችን ለኒቆዲሞስ እንዲህ በማለት የነገረው ይመስላል፤ ‹‹ኒቆዲሞስ ሆይ እየነገርሁህ ያለሁት ስለ ሌላ ልደት ነው፡፡ ስለምን ነው ንግግሬን ወደ ምድራዊ ነገር የምታወርደው? የምነግርህ ነገር ስለምን በተፈጥሮ ሕግ እንዲገዛ ታደርጋለህ? ይህ ልደት በሥጋ (በምጥ) ከሚደረገው ትውልድ የተለየ ነው፡፡ አጠቃላይና የተለመደ ከኾነ ልደት ራስህን አውጣ፡፡ እኔ ሌላ ልደት በሚገኝበት መንፈሳዊ ዓለም ሾሜሃለሁና፡፡ ሰዎች ዂሉ ከዚህ አዲስ ልደት እንዲወለዱ እወዳለሁ፡፡ አዲስ ዓይነት ልደትን ይዤ ወደ ምድር መጥቻለሁ፡፡ ሰውን የፈጠርሁት ከምድር አፈርና ከውኃ ነበር፡፡ ይህ ያገለግለኛል ብዬ የፈጠርሁት ምርጥ ዕቃ የተፈጠረበትን ዓላማ ዘንግቶ አግኝቸዋለሁና እንደገና ከአፈርና ከውኃ ልሠራው አልፈቅድም እንደገና በውኃና በመንፈስ እንዲወለድ እፈቅዳለሁ እንጂ፡፡››
ከመካከላችን እግዚአብሔር ‹‹ሰውን እንዴት ከውኃ ፈጠረው?›› ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ምላሹን የሚያገኘው ግን የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ ሲቻል ነው፤ ‹‹ሰውን እንዴት ከምድር አፈር አበጀው? ጭቃን እንደምን አድርጋችሁ ወደ ተለያየ ክፍል ትከፋፍሉታላችሁ? አጥንት፣ ነርቭ፣ የደም ሥር፣ የደም ቧንቧ ከየት ተሠሩ? ቆዳ፣ ደም፣ ጉበት ከየት ተሠሩ? ይህ ታላቅ ሥራ ለምን የተከናወነ ይመስላችኋል? የተለያየውስ ቀለም? እነዚህ ዂሉ ዓይነቶች ውሁዶች ከየት ተገኙ?›› እነዚህ ዂሉ ነገሮች የምድርም የጭቃም አካል አይደሉምና፡፡
ምድር ዘርን ስትቀበል እንዴት አድርገው ሥር ይሰዳሉ? ነገር ግን በእኛ አካል ውስጥ ሲኾኑ እነዚህ ዘሮች ይፈጫሉ፡፡ ምድር ዘርን ምን መግባ ዘር ፍሬ እንዲያፈራ ታደርጋለች? እንደ ገናስ ሰውነታችን እንዴት በእነዚህ ዘሮች ይገነባል? ምድር ውኃን ትቀበላለች፤ ወደሚያፈራ ወይንም ትቀይረዋለች፡፡ የእኛ ሰውነት ግን ወይንን ተቀብሎ ወደ ውኃ ይቀይረዋል፡፡ በአሳብ የምትሰጠው ፍሬ ሁሉ የእርሷ ውጤት መሆኑን በምን በምን በምን መንገድ ነው የሚለውን ግን ማስረዳት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ምድር በፍሬዋ ሰውነታችንን ታጠግባለች፤ በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ብቻ ነው እነዚህ ዂሉ ነገሮች የምድር ውጤቶች ናቸው ብለን እንድቀበል የሚያደርገን፡፡
እነዚህ ዂሉ ዓይነት ተጨባጭ ነገሮች በየቀኑ የሚከሠቱ ስለ ኾነ እምነት የሚይጠይቁ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ የኾነው ጉዳይ በቂ ትኩረትና ቅድምና ማግኘት እንደሚኖርበት እንገነዘባለን፡፡ የማይንቀሳቀሰው ምድር ለእግዚአብሔር ፈቃድ መልስ ይሰጣል፡፡ ምድር የምትሸከመው ይህ ዂሉ ነገር የተገኘው ለዚህ ፈቃድ ነውና፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታ ከመረዳታችን በላይ የኾነ ጽንፍ የያዘ ብዙ ምልክት ይፈጠራል፡፡ ከመካከላችን አንዱ፡- ‹‹ውኃ ለዳግም ልደት ለምን ያስፈልጋል?›› ብሎ ቢጠይቅ ምላሹ ‹‹ይህ ልደት አምላካዊ ጠቀሜታ አለው›› የሚል ነው፡፡ መቃብር፣ መቀበር እምነት፣ ሕይወትና፣ ትንሣኤ እነዚህ ዂሉ ምሥጢራት በጥምቀት ጊዜ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ ጭንቅላታችንን ውኃ ውስጥ እንነክራለን፤ ወደ መቃብር እንደምንወርድ ዂሉ አሮጌውን ሰውነታችንን እንቀብር ዘንድ ጭንቅላታችንን ስናነሣ አዲሱ ሰው በተመሳሳይ ኹኔታ ይገኛል፡፡‹‹ከመንፈስ የሚወለድ እርሱ ማነው? እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዶ በአእምሮው መንፈስ ከሚታደስ ሰው በስተቀር፤››ተብሎ እንደ ተጻፈ (ኤፌ. ፬፥፳፫)፡፡
በእርግጥ ይህ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ እንደ ገና የተወለደው ሰው ነው፡፡ ይህ በዘላለማዊ ሕይወት የመተማመን ውጤት ነው፡፡ ይህም በጥምቀት አማካኝነት የሚፈጸም ነው፡፡ በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ሰው እንደ ምሕረቱ መጠን በአዲስ ልደት በሚኾነው መታጠብም በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ መንፈሳዊ ልጅነትን የተቀበለ ነው፡፡ በሌላ ንባብ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፤ ‹‹በመንፈስ ቅዱስ ስም ትጠመቃላችሁ›› (ሐዋ. ፲፩፥፲፮)፡፡ ከውኃና ከመንፈስ ከተወለደ ወገን ውጭ በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቀ ማነው? ለዚህም ነው ጌታችን ‹‹… ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለዳችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻላችሁም›› በማለት በጥምቀት የምናገኘውን ልጅነትና ዘለዓለማዊ መንግሥት የነገረን፡፡
በምሥጢረ ጥምቀት የኀጢአት እሥራት ይፈታል፡፡ ስለዚህም ሕፃናት ሳይቀሩ ይጠመቃሉ፡፡ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይቻለውምና፡፡ ጥምቀት ኀጢአታችን ዂሉ ያጥባል፡፡ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መቅደስ እንድንኾን ያደርገናል፡፡ ሰማያዊ ተፈጥሮአችንን ያድሳል፡፡ ይህም በመንፈስ ቅዱስ ግብር የሚፈጸም ነው፡፡ በጥምቀት ሰው ከሰይጣን ኀይል ነጻ ይኾናል፤ ይህም በመንፈስ ቅዱስ የሚከናወን ነው፡፡ የተጠመቀውን ሰው የሚቀድስና የሚያነጻ መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሰው ላይ ሰይጣን የወደደውን ያደርግበት ዘንድ አቅሙ አይኖረውም፡፡ ሰው በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር አንድነትን ሲፈጥር እንደ ገና ከመወለዱ ባሻገር ክርስቶስን በዂለንተናው ይለብሰዋል (ገላ. ፫፥፳፯)፡፡ ይህ ምሥጢር በንባብ ብቻ የምንረዳው አይደለም፡፡ የፍቅር መግለጫ ነውና፡፡ ይህንን የምንረዳው ጌታ ሥጋችንን ተዋሕዶ እኛን ለማዳን ሲል በእኛ መጠን በመወለዱ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡