ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – የመጀመሪያ ክፍል
በዲ/ን ታደለ ፈንታው
መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ብዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና እምነት የተቀላቀሉበትን ምሥጢር የሚያስረዳ ምዕራፍ ነው፡፡ ድኅነትን በትጋት ለመፈጸም የሚታገሉ ክርስቲያኖች ይኼንን ምዕራፍ ሲያነቡ ከኒቆዲሞስ ጎን መቆማቸው የሚያጠራጥር አይኾንም፤ ከጌታ ጋር ምሥጢራዊ የኾነ ውይይትን መቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ በሕይወታቸው የተከፈተ የአዲስ ኪዳን መንገድ እንዳለ ሲገነዘቡም ጌታን ይከተላሉ፡፡ ከእርሱ ጋር ከቅዱስ መንፈሱም ጋር አንድ ይኾናሉ፡፡ አዲስ ልደትን ያገኛሉ፤ ይህም በጥምቀት የሚገኝ የሥላሴ ልጅነት ነው፡፡
ይህ ምዕራፍ መልካም ሥነ ምግባር በነበረው ፈሪሳዊ ሕያውና መንፈሳዊ በኾነው ምንጭ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የነበረውን ውይይት ይዟል፡፡ ኒቆዲሞስ እንደ ፈሪሳዊ በአይሁድ ትውፊትና በብሉይ ኪዳን ትምህርት የታጠቀ ነው፡፡ ጠንካራ ሞራል እንደ ገነባ ሰው ወደ ጽድቅ የሚወስደውን ትውፊት የሚያውቅ ሰው በፈቃዱ መታዘዝ እንዳለበት የሚያምን ነው፡፡ ይህ የሚኾነው ደግሞ ሰው በሚያደርገው ጠንካራ ትግል እንደ ኾነ ያምናል፡፡ ይህ ትግል በሰው በጎ ፈቃድና ሕጉን በደረቁ በመተርጐም እንደሚገኝ ያምናል፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታን ያገኘው ሕጉን የሚቃወም ኾኖ ሳይኾን ሕጉን በጥልቀት የሚተረጕም አይሁዳዊ ኾኖ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ወደ መድኀኒታችን ከተሳቡ ወገኖች መካከል ወንጌላዊው የኒቆዲሞስን ጉዳይ በትኩረት የጻፈው፡፡
ወንጌላዊው እንደ ነገረን ኒቆዲሞስ ጌታ ከእግዚአብሔር እንደ መጣ አወቀ፤ አመነም (ዮሐ. ፫፥፪)፡፡ ነገር ግን ምናልባት ኒቆዲሞስ ጌታ ትምህርቱን ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያስተምር ሊያስብ ይችላል፡፡ የሕጉን ጥሬ ትርጕም እንጂ ፍካሬያዊ ትርጕም አልተገነዘበም፡፡ የአይሁድን ኑሮ ሊያሻሽል የመጣ ነው ብሎም ሊያስብ ይችላል፡፡ የኒቆዲሞስ አመለካከቱና ልምዱ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን አዲስ ሕይወት ለመቀበል አያበቃውም፡፡ በአዲሱ ልደት የሚገኘው የጸጋ ልጅነት አይገነዘበውም፡፡ የመንፈሳዊው ሕግ ጥቅም ግን ይህ ነበር፡፡ ሥጋዊውን ከመንፈሳዊ ምድራዊውን ከሰማያዊ መለየት ያስችላል፡፡ ጌታ የኒቆዲሞስን አሳቡን፣ ልቡን፣ ስሜቱን፣ ዕውቀቱን ዂሉ ወደ ሰማያዊ ነገር እንዲያሸጋግረው ፈቀደ፡፡ ይህን በማድረግ ከሰማይ የወረደው እርሱም በሰማይ የነበረው እንደ ኾነ ይገነዘባል፡፡ ወደ ሰማይ መውጣትም የሚቻለው እርሱ ነው፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ወገኖችን ከፍ ከፍ የሚያደርጋቸው፤ ከፍ ያለውንም ነገር እንዲመለከቱ የሚያደርጋቸው እርሱ ነው፡፡
የኒቆዲሞስና የጌታ ግንኙነት ትኩረታችንን ወደ ክርስቶስ እንድናደርግ ያደርገናል፡፡ ለእያንዳንዱ የሰው ልጅ ነፍስ መዳን ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ ከእያንዳንዱም ወገን ጋር ሲነጋገር ያለውን ትሕትናም እንገነዘባለን፡፡ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲወያይ የአዲሱን ልደት ጠባይ ዘርዝሯል፡፡ ኒቆዲሞስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ማወቅ ፈልጓል፤ ይኼንን መንግሥት ለማወቅ በውኃና በመንፈስ ይጠመቅ ዘንድ ግድ መኾኑን ያስረዳል፡፡ ይህ ኹኔታ አስፈላጊ ነው፤ ክርስቲያን ዘወትር የእግዚአብሔር ልጅ ኾኖ እንዲኖር ያስችለዋልና ይጠመቅ ዘንድ የግድ ነው፤ በመንፈሱም እንዲኖር ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ጌታ ከምድራዊ ነገሮች ያወጣና አሳባችን ሰማያዊ በኾነው ጉዳይ እንዲያዝ ያደርጋል፡፡ ይህንን ማድረግ የምንችለው ከሰማያዊው ጋር ኅብረት ስንፈጥር መኾኑን ይነግረናል፡፡
ጌታ ጥምቀቱን ከመስቀሉ ጋር አያይዞታል፡፡ እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጆች ዂሉ ያለውን እውነተኛ ፍቅር የገለጠበት፣ የባሕርይ ልጁን ወደ ዓለም በመላክ ዓለሙ ዘላለማዊ ሕይወትን ያገኝ ዘንድ ልጁ ከፍ ከፍ ያለበትም የነገሠበትም ዙፋኑ ነውና፡፡ አዲሱን ልደትን በማንሣት ጌታ ከፍርሃት ባርነት አውጥቶ መለኮታዊ የኾነውን ብርሃን እንድንመለከት ያደርገናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ጌታ ሲጠመቅ የነበረውን ኹኔታ ሲነግረን ለሚያምኑ ወገኖች ያለውን አንድምታም ሲገልጽ ደስታው ፍጹም ነበር፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ ከሰጠው ትምህርት መካከል ከምዕራፍ ፩ – ፫ ስለ አዲሱ ልደት ማብራሪያ ይሰጣል፡፡
ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የኾነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንደ ሰው ነበረ፡፡ ‹ኒቆዲሞስ› የአይሁድ ስም ሲኾን ትርጓሜው ‹ሕዝብን ያሸነፈ› ማለት ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የአይሁድ አካል የሰንሃድሪን አይሁድ ሸንጎም አባል ነው፡፡ የክርስቶስ መለኮታዊ ጥሪ መላውን የሰው ልጆች ያካተተ ነው፡፡ የመደብ ልዩነት አልተደረገበትም፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ሓላፊነት ከነበሩ የመንግሥትና የሃይማኖት መሪዎች መካከል ለዚህ ጥሪ መልስ የሰጡ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ከፈሪሳውያን መካከል እጅግ ጥቂቶች፤ ከጥቂቶቹ አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ በአይሁድ ሸንጎ የተከበረ ሰው ነበረ፡፡ ጌታ ግን ይህችን አንዲት ለመዳን የወሰነች ነፍስ ዝቅ አላደረጋትም፤ ሞትን የተቀበለው ስለእያንዳንዱ ነፍስ ነውና፡፡
ፈሪሳውያን ለመለኮታዊው እውነት የሰጡት መልስ ጥላቻና የዐመፅ መንፈስን የተመላ ነው፡፡ ነገር ግን ከተማሩ አይሁድ መካከል ጌታን ለማግኘት የቸኮሉ በሩም ተከፍቶ የጠበቃቸው ጥቂቶች ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ በተማሩም ባልተማሩም ወገኖች ላይ ይሠራል፡፡ በተራውም ሕዝብ፣ በአለቃውም፣ በየዋሁም፣ በዐመፀኛውም ላይ ይሠራል፡፡ ኒቆዲሞስ ደረጃው ከዐመፀኞቹ ቢኾንም ወደ ጌታ መጣ፤ ጊዜው ሲደርስ የቻለውን ያህል ይጠይቅና ያውቅ ዘንድ ሞከረ፡፡ በጥያቄ ላይ እንደ ነበረ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ጊዜው ሲደርስ ለደቀ መዛሙርቱ ያልተቻለው ለዚህ ሰው ተቻለ፡፡ ከጲላጦስ አስፈቀዶ አዲስ ባሳነጸው መቃብር ላይ እንዲቀበር አደረገ፡፡
ቤን ረጊን በአይሁድ ታሪክ መጽሐፍ ስለ ኒቆዲሞስ ሲናገር ይህ ሰው በጣም ሀብታም ከመሆኑ የተነሣ በኢየሩሳሌም የነበሩ ብዙዎችን ለብዙ ዓመታት ይረዳ እንደ ነበር ይናገራል፡፡ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ ‹‹መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከኾነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለም፡፡ መምህር ኾነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን›› አለው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ኒቆዲሞስን በብዙ ቦታዎች ጠርቶታል፡፡ ጌታን ማታ ማታ ይጐበኝ እንደ ነበረም ገልጧል፤ ይህ ኹኔታ ሦስት ጊዜ ያህል ተጠቅሷል (ዮሐ. ፫፥፪፤ ፱፥፴፱፤ ፯፥፶)፡፡
ኒቆዲሞስ ስለ ምን ወደ ጌታ በምሽት መጣ
የመጀመሪያው ምክንያት ጌታችን በአደባባይ የሚያስተምረውን ትምህርት ከሰዎች መስማቱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ከምንም በላይ ጌታ በአደባባይ የሚያደርገውን ምልክት በሕዝብ መካከል በግልጽ መጥቶ ማየት አልወደደም፡፡ ድኅነትና ነፍስን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በጥሞና ከጌታ ሥር ቁጭ ብሎ መነጋገር ልቡ ፈቅዷል፡፡ ‹‹ቃሌስ በቅንነት ለሚሔድ በጎ አያደርግምን?›› (ሚክ. ፪፥፯) ተብሎ እንደ ተጻፈ ኒቆዲሞስ የቅንነትን መንገድ መርጦ ወደ ጌታ ቀርቧል፡፡ ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ይነጋገር ዘንድ ወደደ፡፡ ጌታ እንኳን ከሕዝቡና ከደቀ መዛሙርቱ ተለይቶ ከአብ ጋር ሲነጋገር የሚያድርበት ጊዜ ነበር፡፡ እኛማ ሌሊቱን በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር እንደምን መነጋገር ይገባን ይኾን? በተለይ በሌሊት ዂሉንም ነገር ትተን ከጌታ ጋር መገናኘት ይጠበቅብናል፡፡ አዲሱን ሕይወትና የዚህን ሕይወት ባሕርይ፣ በዚህ ሕይወትም ውስጥ ካለች ከመንፈስ ኅብረት ተካፋዮች እንኾን ዘንድ ይገባናል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ምናልባት ጥበብን ለመማር የማታው ጊዜ የተሻለ እንደ ኾነ በመረዳቱ ነው፡፡ ጌታ ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምር እንደሚውል ያውቃል፡፡ ስለዚህም ኒቆዲሞስ ጌታን በምሽት ጠብቆ ለማግኘትና ለማግኘትና የድኅነትን ትምህርት ለመማር ወደደ፡፡
ሦስተኛው ምክንያት አንዳንድ ምልክቶችን ከተመለከተ በኋላ ጌታን ለማግኘት የመጀመሪያውን ዕድል በምሽት ማግኘቱ ነው፡፡ ዂሉም ሰው ሲተኛ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መንፈሳዊ ምሽትን ማሳለፍ ፈልጓል፡፡ ምናልባትም እንዲህ ዓይነት ዕድል ወደፊት ሊገጥመው እንደማይችል ሥጋት አድሮበት ሊኾን ይችላል፡፡
አራተኛው እንደ ነቢዩ ዳዊት ምሳሌውን ሊከተል ፈልጎ ነው፡፡ ዳዊት ሌሊቱን ለምስጋና ይጠቀምበት ነበርና (መዝ. ፴፮፥፮፤ ፻፲፱፥፻፵፰)፡፡
ይቆየን