ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – ሦስተኛ ክፍል

በዲ/ ታደለ ፈንታው

መጋቢት ፲፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

‹‹ኢየሱስም መልሶ እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው››€

ኒቆዲሞስ ምልክትን ማድረግ ለክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ለማመኑ ማሣያ አድርጎ ቆጥሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ረበናት እምነትን ምልክት ከመሥራት ጋር አያይዘውታልና፡፡ ስለ ክርስቶስ ማንነት ለመመስከር ከዚህ ወንዝ ባሻገር ያቋረጠው የለም፡፡ ስለዚህ ጌታን በጎነት ያለው መምህር፣ የእግዚአብሔር ሰው አድርጎታል፡፡ እግዚአብሔር ይስሐቅን ‹‹አትፍራ፤ እኔ ከአንት ጋራ ነኝና›› (ዘፍ. ፳፮፥፳፬) እንዳለው ሰው ዓይነት አድርጎ ገምቶት ነበር፡፡ ወይም እንደ መበለቲቱ ልጅ ‹‹ኢያሱ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ ከአንተም ጋር እሆናለሁ›› (ኢያ. ፩፥፭) ያለው ዓይነት ነቢይ ነበር ጌታ ለኒቆዲሞስ፡፡ ሌሎች ብዙ አለቆችና ነቢያት ተመሳሳይ ልምድ ነበራቸው፤ ነገር ግን ኒቆዲሞስ ምንም እምነትን ይዞ ቢመጣም ከፈሪሳውያን ጠባብ አስተሳሰብ ልጓም እንዳይወጣ የሚያደርግ አእምሮ ነበረው፡፡ የተማረውም ይኼንን እውነታ ነው፡፡ በጌታና በኒቆዲሞስ መካከል የነበረው ውይይት የሚከተሉት ነጥቦች የትኩረት አቅጣጫዎቹ ነበሩ፤

፩. የዳግም ልደት አስፈላጊነት እርሱም ውስጣዊው ዓለም የተሻለ እንደ ኾነ የሚያሳይ ነው፤ ይኸውም የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፡፡ ይህ አባባል በቅብጥ፣ በሶርያ፣ በላቲን በመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጽሑፍ የተካተተ ነው፡፡ ዮስጢኖስ፣ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ፣ ጠርጡለስ፣ አውግስጢኖስና፣ ዠሮም ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ጌታችን ኒቆዲሞስን እንደ ገና እንዲወለድ እንደጋበዘው ተረድቷል፡፡ ይህ አስደነቀው፡፡ አሳቡ በልቡ ውስጥ መዳህ ጀምሯል፡፡ ስለዚህም ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል?›› አለ፡፡

፪. አዲሱ ልደት ከላይ ነው ሰማያዊ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በቅዱሱና በሰማያዊው የእግዚአብሔር መንፈስ ብቻ የሚፈጸም ነው፡፡ የሰውን አሳብ ዂሉ ያለፈ ስጦታ ነው፡፡

፫. አዲሱ ልደት የሚፈጸመው በውኃና በመንፈስ ነው፡፡

፬. ይህ ልደት በኀይል ያለ በነፍስ የተመሰለ ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ምሥጢሩን ሊገነዘበው አይችልም፡፡

በአይሁድ ጽሑፍ እውነት የሚለው ቃል መደገሙ በእውነት ቅዱስ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ጌታችን የሚናገረው ነገር በጣም ጠቃሚና ትኩረት የሚያሻው መኾኑን ለመናገር ይጠቀምበታል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርጋታ ለኒቆዲሞስ የገለጸለት ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ መምህር መኾኑን ማመን ብቻውን በቂ አለመኾኑን፣ ተአምራቱንም ማድነቅና የተለዩ መኾናቸውን ማወቅ በራሱ ግብ አለመኾኑን ነው፡፡ በእርግጥም የሚያስፈልገው እንደ ገና መወለድ ነው፡፡ እርሱም ሰማያዊ የኾነ ልደት ነው፡፡ ሰማያዊ መንፈሳዊ የኾኑ ጉዳዮችን ለማየት ያስችላልና፡፡ በእናቱ ማኅፀን ያለ ፅንስ በዚህ ዓለም እየኾነ ስላለው ነገር የሚያውቀው ነገር የለም፡፡

በተመሳሳይ ኹኔታ አንድ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት መመልከት አይቻለውም፡፡ እንደ ገና ከተወለደ ብቻ ነው የአዲሱን ዓለም ብርሃን መመልከት የሚችለው፡፡ ሊያይ የሚለው ጌታችን አጽንዖት ሰጥቶ የተናገረው ግሥ ለእውነተኛ ክርስቲያን አስፈላጊ ነው፡፡ አዲሱን ልደት ያጣጥም ዘንድ ስለ ተወለደ እንዲመካ አይደለም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊመለከት ለመንግሥቱም እንደሚገባ ሊመላለስ ይገባዋል እንጂ፡፡ ይህ ማለት አእምሮውና ልቡ ሰማያዊ በኾነ ነገር ላይ ማተኮር አለበት ማለት ነው፡፡ ከሰማያዊ ሕግ ጋር አብሮ የሚሔድ ሕግን ያለማወላወል ሊከተል ይገባዋል፡፡ አዲስ ግብ፣ አዲስ ተስፋ አዲስ ኀይልን ገንዘብ አድርጎ፡፡

በአዲሱ ልደት ክርስቲያን በዓይነቱ የተለየ ኑሮን መኖር ይጀምራል፤ አሮጌውን የሰውነቱን ሕንጻ አፍርሶ መሠረቱ ክርስቶስ የኾነውን አዲስ ሕንጻ በማነጽ አሮጌው ሰዎችን ተወግዶ የክርስቶስን መልክ የያዘው አዲሱ ሰው ሊታይ ይገባዋል፡፡ አስቀድመን ኀጢአት ጥንተ ተፈጥሮአችንን ስላጠፋው፣ የልባችንም ጥልቅ በኀጢአት ተይዞ ስለ ኖረ፣ ሥጋውያን በሥጋ ሕግና ፈቃድም የምንመራ ኾነናል፡፡ የምንመራውም የመልካም ነገር ጠላት በኾነ በዲያብሎስ ነበረ፤ ስለዚህ አዲሱ ልደት ልንሸሸው የማይገባ ጠቃሚ ጉዳይ ኾኖ ቀርቧል፡፡ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ›› የሚለው የጌታ ቃል ለዚህ እውነት ማሳያ ነው፡፡

የእግዚአብሔር መንግሥት ምንድን ነው? ከሰማያዊው መሲሕ ሌላ መመልከት እንደሌለብን የምታሳስብ መንግሥት አይደለችምን? በእኛ መካከል መንግሥቱን መሥርቶ ይኖራል፡፡ ከእርሱ ጋር አንድነትን ፈጥረን የምናየው፣ የምንኖረው ዂሉ ለዚህ ሕይወት እንደሚገባ ነው፡፡ እርሱ ቅዱስ ስለ ኾነ እኛም ቅዱሳን እንኾናለን፡፡ በእኛ የሚኖረው የእግዚአብሔር መንግሥት ትክክለኛ ትርጕምም ይኼው ነው፡፡ ጌታ ‹‹መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ›› አለ (ማቴ. ፬፥፲፯)፡፡ እንደ ገናም በእግዚአብሔር መንግሥት ያለንን ሥፍራ ሲናገር ‹‹መንግሥተ ሰማያት በመካከላችሁ ናት›› ብሏል (ሉቃ. ፲፯፥፳፩፤ ራእ. ፩፥፮)፡፡

ይህ መንግሥት ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረትን የምንፈጥርበት መንግሥት በመኾኑ እንዲህ ተብሏል፤ ‹‹የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የኾነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም›› (ሮሜ. ፲፬፥፲፯)፡፡ ይህ መንግሥት ለዘላለማዊ ሕይወት ዋስትና ነው፡፡ ወደ ሰማይ እንድንጓዝ ጌታ በጌትነቱ ሲመጣ አስደናቂውን ክብር እንድንካፈል ያደርገናል፡፡ ከምንም በላይ አሳባችንን ከፍ ከፍ አድርጎ ውስጣዊ ነፍሳችንን የመጨረሻውን ቀን እንድትመለከት ጌታ ሲመጣ ሰማያዊ ዘውድን ደፍተን ያለ ፍርሃት በፊቱ እንቆም ዘንድ የሚያስችለንን ጸጋ እንይዝ ዘንድ ያስችለናል፡፡

የጌታን ቃል እንደ ገና በሌላ አባባል እንግለጠው ብንል ‹‹ዳግመኛ ካልተወለድህ ከመንፈስ ጋር ኅብረት ካልፈጠርህበጥምቀት ልጅነትን ካላገኘህ፣ እኔን በተመለከተ ትክክለኛ የኾነውን አሳብ አታገኝም›› የሚል ይኾናል፡፡ ኒቆዲሞስም ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?›› በማለት ጠየቀ፡፡ የኒቆዲሞስ ጥያቄ የእውቀት ድካሙን ይገልጣል፡፡ ጌታ የሚናገረው በመንፈሳዊ ቋንቋ ነው፡፡ የኒቆዲሞስ ልብ ነገሮችን የሚያገናኘው ቁሳዊ ዓለማዊ ከኾኑ ነገሮች ጋር ነው፡፡ ቁሳዊ ነገሮችን ከልቡናው ከአእምሮው ካላወጣ መንፈሳዊና ሰማያዊ የኾኑ ምሥጢራትን እንደምን ሊገነዘብ ይችላል? ያኔ ነው ወደ እውነት መድረስና በእግዚአብሔር መንፈስ አዲስ መንፈሳዊ ጉልበትን ይዞ ምሥጢርን መረዳት የሚቻለው፡፡

ይህ ዂሉ ነገር እያለ ኒቆዲሞስ ጀርባውን ለጌታ አልሰጠም፤ እርሱ የጎደለው አንድ ነገር እንዳለ አምኖ ትምህርቱን ቀጥሏል፡፡ በግብሩ ምንም እንኳን መምህርና አለቃ ቢኾንም በትሕትና እውነተኛ የኾነ ነገርን ለመማር የተዘጋጀ መኾኑን ገልጧል፡፡ ነገር ግን ጌታ የሚለው አዲስ ልደት የማይቻል እንደ ኾነ ገምቷል፡፡ አስደናቂ ሰው ነው፡፡ ረጅም ዘመን የትምህርትና የአመራር ልምድ ያለው ሰው ከጌታ እግር ሥር ተንበርክኮ አዲስ ነገርን ሲማር መመልከት ያስደንቃል፡፡ ለእውነተኛ አለቃ ጌታ የሰጠው ምሳሌ አስቸጋሪ ሊኾንበት ይችላል፡፡ አሁን ኒቆዲሞስ ስለ ትምህርትና ስለ አመራር ልምዱ ሲመካ አንመለከተውም፡፡ እስከ መጨረሻው እስትንፋሱ ድረስ ሲማር እንጂ፡፡ አምብሮስ እንዲህ ይላል፤ ‹‹የኒቆዲሞስኔታ የሚያሳየን መማር የማያስፈልገው እግዚአብሔር ብቻ መኾኑን ነው፡፡››

ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጣ፤ ከፍ ያሉ ነገሮችን አዳመጠ፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ተራ ሰው የሚገልጣቸው አይደሉም፡፡ ማንም ሰውም ከዚህ አስቀድሞ ሰምቷቸው አያውቅም፡፡ በቅፅበት ኒቆዲሞስ ወደ ከፍታ ወጣ፤ ነገር ግን መረዳቱ ጨለማ ነበር፡፡ ነገር ግን በራሱ ማስተዋል ገና የቆመ በመሆኑ ሊሸከማቸው ስላልቻለ ወደቀ፤ የጌታን ቃል እንዴት ሊሆን ይችላል? በማለት ጠየቀ፡፡ ጌታ የተናገረውን ነገር እንዲያብራራለት ሰው ከሸመገለ በኋላ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን በማለት ማብራሪያ ጠየቀ፡፡ ኒቆዲሞስ ስለ መንፈሳዊ ልደት ሰምቷል፡፡ ነገር ግን በመንፈስ አልተለማመዳቸውም (አያውቀውም)፡፡ የተማመነውም ቁሳዊ መረጃ ላይ ነው፤ ይህን ትልቅ ምሥጢር ለመረዳትና ለመተርጐም ምሳሌ አድርጎ ያቀረበው የሰውን የሥጋ ልደት ነው፡፡ ይህን ኹኔታ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፤ ‹‹ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፡፡ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ኾነ ሊያውቀው አይችልም›› (፩ኛ ቆሮ. ፪፥፲፬)፡፡

በዚህ ዂሉ ነገር ኒቆዲሞስ ክብርና ጉጉት ይታይበታል፡፡ ጌታ የነገረው ነገር አላስቆጣውም፡፡ ነገር ግን ይህ ኹኔታ የማይቻል መኾኑን አስቦ ጥያቄ ጠይቆ ዝም አለ፡፡ ሁለት ነገሮችን ተጠራጥሯል፡፡ ምን ዓይነት እንደ ገና መወለድ እና የእግዚአብሔር መንግሥት፡፡ አይሁድ በየትኛውም ጊዜ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የተናገሩት ነገር የለም፡፡ ስለ ዳግም ልደትም እንዲሁ፡፡ ስለነዚህ ነገሮች ሰምተውም አያውቁም፡፡ ኒቆዲሞስን ያስደነቀውም ነገር ይህ ነው፡፡

ቅዱስ አውግስጢኖስ እንደተ ተናገረው ይህ ሰው ከአዳምና ከሔዋን የሚደረግ ልደትን ሰምቷል፤ ከእግዚአብሔርና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሚደረገው ልደት ግን አያውቅም፡፡ የሚያውቀው ዘርን የሚተኩ ወላጆች በሞት ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ነው፡፡ ነገር ግን ሕይወትን ስለሚሰጠው ስለ አዲሱ ልደት ያለው ግንዛቤ ከመረዳት በታች ነው፡፡ ንብረታቸውን የሚወርሱ ልጆችን የሚወልዱ ቤተሰቦች ያውቃል፡፡ ነገር ግን ዘወትር የሚኖሩ ልጆችን የሚወልዱ የማይሞቱ ወላጆችን በተመለከተ እውቀት የለውም፡፡ ሁለት ዓይነት መወለድ አለ፡፡ አንደኛው በምድር የሚደረግ ሁለተኛው ሰማያዊ፡፡ የመጀመሪያው ከሥጋና ከደም ሁለተኛው ከውኃና ከመንፈስ፤ የመጀመሪያዎቹ ለሞት የተጋለጡ ናቸው የኋለኞቹ ዘላለማውያን ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የተወለዱት ከወንድና ከሴት የኋለኞቹ ከእግዚአብሔርና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ኒቆዲሞስን በተመለከተ የሚያውቀው አንድ ልደትን ብቻ ነው፡፡

ይቆየን