ኒቆዲሞስ እና አዲሱ ልደት – ሁለተኛ ክፍል
በዲ/ን ታደለ ፈንታው
መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ ዘንድ እየሔደ የመማሩ አምስተኛው ምክንያት ለካህናት አለቆች ወሬው ሊደርስ ይችላል ብሎ ከፍርሃት የተነሣ ነው፡፡
ስድስተኛው ደግሞ ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ ዘንድ መድረሱን አይሁድ ቢያውቁ ጌታችንን ለመዋጋት ቁጣቸውን ይጨምርላቸዋል፡፡ ኒቆዲሞስን ራሱን ለመጉዳት አይሁድ ፈሪሳውያን ሊነሣሡበት ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን በጌታ ትምህርት ቢማረክም በቀን እንዳይሔድ እምነት አንሶት ሊሆን ይችላል፡፡
ሰባተኛው ምክንያት ከምንም በላይ ጌታ የዓለም ብርሃን መኾኑን በእርግጠኝነት አለመረዳቱ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ነው፤ የእስራኤል መምህር ነው፡፡ ሰማያዊውን ደስታ ገንዘብ ያደርግ ዘንድ አዲስ ልደት የሚያስፈልገው ሰው ነው፡፡ በምሽት ሲመጣ ደካማ የሆነ እምነትን ይዞ ነበር የመጣው፤ ነገር ግን የጌታ በር ተከፍቶ አገኘው፡፡ ጌታ ስሜቱን ሊጎዳው አልወደደም፡፡
ዂሉ ነገር የሚቆጠረው እምነት እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ቀስ በቀስ በልቡ ውስጥ እንደሚያድግ ነበር፡፡ ጌታ የፈለገው ያች ቅንጣት አብባ፣ አፍርታ፣ ጌታ በሚሰቀልበት ጊዜ ትልቅ ዛፍ ትኾን ዘንድ ነበረ፡፡ እንደዚያ ሲኾን ነው በዚያ እምነት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው በድፍረት የጌታን ሥጋ የቀበረው፡፡
ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በተገናኘ ጊዜ የአይሁድ ድካም በእርሱም ላይ ይንጸባረቅ ነበር፡፡ አስቀድመን እንዳልነው በብርሃን ሳይኾን በጨለማ የመምጣቱም ምክንያት ይህ ነበር፡፡ ነገር ግን መሐሪው አምላክ አልጠላውም፤ ትምህርቱንም አልከለከለውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ከጌታው ጋር በፍቅር ለመነጋገር ቻለ፡፡ ጌታችንም ከፍ ያለውን ምሥጢር ገለጠለት፡፡ ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ ከአይሁድ የተለየ ቢኾንም ጌታን የቆጠረው ሰው አድርጎ ነው፡፡ ይናገረው የነበረው እንደ ነቢይ ነው፡፡ ያደረገውን ምልክት እያደነቀ ነበር የጠየቀው፡፡ ‹‹መምህር ሆይ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን … እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከኾነ በስተቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና›› ነበር ያለው፡፡
ኒቆዲሞስ ጌታ በተናገረው አዲስ ልደት ተደንቋል፡፡ ልክ እንደ ሌሎች አይሁድ ዘመዶቹ የአብርሃም ዘር በመኾኑ የሚመካ ነው፡፡ ጌታ ደግሞ እንደ ገና ተወለድ እያለው ነው፡፡ አይሁድ ለእግዚአብሔር የተመረጡና የተወደዱ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥሩ ነበር፡፡ በነቢያትና በተስፋው ቃል ኪዳን የተቀደሱ ሕዝቦች ነን ይሉ ነበር፡፡ ከምንም በላይ እግዚአብሔር ከእነርሱ አባቶች ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር፡፡ ልዩ መቅደስና መሥዋዕትም ነበራቸው፡፡
ኒቆዲሞስ እስራኤላዊ ብቻ አልነበረም፤ ፈሪሳዊም ጭምር እንጂ፡፡ ምን ዓይነት ከዚህ የበለጠ ልደት ጌታ ይሰጠኛል ብሎ ሊያስብ ይችላል? አይሁድ መሲሑ ሲመጣ የእስራኤል መንግሥት እንደሚያምንበት እንደ ገናም እንደሚወለዱ ይገምታሉ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ በነበራቸው ኩራትና ትምክህት አንጻር ሲመዝኑት ይህ የሚኾን አይመስላቸውም ነበር፡፡ እነርሱ አሁን ከያዙት የአብርሃም ልጅነት የከበረ ልደት ያለ መስሎ አይታያቸውም ነበር፡፡ ስለ ትውልድ አገራቸው ይመኩ ነበር፤ ስለዚህ ሌላ ልደት መስማት የሚኾንላቸው አይደለም፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ኒቆዲሞስን ‹‹ኒቆዲሞስ ሆይ፥ ስለ ምን በምስጢር በምሽት መጣህ? ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ የእግዚአብሔር የሆነውንም ነገር እንደሚናገር እያወቅህ፡፡ ስለምን ከእርሱ ጋር ነገሮችን በግልጽ አልተወያየህም?›› ዓይነት ጥያቄዎችን አልጠየቀውም፡፡ አልወቀሰውምም፡፡ ነቢዩ እንዲህ ይላል፤ ‹‹አይጮኽም፤ ቃሉንም አያነሣም፡፡ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም፡፡ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጨስንም ክር አያጠፋም›› (ኢሳ. ፵፪፥፫)፡፡ ጌታ ራሱ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ዓለሙን ላድን እንጂ በዓለሙ ልፈርድ አልመጣሁም›› (ዮሐ. ፲፪፥፵፯)፡፡
የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትሕትና ተመልከቱ! ‹‹እኔ ዂሉን በራሴ ማድረግ ይቻለኛልና የማንም ርዳታ አያስፈልገኝም፡፡ እኔ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ የያዝኩት ኀይል የአባቴን ኀይል ነው …›› አላለም፡፡ ይህንን ቢል ለሚያዳምጡት ወገኖች ቃሉን መቀበል ከባድ በኾነ ነበር፡፡
ነገር ግን ድርጊቱን ሲፈጽም በተመሳሳይ መንገድ አልነበረም፤ ምልክትን ሲያደርግ በኀይል ነው፤ ስለዚህም እንዲህ አለ፤ ‹‹ልትነጻ እወዳለሁ›› (ማቴ. ፰፥፫)፤ ‹‹ጣቢታ ተነሽ›› (ማር. ፭፥፬)፤ ‹‹እጅህን ዘርጋ›› (ማር. ፫፥፭) ‹‹ኀጢአትህ ተሰረየችልህ›› (ማቴ. ፱፥፪) ‹‹ፀጥ በል›› (ማር. ፬፥፴፱) ‹‹አልጋህን ተሸከምና ሒድ›› (ማቴ. ፱፥፮)፤ ‹‹አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ›› (ማር. ፭፥፰)፤ ‹‹ማንም ስለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ቢላችሁ ‹ለጌታ ያስፈልገዋል› በሉት›› (ማር. ፲፩፥፫)፤ ‹‹ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኾናለህ›› (ማር. ፳፫፥፵፫)፤ ‹‹ለቀደሙት ‹አትግደል› እንደተባለ ሰምታችኋል፡፡ የገደለም ዂሉ ፍርድ ይገባዋል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ዂሉ ፍርድ ይገባዋል›› (ማቴ. ፭፥፳፩)፤ ‹‹ተከተለኝ፤ ሰውን አጥማጅ አደርግሃለሁ›› (ማቴ. ፩፥፲፯)፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የጌታችንን አምላክነትና ትሕትና ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ስለዚህ ነው ጌታ ኒቆዲሞስን በግልጥ ያናገረው፤ ነገር ግን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን በመግለጽ አልጀመረም፤ ምልክት የሚያደርገው በተመሳሳይ ሥልጣን መኾኑን አልገለጠለትም፡፡››
በማንኛውም ኹኔታ የጌታችንን ታላቅ ሥልጣን እንመለከታለን፡፡ አምላካዊ ሥራን ሲሠራ ማንም ወገን በእርሱ ላይ ስሕተትን ማግኘት አይቻለውም፡፡ ነገር ግን ሊያጠምዱበት የሚቻላቸው በአንድ መንገድ ብቻ ነው እርሱም በንግግሩ ብቻ ነው፤ ማለት ንግግሩን በተሳሳተ መንገድ በመተርጐም፡፡ ኒቆዲሞስ በስሙ ከሚያምኑ ከጌታ ጋር ግን ግንኙነት ከሌላቸው ወገኖች አንዱ ነበረ፡፡ ስለዚህ በምሽት ወደ ጌታ ዘንድ መጣ፡፡ የመጣው ወደ ብርሃን ቢኾንም በጨለማ መጣ፡፡ ምንም እንኳን ኒቆዲሞስ የመጣው ወደ ጌታ ቢኾንም የመጣው በምሽትና የሚናገረው በጨለማ ነፍሱ ነበር፡፡ ስለዚህ በሰው ዂሉ ላይ የሚያበራውን ብርሃን የሚናገረውን መልእክት ሊረዳው አልተቻለውም፡፡
ኒቆዲሞስ መምህር ነበረ፡፡ ወደ እውነተኛው ብርሃን በጨለማ የመምጣቱ ምሥጢርም ምናልባት ለክብሩ ተጠንቅቆ ይኾናል፡፡ የሚያናግረውን ጌታ አምላክነት ገና አላወቀም ነበርና ፈራ፡፡ ኒቆዲሞስ በምሽት ወደ ጌታ የመጣው ለመጠመቅ አልነበረም፡፡ ለመማርና የጌታ ደቀ መዝሙርም ለመኾንም አይደለም፡፡ በአይሁድ ትውፊት መሠረት ማንም ወገን በምሽት ወደ አይሁድ እምነት፣ ለመገረዝ ወይም ለመጠመቅ አይመጣም፡፡ ይህ ሕግን መተላለፍ ነው፡፡ እንደ ተማሪ ከጌታ ሥር ቁጭ ብሎ ለመማር ሳይኾን የጌታን አሳብ ለማወቅና በጎዳናውም ይጓዝ ዘንድ ነው፡፡
የአይሁድ መምህር ‹‹ረቢ›› ብሎ ጌታን መጥራት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የሕዝብ አለቃ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሰው በትሕትና ረቢ ብሎ ሲናገር መመልከት በእርግጥም ያስደንቃል፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታን የጠየቀው ነፍሱ ስለምትድንበት ኹኔታ ብቻ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ስለ ጌታ አንድ ነገር ያውቃል፤ ጌታ በአይሁድ ምሁራን ወይም በታወቀ የአይሁድ ትምህርት ቤት ገብቶ የተማረ አይደለም፡፡ ትምህርቱ ከሰማይ ነው፡፡ ጌታ የያዘው የእውነትን ኀይል እንጂ የሰይፍን ኀይል አለመኾኑን ተገነዘበ፡፡ ከምድራዊው ጥበብ ባለፈ ፍጹም መለኮታዊ ጥበብ እንደሚናገርም ተገንዝቧል፡፡ የሚያደርገው ምልክት በመለኮታዊ ኀይል መኾኑን አስተውሏል፡፡
በጣም አስደናቂው ንግግሩ ደግሞ ‹‹መምህር ሆይ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን›› የሚለው ነው፡፡ ምናልባት ከእርሱ ጋር ሌሎች ሰዎች እንዳሉ ያመለክታል፤ ወይም ፈሪሳውያንን ወክሎ እየተናገረ ይኾናል፡፡ ምክንያቱም ምግባቸውም መጠጣቸውም ወሬአቸውም ክርስቶስ ኾኗልና፡፡ ከእነርሱ መካከል ኒቆዲሞስ የሚያምነውን እምነት የሚያምኑ ፈሪሳውያን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ መካከል ጌታን በግልጥ ወይም በስውር ሊያገኘው የፈለገ ወገን የለም፡፡
ይቆየን