‹‹ኑ ምሳ ብሉ›› (ዮሐ.፳፩፥፲፪)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ግንቦት ፱፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ይህን ኃይለ ቃል የተናገረው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቃሉን ደግሞ የሚበላ ፈልገው ዓሣ ለማጥመድ ሌሊቱን ሲደክሙ ለነበሩ ግን የሚፈልጉትን ሳያገኙ በረኀብ ዝለው በፍለጋ ደክመው ለነበሩ ለቅዱሳን ሐዋርያት ነው፡፡ ሞትን በሞቱ ገድሎ፣ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አብሥሮ፣ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለቅዱሳን ሐዋርያት በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ተገለጠላቸው፤ ይህ ከትንሣኤው በኋላ ሲገለጥላቸው ሦስተኛው ጊዜ ነው፡፡ መጀመሪያ ሲገለጥላቸው አይሁድን ፈርተው በፍርሃት ተሸብበው በራቸውን ዘግተው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ በነበሩ ጊዜ በዝግ ቤት ገብቶ ፍርሃትን አስወገደላቸው ተስፋቸውን ቀጠለላቸው፤ ለተረበሸው ልባቸው ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› በማለት ሰላምን ሰጣቸው አረጋጋቸው፡፡ (ሉቃ.፳፬፥፴፮፣ዮሐ.፳፥፲፱)
ዳግመኛም በሌላ ጊዜ የተቸነከረ እጁን፣ የተወጋ ጎኑን ካላየው ካልዳሰስኩ አላምንም ላለው ትንሣኤውን ማመን (መቀበል) ተስኖት ለነበረው ቅዱስ ቶማስ ባለበት ዳግመኛ በዝግ ቤት ሳሉ ተገለጠ፤ የተወጋ ጎኑንና የተቸነከረ እጁንም አሳያቸው፤ ቅዱስ ቶማስም አይቶና ዳሶ አምላኩ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን አመነ፤ ‹‹ጌታዬ አምላኬ›› ብሎ መሠከረ፤ የእምነት ተከፍሎ ነበርና ይህን ለማጽናት ያመኑ እንጂ የተጠራጠሩ እንዳይሆኑ ተገለጠላቸው፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፬-፴)‹‹ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም›› ብሏልና ለጨለማው ዓለም ስለ ብርሃን ክርስቶስ እንዲመሰክሩ በኃጢአት የመረረውን ዓለም በወንጌል ጨውነት ሊያጣፍጡ በንጹሐ ባሕርይ ክርስቶስ ንጹሕ ደም መፍሰስ ዋጋ ለተከፈለላቸው ለአዳም ልጆች የምሥራች እንዲሰብኩ መርጧቸዋልና በጥርጥር ማዕበል እንዳይመቱ አምነው እንዲያሳምኑ እምነታቸውን ሊያጸና ተገለጠ፡፡ (ዮሐ.፮፥፴፯)
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ተገለጠላቸው በዚህ ሥፍራ በዚህ ወቅት መገለጡ ቅዱሳን ሐዋርያት የሚበላ ነገር ፈልገው ዓሣ ያጠምዱ ዘንድ ቅዱስ ጴጥሮስን ተከትለው ወደ ጥብርያዶስ ባሕር ተጓዙ፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አብሯቸው በነበረ ጊዜ ኅብስት አበርክቶ ይመግባቸው ነበር፤ ምግብን እየገዙም ይመገቡ ነበር፤ ‹‹…ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበር…›› (ዮሐ.፬፥፰) እንዲል በወንጌል፤ ከጌታችን ሞት በኋላ ግን የሚመገቡት አጡ፤ ዓሣ ለማጥመድ ወደ ቀደመ ግብራቸው መመለስን መረጡ፤ ቀድሞ ጌታችን መርጦ ሲጠራቸው ‹‹…ኑ ተከተሉኝ፤ ሰውን የምታጠምዱ እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ›› አላቸው፤ ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት…›› (ማቴ.፬፥፲፱ ) እነርሱም ሁሉን ጥለው በእምነት ተከተሉት፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ጌታችንን ‹‹…እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን…›› በማለት የጠየቀው ሁሉን ትተው ተከትለውቷልና። (ማቴ.፲፱፥፳፯)
በዋለበት እየዋሉ ባደረበት እያደሩ የእጁን ተአምራት እያዩ የቃሉን ትምህርት እያደመጡ አንዳች ሳይጎድልባቸው አብረውት ነበር፤ የተነገረው ትንቢት ደርሶ፣ ምሳሌው እውን ሆኖ፣ በፈቃዱ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ፣ ዓለም በእጁ መዳፍ ያለች ጌታ ሙስና መቃብርን ያጠፋልን ዘንድ በከርሠ መቃብር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በተስፋ መቁረጥ ተሸብበው በእምነት ተከፍሎ ተይዘው ‹‹አንዳች አትጨነቁ›› የሚለውን አምላካዊ ቃል ቢያውቁትም ተቸግረው የጣሉትን መረብ የሚበላ ዓሣ ያጠምዱበት ዘንድ አነሡ፤ ግን ‹‹ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም..›› ብሏልና ሌሊቱን ሙሉ ቢደክሙም አንዳች ነገር አላገኙም፡፡ (ዮሐ.፲፭፥፭)
ባሕረ ጥብርያዶስን እነ ቅዱስ ዮሐንስ ጠንቅቀው ያውቁታል፤ በቀደመ ሕይወታቸው ከአባታቸው ከዘብድዮስ ጋር ሆነው ዓሣ በማጥመድ ሥራ ተሠማርተው ሕይወታቸውን ይገፉ ነበርና፤ አሁን ግን ባሕሪቱ ነፈገቻቸው፤ ከፈጣሪዋ አልታዘዘችምና ያለ ፈቃደ እግዚአብሔር ለሚከወን ተግባር ተፈጥሮ እንኳን ፈቃዷን ትነፍጋለች፤ አንዴ ከተጠራን የዓለምን ክፉ ሐሳብ ትተን መከተል ከጀመርን በኋላ ሕይወት ምንም እንኳን ብትከፋብንም ጊዜያዊ ችግራችንን ለመቅረፍ ወደ ተውነው የክፋት ሥራ መመለስ አይገባም፡፡
ብዙ ጊዜ ለምንሠራቸው የስሕተት ሥራዎች እንደ ምክንያት የኑሮ ጉድለታችንን፣ ማጣታችንን፣፣መቸገራችንን ለሽንፈታችን ምክንያት አድርገን ማቅረቡ አግባብነት የለውም፤ ‹‹ምን ላድርግ እንዲህ ስለሆነ እኮ….ተቸግሮ እኮ ነው…›› የሚሉ ምክንያቶች ከተጠያቂነት አያድኑንም፤ አበው ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹እንግዲህ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ..›› በማለት ጌታችን በማይታበል ቃሉ ነግሯቸው ነበር፤ (ማቴ.፮፥፴፪) ግን ተጨንቀው የሚበላ ፍለጋ ወጡ፤ ‹‹ለምኑ ይሰጠችኋል›› የሚለውን የርኅራኄ ቃሉን አስታውሰው ቢለምኑ ከሌት ቁርና ብርድ ጋር እየታገሉ የዕለት ምግባቸውን ፍለጋ ባልተንገላቱ ነበር! (ማቴ.፯፥፯) ባሕረ ገሊላም እንደቀደመው ጊዜ በውስጧ ያሉትን ፈጣሪ ለምግበ ሥጋነት የፈጠራቸውን ዓሣ ሳትሳሳ በለገሰቻቸው ነበር፤ ግን ያለእርሱ ፈቃድ አንዳች ማድረግ አይቻልምና የባሕሪቱን ጓዳ ጎድጓዳዋን ውስጠ ምሥጢሯን ለሚያውቁ ከዓሣ አጥማጅነት ለተጠሩ ቅዱሳን ሐዋርያት የሚሹትን ዓሣ ለማጥመድ ባልተቸገሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ሳይዙ መሮጥ ድካም እንጂ ከፍጻሜው ሥፍራ መድረስ አይቻልም፡፡ እግዚአብሔርን ሳይዙ መሥራት መገንባት ከንቱ ነው፤ ‹‹እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ…›› (መዝ.፻፳፯፥፩) እንዲል ቃሉ፤ ሩጫችን፣ ዕቅዳችን፣ ክንውናችን ከእርሱ ጋር በእርሱ ፈቀድ ካልሆነ ብንገነባ ይናዳል፤ ብናንጽ ይፈርሳል፤ ብንሮጥ ይርቃል፡፡
ቅዱሳን አበው ሐዋርያት ሌሊት ሙሉ ደከሙ ሐሳባቸው ሳይሞላና የልባቸው ሳይደርስ የፈለጉትን ሳያገኙ ሌሊት ለብርሃን ጊዜውን ለቀቀ ሩኅሩኅ ጌታ ድካማቸውን አየ፤ የሚሹትን ይሰጣቸው ከድካማቸው ያሳርፋቸው ዘንድ ተገለጠላቸው፤ የሚበላውን ማዕድ ቢያዘጋጅም የልባቸው ይደርስ ዘንድ ወደፊት ሰዎችን ከዓለም ባሕር በወንጌል መረብነት ያጠምዱ ዘንድ እንዳላቸው ሲያስረዳ መረባቸውን በስተቀኝ እንዲጥሉ አዘዛቸው፤ ፍቅረ ቢጽን፣ ትሕትናን አስተምሯቸዋልና ጌታችን እንደሆነ ሳያውቁ እንኳን በትሕትና እሺ አሉ፤ መልካም የሆነ ሐሳብን ሰዎች ሲለግሱን እኛ ያላየነውን መልካም አቅጣጫ ሲጠቁሙን ለመልካም ነገር እስከ ሆነ ድረስ መሞከሩ አይጎዳም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ መረቡን በስተቀኝ እንዲጥሉት ሲነግራቸው በቅንነት ቅን ሐሳቡን ተቀብለው በስተቀኝ መረባቸውን ጣሉ፤ መረባቸው እስኪጨናነቅ ድረስ በዓሣ ተሞላ፡፡
ቀኝ የመልካም ነገር ምሳሌ ነው፤ ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት በዝማሬው ‹‹ቀኝህ ጽድቅን የተመላች ናት…›› (መዝ.፵፯(፵፰)፥፲ እንዲል፤ በቀኝ ጽድቅ አለ፤ በሌላኛው ዝማሬው ክቡር ዳዊት ‹‹..በቀኝህም የዘለዓለም ፍስሓ አለ…›› (መዝ.፲፮፥፲፩) በቀኙ ተድላ ደስታ አለ፤ የአብ ቀኝ እጁ እግዚአብሔር ወልደ አጠገባቸው በቆመ ጊዜ የፈጠራት ባሕር ታዘዘችላቸው፤ ኀዘናቸው ርቆ ደስታን ተላበሱ፡፡ በቅንነት እግዚአብሔርን አምነን እንሥራ፤ ዕቅዳችን ይሠምራል ግባችን ይሳካልና፤ ጽድቁን ፈልገን ስናገለግል የሚያስፈልገንን እርሱ ይሰጠናል፡፡ የሚበላውን አዘጋጅቶ ‹‹..ኑ ምሣ ብሉ !›› በማለት ጠራቸው፤ ‹‹አስቀድማችሁ ጽድቁን እሹ፤ ሌላው ይጨምርላችኋል›› በማለት በአማናዊ ቃሉ የተናገረ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቁን ሽተው ተከትለውታልና ምግባቸውን አብስሎና ማዕዱን አሰናድቶ ይመገቡ ዘንድ ጠራቸው፤ (ማቴ፮፴፫) አምላካችን ሲሰጥ እንዲህ ነው! ጥቂት ሲለምኑት አብዝቶ ይሰጣል፤ እንደሌላቸው እያወቀ የሚበላ ነገር ጠየቃቸው፤ የሚሰጠውን ነገር ስጡኝ በማለት ይጀምራል፤ የሌላቸውን ሊሰጥ ወደ እነርሱ ሄደ፤ ‹‹…ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም …›› ብሏቸዋልና አልተዋቸውም፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፲፰)
የሰላም አምላክ፣ ምስካየ ኅዙናን፣ አምላከ ነዳያን ያጣነውን ሰላም ሰጥቶ ከጭንቀታችን ያረጋጋን፤ ይራራልን፤ ከድካማችን ያሳርፈን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን!