‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ››
ክፍል ዘጠኝ
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሰኔ ፲፱፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ተወዳጆች! እንዴት ሰነበታችሁ? በክፍል ሰባት እና ስምንት “ምንኩስና ዛሬ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እያጋጠመው ያለውን ተግዳሮት” አንስተን የተወሰኑ ችግሮችን ለማቅረብ ሞክረን ነበር፤ክብረ ምንኩስና ነገ ምን መሆን አለበት? እንዴትስ የተሻለ እናድርገው? የሚለውን በዚህ በክፍል ዘጠኝ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ!
የምንኩስና መሠረቱ፡- ሄኖክ በተባሕትዎ ጀማሪነት ለመዓሳባን፣ መልከ ጼዴቅና ኤልያስ በድንግልናዊ ሕይወት ጀማሪነት ለደናግላን አብነት ወይም መሪ መሆናቸውን ተያይዞ ከመጣው የምንኩስና ታሪክ እንረዳለን፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅም ነቢያቱን ሄኖክና ኤልያስን አብነት አድርጎ ሠላሳ ዘመን በገዳም ተወስኖ እህል ሳይበላ የግመል ጸጉር ለብሶ ወገቡን በጠፍር ታጥቆ የማርና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ በግብረ ተባሕትዎ ጸንቶ ኖሯል፡፡ (ማቴ.፫፥፬)
ሥርዓተ ምንኩስና እንዲህ በመንፈሰ እግዚአብሔር የተመራ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹ቤቱን ወንድሙንና እኅቱን፣ አባቱንና እናቱን፣ ሚስቱንና ልጆቹን፣ ንብረቱን ትቶ በስሜ አምኖ ይከተለኝ፤ የዚህን ሁሉ መቶኛ እጥፍ ያገኛል የዘለዓለም ድኅነትም ያገኛል›› ብሎ ስለ መዓርገ ምንኩስና ትክክለኛ ትርጉም ሰጥቶ የተናገረውን ቃል መሠረት በማድረግ በርካታ መነኮሳት በየገዳማቱ እንደ ከዋክብት አሸብርቀው እንደጨረቃ ደምቀው የቅድስና፣ የንጽሕና፣ የመልካም ምግባር፣ ትጋትና የታታሪነት ምሳሌና አብነት ሆነው የኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት መናንያን ነበሩ፤ አሁንም አልፎ አልፎ ከሥርዓተ መነኮሳት ያላፈነገጡ በየገዳማቸው አሉ፡፡ (ሉቃ.፲፰፥፳፱)
ይሁን እንጅ አሁን አሁን ለምንኩስና ሥርዓት የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ፣ በየገዳማቱ የምንኩስና ሕግ እየላላ በመምጣቱ፣ ማን ይመነኩሳል? ማን ያመነኩሳል? የት ይመነኩሳል ወዘተ የሚለው መቸቱ ብዙም ትኩረት ተሰጥቶ ስላልተሠራበት ችግሮች እየሰፉ፣ ገዳማዊ ሕይወት ቦታ እያጣ፣ ምንኩስና ጌታ እንደተናገረው በዚህ ዓለም ደስታን የሚሰጡ ነገሮችን ሁሉ ስለ ሰማያዊ ደስታ፣ በዚህ ዓለም ፍቅር የሚሰጡ ቤተ ሰቦችን ሁሉ ስለ ክርስቶስ ፍቅር መተው መሆኑን ጌታ ያስተማረውን በመዘንጋት ምንኩስና ለሹመት፣ ምንኩስና ለምድራዊ ክብር፣ ምንኩስና ዘመድ አዝማድን ለመጥቀሚያና የራስን ሥጋዊ ድሎት መፈጸሚያ ሆኖ እየታየ ይገኛል፡፡
የነገዋ ቤተ ክርስቲያን የተስተካከለ ቁመና እንዲኖራት ምንኩስና አምድ ሆኖ ያገለግል ዘንድ ችግሮቹን ነቅሶ አንሥቶ መወያየት ብቻ ሳይሆን ምን ይደረግ የሚለውንም የመፍትሔ ሐሳቦች መጠቆም ያስፈልጋል፡፡
፩ኛ.ከቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅ፡-
ሀ. መነኮሳትን በከተማ አለመሾም፡-
ምንኩስና ችግር ላይ እንዲወድቅ መነኮሳት ጥለውት ንቀውት ወደሄዱት ዓለም እንዲመለሱ፣በዚህም ምክንያት ገዳማዊ ሕይወት እንዲዘነጋና ገዳማት ወና እንዲሆኑ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው መነኮሳትን በከተማ አድባራትና በየመምሪያው ብሎም በሌሎች ተቋማት ላይ መሾም ነው፡፡ የቦሮሜዳው ሊቅ መምህር ኃይለማርያም ዘውዱ ‹‹ከገዳም ፈልሰው የሚመጡ መነኮሳትን ተቀብሎ የቢሮ ሥራ መስጠት ከከተማ እንዲኖሩ ማድረግ ገዳማትን እንደማፍረስ ሕይወተ ምንኩስናንም ያልተገባ ቦታ እንደ መጣል ነው›› ይላሉ፡፡
ገንዘብን ንቆ የሄደን ገንዘብ ላይ፣ ቤተ ሰብን ትቶ ክርስቶስን መርጦ የሄደን ሰው፣ ቤተ ሰብ ላይ፤ሀብትን ንብረትን የዚህን ዓለም ባለጸግነት ምቾትና ሥጋዊ ድሎትን መንኖ የሄደን መነኩሴ ጎትቶ ከገዳም አስወጥቶ እጅግ ፈታኝና የተወሳሰበ ችግር ባለበት ሥልጣን ላይ መሾም የችግሩ ምንጭ እንደሆነ ይታመናል፡፡ እነዚህን መናንያን በገንዘብ ላይ ሹሞ ገንዘብን እንዲጠሉ መጠበቅ አጉርሶ አታላምጡት የማለት ያክል ነው፡፡ ሹመት በጠባዩ ክፉ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ከሚፈታተኑ ሰብእናውንም ከሚያስገምቱ ነገሮች ዋነኞቹ ሹመትና ገንዘብ ናቸው፡፡
መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ እነዚህን ሁለቱን የሰው የክፋቱ መገለጫዎች ናቸው ይላሉ፤ አንድ ሰው የተደበቀ ማንነቱ የተሠወረ ገመናው የሚገለጠው ወይ ሥልጣን ሲይዝ ወይ ገንዘብ ሲኖረው እንደሆነ ይነገራል፤ ጠብቄ ከሴት ርቄ መኖር እፈቅዳለሁ ብሎ የመነ ነን ሰው ወደ ዓለም ማምጣት በሀብትና በንብረት ላይ መሾም ያልተገባ ፈተና በተሸመው ሰው ላይ እንደሚያመጣ መረዳት ያስፈልጋልና ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንን ችግር ብትረዳው መልካም ነው፡፡
መሾም መሻር፣ መቅጠር ማባረር፣ መስጠት መከልከል፣ የቻለ መነኩሴ ቢፈተን ዘረኛ ቢሆን፣ አድሎ ቢፈጽም፣ ሴት አይቶ ቢመኝ፣ ተጣልቶ ቢሰዳደብ፣ ቂመኛ በቀለኛ ቢሆን ወዘተ የሚያስገርም አይሆንም፤ ምክንያቱም በጾም በጸሎት፣ በትጋት በጽሕፈት በድጉሰት በስግደት በተግባረ እድ በአበው ቀኖና ተወስኖ አጋንንትን ድል ከሚነሳበት ገዳም አውጥተን የስግደት የጸሎት የትሩፋት የተጋድሎ ጊዜውን በቢሮ ብሮክራሲ ወጥረነው የምንኩስና ፍሬ ልንፈልግበት አንችልም፡፡
ይህ ማለት ዓሣውን ከባሕሩ አውጥቶ በሕይወት እንዲኖር መመኘት ነው የሚሆነው፡፡‹‹በዚህ ዓለም የሚገኝ ክብር ሁሉ ኃላፊ ነው፤ ከሞቱ በኋላ የሚገኝ ክብር ግን የማያልፍ ነው፡፡አንድ ጊዜ ጸሎት አንድ ጊዜ ጨዋታ፣አንድ ጊዜ ሀብት መውደድ አንድ ጊዜ ሀብት መጥላት፣አንድ ጊዜ በሰፊ መክተት አንድ ጊዜ መዞር ለመነኩሴ እንዲህ ያለ ሁሉ እየሰበሰቡ መበተን ነው›› ይላል፡፡(መጽ.ምዕዳን ገጽ ፻፶፭)
ለ. ሥርዓተ ገዳምን ማጠናከር፡-
ቀደም ባሉት ዓመታት ለገዳማት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን እጅግ ብዙ ገዳማት ቢኖሯትም ብዙዎቹ ጠፍ ሆነዋል፤ መናንያኑ ተበትነዋል፤ አንዳዶቹ በሽህና በመቶዎች የሚቆጠር መናኝ የነበረባቸው አሁን ላይ ጥቂት መናንያንን ብቻ ይዘው ይገኛሉ፤ አንዳንዶቹ የዕውቀት ማዕከል የሥልጣኔ መነሻ እንዳልነበሩ ዛሬ ላይ ምንም የማይታይባቸው ሆነዋል፡፡ድህነት ፈትኗቸው የዓመት ልብስ የዕለት ጉርስ አጥተው መናንያኑ ከገዳም የወጡበት፣ አንዳንዴም ከላይ እንደገለጽነው በዓለም በሚኖሩ የከተማ መነኮሳት ቅንጡ አኗኗር ተማርከው ከተማ የሚገቡ በመብዛታቸው ገዳማት ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡
በርግጥ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱሳት ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶችን ማዕከል ያደረገ ሥራ በመሥራቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል ከምንም በላይ ግን የቤተ ክህነቱንም የሌሎችንም ትኩረት ማግኘት ችሏል፡፡ ቢሆንም ግን በቂ አይደለም፡፡ ሲኖዶሱም ሆነ በየደረጃው እስከ ወረዳ ብሎም እስከ አጥቢያ የተዘረጋው ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ከፍ ለማድረግ፣ ክብሯን ለማስጠበቅ ለገዳማት ትኩረት መስጠት፣እንደ ቀድሞው የኦርቶዶክሳዊ ተግባረ ዕድ ማዕከላት እንዲሆኑ፣ የቅድስና የመንፈሳዊነት ማሳያ ቦታዎች እንዲሆኑ የታፈሩና የተከበሩ የምእመናንም ኩራት የሆኑ አባቶች በዚያ መኖር እንዲችሉ በጀት መመደብ፣ ሥልጠና መስጠት፣ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ መተግበር፣ መናንያኑ ሁለገብ ዕውቀት ከመንፈሳዊነት ጋር እንዲይዙ የሚያደርግ ስልት መንደፍ፣ በከተማ ካሉት ይልቅ በገዳም ላሉት መነኮሳት ክብርና ቦተ መስጠት ይገባል፡፡
ከምንም በላይ ግን ወደ ዓለም የሚፈልሱ በየሥርቻው ተሸጉጠው ክብረ ምንኩስናን የሚያዋርዱትን፣ በአበው አስኬማ የሚነግዱትን ሥራ ፈት መነኮሳትን መቆጣጠሪያ ሥርዓት ማበጀት፣ የት፣ መቼና በማን እንደመነኮሱ መጠየቅ፣ መነኮሳት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በልዩ ፈቃድና ዕውቅና በደብዳቤ ወይም በይለፍ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ የጋራ የገዳማት ደንብ ማዘጋጀት፣ ከዚያ ባለፈ ባልተገባ ቦታ የሚገኙትን በወንጀልና በሚያስነቅፍ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ያለይሉኝታ በሕግ መጠየቅና ማጋለጥ ቢቻል መልካም ነው፡፡
፪ኛ.ከመነኮሳት ከራሳቸው የሚጠበቅ፡-
‹‹ምንኩስናሰ ዘእምፈቃድ ይእቲ ወአኮ በግብር›› እንዳሉ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ምንኩስና የፈቃድ ሕግ ናት፡፡ አንድ ሰው ሲመንን ሲመነኩስ ተገዶ ሳይሆን ፈቅዶ ስለሆነ ወዶ ፈቅዶ የገባበትን፣ምንኩስና ሊጠብቀው እስከመጨረሻው ጸንቶበት ዘለዓለማዊ መንግሥቱን ሊወርስበት ይገባል፡፡ ‹‹መነኮሳትም ምድራዊ መላእክት ሰማያዊ ሰዎች ናቸው፡፡ እንደ ችሎታቸው መጠን በሥራቸውም ሁሉ የሐዋርያት ምሳሌዎች ናቸው፤ ከዓለም ፍጥረት በመለየት ፈቃደ ሥጋቸውን በመተው እስከ ሰውነታቸው ድረስ ሥራውን ሁሉ በመናቅ ስለ ትእዛዙ ስለ ፍቅሩ ፈቃዱን ለመፈጸም ያዘዛቸውን ትእዛዝ ስለሚያደርጉ እርሱንም ብቻ ከአባቶች ከልጆች፣ ከሚስት ከገንዘብ ይልቅ ፈጽሞ ስለሚወዱ ነው፡፡ ዛሬ በፈቃዳቸው ከሚሠሯት ድካም ዕረፍት ስለማድረግ ከኋለኛውም ዓለም ፍርድ ፈጽሞ ስለመዳን ብፁዓን ናቸው፡፡ ብፁዓን ግን በፈቃዳቸው ስለሚሠሩት ስለ ኃላፊው ድካም የመንግሥተ ሰማያት ማደሪያ ስለተዘጋጀላቸው ፈጽሞ ብፀዓን ናቸው››ይላል፡፡ (ፍት ነገ አን ፲፥፫፻፵፬)
ስለ ክርስቶስ ፍቅር ብሎ የሚስትን ፍቅር የልጅን ደስታ የተወ፣ ፍጹም ለመሆን እናቱና አባቱን ወንድሙን እኅቱን የተለየ፣ ራሱን ስለመንግሥተ ሰማያት ድሃ በማድረግ ሀብት ንብረቱን ሸጦ ለነዳያን የመጸወተ፣ ወይባ ለብሶ፣ ጠፍር ታጥቆ ለእግሩ ጫማ ለእጁ በትር ሳይኖረው ፈጣሪውን አምኖ ሁሉን ትቶ የመነነ ገዳም የገባ፣ በእንጦንስ በመቃርስ ሥርዓተ ምንኩስና ሊኖር የወሰነ መነኩሴ ወደ ዓለም ሲመለስ፣ ሀብት ንብረት ሲያግበሰብስ መታየት እንደ እሪያ ታጥቦ ጭቃ መሆን ወይም እንደውሻ ወደ ትፋት መመለስ ስለሚሆን መነኮሳት ከክብር የሚያሳንሳቸው ከማኅበረ መነኮሳት የሚነጥላቸው በመሆኑ ቆም ብለው ማሰብ ያስፈልጋቸዋል፡፡
‹‹መነኩሴ የምንኩስናውን ሕግ ንቆ ከገዳሙ ቢወጣ በዚያ ይኖር ዘንድ ወደ ከተማ ቢሄድ በዚያች ውስጥ ባሉት በሕዝባውያን ማዕረግ ይኑር በሕዝባውያን አምሳል እንጅ መነኮሳትን ይመስል ዘንድ አይገባውም››ይላል፡፡(ፍት.ነገ.አን.፲፥፬፻፭) ይህ ማለት ከገዳም መውጣት፣ በዓለም በሀብት በሹመት መኖር፣ እንደ ሕዝባዊ እንጅ እንደ መነኩሴ አያስቆጥርም የምንኩስናን ሕግ ጥሷል፤ አቃሏል፤ በገዳም ሥርዓት ሊኖር አልወደደምና ከማኅበረ መነኮሳት ተለይቷልና እንደ መነኩሴ ሊኖር አይገባውም፤ አርአያም አይሆንምና እያለን ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ሞት የለምና ወደ ገዳም ለመመለስ በአጽንዖ በአት የሚገኘውን ክብር ቢመለከቱ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ክብር ልዕልና ይሆናሉ፡፡
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!