‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ››
ክፍል ዐሥር
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሐምሌ ፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ነገን ዛሬ እንሥራ በሚል ርእስ ጀምረን በርካታ ጉዳዮችን የዳሰስንበትን ጽሑፍ በክፍል ከፋፍለን ስናስነብባችሁ ቆይተናል፡፡ ነገን ዛሬ ለመሥራት፣ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን የተሻለች ለማድረግ፣ ወደ ቀደመ ክብሯ፣ መታፈሯና መከበሯ ለመመለስ ይቻል ዘንድ ክብረ ምንኩስናን ማጠናከር፣ ገዳማዊ ሥርዓትን መጠበቅ፣ አሁን የሚታዩ ተግዳሮቶችን ማስወገድ የዚህ ትውልድ ግዴታ መሆኑን አንሥተን ክብረ ምንኩስና ነገ የተሻለ እንዲሆን ከቤተ ክርስቲያን የሚጠበቁ እና ከመነኮሳት የሚጠበቁ ጉዳዮችን በክፍል ዘጠኝ አስነብበናችኋል፡፡ ክፍል ዐሥርን (የመጨረሻውን ክፍል) ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!
ከመነኮሳት የሚጠበቅ…. (ከባለፈው የቀጠል) ፡-
ሀ. በተጋድሎ ቢጸኑ፡– መነኮሳት በተጋድሎ መጽናት አለባቸው፡፡ በትንሹም በትልቁም ፈተና መውደቅ፣ በፍቅረ ንዋይ መሸነፍ፣ ለሥጋዊ ምቾትና ክብር መታለል የለባቸውም፡፡ ‹‹እንደሚቃጠል መሥዋዕት ተፈትነው የሚገባቸውንም ዋጋቸውን ሰጣቸው›› ተብሎ ስለ ጻድቃን ተነግሯልና ተፈትነው ዋጋቸውን ሊያገኙ የዲያብሎስን ውጊያ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና በትሩፋት አገልግሎት ድል እንደሚነሡት አምነው ሥጋቸውን እስከ ክፉ መሻቱ ሰቅለውት መንነዋልና ሊበረቱ ይገባቸዋል፤ ምክንያቱ እነርሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ናቸውና፡፡ (፩ኛጴጥ.፩፥፯-፱፣ገላ. ፭፥፳፩)
በመጽሐፈ አክሲማሮስም ላይ ‹‹ከአዳም ልጆች ሰይጣንን ተዋግቶ ድል ሳይነሣ ወደ ገነት የሚገባ የለም›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ እንኳንስ መነኮሳት ቀርቶ ብር ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ጽሩይነቱ ሲታወቅ፣ ለንጉሥ እንደሚቀርብ ሁሉ የአዳም ልጆች ሁላችን ስመ ሥላሴን ጠርተን፣ በሕግና በቀኖና ኖረን፣ ኪዳነ ቅዱሳንን፣ ተስፋ ቅዱሳንን አስበን፣ ከጸብዓ አጋንንት ተዋግተን ድል እንድንነሣና መንግሥተ እግዚአብሔርን እንድንወርስ እንደሚገባን ያስረዳናል፡፡ (ገጽ.፻፺፩፤ጥበብ ፫፥፭-፯)
ስለዚህ አባቶቻችን መነኮሳት ከሚያማልለውና ብዙዎቹን ስቦ ካስቀረው፣ ይሁዳን ከሐዋርያት ከነጠለው ፍቅረ ንዋይ፣ ዴማስን ከመምህሩ ቅዱስ ጳውሎስ ከለየው የተሰሎንቄ ድምቀት፣ ብዙዎቹን ለመከራ ከዳረገው ፍቅረ ሹመት፣ ራሳቸውን ቢቆጥቡ፣ ለጾም ለጸሎት፣ ለስግደት፣ ለተግባረ ዕድ፣ ለንባብና ለአጽንዖ በአት ትኩረት ቢሰጡ ክብረ ምንኩስና ይመለሳል፤ገ ዳማዊ ሕይወት ነፍስ ይዘራል፤ ምድራችንም ትባረካለች፡፡
ለ. ከዘረኝነት ቢቆጠቡ፡– ዘረኝነት ትልቁ የዘመናችን ካንሰር ነው፡፡ ብዙዎቹን ገዝግዞ ገዝግዞ ነቀዝ እንደበላው እህል ወይም ምስጥ እንደ በላው እንጨት ቀፎ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ ደዌ ምክንያት ሀገራችንም ቤተ እምነቶቻችንም በጽኑ ከታመሙ ዋል አደር ብለዋል፡፡ ከሁሉ የሚከፋው ግን ጠጋኞቹ መሰበራቸው፣ ሐኪሞቹ መታመማቸው ነው፡፡ ይህ ክፉ ደዌ በፖለቲከኞች፣ በተራው ሰው ብቻ መወሰን አልቻለም፡፡
ይልቁንም የተሰበረውን የሚጠግኑት፣ የተቆረጠውን የሚቀጥሉት፣ የታመመውን በትምህርታቸው በጸሎታቸው፣ በምክራቸውና በተግሣፃቸው የሚያክሙት፣ የሚፈውሱት፣ በወገን፣ በነገድ፣ በቋንቋ፣ በጎሳ የማይወሰኑት፣ ለሕዝብም ለአሕዛብም አባት የተባሉት መነኮሳት ብሎም ጳጳሳት ጭምር በዘረኝነት ደዌ ተለክፈው ይታያል፡፡ ምንኩስናን የምናድነው፣ ክብርና ሞገስ እንዲኖረው የምናደርገው፣ የሁሉም ወገን የሁሉም አባት የሆኑ፣ የእገሌ የእነ እገሌ አባት የማይባሉ መነኮሳትን በመፍጠር ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ማድረግ የሚቻለው መነኮሳት ከወቅቱ በሽታ ራሳቸውን ሲጠብቁ ነውና አባቶቻችን ይህን ቢያደርጉ መልካም ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ገድል ውስጥ አንድ ታሪክ አለ፡፡ አቡነ ክፍለ ማርያም ዘዲባጋ የሚባሉ ትውልዳቸው እንደርታ የሆኑ በ፲፬ ዓመታቸው የመነኮሱ ቅዱስ መናኝ ነበሩ፡፡ በቅድስና የሚኖሩ የበቁ አባት ሲሆኑ በአንድ ወቅት ወደ አክሱም ወላጆቻቸው ካሉበት ቦታ ደረሱ፡፡ ከቅዳሴ በኋላ ጸሪቀ መበለት ቆርሰው ሲያድሉ ወላጅ እናታቸው ከስተውና ጠቁረው ስላዩአቸው ለእናታቸው አድልተው በብዙ ሰጧቸው፡፡
እናትየው ግን ልጃቸው ስለመሆናቸውም የተደረገላቸውንም አልተረዱም ነበር፡፡ ጻድቁ ከብቃታቸው የተነሣ መና ከሰማይ የሚወርድላቸው፣ ውኃ ከዓለት የሚፈልቅላቸው የነበረ ሲሆን ለእናታቸው አድልዎ ስላደረጉ ጸጋቸው ተነሣባቸው፡፡ አባታችንም ይህን ባወቁ ጊዜ ‹‹ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ›› እያሉ ከሰው ሳይገናኙ ዋሻ ገብተው በአት አጽንተው ፲፩ ዓመት ሙሉ በልቅሶና በዋይታ እግዚአብሔርን ለምነው ይቅር ተብለው የቀደመ ጸጋቸውና ክብራቸው ተመልሶላቸዋል፡፡
ለወለደች እናት፣ በዚያውም ከስታና ጠውልጋ፣ ጠቁራና ተጎሳቁላ በማየታቸው ትንሽ ቁራሽ ጸሪቀ መበለት መስጠት ይህንን ያህል ዋጋ የሚያሳጣና ጸጋን የሚያስነሣ ከሆነ ዛሬ “ለብሔሬ፣ ለቋንቋዬ፣ ለወንዜ፣ ለሰፈሬ” እያሉ በየመድረኩ በየሚድያው የቤተ ክርስቲያንን መከራ የሚያራዝሙ፣ የምእመናንን መከራ ያጸኑ፣ ገዳማዊ ሕይወትን የዘነጉ ብዙዎች መነኮሳት ከዚህ ክፉ ወጥመድ ማምለጥ እንደ ጻድቁ አባ ክፍለ ማርያም ‹‹ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ›› ብለው በጸጸት፣ በንስሐ የሚመለሱበትና ከዘረኝነት የሚላቀቁበት የሚገባ ሰዓት ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ጻድቁ ከደረቅ ጭንጫ ላይ ውኃ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ነበር፡፡ ኅብስትም ከሰማይ እያወረዱ ይመግቡ ነበር፤ በኋላም እንደ ሄኖክና ኤልያስ ወደ ብሔረ ሕያዋን ዐርገዋል፡፡ ከመነኮሱ በኋላ እናቴ አባቴ ወገኔ ዘመዴ ማለት፣ በጎጥ በዘር፣ በቋንቋ መቧደን ምን ያህል በደል እንደሆነ ከጻድቁ ታሪክ እንረዳለን፡፡
ቤተ ክርስቲያንን ሸክሟን ያከበደው በዘር በቋንቋ የተቧደኑ የሃይማኖት አባቶች መብዛታቸው መሆኑን የምንክደው አይደለም፡፡አቡነ ዳንኤል ዘቦረና የተባሉ ሌላ ኢትዮጵያዊ ጻድቅም ዘረኝነትን ይጸየፉና ይዋጉት ነበር፡ ስለ ዘራቸው ስለ እናትና አባታቸው አጥብቀው ሲጠይቋቸው ‹‹እናቴ አክሱም አለች፤ አባቴ ልጇ ነው›› ይሉ ነበር፡፡ እናታችን የተባለች ጽዮን ማርያም ስትሆን አምላክን የወለደች በመሆኗ አምላካችን ልጇ እንደሆነ መነኩሴው መስክረዋል፡፡(መዝገበ ቅዱሳን ገጽ ፺፫-፺፬)
ስለዚህ መነኮሳት አባቶቻችን እናቶቻችን አጥብቀው ሊጠነቀቁበት የሚገባ የገቡትም ቶሎ ሊወጡበት የሚገባው ትልቅ ደዌ፣ ዘረኝነት ነው፡፡ የበቁት የተሰናከሉበት፣ ጸጋቸውን ያጡበት ትልቅ በደል መሆኑን ቢረዱትና ቢመለሱ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹ሰው ጸጋውን የሚያውቀው ሲያጣው ነው›› እንዲሉ አበው ጸጋቸውን ካጡት በኋላ ወዮልኝ ከማለት ያድናልና፡፡
፫ኛ. ከምእመናን የሚጠበቅ፡–
መነኮሳት በሥጋዊ ፈተና እንዲወድቁ ክብረ ምንኩስና እንዲቃለል፣ መነኮሳትን በማክበር ሰበብ ኃጢአት የሚያለማምዱ ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ከመነኮሳት ጋር ያላቸውን ግንኙነት መቀነስ፣ ገንዘብ ለጠየቃቸው፣ መነኩሴ ነኝ ላላቸው ሁሉ ልባቸውንም እጃቸውንም ከመዘርጋት ቢቆጠቡ፣ በቡድንም በተናጠልም በገዳማት በግብረ ምንኩስና ለጸኑና በአገልግሎት በጸሎት ለሚተጉት መነኮሳት ድጋፍ ቢያደርጉ፣ በስሕተት የወደቁ የአባቶቻቸውን ገመና ከመንዛት ይልቅ በተቻለን ዓቅም ድጋፍ ማድረግ፣ የግንኙነት ቦታንና ሁኔታን በመወሰን፣ ለክብረ ምንኩስና የራሳቸውን ድርሻ ቢወጡ መልካም ነው፡፡
ውድ ተከታታዮቻችን! ‹‹ነገን ዛሬ አንሥራ›› በሚል ርእስ የሚነሡ ጉዳዮችን ነገን ዛሬ ለመሥራት ዋና መሠረቶች ናቸው፡፡ ቅድሚያ ሰጥተን ብንሠራ ነገን የተሻለ ለማድረግ ይረዳሉ በሚል ስለክብረ ክህነትና ክብረ ምንኩስና በተከታታይ ዐሥር ክፍላት ያቀረብንላችሁን ጽሑፍ በዚህ ፈጸምን፡፡ ነገን ዛሬ ለመሥራት እነዚህን ቀዳሚ አድርገን እንድንሠራ ለማስገንዘብ ያህል አቅርበናላችኋል፡፡
ነገር ግን የነገዋን ቤተ ክርስቲያን የተሻለችና ለትውልዱ እስከ ሙሉ ክብሯ እንድትተላለፍ ክህነትንና ምንኩስናን ቅድሚያ ሰጥተን መሥራት እንዳለብን ብናመለክትም ብቸኛ መፍትሔ ናቸው ማለታችን ግን አይደለም፡፡ ነገን ዛሬ ለመሥራት ሌሎችን ትኩረት ሰጥተን ልንሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በተመለከተ ደግሞ በሌላ ጊዜ ይዘንላችሁ እንቀርባለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!