ነገረ ጳጕሜን

መምህር ተስፋ ማርያም ክንዴ
ነሐሴ ፴፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ጳጕሜን የሚለው ቃል “ኢፓጎሜን ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም “የተረፉ፣ ትርፍ ቀናት” ማለት ነው። ከምን የተረፉ ካልን ዓመቱ በሠላሳ በሠላሳ ቀናት ተለክቶ የሚተርፉ ዕለታት ማለት ናቸው። ዓመቱን በ፴ በ፴ ወስኖ መቁጠርን ኢትዮጵያ ከየት አገኘችው? ካልን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ እንደሆነ መጽሐፍ ተባብረው ይመሰክራሉ። (ዘፍ. ፯፥፳፬፣ ኩፋሌ ፮፥፴፪፣ ራእይ ፲፩፥፪፣ አቡሻክር አንቀጽ ፰)።

በዚህም የመጽሐፍ ቃል መሠረት የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዓመት ከዐሥራ ሁለቱ ወር የተረፉትን ዕለታት ከወር ባነሱ ዑደታት ሳይክሎች በዕለት፣ በኬክሮስ፣ በካልዒት፣ በሳልሲት፣ በራብኢት፣ በሐምሲትና በሳድሲት ሰፍረውና ቀምረው በዓመት አምስት ቀን ከ፲፭ ኬክሮስ ከ ስድስት ካልዒት አድርገው እነዚህን ዕለቶች ጳጕሜን ብለው ዐሥረኛ ወር አድርገዋቸዋል።

ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያን ብቸኛ የባለ ፲፫ (13) ወራት መባላቸው ግን ዕለቷ በሌሎች አልኖር ብላ ሳይሆን ሌሎች እንዲሁ በዘፈቀደ ከሌላው ወር ጋር ደርበው ሲያከብሯት ኢትዮጵያና ግብፅ ግን ከላይ ከኬክሮስ እስከ ሳድስት ባሉት ጥቃቅን የጊዜ መስፈሪያዎች ሰፍረውና ቀምረው ስለሚያውላት ነው፡፡ የዓለም ሀገራትም አንዳንዶቹ ከወራቸው ደርበው የወሩን ቁጥር አንዳንድ ፴(30) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፴፩(31) እያደረጉ አሽባጥን (የካቲትን)፣ ለይተው በ፫(3)ቱ ዓመት ፳፰(28) በ፬(4)ኛው ፳፱(29) እያደረጉ ጳጉሜን ደርበው ያውሏታል። እንደዚህ ከሚያከብሩ ሀገሮች መካከል ሮማውያን (አፍርንጅ)ና ሶርያ ይጠቀሳሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በ፰(8)ኛው ወር መጨረሻ ስሟን ለዋህቅ ብለው ስለሚያከብሯት ነው። አንድም ጳጕሜን ማለት ከሕፀፅ ጋር ሲሰላ በዓመት የሚገኝ የፀሐይና የጨረቃ ዑደት ትርፍ ማለት ነው።

ኢትዮጵያ በራሷ ሊቃውንት እየቀመረች ለዘመናት ይዘው የመጣችው የራሷ የዘመን ቆጠራ ያላት በመሆኑ በራሷ የዘመን ቆጠራ ሃይማኖታዊ ሥርዓቷን፣ ባህሏንና ማንነቷን ስታከናውን ኑራለች፤ ወደ ፊትም ትኖራለች። ይህን የማያውቁና የማይረዱ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ግን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያ ጳጕሜንን እንደሌሎች ሀገሮች ከወሯ ደርባ ማክበር አለባት ወይም መተው አለባት ሲሉ ይደመጣሉ።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ እነርሱ እንዳሉት ጳጕሜንን ከሌሎች ወራት ደርባ ብታከብር ምን ነገር ይፋለሳል?ብለው ለሚጠይቁ ሰዎች የሚከተሉትን ጥቂት ማሳዎች እናቀርባለን።

አንደኛ ቤተ ክርስቲያናችን በጳጕሜን ወር በርካታ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን የምታከናውን ሲሆን ከእነዚህም አንዱ ዕለተ ምጽአትን ታከብራለች። መምህራን ጳጕሜን ከክረምት ወደ በጋው የምንሸጋገርባት ናት፤ ክረምት ደግሞ ከላይ ዝናብ፣ ከታች ጎርፍ፣ ነጎድጓድና መብረቅ ወዘተ የሚበዛበት ነው፡፡ የዚህ ዓለም ምሳሌ በጋው ደግሞ ክረምቱ የሚያልፍበት ብርሃን የሚወጣበትና አዝመራው የሚያፈራበት ነው ብለው ከምጽአት በኋላ በምንወርሰው መንግሥተ ሰማያት ይመስሉና በዚህ ወር ዕለተ ምጽአትን እንድናስብ አድርገውናል።እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ዕለተ ምጽአትን በዚች ወር ብቻ ሳይሆን ዘወትር እርሱን እያሰብን ክፉ ከመሥራት እንድንጠበቅ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ (ማቴ. ፳፬ እና ፳፭) ስለዚህ ጳጉሜን ወር አታክብሩ ማለት ሃይማኖታችሁን፣ ባህላችሁንና ታሪካችሁን ተው እንደማለት ይቆጠራል፤ ሰው ደግሞ ይህን ማንነት ትቶ እንደ እንስሳት ሊኖር አግባብ አይደለም።

ሁለተኛ በዚህ ወር ከመልአኩ ሩፋኤል በዓል በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ርኅዎ ሰማይን (የሰማይ መከፈት) እናከብራለን። ርኅዎ ሰማይ ጳጕሜን ሦስት ይከበርና ከዚያ ማግስት ያለውን ቀን አንድ ብሎ ቆጥሮ በየ ፶፪ ቀኑ በዓመት ሰባት ጊዜ ይከበራል። ርኅዎ ሰማይ ማለት የሰማይ መከፈት ማለት ነው። በሰማይ መከፈትና መዘጋት ኑሮበት ሳይሆን ጸሎት የሚያርግበት፣ ያልታየ ምሥጢር የሚታይበት እንደሁነ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን። ከዚህ በተጨማሪ በጳጕሜን ወር ብዙ ምእመናን በመጾምና ጸበል በመጠመቅ በነጻ መንፈሳዊ ትሩፋቶችን በማከናወን አዲሱን ዓመት ለመቀበል የሚዘጋጁባት ዕለት ናት።

ሦስተኛ የጨረቃ ወርኃዊ ልደትና የወቅቶች መፋለስ፡-ጨረቃ የራሷ የቀን የ፲፭ ቀን የወርና የዓመት ዑደት አላት። ለማሳያ ያህል የያዝነው ዓመት የ፳፻፲፯ ዓ.ም የዓመት ዑደቷን የምትጨርሰው በፀሐይ ነሐሴ ፲፰ ቀን ነው። ይህ ማለት የመስከረም ጨረቃ ነሐሴ ፲፱ ቀን ትወለዳለች፡፡ ከነሐሴ ፲፪ ከጳጕሜን አምስት ስናመጣ ፲፯ ይሆናል፡፡ የመስከረም ወር ጨረቃ የምትቆየው ፳፱ ዕለት ስለሆነ ይህን ለመሙላት ከመስከረም ፲፪ እናመጣና በሚቀጥለው ቀን የጥቅምት ጨረቃ ትወለዳለች፡፡ ስለዚህ ጳጕሜን የለችም ማለት ግን የመስከረም ወር ጨረቃ መስከረም ፲፪ ቀን መጨረሷን ትታ ወደ ፲፯ ትሄዳለች ማለት ነው። ይህ ደግሞ መምህራን ከሠሩት የጨረቃ፣ የወር መንገድና የዓመት መንገድ ጋር የተፋለሰ ይሆናል።

አራቱን ወቅቶችንም ብናይ እንደዚሁ መፋለስ ይፈጥራል፡፡ አንድ ቀን ስንል የራሱን ኬንትሮስ ከኬንትሮሱ ጋር የራሱን ፊደል ከፊደሉ ጋር የራሱን የፀሐይ ኆኅት እንዲሁም በመራሂ ወተመራሂ ሕግ የራሱን የቀን የወር የ፲፪ ወርና የዓመት ከዋክብትን ይዞ የሚጓዝ ነው እንጂ እንደፈለገ አንዱን ዕለት ከአንዱ የምንጨምረው አይደለም፡፡ በጥቅሉ በቁጥር መምህራን ዘንድ አንዱን ዕለት እንደፈለግን ከአንደኛው ዕለት ጋር ደርበን እናውል ማለት አንዱን እጅ ከአንዱ እጅ፣ አንዱን እግር ከአንዱ እግር ጋር እንጨምር እንደማለት እንደሚቆጠር ልብ ማለት ይገባል።

ሲጠቃለል ኢትዮጵያ የራሷ ባህል፣ ታሪክና ሃይማኖት ያላት ይህንም በትውፊትና በመጽሐፍ ቅዱስ ይዛ የቆየች ሀገር ናት፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ውሸት ቢናገርና በውሸታሞች መካከል ቢደገፍ ሌሎችም ውሸት ይናገሩ እንደማይባል ኢትዮጵያም ሌሎች በንጉሣቸው በጣዖታቸው ስም በየጊዜው እየቀያየሩ የዘመን ቆጠራን ቢያከብሩ የራሷን እውነት ትታ የእነርሱን ውሸት ትቀበል እንደማይባል መረዳት ይጠይቃል።

ስብሐት ለእግዚአብሔር!