ነገረ ድኅነት በትንቢተ ነቢያት (የመጀመሪያ ክፍል)
ታኅሣሥ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ
ቅዱሳን ነቢያት ሀብተ ትንቢትን ከእግዚአብሔር የተቀበሉ፣ ፈጣሪያቸውን የተከተሉ፣ በመንፈሰ ረድኤት የተቃኙ እንደ መኾናቸው እግዚአብሔር በሰጣቸው ሀብተ ትንቢት ተመርተው ስለ እግዚአብሔር አዳኝነት መስክረዋል፤ ስለ ሰው ልጅ ድኅነትም አስቀድመው ትንቢት በመናገር የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን የማዳን ቀን በተስፋ እንዲጠባበቅ አስተምረዋል፡፡ በትምህርታቸውም እንደ ብረት የጠነከረውን፣ እንደ ዐለት የጠጠረውን፣ በአምልኮ ጣዖትና በገቢረ ኃጢአት የሻከረውን የሰው ልጆችን ልቡና ወደ እግዚአብሔር አቅርበዋል፡፡ ነቢያት መንፈሳዊነትን የተላበሱ፤ በትንቢታቸውና በትምህርታቸው የአሕዛብን ልቡና ያስደነገጡ፤ ዓላውያን ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው፡፡
በዘመናቸውም አምላክ ከሰማይ ወርዶ (ሰው ኾኖ) ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጥፋት ወደ ድኅነት እንዲመልሳቸው እግዚአብሔርን ለምነዋል፤ ሱባዔ እየቈጠሩ፣ ትንቢት እየተናገሩም የተስፋውን ዕለት ሲጠባበቁ ኑረዋል፡፡ ለዚህም ነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፡፡ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም፤›› (ማቴ. ፲፫፥፲፯) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው፡፡ የነቢያቱ የትንቢታቸው ፍጻሜ፣ የልመናቸው መደምደሚያም ነገረ ድኅነት ነው፡፡ በመኾኑም ሰውን ለማዳን ወደ ዓለም የሚመጣውን እግዚአብሔርን በትንቢታቸው በሚከተሉት ምሳሌያት ገልጸውታል፤
፩. እጅ (ክንድ)
እጅ ቢወድቁ ተመርጕዘው ይነሡበታል፡፡ እጅ የወደቀውን ንብረት ከአካል ሳይለይ ለማንሣት፣ የራቀውን ለማቅረብ፣ የቀረበውን ለማራቅ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ወልድም ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ከእግዚአብሔር ርቆ የነበረውን አዳምን ወደ እርሱ አቅርቦታል፤ ከወደቀበት አንሥቶታል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱሳን ነቢያት እግዚአብሔር ወልድን ‹‹እጅ (ክንድ)›› እያሉ የሚጠሩት፡፡ ‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ ነኪር እለ ከንቶ ነበበ አፉሆሙ ወየማኖሙኒ የማነ ዐመፃ፤ እጅህን ከአርያም ላክ፤ አድነኝም፡፡ ከብዙ ውኆች፣ በአፋቸውም ምናምንን ከሚናገሩ፣ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከኾነ ከባዕድ ልጆች አስጥለኝ፤›› እንዲል (መዝ. ፻፵፫፥፯-፰)፡፡ ከዚህ ላይ ነቢዩ ዳዊት ‹‹እጅ›› በማለት የጠራው ከሦስቱ አካላት አንዱን እግዚአብሔር ወልድን ነው፡፡ ‹‹አፋቸው ምናምን የሚናገር፣ ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ የኾነው ውኆች›› የሚላቸው ደግሞ ዲያብሎስንና ሠራዊቱ አጋንንትን ነው፡፡ ደቂቀ ነኪር (የባዕድ ልጆች) ማለቱም አጋንንት ከክብራቸው ስለ ተዋረዱ በባሕርያቸው ለሰው ልጆችም ለብርሃናውያን መላእክትም ባዕዳን ናቸውና፡፡
እስራኤል ዘሥጋ በጸናች እጅ፣ በተዘረጋች ክንድ ከግብጽ ባርነት፣ ከፈርዖንና ከሠራዊቱ ግዞት ነጻ መውጣታቸው ነገረ ድኅነትን የሚመለከት ምሥጢር ይዟል፡፡ ‹‹በጸናች እጅ፣ በተዘረጋች ክንድ ይለቃችኋል፤ ከአገሩም አስወጥቶ ይሰዳችኋል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዘፀ. ፮፥፩)፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹የጸና እጅ፣ የበረታ ክንድ›› የተባለው ዓለምን በሙሉ ከኃጢአት ባርነት፣ ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነጻ ያወጣው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ክንዱን በመስቀል ዘርግቶ በትረ መስቀሉን አንሥቶ በልዩ ሥልጣኑ ዲያብሎስን የቀጣው፣ ሞትን የሻረው፣ ሲኦልን የበረበረው ኃይለኛውን አስሮ ያለውን ዅሉ የነጠቀው እርሱ ነውና፡፡ ‹‹እሙታን ተንሢኦ ሲኦለ ከይዶ በሞቱ ለሞት ደምሰሶ፤ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሥቶ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ሞትን በሞቱ አጠፋው (ደመሰሰው)›› እንዲል መጽሐፈ ኪዳን፡፡
መድኀኒታችን ክርስቶስ ‹‹አልቦ ዘይክል በዊአ ቤተ ኀያል ወበርብሮተ ንዋዩ ለእመ ኢቀደመ አሲሮቶ ለኀያል፤ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኀይለኛው ቤት ገብቶ ገንዘቡን መዝረፍ የሚቻለው የለም›› (ማቴ. ፲፪፥፳፱) በማለት እንደ ተናገረው እርሱም ዲያብሎስን አስሮ በሲኦል ተግዘው ይኖሩ የነበሩ ነፍሳትን ዅሉ ነጻ አውጥቷቸዋል፡፡ አምላካችን ‹‹የጸና እጅ›› የተባለ አምላክነት፣ አለቅነት፣ ጌትነት በአጠቃላይ መለኮታዊ ሥልጣን ገንዘቡ ነውና፡፡ ይህ የጸና እጅ ሰማያትን የዘረጋ፣ ምድርን የመሠረተ፣ ሰውን ለማዳን በመስቀል ላይ የተዘረጋ ኃያል ክንድ ነው፡፡ ዓለም የሚድንበት በእጅ የተመሰለው አካላዊ ቃል ወልደ እግዚአብሔር ሕያው መኾኑን ‹‹የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም፤›› (ኢሳ. ፶፱፥፩) በማለት ልዑለ ቃል ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ተናግሯል፡፡ ስለዚህም ነቢያቱ ‹‹እጅህን ላክልን›› እያሉ እግዚአብሔርን ሲማጸኑት ቆይተዋል፡፡ ይህን ብርቱ ክንድ ዓለም እንዳልተረዳውም በትንቢታቸው አስገንዝበዋል፡፡ ነገረ ድኅነት ከብዙዎች አእምሮ የተደበቀ ምሥጢር ነበርና፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ በነቢያት የተነገረውን የነገረ ድኅነት ትንቢት የሰው ልጅ አምኖ እንዳልተቀበለው ሲያስረዳ ‹‹ጌታ ሆይ፣ ነገራችንን ማን ያምነናል? የእግዚብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጧል?›› (ኢሳ. ፶፫፥፩) በማለት ተናግሯል፡፡ ጌታችን በሕዝቡ ፊት አምላክነቱን የሚገልጹ ተአምራቱን ቢያደርግም አስራኤል ግን አምላክነቱን አምነው አለመቀበላቸው ለዚህ ማስረጃ ነው (ዮሐ. ፲፪፥፴፮-፵)፡፡ ቅዱስ ዳዊትና ኢሳይያስ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ ዓለም የሚመጣውን አምላክ ነገረ ድኅነትን በሚመለከት ምሥጢራዊ ቃል ‹‹እጅ ክንድ›› እያሉ ጠርተውታል፡፡
፪. የመዳን ቀንድ
ቀንድ የሥልጣን፣ የኀይል መገለጫ ነው፡፡ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና ‹‹ወተለዓለ ቀርንየ በአምላኪየ ወመድኃኒየ፤ ቀንዴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ከፍ ከፍ አለ›› (፩ኛ ሳሙ. ፪፥፩) ማለቷ ለጊዜው ስላገኘችው ክብርና የልጇን የሳሙኤልን ሥልጣን (ነቢይነትና ምስፍና) ስትናገር፤ ፍጻሜው ግን ቀንድ የተባለ ዓለም የዳነበት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ስታመለክት ነው፡፡ ቅዱሳን ነቢያትም እግዚአብሔር ወልድን ‹‹የመዳን ቀንድ›› ብለውታል፡፡ በመዝሙረ ዳዊትም ከዳዊት ወገን ተወልዶ ዓለምን የሚያድነው ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቀንድ›› በሚል ቃል ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ወበህየ አበቊል ቀርነ ለዳዊት ወአስተዴሉ ማኅቶተ ለመሲሕየ፤ በዚያም ለዳዊት ቀንድን አበቅላላሁ፡፡ ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ፤›› ተብሎ እንድ ተጻፈ (መዝ. ፻፴፩፥፲፯)፡፡
እንስሳት ጠላታቸውን የሚከላከሉት፣ ኀይላቸውንም የሚገልጡት በቀንድ ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆችም ከጠላታችን ሰይጣን ውጊያ ራሳችንን የምንከላከለውና ድል የምናደርገው በእርሱ ኀይል ነውና ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹የመዳን ቀንድ›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ‹‹ብከ ንዎግዖሙ ለኵሎሙ ፀርነ፤ ጠላቶቻችንን ዅሉ በአንተ እንወጋቸዋለን፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ (መዝ.፵፫፥፭)፡፡ ካህኑ ዘካርያስም በቅዱሳን ነቢያት ‹‹የመዳን ቀንድ›› እየተባለ የተጠራው ክርስቶስ በሥጋ የሚገለጥበት ጊዜ መድረሱን ሲያስረዳ ‹‹አንሥአ ለነ ቀርነ መድኃኒትነ እምቤተ ዳዊት ገብሩ በከመ ነበበ በአፈ ነቢያቲሁ ቅዱሳን እለ እምዓለም፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤›› (ሉቃ.፩፥፷፱) በማለት ተናግሯል፡፡ ‹‹እምቤተ ዳዊት ገብሩ›› ማለቱም ነቢዩ ዳዊት ‹‹ቀንድ›› እያለ ትንቢት የተናገረለት ክርስቶስ የዳዊት ወገን ከኾነችው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሚወለድ ሲያመለክት ነው፡፡
፫. የማን (ቀኝ)
ቀኝ የኃይል፣ የሥልጣን፣ የመልካም ነገር ምሳሌ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን መሪዎች ሰዎችን ለአገልግሎት ሲልኳቸው ቀኝ እጃቸውን ዘርግተው ይጨብጧቸው ነበር፡፡ በሥራቸው ዅሉ ከእነርሱ እንደማይለዩ የሚያረጋግጡላቸውም ቀኝ እጃቸውን በመስጠት ነበር፡፡ በዚህ ትውፊት መሠረትም ቅዱሳን ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ቅዱስ ጳውሎስን በቀኝ እጃቸው ጨብጠውታል፡፡ ይህንንም ‹‹የተሰጠኝን ጸጋ ዐውቀው አዕማድ የሚሏቸው ያዕቆብና ኬፋ፣ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ፣ እነርሱ ወደ ተገረዙት ይሔዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ ገልጦታል (ገላ.፪፥፱)፡፡
ቅዱሳን ነቢያት ዲያብሎስን ከነሠራዊቱ ድል ነስቶ ዓለምን የሚያድነውን፤ ኀያል፣ ጽኑዕ የኾነውን አምላካችንን ክርስቶስን ‹‹ቀኝ›› ብለውታል፡፡ ‹‹የማነ እግዚአብሔር ገብረት ኃይለ የማነ እግዚአብሔር አልዓለተኒ፤ የማነ እግዚአብሔር ገብረት ኃይለ፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፡፡ የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፡፡ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፤›› እንዲል (መዝ.፻፲፯፥፲፮)፡፡ ይህም ‹‹የእግዚአብሔር ቀኝ›› የተባለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድንቅ ጥበቡ፣ በልዩ ሥልጣኑ አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን በሲኦል ተጥለው የነበሩ ነፍሳትን ከፍ ከፍ እንዳደረጋቸው (ወደ ገነት እንደመለሳቸው) የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ ቅዱስ ዳዊት የተስፋውን ቃልና የመዳኛውን ቀን መድረስ እየተጠባበቀ ‹‹ወይድኃኑ ፍቁረኒከ አድኅን በየማንከ ወስምዓኒ፤ ወዳጆችህ እንዲድኑ፣ በቀኝህ አድን፤ አድምጠኝም፤›› በማለት ይጸልይ ነበር (መዝ.፶፱፥፭)፡፡
ይቆየን