ነገረ ትንሣኤ – የመጀመሪያ ክፍል

በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ

ሚያዝያ ፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ጌታችን የሞተው በሥጋው ወይስ በመለኮቱ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጌታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት ‹‹እንደ ቃልህ ይንልኝ›› ባለችው ጊዜ መለኮትና ትስብእት ሁለትነትን አጥፍተው በአካልና በባሕርይ ተዋሐዱ፡፡ መለኮት ባሕርያዊ ታላቅነቱን ሳይለቅ በየጥቂቱ ማደግን ከሥጋ ገንዘብ አደረገ፤ ሥጋም ባሕርያዊ ታናሽነቱን ሳይለቅ ከሦስቱ አካላት እንደ አንዱ ኾነ (ዘፍ. ፫፥፳፪)፡፡ ይህ ተዋሕዶ አንዱን ለአንዱ ያስገዛ ተዋሕዶ ነው፤ መራብ፣ መጠማት፣ ሞት፣ ድህነትና እነዚህን የመሳሰሉት ዂሉ ያለ ተዋሕዶ ለመለኮት ሊስማሙ አይችሉም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ባለጠግነት፣ ሕይወት፣ ዘለዓለማዊት መንግሥት፣ የማነ አብ፣ ዘባነ ኪሩብና እነዚህን የመሳሰሉት ዂሉ ለሥጋ ይነገሩ ዘንድ የሚገባቸው አልነበሩም፤ ተዋሕዶ ምክንያት ኾኖ የመለኮትን ለሥጋ የሥጋን ለመለኮት ሰጥተን እንድንናገር አድርጎናል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም በድርሳኑ ‹‹እንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል፤ ወእንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ፤ የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃልም ገንዘብ ለሥጋ ›› ብሎ መናገሩም ይህንን የተዋሕዶ ፍጹምነት ለመግለጥ ነው፡፡

ሊቁ ይህን ምሥጢር ለማስረዳት የተጠቀመበት ምሳሌ የብረትና የእሳት ተዋሕዶ ነው፤ ብረት ሠሪ ብረቱን ከእሳት ሲጨምረው ብረቱ የእሳትን ባሕርይ ገንዘብ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩና ውዕየቱ የእሳት፤ ቅርፅና መጠኑ ደግሞ የብረት ይኾናል፡፡ ብረት ሠሪው በመዶሻ ብረቱን ሲቀጠቅጠው ሊያዝ የማይችለው እሳት ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሲቀጠቀጥ እናያለን፡፡ ከብረቱ ጋር እሳት ባይዋሐድ ኖሮ ብረቱን ማስተካከል አይቻልም ነበር፡፡ መለኮት ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜም ሊይዙት ሊጨብጡት የማይቻል እሳተ መለኮት ተይዞ ተደበደበ፡፡ መለኮት በሥጋ መከራ ባይቀበል ኖሮ የሰው ባሕርይ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ እንደ ምን ይችል ነበር? ኀጢአት ያቀዘቀዘውን ባሕርያችንን ያስተካከለው መለኮት በሥጋ የተቀበለው መከራ ነው፡፡ እንደዚያማ ባይኾን ኖሮ ከአቤል ጀምሮ በግፍ የተገደሉ ብዙ ቅዱሳን መከራቸው ለምን አላስታረቀንም? የዕሩቅ ብእሲ ደም ሰውን ከኀጢአት ሊያነጻው ባለ መቻሉ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን በገለጸበት ቅዳሴው ‹‹ኦ አእዳው እለ ለኃኳሁ ለአዳም ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ኦ አእጋር እለ አንሶሰዋ ውስተ ገነት ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ኦ አፍ ዘነፍሐ ውስተ ገጹ ለአዳም መንፈሰ ሕይወት ሰረበ ብሒአ፤ አዳምን የሠሩ እጆች በቀኖት ተቸነከሩበገነት የተመላለሱ እግሮች በቀኖት ተቸነከሩ፤ በአዳም ላይ የሕይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ መራራ ሐሞትን ጠጣ›› በማለት ያደንቃል፡፡ አዳምን የሠሩ የመለኮት እጆች ወይስ የትስብእት? በገነት ሲመላለሱ አዳም የሰማቸው እግሮች የመለኮት ወይስ የትስብእት? በአዳምስ ላይ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎ ልጅነትን ያሳደረበት ማን ነው? ሥጋ ነው እንዳንል ሊቁ እየተናገረ ያለው ቅድመ ተዋሕዶ ስለ ተፈጸመ ታሪክ ነው፤ መለኮት ነው እንዳይባል የመለኮት እጅና እግር በችንካር የሚመታ፣ አፉም እንኳን መራራውን ጣፋጩን ሊጠጣ የማይችል ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ የሊቁ ቃል ይመልሰንና መለኮት በሥጋ መከራን እንደ ተቀበለ ያስረዳናል፡፡ እንደ ሰውነቱ ‹‹ተቸነከረ መራራ ጠጣ›› እንላለን፡፡ እንደ አምላክነቱ ደግሞ የአዳም ፈጣሪ እንደ ኾነ እንናገራለን፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የተናገረው ቃል ቀዳማዊው ደኃራዊ፣ ደኃራዊው ቀዳማዊ መኾኑን የምንረዳበት አንቀጽ ነው፡፡ በጥንተ ፍጥረት ያልነበረ ሥጋ ፈጣሪነትን በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጓል፡፡ ዓለምን የሠሩ መለኮታዊ እጆችም በሥጋ መከራን ተቀብለዋል፡፡ ስለዚህ የቀራንዮው መስቀል መለኮት ከትስብእት፣ ተስብእት ከመለኮት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመኾኑ የተቀበለው እንጂ ለሥጋ ብቻ የሚሰጥ አይደለም፡፡ መከራ የተቀበለው መለኮት ለብቻው ቢኾን ኖሮ አይሁድ እንዴት አድርገው መስቀል ያሸክሙታል? በገጸ መለኮቱ ፊት ቆመው እንደ ምን ይሳለቁበታል? በብርሃን የተከበበ ፊቱን መላእክት፣ ሐዋርያት ስንኳን ሊያዩት አይቻላቸውምና (ማቴ. ፲፯፥፩-፱)፡፡ ለመለኮትስ መሥዋዕት በሚኾን ገንዘብ ሥጋና ደም አለውን? መለኮት ለብቻው ቢሰቀል ኖሮ ደም እንዴት ይፈሳል? ሥጋስ ከየት መጥቶ ‹‹እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው›› ልንባል እንችላለን? (ዕብ. ፲፥፩-፲፱)፡፡

ሞት በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም እንደ ገባ፣ ሞትን የሚገድል ሞት ደግሞ በሁለተኛው አዳም በክርስቶስ በኩል ኾነ፡፡ መለኮት በሥጋው የሞተው ሞት እንጅ ሞትን የገደለው የዕሩቅ ብእሲ ሞት ብቻ አይደለም፡፡ የዕሩቅ ብእሲ ደም እንዴት ሥርየትን ሊሰጠን ይችላል? የዕሩቅ ብእሲ ሥጋስ እንዴት «ወሀቤ ሕይወት» ሊኾን ይችላል? ሞትን ያመጣ ሥጋ ዛሬ ግን ሕይወትን ለሙታን የሚያድል የሕይወት ምንጭ ኾነ (ዮሐ. ፬፥፲)፡፡ ዂሉን ይዞ የሞተው የአዳም ሥጋ ዛሬ ለዂሉ ሕይወትን ሰጠ፤ መቃብር የገዛው ባሕርያችን ዛሬ ዂሉን ከእግሩ በታች አድርጎ ገዛ፡፡ ለዚህ ዂሉ ምክንያቱ ምሥጢረ ተዋሕዶ ነው፡፡ ስለዚህ መለኮት በሥጋ ሞተ፤ ሥጋም በመለኮት ሕያው ኾነ ብለን እንናገራለን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ›› ብሎ መናገሩም ለዚህ ምስክር ነው (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፰)፡፡ መልክአ ኢየሱስም ‹‹ሰላም ለበድነ ሥጋከ እመለኮቱ ዘኢተፈልጠዓት አሐቲ ከመ ቅበተ ዐይን ኅዳጠ፤ ለዐይን ጥቅሻ ለምታክል ሰዓት ስንኳን ከመለኮቱ ያልተለየ በድነ ሥጋህን ሰላም እላለሁ›› ይላል፡፡

በዕለተ ዓርብ መስቀል ላይ የዋለው የክርስቶስ ሥጋ ከመለኮቱ አልተለየም፡፡ በእርግጥ የሥጋ ሕይወት ነፍስ ተለይታዋለችና ሥጋው ‹‹ምውት›› ወይም ‹‹በድን›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሆኖም ጌታችን በመለኮታዊ ባሕርዩ ሞት አያሰጋውም፤ አይስማማውም፡፡ ስለዚህም ሕያው ሥጋ ነው፡፡ ሕያው መኾኑንም ከሞተ በኋላ ለንጊኖስ በጦር በወጋው ጊዜ ደምና ውኃ ከጎኑ በመፍሰሱ እናረጋግጣለን፡፡ ከሞተ ሰው ደም ይወጣ ዘንድ የተፈጥሮ ሕግ አይደለምና፡፡ ምውትነቱን ደግሞ ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› ብሎ በፈቃዱ ነፍሱን በመስጠቱ እናረጋግጣለን፡፡ በአጠቃላይ ቃል፣ ሥጋ መኾንን የወደደው የሥጋን ድካም ለማገዝና በሥጋ ድካም ጠንካራውን ጠላት ዲያብሎስን ለማሸነፍ ነው፡፡ በመኾኑም በአራት ዓለማት ውስጥ በሰው ላይ ይደርሱ የነበሩ ችግሮቹን በአካል ተገኝቶ አስወግዶለታል፤ እነዚህም ማኅፀነ አንስት፣ ምድር፣ መቃብርና ሲኦል ናቸው፡፡

መርከስ እንጀምርበት በነበረው ማኅፀን መቀደስን እንደ ጀመርን ማረጋገጫ ይኾነን ዘንድ በእመቤታችን ማኅፀን የመላእክት ቅዳሴ ይሰማ ነበር፡፡ የሴት ማኅፀን ርኵሰት የሚጀመርበት የሰው ልጆች ዓለም ነበረ፤ ዛሬ (ጌታችን ሲወለድ) ግን «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ» ተብሎ የሚመሰገንበት ቦታ ኾነ፡፡ ሴቶች ከወለዷቸው ዂሉ ሕዝቡን ከኀጢአት ሊያድናቸው የተቻለው ማንም አልነበረም፤ ዛሬ ግን ከኃጢአት ንጹሕ ኾኖ ኃጢአትን የሚያርቅ ጌታ ተገኝቶበታል፡፡ ርኵሰታችን ከሚጀምርበት ከማኅፀን ጀምሮ የርኵሰታችን ዋጋ እስከ ኾነችው ሲኦል ድረስ በሔድንበት ሒዶ ችግራችንን አስወገደልን፡፡ ይህን ሲያደርግ ግን መለኮት ከሥጋ የተለየበት አንዳች እንኳን ጊዜ እንደ ሌለ እናምናለን፡፡

«ተራብሁ» (ሉቃ. ፬፥፪) ብሎ መናገር የሚስማማው ለሥጋ ብቻ ቢኾንም፣ መለኮትም በሥጋ እንደ ተራበ እንናገራለን፡፡ ኅብስት አበርክቶ መመገብ የሚቻለው ለባለ ጠጋው መለኮት ቢኾንም ለሥጋም ተገብቶታል፡፡ ጌታችን፣ ሣምራዊቷ ሴት ውኃ በከለከለችው ጊዜ ‹‹የሚለምንሽ ማን እንደ ነ ብታውቂስ ኖሮ አንች በለመንሽው፣ እርሱም ደግሞ የሕይወትን ውኃ በሰጠሽ ነበር›› ሲል የሰማነው በሥጋው ነው፡፡ ለራሱ የሌለው ሥጋ ለሌላው መስጠት ጀምሯልና፡፡ ሞትንም ስናነሣ ለሥጋ ብቻ ሳይኾን መለኮትም በሥጋ እንደ ሞተ፤ መለኮትም በሥጋ በመቃብር እንዳደረ እንናገራለን፡፡ ይህን የምንናገረው ግን እርሱ ሞቶ ለሙታን ሕይወትን የሚሰጥ መኾኑን ሳንረሳ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሊቁ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ውእቱ ውስተ መቃብር ወያነሥእ ሙታነ፤ እርሱ በመቃብር ያደረ ሲን ሙታንን ያስነሣል›› ሲል የሚናገረው (ሃይማኖተ አበው፣ ፲፩፥፬)፡፡

ይቆየን