ነገረ ትንሣኤ – ሦስተኛ ክፍል
በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ
ሚያዝያ ፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
በዓለ ትንሣኤ፣ ‹ፋሲካ› እየተባለ የሚጠራበት ምክንያት
የፋሲካ በዓል በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ፓሳህ› ይባላል፤ ትርጕሙም ‹ማለፍ› ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለ ትንሣኤ አንደኛ ሞት፣ ከእስራኤል መንደር ያለፈበት ስለ ኾነ ነው፤ ግብፅ በረሃብ እንዳትመታ ፈርዖናቸው ያደረገው ነገር ባይኖርም መጻተኛውና ወደ ወኅኒ የወረደው ዮሴፍ ግን የረሃብ ሞትን ወደ ግብፅ እንዳይገባ ከለከለው፡፡ ዳሩ ግን ዮሴፍ ሲያልፍ የዮሴፍን ታሪክ የማያውቅ ሌላ ፈርዖን ተሾመና በእስራኤል ላይ የሞት ሕግ አወጣ (ዘፀ. ፩፥፲፩)፡፡
‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፡፡ እርሱ ራስ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኰና ሰኰናውን ትነድፋለህ›› (ዘፍ. ፫፥፲፭) ተብሎ የተነገረለት ዲያብሎስ ራስ ራሱን የሚቀጠቅጥ ወንድ እንዳይወለድ በማሰቡ ሕፃናትን ከማኅፀን እያስቀረ፤ ለመቃብርም እያቀበለ እስከ ሙሴ ዘመን ደረሰ፡፡ ከሙሴ መምጣት በኋላ ሞት የእስራኤልን መንደር ለቅቆ ወደ ግብፃውያን መንደር እንዲገባ ምክንያት የኾነው ዕለትም ፋሲካ ይባላል፡፡ በዚህ በዓል ላይ እስራኤላውያን የበግ ጠቦት አርደው የቤታቸውን ጉበን የቀቡትን ደም የተመለከተው ሞት እነርሱን ትቶ የግብፃውያንን የበኵር ልጆች ገደለ፡፡ እስራኤላውያን ‹‹ቀሣፊያችን ተቀሠፈ›› ሲሉ በዓላቸውን ‹ፋሲካ› አሉት፡፡
እኛም በሐዲስ ኪዳን የጌታችንን ትንሣኤ ፋሲካ የምንለው ሞት ከእኛ ያለፈበት የመጀመሪያው በዓላችን በመሆኑ ነው፡፡ ስለ ብዙዎች ይቅርታ የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም በግብፅ ከተሠዋው በግ ይልቅ የከበረ መሥዋዕት ነውና ያሉትን ከማዳኑም ባሻገር የሞቱትንም ከመቃብር አውጥቷል፡፡ በእርሱ ትንሣኤ ሞት ከእኛ ማለፉንና የሰው ባሕርይ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱንም ‹‹ለምንት ተኀሥሣሁ ለሕያው ምስለ ምዉታን፤ ሕያዉን ከሙታን ጋር ስለ ምን ትፈልጉታላችሁ›› ከሚለው ኃይለ ቃል እንረዳለን (ማቴ. ፳፰፥፮)፡፡ ምዉታን ያላቸውም አጋንንት ናቸው፡፡ በጌታችን ትንሣኤ ሰው ከሙታነ ሕሊና ከአጋንንት ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ‹‹ኦ! አዳም መሬት አንተ ወትገብዕ ውስተ መሬት፤ አዳም ሆይ ቀድሞም መሬት ነህ፤ ወደ መሬትነትህም ትመለሳለህ›› የሚለው አዋጅ አሁን ተቀይሯል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ከሚያረጀው ወደማያረጀው፣ ከሚበሰብሰው ወደማይበሰብሰው ሰውነት የተሸጋገርንበት በዓል ነው፡፡ ይህ ዂሉ መሸጋገር የተፈጸመው በፋሲካው በግ ምክንያት በመኾኑ ክርስቶስን ፋሲካችን እንለዋለን (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፯)፡፡
ሁለተኛ ‹‹መሥዋዕተ ኦሪት አለፈ፤ መሥዋዕተ ወንጌል ደረሰ›› የምንልበት ወቅት ስለ ኾነ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠበት ዕለት በፋሲካ የተጀመረችውን ሕግ በፋሲካ ይሽራት ዘንድ የሚያልፈውን መሥዋዕተ ኦሪት አስቀድሞ፣ የሚመጣውን መሥዋዕተ ወንጌል አስከትሎ ፋሲካን አደረገ፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ‹‹ዝ ውእቱ ደምየ ዘይትከአው ለሐዲስ ሥርዓት በእንተ ቤዛ ብዙኃን፤ ስለ ብዙዎች ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው›› (ማቴ. ፳፮፥፳፰) በማለት ወደ ሐዲስ ኪዳን መግባታቸውን አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ አሮጌውን ትተን ወደ አዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት በዓል በመኾኑ ፋሲካ እንለዋለን፡፡
ሦስተኛ የደስታችን ማረጋገጫ ስለ ኾነ ነው፡፡ ‹ፋሲካ› ማለት በግእዝ ቋንቋ ‹ደስታ› ማለት ነው፡፡ ደስታችን የተረጋገጠው በጌታችን ትንሣኤ ሲኾን ፍጻሜውን የሚያገኘው ደግሞ በትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን በዕለተ ዓርብ በቈረሰው ቅዱስ ሥጋውና ባፈሰሰው ክቡር ደሙ ተመሥርታለች፡፡ ምንም እንኳን በሕዝብና በአሕዛብ ፊት ደስታዋን የምትገልጥበት ጊዜ ገና ቢኾንም፣ በትንሣኤው ግን በዝግ ቤት ውስጥ ኾና የክርስቶስን ሰላምታ ተቀብላ ተደስታለች (ዮሐ. ፳፥፲፱)፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ደስ ትሰኛለች›› እያልን የምንዘምረው፡፡
ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቶስ የትንሣኤዋ በኵር ኾኖ ተነሥቶላታልና ሊገድሏት በሚጎትቷት ሰዎች ፊት ለሽልማት እንደ ተጠራ ብላቴና ደስ እያላት ትቀርባለች (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳)፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደስታዋን በትንሣኤ ፍጹም እንደምታደርገውም ቅዱስ አርክዎስ በሃይማኖተ አበው ፱፥፩ ላይ ‹‹በዛቲ ዕለት ተፈጸመ ፍሥሐሃ ለቤተ ክርስቲያን፤ በዚች ቀን የቤተ ክርስቲያን ደስታ ፍጹም ኾነ›› በማለት ይመሰክርላታል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የጌታችን ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ ይጠራል፡፡
ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ምክንያት
የመጀመሪያው አዳም ለሞትና ለኀጢአት በኵር ሆኖ ነበርና ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ሞት ሲገዛን ኖሯል (ሮሜ. ፭፥፲)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስ ላንቀላፉት (ለሙታን) በኵራት ኾኖ ከሙታን ተነሥቶአል” በማለት ጌታችን የትንሣኤያችን በኵር መኾኑን ነግሮናል (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳)፡፡ ከጌታችን በፊት የሞቱና ከሙታን የተነሡ አሉ፡፡ ነገር ግን የጌታችን ትንሣኤ ከሌሎች ትንሣኤ የተለየ ነውና በኵረ ትንሣኤ (የትንሣኤ መጀመሪያ) ይባላል፡፡ ጌታችን በኵረ ትንሣኤ መባሉም፡-
አንደኛ ሞቱ፣ ሞትን ስላጠፋ ነው፡፡ የጌታችን ሞት ከሌሎች ሙታን የተለየ ነው፡፡ ሞትን በመግደል ድሩን ሳይኾን የችግሩን ምንጭ ሸረሪቱን አጥፍቶታል፡፡ ኀጢአት፣ ሞት፣ መቃብር እነዚህ ሦስቱ ተያያዥ ነገሮች ናቸው፡፡ ኀጢአት ከሌለ ሞት፣ ሞትም ከሌለ መቃብር አይኖርም፡፡ ሞት ሲሞት ሙታን ተነሡ፤ የሞት ጥላ ሲገፈፍ መቃብራት ተከፈቱ፡፡ በክርስቶስ ሞት ኀጢአት ከሥሯ እንደ ተነቀለች ዛፍ ላታፈራ፣ ላትለመልም ለዘለዓለም ተነቀለች፡፡ ሞትም ሙታንን ለቆ ጠፋ፤ መቃብርም ባዶ ኾኖ ተከፈተ፡፡ ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋ ‹‹ሞተ ዘቦአ ቀዳሚ ውስተ ዓለም በቅንዓተ ሰይጣን አብጠልከ በምጽአቱ ለዋሕድ ወልድከ መድኃኒነ፤ በሰይጣን ተንኮል ከልጅህ መምጣት አስቀድሞ ወደ ዓለም የገባ ሞትን በልጅህ ሰው መኾን አጠፋህ›› እያለች የምታመሰግነው (ሥርዓተ ቅዳሴ)፡፡
ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ሁለተኛው ምክንያት የጌታችን ትንሣኤ የመጀመሪያው ሐዲስ ትንሣኤ ስለ ኾነ ነው፡፡ ከእርሱ በፊት ከሙታን የተነሡ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም በሚበሰብስ ሥጋ ተዘርቶ በማይበሰብስ ሥጋ መነሣት የቻለ ማንም አልነበረም፡፡ ሌሎቹ ሙታን ለዘለዓለም ሞትን ማሸነፍ በሚችል ሞት የተነሡ አልነበሩምና (፪ኛ ነገ. ፲፫፥፳፩)፡፡ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ የተነሡት እንደነአልዓዛር ያሉትም ዳግመኛ መሞትና መነሣት አለባቸው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ እኛም ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ እንደ መላእክት ኾነን እንኖራለን፡፡ በሚፈርስ፣ በሚበሰብስ ሥጋ ተዘርተን (ሞተን)፣ በማይፈርስ፣ በማይበሰብስ ሥጋ እንነሣለን፡፡ የትንሣኤያችን በኵር ክርስቶስ ነውና፡፡
ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ሦስተኛው ምክንያት፣ ትንሣኤው ስለ ዂላችንም ቤዛ የተደረገ ትንሣኤ ስለ ኾነ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ስለ ዂላችን (ለዓለም) የሞተ የለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እስመ ኵሉ ፆሮ ይፀውር፤ ዂሉም የራሱን ሸክም ይሸከማል›› ብሎ እንደ ተናገረው (ገላ. ፮፥፭)፣ አባቶቻችን በራሳቸው ዕዳ ሲሞቱ ምንም ዕዳና በደል የሌለበት ክርስቶስ ግን ለፍጥረት ዂሉ ዕዳ ሊደመስስ በፈቃዱ ሞተ፡፡ ሞቱ ስለ ዂላችን እንደ ኾነ ዂሉ ትንሣኤውም የዂላችን ሕይወት ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነን የአይሁድ ፍርሃት ነው፡፡ አይሁድ ‹‹በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ማለቱን ሰምተናል፤ ደቀ መዛሙርቱ ሌሊት መጥተው እንዳይሰርቁት፣ ‹ተነሣም› ብለው ለሕዝብ እንዳያስተምሩ ...›› ነበር ያሉት (ማቴ. ፳፯፥፷፪-፷፭)፡፡
ይህ የአይሁድ ፍርሃት የዲያብሎስም ጭንቀት ነው፡፡ ጌታችን ክብርት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ሲለያት ዲያብሎስ ነፍሱን በሲኦል ውጦ፣ ሥጋውን በመቃብር ረግጦ ማስቀረት እንዳልተቻለው ስለ ተረዳ አይሁድን እንዲህ እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ትንሣኤውን ዐይተው ያምኑ ዘንድ ይህን ማለታቸው የጌታ ፈቃድ ነበር፡፡ አምነው ባይጠቀሙበትም የጌታ ትንሣኤ ላመኑትም ላላመኑትም ሕይወት ነውና፡፡ ስለዚህ ነው የጌታችንን ትንሣኤ በኵረ ትንሣኤያችን የምናደርገው፡፡
ትንሣኤ ዘጉባኤ
በእሳት ተቃጥለው፣ በአራዊት ተበልተው ወደ ዐመድነትና አፈርነት የተለወጡ ሰዎች፣ በዕለተ ምጽአት ከሞት የሚነሡት እንዴት ነው? እንደ ገና ሰው ኾነው ይፈጠራሉ ማለት ነው?
በመጀመሪያ ካለመኖር ወደ መኖር እንድንመጣ ያደረገን ጥበበ እግዚአብሔር ነው፡፡ ያለዚያማ እንዴት ኾኖ ነው ከአባት የተከፈለው ዘር ከሴት ደም ጋር ተዋሕዶ፣ ብጥብጥ የነበረው ረግቶ፣ የአጥንት ምሰሶ የጅማት ማገር ተሠርቶለት ቅዱስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚኾነው? በእርግጥ እንዲህ ኾኖ የተጀመረው ህልውናችን በሞት ሲቋረጥ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በመቃብር ውስጥ ቀልጦ ለመቅረት እንጂ ተመልሶ ለመብቀል አልነበረም፡፡ የሰው ልጅ እንደ አዝርዕት ከሞተና ከፈረሰ በኋላ አካል ኖሮት የሚነሣ ነው፡፡ ያለ ዝናም የአዝርዕት ምን ትንሣኤ አላቸው? ያለ ክርስቶስ ደም መፍሰስስ የሰው ልጅ ማን ከሞት ሊያስነሣው ይችላል? የጌታችን ደም ሲፈስ ግን መቃብራት ተከፈቱ፤ ዐለቶች ተሰነጣጠቁ፤ ከሙታን ወገን ብዙዎቹ ተነሡ፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቦኑ ለከንቱ ፈጠርኮ ለኵሉ እጓለ እመሕያው፤ በውኑ ሰውን ዂሉ ለከንቱ ነገር ፈጥረኸዋልን?›› የሚለው የአባቶቻችን ጥያቄ ምላሽ አገኘ (መዝ. ፹፰፥፵፯)፡፡
ሞት እንደ ገበሬ፣ መቃብር ደግሞ እንደ እርሻ ኾኖ የሰው ልጆች በዚህ ምድር በመበስበስ በመፍረስ እንዘራለን፡፡ እንዲህ ካልኾንን ትንሣኤ የለንም፡፡ በኋላም ተለውጠን በአዲስ ሥጋ እንነሣለን፡፡ ባሕርይ መልአካዊ፣ ባሕርይ ሥጋዊ፣ ባሕርይ እንስሳዊ ለዂላችንም በተፈጥሮ ይሰጡናል፡፡ ስንሞት ባሕርይ እንስሳዊ እና ባሕርይ ሥጋዊ ይለዩናል፡፡ ባሕርይ መልአካዊ ግን በባሕርዩ ሞት ስለ ሌለበት አብሮን ይኖራል፡፡ በምንም ዓይነት ሞት ብንሞትም ይህ የማይቀር ጉዳይ ነው (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፴፭-፵፬)፡፡ ትንሣኤ፣ የሰው ልጅ ፍሬ ሠላሳ፣ ስልሳና መቶ ፍሬ አፍርቶ የሚታይበት ወቅት ነው፡፡
ዕፅዋትና አዝርዕት ከፈረሱ፣ ከበሰበሱ በኋላ አንዱ በራሱ፣ ሌላው በጎኑ፣ ሌላው በሥሩ ያፈራል፡፡ ከሥሩ የሚያፈራው የባለ ሠላሳ፣ ከጎኑ የሚያፈራው የባለ ስልሳ፣ ከራሱ የሚያፈራው የባለ መቶ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ዳግም ልደት›› ተብሎ ይጠራል፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮዎች ሁለት ዓይነት ሲኾኑ፣ እነዚህም ጥንተ ተፍጥሮና ሐዲስ ተፈጥሮ ይባላሉ፡፡ ጥንተ ተፈጥሯችን በአዳም በኩል የተደረገው ተፈጥሯችን ሲኾን፣ ሐዲስ ተፈጥሮ የምንለው ደግሞ በክርስቶስ በኩል የተደረገውን የባሕርያችንን መታደስ ነው፡፡ ልደታችን ግን ሦስት ወገን ነው፡፡ አንደኛው ሥጋዊ፣ ሁለተኛው መንፈሳዊ፣ ሦስተኛው ደግሞ ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ይህም “ልደተ ሙታን እመቃብር” ይባላል፡፡ ይኸውም የሙታን ከመቃብር መወለድ ማለት ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት ማለትም በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሞት የምንነሣውም በዚህ መልኩ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡