ነገረ ትንሣኤ – ሁለተኛ ክፍል
በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ
ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት
ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሲገንዙት ጌታችን ‹‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት› … እያላችሁ ገንዙኝ›› ብሏቸዋል፡፡ ይህ ቃል አንደኛ ጌታችን የቀደመውን መርገም እንደ ሻረው የተረዳንበት ነው፡፡ በዘመነ ኦሪት የሞተ ሰው ብቻ ሳይሆን በድኑን የነካውም ርኩስ ነበር፡፡ ይህ ልማድ ለመሻሩ ማረጋገጫችን “ቅዱስ እግዚአብሔር” የሚለው ቃል ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሞት አንዱ የሕይወት መንገድ እንጂ ለሲኦል እና ለመቃብር የሚያሰጥ ፍርድ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ጌታችን መለኮታዊ ባሕርይው የተለየው መስሏቸው እንደ ነበር ያስረዳናል፡፡ በግዕ ነባቢ የተባለው ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ለዘመናት አበው ያቀረቡትን የሕይወት ጥያቄ ለመመለስ ነው፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስም ፈጽሞ ሕይወት እንደ ተለየው በማሰብ ይገንዙት ነበርና ይህን ጥያቄአቸውን ለመመለስ በቃሉ አናግሯቸዋል፡፡ በሥጋ ቢሞት በመንፈስ ግን ሕያው ነውና፡፡
ሦስተኛ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ እውነተኛ መሥዋዕት መኾኑን ለማስገንዘብ የተነገረ ቃል ነው፡፡ እስካሁን የቀረቡት መሥዋዕቶች ዂሉ ሞት የገዛቸው ነበሩ፡፡ ክርስቶስ ግን ከሞት አገዛዝ ውጪ በመኾኑ ከሞተ በኋላ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር በሉኝ›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ‹‹ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት›› እንዲሉት መናገሩም በሥጋው ቢሞት በመለኮቱ ግን ሕያው መኾኑን ለማስረዳት ነው፡፡ አራተኛ ባሕርየ መለኮቱ በሥጋው መከራ እንደ ተሳተፈ ለማሳወቅ ነው፡፡ መለኮት የሥጋን ውርደት፣ ሥጋም የመለኮትን ክብር ካልተሳተፈ የተዋሕዶ መገለጫው ምን ሊኾን ይችላል? ያለ ሥጋ እንዴት ኾኖ በድርብ በፍታ፣ በተልባ እግር ልብስ ሊሸፈን ይችላል? ያለ መለኮትስ ከሞት በኋላ እንዴት ሊናገር ይችላል? የሥጋ ሕይወት ነፍስ ናትና፡፡
የሙታን ሕይወታቸው፣ በመቃብር ላሉት ትንሣኤያቸው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና መቃብር ሊወስነው አይችልም፡፡ ደቀ መዛሙርቱን ሳይቀር ‹‹ሙታንን አንሡ›› ብሎ ሥልጣንን የሰጠ ጌታ እንዴት በሞት ግዛት ውስጥ ሊወሰን ይችላል? አይደለም! ‹‹በመቃብር አደረ›› እንላለን እንጅ ‹‹መቃብር ወሰነው›› አንልም፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ውእቱ ውስተ መቃብር›› ካለ በኋላ ‹‹ውእቱ አፍኣ እመቃብር፤ እርሱ ከመቃብር ውጭም አለ›› ብሏል፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታ ሲገንዙት በሰማይ ደግሞ በባሕርይ ክብሩ ጸንቶ አለ፡፡ በምድር መከራ በሚያጸኑበት አይሁድ ፊት መከራን ይቀበላል፤ በሰማይ ደግሞ ከመላእክት ምስጋና ይቀርብለታል፡፡
እነዚህ ዂሉ መለኮት በሥጋ መሞቱንና መከራ መቀበሉን፤ ሥጋም በመለኮት ሕይወት፣ መድኃኒት መባሉን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ እንዲህ ስንል ግን ‹‹መለኮት ሞተ›› እንዳንል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹በሥጋው ሞተ›› ትላለች እንጂ ‹‹በመለኮቱ ሞተ›› አትልም፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ለእመ ትቤ መለኮት ሞተ አንተ ቀታሊሆሙ ለአብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ መለኮት ሞተ የምትል ከኾነ የአብ የመንፈስ ቅዱስ ገዳይ አንተ ነህ›› ብሏል (ሃይ. አበ. ፲፩፥፲፫)፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ አንድ ናቸውና፡፡ ስለዚህ ‹‹መለኮት በሥጋ ሞተ፤ ሥጋ በመለኮት ሕያው ኾነ›› የሃይማኖታችን ትምህርት ነው፡፡
ጌታችን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ስለ መነሣቱ
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱ አስቀድሞ ‹‹ነፍሴን ላኖራትም፣ ላነሣትም ሥልጣን አለኝ›› በማለት ተናግሯል (ዮሐ. ፲፥፲፯-፲፰)፡፡ በሐዋርያት ሥራ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው›› ተብሎ ተጽፏል (ሐዋ. ፪፥፲፭-፳፮)፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹ጌታችን ከሙታን የተነሣው በራሱ ሥልጣን አይደለምን? እነዚህ ኃይለ ቃላትስ አይጋጩምን?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ወደ ምላሹ ስንመጣ ነገረ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ዓይነት አንድምታ አለው፡፡ ሐዋርያት ስለ እርሱ በጻፉት በሰበኩት ቃል ዂሉ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ መኾኑን ለማስረዳት አንዳንድ ጊዜ ፍጹም ሰው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፍጹም አምላክ ሲያደርጉት እንመለከታለን፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ‹‹የሚያበረታው መልአክ መጣ፤ ከብርቱ ጩኸትና ልመና ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ጸሎቱ ተሰማለት›› (ዕብ. ፭፥፯) በማለት ጌታችንን ከአዳም ልጆች እንደ አንዱ በማስመሰል ደካማ ቃላትን ተናግሮለታል፡፡ በዚህም አምላካችን ክርስቶስ ድካማችንን ለማገዝ መድከሙን እንረዳበታለን፡፡ ኀይለኛውን ጠላታችንን አስሮ፣ ሲኦልን በርብሮ ነፍሳትን ነጻ እስኪያወጣ ድረስ ጌታችን ደክሞ ታይቷልና ደካማ ቃላት ተነገሩለት፡፡ ለመለኮትማ ከአንዱ ወደ አንዱ ይሔድ ዘንድ ጎዳና አለበት እንዴ? በእውነት ስለ ሥጋ ድካም ይህ ዂሉ ተባለ፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍትም ሰው መኾኑን እንደ ነገሩን ዂሉ ፍጹም አምላክ መኾኑንም ሲመሰክሩ ‹‹ተኀድገ ለከ ኃጢአትከ፤ ፈቀድኩ ንጻሕ፤ ኀጢአትህ ተደመሰሰልህ፤ ፈቅጃለሁ፥ ንጻ›› እያለ በሥልጣኑ ኀጢአተኞችን ከበደል ነጻ እንደሚያደርግና ሕሙማንን እንደሚፈውስ ነግረውናል፡፡ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ይህን ያደርግ ዘንድ ሥልጣን ያለው የለምና፡፡ በዚያውም ላይ ነፋሳትን ሲገሥፅ፣ አጋንንትን ሲያስደነግጥ ዐይተን፤ እንደ አምላክ ባለ ሟሎች በእግዚአብሔር ስም ሳይኾን በራሱ ስም ተአምራትን ሲያደርግ ስንመለከተው አምላክ መኾኑን አወቅን፡፡ ስም አጠራሩን ስንመለከት አንዳንድ ጊዜ ‹‹ወልደ ዳዊት››፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ወልደ እግዚአብሔር›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹‹ወልደ ዳዊት›› በመባሉ ምድራዊ ልደቱን፣ ‹‹ወልደ እግዚአብሔር›› በመባሉ ደግሞ ሰማያዊ ልደቱን ተረዳን፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ‹‹ወልደ ዳዊት›› እየተባለ የመጠራቱ ምሥጢርም እኛ ሰማያውያን እንሆን ዘንድ እሱ ምድራዊ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ሲነገር ማንኛውም ምእመን የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ሊል ይገባል፤
፩ኛ ለካሣ የተነገሩ ቃላት መኖራቸውን
በቅዱስ ወንጌል ‹‹አባቴ ላከኝ፤ ይህን ሥልጣን ከአባቴ ተቀብያለሁ›› የሚሉ ቃላት በተደጋጋሚ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ ያ ማለት ግን ምድራዊ አባት በልጁ፣ ልጅም ለአባቱ እንደሚያደርገው በአብ እና በወልድ መካከል ማዘዝ፣ መታዘዝ፣ መላክ፣ መላላክ ኖሮ አይደለም፡፡ ‹‹ኢይኤዝዞ አብ ለወልዱ በከዊነ አብ ወኢየዐቢ ወልድ በከዊነ ወልድ፤ አብ ልጁን አባት በመሆን አያዝዘውም፤ ወልድም ልጅ በመሆኑ እንቢ አይልም›› እንዳለ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡ ታዲያ ለምን እንዲህ ይላል ያሉ እንደ ኾነ ቀዳማዊ አዳም ባለ መታዘዙ የመጣበት መከራ፣ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ እስከ መስቀል ድረስ ባደረገው መታዘዝ እንደ ተወገደለት ለማስረዳትና የአዳምን አለመታዘዝ በመታዘዝ ለመካሥ ነው፡፡
፪ኛ ጌታችን ፍጹም ሰው መኾኑን ለማስረዳት የተነገሩ ቃላት መኖራቸውን
ጌታችን ‹‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች›› ሲል ኀዘን የሚስማማው ሰውነትን እንደ ተዋሐደ ለማስረዳት ነው፡፡ ‹‹… ዋጋችሁ ብዙ ነውና ደስ ይበላችሁ›› እያለ የምሥራችን የሚሰብክ ጌታ እንዴት አዘነ ተብሎ ይነገርለታል?
፫ኛ የጠፉትን ለመፈለግ የተነገሩ ቃላት መኖራቸውን
ጌታ ‹‹አንቺ ሆይ፥ ውኃ አጠጭኝ›› ማለቱ ለሣምራዊቷ ሴት የሕይወትን ውኃ ለማጠጣት እንጂ እርሱ ውኃ ስለ ጠማው የተናገረው አይደለም፡፡ እንዲያማ ቢኾን ኖሮ በኋላ ውኃ ሲጠጣ ባየነው ነበር! ከዚያ ይልቅ ለሴቲቱ የሕይወትን ውኃ አጠጥቶ መሔዱን ስንመለከት ቃሉ የጠፋችውን ሴት ለመፈለግ የተነገረ መኾኑን እንረዳለን፡፡ ከላይ የተነሣው ጥያቄም ከእነዚህ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ለመነሣት እንደ አልዓዛር፣ እንደ ወልደ መበለት ድምፅ የሚያሰማውና ከመቃብሩ በር ላይ ተንበርክኮ የሚጸልይለት ጻድቅ አያስፈልገውም፡፡ በገዛ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል እንጂ፡፡ ለዚህም ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ›› ማለቱን ልብ ይሏል (ዮሐ. ፪፥፲፱)፡፡ በዚህም ሰውነቱን ከሞት እንደሚያነሣው ሥልጣን እንዳለው አሳይቶናል፡፡
በመሠረቱ ‹‹እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው›› (ሐዋ. ፪፥፲፭-፳፮) የሚለው ኃይለ ቃል፣ እግዚአብሔር እንዳስነሣው እንጂ አብ እንዳስነሣው የሚናገር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በሚለው ስም አብ ብቻ ሳይኾን ወልድና መንፈስ ቅዱስም ይጠሩበታል፡፡ አባቶቻችን የዚህን ኃይለ ቃል ምሥጢር ሲያስረዱ ‹‹እግዚአብሔርነቱ አስነሣው›› ብለው ይተረጕሙታል፡፡ ይኸውም ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ስም ባሕርያዊ ስም እንጂ አካላዊ ስም ስላልኾነ ነው፡፡
አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔር አምላክህ ቀባህ … እግዚአብሔርም የናዝሬቱን ኢየሱስን በኃይልና በመንፈስ ቀባው … እግዚአብሔርም ከሙታን መካከል ለይቶ አስነሣው …›› ሲል ሲሰሙ የእምነት መሠረታቸው ይናወጥባቸዋል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ በመጽሐፈ ምሳሌ ፰፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕም ‹‹ጥበብ ‹ጌታ ፈጠረኝ› አለች እንጂ ‹አብ ፈጠረኝ› አላለችም፤ ወልድ ስለ አባቱ መናገር በፈለገ ጊዜ ‹አባቴ› ብሎ ለይቶ የሚናገር አይደለምን?›› በማለት ለአርዮሳውያን የሰጠውን ምላሽ መመልከቱ ለዚህ ይጠቅማል (ሃይ. አበ. ፸፮፥፲፫)፡፡ ስለዚህ ‹‹አብ አነሣው›› ብለው ለሚሳሳቱ፣ ለሚያሳስቱ ወልድ በሥልጣኑ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ መኾኑን እንነግራቸዋለን፡፡
ሴቶች የጌታችንን ትንሣኤ የማየታቸው ምሥጢር
ቅዱስ ጳውሎስ ሴቶች በማኅበር መካከል መናገርና ማስተማር እንደማይገባቸው ተናግሯል (፩ኛ ቆሮ. ፲፬፥፴፭)፡፡ አንዳዶቹ ጌታችን ወደ መቃብሩ የሔዱትን ሴቶች ‹‹ወደ ገሊላ እንዲሔዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ›› ማለቱን በመጥቀስ ሴቶች ወንጌል ማስተማር ይችላሉ የሚል መከራከሪያ ያነሣሉ (ማቴ. ፳፰፥፩-፲)፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት የቀናን ይመስላቸውና ሲሳሳቱ እናያቸዋለን፡፡ የሴቶችን አለመስበክ ሲያስተዉሉ፣ ሴቶች የማይገቡባቸው ገዳማትን ሲያዩ እንደ መብት ጥሰት የሚቈጥሩት አሉ፡፡ አዳም ጥንት ሲፈጠር ያለ ሴት ብቻውን ለአንድ ሱባዔ ቆይቷል፡፡ ሴት የማይገባባቸው ገዳማት መኖራቸው ከሔዋን መገለጥ በፊት የነበረውን አዳም ለመግለጥ እንደ ሆነ መረዳት ይገባል፡፡
ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን መሰብሰብ ሲጀምር ሠላሳ ስድስቱን ሴቶች እንዲኾኑ ማድረጉ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሴቶች ለወንጌል አገልግሎት መጠራታቸውን ልናምን ይገባናል፡፡ ከተጠሩት ቅዱሳት አንስት መካከልም ወንጌልን ሰብከው ብዙዎችን ወደ ማመን እንደ መለሷቸውና እንዳስጠመቋቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ እንዲህ ስላልን ግን በጉባኤ ወጥተው ያስተምሩ ነበር ማለታችን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የከለከለውም ይህንኑ ነው፡፡ በእርግጥ ሴቶች፣ ሴቶችን ሰብስበው ያስተምሩ ነበር፡፡
ለማርያም መግደላዊት መጀመሪያ ትንሣኤውን የገለጠውና ‹‹ሒደሽ ለወንድሞቼ ንገሪያቸው›› ብሎ የላካት ለምንድን ነው? ከተባለ ሞት ወደ ዓለም ሲገባ የተሰበከው በሴት አንደበት ነበር፤ በሴት እጅ በተቈረጠ ዕፀ በለስ፣ በሴት አንደበት በተሰበከ ስብከት ሞት ወረሰን፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶቹ ርስት አይካፈሉም፤ ከቍጥር ገብተው አይቈጠሩም ነበር፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች በእርሱ ቤዛነት እንዳስቀረላቸው ለማጠየቅ ጌታችን ለሴቶች ተገለጠ፡፡ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ሴት፣ ሞትን በሰበከችበት አንደበቷ ትንሣኤውን እንድትነግር፤ ወደ ዕፀ በለስ በሮጠችባቸው እግሮቿ ወደ ሐዋርያት እንድትገሰግስ አደረገ፡፡ በዚያውም ላይ ቀዳማዊ አዳም ከእንቅልፉ ሲነቃ ከጎኑ ያገኛት ሔዋንን ነበር፡፡ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ከሞት በተነሣ ጊዜ ከመቃብሩ በአፍኣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ተገኝተዋል፡፡
ይቆየን