ነቢዩ ዮናስ (ክፍል ሁለት) /ለሕፃናት/

የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በወልደ ኢየሱስ /ቤካ ፋንታ/


እግዚአብሔር በጣም የሚወዳችሁ እናንተም እግዚአብሔርን በጣም የምትወዱት ሕፃናት እንደምን ሰነበታችሁልን?

 

ልጆችዬ ባለፈው በክፍል አንድ ጽሑፍ ስለ ደጉ ልጅ ስለ ዮናስ የተማርነውን ታስታውሳላችሁ? ዮናስ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት በባሕር ላይ የሚሄድባት መርከብ ከባድ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ዮናስን ወደ ባሕር ውስጥ ሲጥሉት ንፋሱ ቆመ፡፡ መርከቧም በሰላም መሄድ ቻለች፡፡ ዮናስ ግን ወደ ስምጡ ባሕር እንደገባ አይተን ነበረ ያቆምነው፡፡ ዛሬ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

 

በመጀመሪያ ግን አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፡-

  • ትልቁ በጣም ትልቁ በባሕር ውስጥ ከሚኖሩት ዓሣዎች ሁሉ የሚበልጠው ትልቁ ዓሣ ስሙ ምን ይባላል?

 

ደጉ ዮናስ የመርከቧ ሠራተኞች ከመርከቧ ላይ ወርውረው ወደ ሰፊው ባሕር ሲጥሉት ውኃው ውስጥ ሰመጠ፡፡ ከዚያ ወደ ስምጡ ባሕር ሲገባ በውኃ ስለተከበበ ዮናስ መተንፈስ አቃተው እግዚአብሔርም ለዮናስ አዘነለት እንዳይሞትም አስቦለት በባሕር ውስጥ ካሉት ዓሣዎች ሁሉ በጣም ትልቁን ዓሣ ላከለት፡፡ ትልቁ ዓሣ ስሙ ዓሣ አንበሪ ይባላል፡፡ እግዚአብሔርም ዓሣውን እንዲህ ብሎ አዘዘው “የምወደው ደጉ ዮናስ ውኃው እንዳያፍነውና እንዳይሞት ሂድና ዋጠው፡፡ በሆድህ ውስጥም ለሦስት ቀን እና ለሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡” ሲለው ዓሣ አንብሪው ካለበት ቦታ ፈጥኖ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወዶ ዮናስ ደረሰና ዋጠው፡፡ ከዚያ ወደ ስምጡ ባሕር ውስጥ እየዋኘ ሄደ፡፡

 

ልጆችዬ የሚገርማችሁ ነገር ትልቁ ዓሣ ዮናስን ሲውጠው ዮናስ አልሞተም፡፡ በዓሣው አፍ ገብቶ፣ በጉሮሮው አልፎ መጨረሻ ላይ ሆዱ ውስጥ ሲደርስ ዮናስ ደነገጠ፡፡ ወዲያውም ቆሞ ሲመለከት ያለው ትልቁ ዓሣ ሆድ ውስጥ ነው፡፡ በሆድ ውስጥ ሆኖ መተንፈስ ይችላል፣ ማየት ይችላል፣ መቆም ይችላል፣ መናገርም ይችላል፡፡

 

ዮናስ እግዚአብሔር ዓሣ አንበሪውን ልኮት ከሞት እንዳዳነው ሲያውቅ በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሆኖ በጉልበቱ ተንበረከከና አንገቱን ቀና አድርጎ ወደ ላይ ወደ ሰማይ እያየ “እግዚአብሔር ሆይ ስለምንህ ጸሎቴን ሰምተህ ከሞት ስላዳንከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ በዚህ በዓሣ ውስጥም የዓሣው ጨጓራ እንዳይፈጨኝ ስለጠበቅኸኝ አመሰግንሃለሁ….” እያለ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ሙሉ ሳያቋርጥ ደስ ብሎት እግዚአብሔርን ሲያመሰግነው፣ እያጨበጨበ መዝሙር ሲዘምር እግዚአብሔር የዮናስን ጸሎት ሰማ፡፡ እግዚአብሔርም ዓሣውን “ልጄ ዮናስን ወደ ደረቅ መሬት ሄደህ ትፋው” ብሎ አዘዘው፡፡ ዓሣውም ዮናስን በባሕርl ዳር አጠገብ ወዳለች ነነዌ ወደምትባል ሀገር ተፋው፡፡

 

ዮናስ ከዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሲወጣ ቶሎ ብሎ የሄደው እግዚአብሔር ወደ ላከው ሀገር ወደ ነነዌ ነው፡፡ ዮናስ ከባሕሩ ሲወጣ አንድ ነገርን ተምሮዋል፤ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ብዚ ችግር እንደሚያመጣ አውቆዋል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ ላከው ነነዌ ወደምትባል ሀገር ሄደ፡፡ የነነዌ ሕዝብ ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎዋችኋል፡- ክፉ ሥራ መሥራት ትታችሁ ጥሩ ሥራ እኔ እግዚአብሔር የምወደውን መልካም ሥራ ካልሠራችሁ እቆጣችኋለሁ፡፡ ክፉ ሥራ መሥራት ካልተዋችሁ የምትኖሩበትን ከተማ እሳት ከሰማይ አውርጄ አቃጥላታለሁ፡፡” እያለ እየዞረ ለሕዝቡ ሁሉ ነገራቸው፡፡

 

የነነዌ ሕዝቦች የነቢዩ ዮናስን ቃል ሲሰሙ በጣም ደነገጡ፡፡ እግዚአብሔርም ከተማቸውን እንዳያጠፋባቸው እነርሱንም ይቅር እንዲላቸው ሁሉም ተሰበሰቡና ተማከሩ “እግዚአብሔር በክፉ ሥራችን ምክንያት ተቆጥቶ ሀገራችንን እንዳያጠፋ እንጹም፤ እግዚአብሔር እኮ እየጾምን ከለመንነው ይቅር ይለናል፡፡ ስለዚህ ከአሁን ሰዓት ጀምረን ሁላችንም ምግብ ሳንበላ ውኃ ሳንጠጣ ክፉ ሥራ መሥራት ትተን በጾም ለሦስት ቀን እግዚአብሔርን እንለምነው፡፡” ተባባሉና ሕፃናትም፣ ወጣቶችም፣ እናቶችም፣ አባቶችም፣ እንስሳቶችም ሁሉም “እግዚአብሔር ሆይ ይቅር በለን፣ ከአሁን በኋላ ክፉ ሥራ አንሠራም፣ ጥሩ ሥራ እየሠራን አንተ ያዘዝከንን እንፈጽማለን፡፡” እያሉ ለሦስት ቀን ውኃ ሳይጠጡ፣ ምግብ ሳይበሉ በጾም እግዚአብሔርን ለመኑት፡፡

 

እግዚአብሔርም ወደ ነነዌ ሕዝብ ሲመለከት ሁሉም እየጾሙ አየ፡፡ ሁሉም “ይቅር በለን” ይላሉ፡ የነነዌ ሕዝቦች ክፉ ሥራ መሥራት ትተው እየጾሙ እየጸለዩ ሲለምኑት እግዚአብሔር ከሰማይ ከተማዋን ሊያጠፋ እየፈጠነ የሚወርደውን እሳት እሳት እንዳይወርድባቸው ከለከለው እየወረደ የነበረውም እሳት ጠፋ፡፡

 

ልጆችዬ እግዚአብሔር የሚጾም ልጅን በጣም ነው የሚወደው፡፡ እግዚአብሔርን እየጾምን እየጸለይን ከለመነው በእኛ ላይ ክፉ ነገር አይመጣብንም፣ ቤተሰቦቻችንንም እግዚአብሔር ይጠብቅልናል፡፡ ጾመ ነነዌ የሚባለውን ለሦስት ቀን የሚጾመውን ጾም በሚመጣው ሰኞ ጀምረን እስከ ዕረቡ ለሦስት ቀን እንጾመዋለን፡፡ ታዲያ ልጆች ስንጾም ሳንዋሽ፣ ሳንሳደብ ክፉ ሥራ ሳንሠራ፣ ለእግዚአብሔርም ለቤተሰቦቻችንም እየታዘዝን መጾም ይኖርብናል፡፡ መልካም የጾም ቀናት ይሁንላችሁ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ከነቢዩ ዮናስ በረከትን ያድለን፡፡ አሜን፡፡