ነሐሴና በረከቶቹ
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሐምሌ ፳፮፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ጸጋዎች ባለቤት ናት፡፡ በብዙ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ጸጋዎች የተሞላች ግን ደግሞ በውል ይህን እውነት የማንረዳ ብዙ ዜጎችም ያላት ሀገር ናት፡፡ “አንድ ሰው ጸጋውን የሚያውቀው ሲያጣው ነው” እንደሚባላው መንፈሳዊና ቁሳዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ጸጋዎቿን የምንረዳበትና ጠብቀን ተንከባክበን የምንጠቀምበት ዘመን ይመጣ ዘንድ እንመኛለን፡፡
የዚህች ሀገር ልዩ ጸጋዎች ከሆኑት መካከል ወቅቶች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ምክንያቱም የዐሥራ ሦስት ወር ጸጋ የታደለች በክረምትና በበጋ፣ በጸደይና በበልግ በዐሥራ ሦስት ወር ወራት የተዋቀረ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ተስማሚ ወቅት ያላት ሀገር በመሆኗ ይህ በብዙዎች ዘንድ የማይገኝ ጸጋ ነው፡፡
አሁን ያለንበት ወቅት ወርኃ ክረምት ነው፡፡ ብዙ ዕፅዋትና አትክልቶች ሣርና አበቦች ሕይወት ገዝተው የሚበቅሉበት፣ የተራቆቱ ኮረብታዎች የሚሸለሙበት፣ ምንጮች የሚጎለብቱበት፣በድንጋይና በአሸዋ የተሞሉ አፍላጋት ከአፍ አስከ ገደፋቸው የሚሞሉበት፣ ውኃዎች በነፋሳት ትክሻ ተጭነው ወደ አየር የሚወጡበት፣ ሕይወት ላለው ፍጥረት ሁሉ ምክንያተ ሕይወት ለመሆን በዝናብ መልክ የሚወርዱበት፣ ለሞትና ለሕይወት፣ ለኃጢአትና ለጽድቅ፣ ለኃጥአንና ለጻድቃን፣ ለነፍስና ለሥጋ፣ ምሳሌ የሚሆኑ ብዙ ክስተቶችን የተሸከመ ወቅት ነው፡፡
ከዚህ በፊት በተከታታይ ያቀረብንላችሁ በመሆኑ የዚህ ጽሑፍ መነሻ ምክንያት ስለ ክረምት ማውራት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ትኩረታችን ከክረምቱ ወራት መካከል በአንዱ በነሐሴ ወር የምንዘክራቸውን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክንውኖቹንና (በረከቶቹን) መዳሰስ በመሆኑ በጥቂቱ ለማየት ወድደናል!
ነሐሴ በኢትዮጵያውያን ባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ዐሥራ ሁለተኛው ወር ነው፡፡ አስፈሪውና ማዕበል ከሚበዛበት፣ በነገድጓድና በብልጭልጭታ ከታጀበ፣ ከዝናቡ ጽናትና ከጎርፉ ብዛት የተነሣ ምድር ከምታረገርግበት፣ ጎርፍና ናዳ ከሚበዛበት፣ አስጨናቂ ከሚባለው የሐምሌ ወር ተሻግረን የክረምቱ ጨለማ ቀለል የሚልበት፣ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የተዘራው ሰብል አበባ ለማበብ እምቡጡን የሚያሳይበት፣ አልፎ አልፎ እንደ ጠበል ዓይነት የገብስ ዘሮችና ድንችን የመሳሰሉ የነፍስ አዳኝ ሰብሎች ለምግብነት የሚደርሱበት፣ የሚዘንበው ዝናብ፣ የሚነፍሰው ነፋስ ሁሉ ለሰውም ለከብትም ጤና ነው ተብሎ የሚታመንበት፣ ተወዳጅ ወቅት ነው፡፡
ከምንም በላይ ግን ነሐሴን ስናስብ ልባችን በደስታ የሚሞላው፣ አስኪደርስ የምንጓጓው፣ ትንሹን ትልቁን ቀልብ የሚስበው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ለመገናኘት አባቶችና እናቶች ሱባኤ ለመያዝ፣ ወጣቶችና ሕፃናት ለመጾም፣ ለመቊረብ፣ ካህናት ለሰዓታቱ፣ ሊቃውንት አደግድገው ውዳሴዋን፣ ቅዳሴዋን ለመተርጎም፣ ሁሉም በየፊናቸው የሚያሳዩት ጉጉት የሚያሳዩት ትጋትና ሽር ጉድ ሲታሰብ ነሐሴን ልዩ ያደርገዋል፡፡
ወሮቹን ለቅዱሳን መሰየም ቢቻል ይህን ወር ለእመቤታችን የምንመድበው ይመስለናል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ወር ከእመቤታችን ፍቅር የተነሣ ደካሞች ይበረታሉ፤ ብርቱዎች የበለጠ ይተጋሉ፤ ሕፃናት ልዩ ዓለም ውስጥ ይገባሉ፤ ካህናቱ መምህራኑ ሥጋዊ ደማዊ መሆናቸውን ይዘነጋሉ፤ በመንፈስ ይከንፋሉ፤ በዚህ ወቅት ሁሉም በበረከት ይሞላል፤ ስሟን ጠርቶ “ንዒ ንዒ” ሲላት መሽቶ ይነጋል፤ ምስጋናቸው ዕረፍታቸው፣ ረፍታቸው ምስጋናቸው ከተባሉ መላእክት ጋር የሚያስተባብር ብርታት፣ ትጋት፣ ቅንናዓት፣ ፍቅርና ኅብረት የሚታይበት የአገልግሎት ወር ነውና፡፡ (መጽሐፈ ሰዓታት)
ምናልባትም ነሐሴን ዝናቡን ጸበል ነፋሱን ሕይወት ያደረገው ለነፍስ ለሥጋ፣ ለሰው ለእንስሳ ተስማሚ ያደረገው ምክንያቱም ይህ ይመስለናል፡፡ ሁሉም “ንዒ ንዒ” ይላታል፤ ሁሉም ይማጸናታል፤ ሁሉም ጠርቶ አይጠግባትም፤ እርሷም በምልጃዋ በቃል ኪዳኗ ትራዳለች፤ ሁሉም በፍቅሯ ይሰክራል፤ በበረከቷ ይጠግባል፤ ሽማግሎች ይታደሳሉ፤ ወጣቶች ያስተውላሉ፤ ሕፃናት በፍቅሯ ይጎለምሳሉ፤ ረኃብተኞችም ይጠግባሉ፤ ድውያንም ይፈወሳሉ፤ የሕይወት ቋጠሮ ሁሉ ይፈታል፤ የፍጥረት ሁሉ ተስፋ ይጸናል፤ ፍጹማኑን በአካል፣ ማዕከላውያኑን፣ ወጣንያኑን በራእይ፣ በሕልም እኛን ሰብአ ዓለምን ኃጢአተኞችን በመንፈስ ትጎበኘናለችና፡፡
ይህ ወር የፍጥረት ሁሉ ደስታ የሆነች እመቤታችን የተፀነሰችበት ወር ነው፡፡ ይህ ወር ሐዋርያት ስለ ፍቅሯ ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሩ ዘንድ የጾሙበት ወር ነው፤ ይህ ወር የእመቤታችን ከሙታን ተለይታ የተነሣችበትና ያረገችበት ወር ነው፡፡ ነሐሴ ሐዋርያትም ሱባኤ ገብተው በድጋሚ ትንሣኤዋን፣ ዕርገቷን ያረጋገጡበት ወር ነው፡፡ (መጸሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ፣ ቀን ሰባት እና ፲፮፣ መዝገበ ታሪክ ገጽ ፻፵፪ እና ፻፵፮)
ይህ ወር በሰሜኑ ኢትዮጵያ የልጃገረዶች የደስታ የነጻነት ወር ነው፤ ይህ ወር በጎንደር ‹‹አድርሽኝ›› በሚል ልዩ ትውፍታዊ ሥርዓት፣ በብዙው የሰሜኑ ክፍል በልጅ አገረዶች አሸንድየ፣ አሸንዳና ሶለል፣ በወንዶች ሲራራ ጭዋታ የሚደምቅበ ወር ነው፡፡ (ክብረ በዓላት ገጽ ፪፻፶፬ እና ተከታዮቹ)
ነሐሴ በደብረ ታቦር የጌታችን ብርሃነ መለኮቱ የተገለጠበት፣ ወልደ እጓለ እመሕው ክርስቶስ ራሱን የገለጠበት፣ የቤተ ክርስቲያን ኅብረት በታቦር ተራራ የታየበት የበረከት ወር ነው፡፡በእምነታቸው የተመሰከረላቸው፣ እግዚአብሔር በስማቸው የማለባቸው፣ የሕያዋን ሁሉ አባቶች አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ የሚታሰቡበት ወር ነው ነሐሴ፡፡ (መጸሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ፣ ቀን ፲፫ እና ፳፰) በጥቅሉ የነሐሴ ወር እጅግ የሚናፈቅ፣ በተስፋና ፍቅር የተሞላ ወር መሆኑን፣ የእመቤታችን ፍቅር በልቡናችን ጣዕሟ በአንደበታችን የሚጎላበት ወር ነው፡፡
ቸር እንሰንብት!