ኀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ- የአንተ በሆነ መንፈስ ቅዱስ አንድ መሆንን ስጠን!
በዐለም የክርስትና ታሪክ ውስጥ ምእመናን ከተፈተኑበት ፈተናዎች አንዱ በአንድ በታወቀ መንበር ላይ ከአንድ በላይ ፓትርያርኮች ወይም ፖፖች መሾም ነው፡፡በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀድሞ በነበረ ፓትርያርክ ወይም ፖፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተደርቦ እንደተሾመ የሚነገርለት ቅዱስ አቡሊዲስ ዘሮም ነው፡፡ ቅዱስ አቡሊዲስ (Hippolytus) ተቀናቃኝ ፖፕ የሆነበት መንገድ ከዘመኑ የተነሣ በታሪክ ብዙም ባይገለጽም ተቀናቃኝ ሆኖ የተሾመው ግን ካሊክሰቶስ ቀዳማዊ (Pope Callixtus I) የሮም ፖፕ በነበረበት ዘመን ነበር፡፡ ሆኖም ካሊክስቶስ ሲያልፍ በወንበሩ ከተተካው ከፖፕ ፖንትያን (Pope Pontian) ጋር ታርቆ ችግራቸውን ፈትተዋል፡፡ በመጨረሻም ያረፈው በሰማዕትነት ስለነበረ ተጋድሎው በቅድስና ይታሰባል፡፡ በሮም ካቶሊክ ዘንድ በዓሉ የሚከበርለት ከታረቀው ከፖፕ ፖንትያን ጋር በአንድነት በእነርሱ አቆጣጠር ኦገስት በሚባለው ወራቸው በ13ኛው ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕርቅን አውርዶ ችግርንም ፈትቶ በአንድነት መከበርና መታሰብ የጀመረው ከመጀመሪያው ዐለምአቀፍ ጉባኤ ከጉባኤ ኒቅያ አንድ መቶ ዐመት በፊት ገና ሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደነበረ ታሪካዊ አስረጅ አለው ማለት ነው፡፡
በርግጥ በፖፕ ላይ ፖፕ እየተሾመ መወዛገብ በሮማ ካቶሊክ ታሪክ ደጋግሞ ያጋጠመ ነገር ነበር፡፡አጥኝዎች እንደሚሉት በሮም ካቶሊክ ታሪክ ይህ ችግር ለ42 ጊዜ ያህል ተከስቷል፡፡ ሆኖም ከፍተኛ ውዝግብ ያስከተለው በ14ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የተከሰተውና ለ40 ዐመታት የቆየው ታላቅ ውዝግብ ነው፡፡ከ1378 -1417 እንደቆየ የሚነገርለት ይህ ክፍፍል በሮማ ካቶሊክ ታሪክ ትልቁና በታሪክ ተመራማሪዎችም ዘንድ ትልቁ የምዕራቡ ክፍፍል እየተባለ የሚጠራና ከሦስት በላይ ፖፖች እኔ ነኝ ሕጋዊ ፖፕ በማለት የተወዘጋቡበት ነበር፡፡ መነሻውም በግልጽ ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት የፈጠረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ቢሆንም ከ1414 – 1418 ኮንስታንስ ላይ በተካሔደ ጉባኤ ችግሩን ፈትተው አንድነታቸውን ለመመለስ ችለዋል፡፡
በምሥራቁም ዐለም ድርጊቱ በተለያዩ ጊዜያት ሲከሰት ኖሯል፡፡ለምሳሌ በቁስጥንጥንያው ንጉሥ ታግዞ በእስክንድርያ መንበር በቅዱስ አትናቴዎስ ላይ ተተክቶ የነበረው ጊዮርጊስ በእኛ ሊቃውንት ዘንድም በደንብ የሚታወቅ ታሪክ ነው፡፡ ቆይቶ ደግሞ በተለይ ከጉባኤ ኬልቄዶን በኋላ በአንጾኪያ እና በቁስጥንጥንያ መንበሮች ብዙ ውጣ ውረዶች መፈራረቆችና መተካካቶች መሳደዶች በተደጋጋሚ አጋጥመዋል፡፡
በቅርብ ጊዜ እንኳ በሩስያ፣በሕንድ እና በአርመን ኦርቶዶክሶች ተከስተው የነበሩት መከፋፈሎች ሊዘነጉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ብዙዎቹ ወይም ሁሉም ልዩነቶች ተፈትተዋል፡፡ በግሪክ ኦርቶዶክስ ግን አሁንም ትልቅ ክፍፍል አለ፡፡ ሆኖም የእነርሱ ፖለቲካዊ ጫና የፈጠረው ሳይሆን የትውፊት መለወጥ ነው፡፡ ይኸውም የቀድሞውን ዮልዮሳዊ የዘመን አቆጣጠር ትተው በምዕራባዊ ጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠር መጠቀም ሲጀምሩ ይህንን የተቃወሙት ለብቻቸው ተለይተው ወጥተዋል፤ ስማቸውም ኦልድ ካላንደሪስት ኦርቶዶከስ ቤተ ክርስቲያን (Old Calendarists orthodox Church) የሚል ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ላይ መለያየትና መከፋፈል በሌሎቹም ላይ ቀደም ብሎ ያጋጠመ እና ሲፈቱት የኖረ ችግር መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም በሮም ለ40 ዐመታት የቆየው ውዝግብ ግን ብዙ ችግር ያስከተለ ከመሆኑም በላይ የተፈታበትም መንገድ ብዙ ትምህርት ሊወሰድበት የሚችል ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ ገና ከሉተር መነሣት በፊት ስለነበረ መላው ምዕራብ አውሮፓ በሮም ካቶሊክ ውስጥ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ተወዛጋቢ ፖፖች ደግሞ ትውልዳቸው አንዱ ከፈረንሳይ ሌላኛው ከጣልያን ነበሩ፡፡ ይህም ማለት ተፎከካሪዎቹ ፖፖች በሁለት ሀገርና መንግሥታትም ጭምር ስለሚታገዙ ክፍፍሉ ጠንካራ ነበር፡፡ መንግሥቶቻቸው ደግሞ ሌሎቹን ሀገሮች እየቀሰቀሱ ከፊል የምዕራብ አውሮፓ መንግሥታት አንዱን ሌሎቹ ደግሞ ሌላውን ይደግፉ ስለነበር የጣልቃገብነቱንና ፍላጎት ያለው አካል ብዛትን ስናይ ብዙ ችግሮች እንደነበሩበት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ለአንዳንዶች ሌሎች ሦስተኛና አራተኛ ፖፖችን እስከመሾም ያደረሳቸውም ከዚህ ከመጀመሪያዎቹ የኃያላን መንግሥታት ፍላጎት የተላቀቀ አዲስ ሲሾም ይፈታል ብለው በማሰብ ነበር፡፡ ሆኖም አልተሳካም፡፡ በመጨረሻ ግን አራት ዐመት በወሰደው ጉባኤያቸው ሁሉንም መንግሥታት፤ ካርዲናሎች፤ ሕዝቡን፤ ደጋፊዎቻቸውንና የመከፋፈል ተጠቃሚዎች የነበሩትን ሁሉ አሳምነውና አሸንፈው አንድ መሆን በቁ፡፡ በእውነት ከሆነ እንኳን በቁጥር ከዐሥር በላይ የሆነ ሀገርና መንግሥታትንና ሕዝብ አሸንፈው ለዚህ ከመብቃት በላይ አስደናቂ ነገር የለም፡፡
በእኛ ሀገር የተከሰተውም ምክንያቱ ፖለቲካን ተገን ያደረገ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ፖለቲካን ተገን አድርጎ ቤተ ክርስቲያንን መጉዳት ሲጀመር ይህ የመጀመሪያው አልነበረም፡፡ ከደርግ መምጣት ጋር ተያይዞ ባለ ትልቅ ራእይ በነበሩት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተፈጸመው ግፍ ቢያንስ መንበሩ ወደ እኛ ከመጣ በኋላ ላለው ታሪካችን የመጀመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ምንም እንኳ በየዋሕነት ለነበሩትና በእንዲህ ያለ ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት ግንዛቤ እንዳልነበራቸው ግምት በምንወስድላቸው አባቶች ላይ ሙሉ በሙሉ ለመፍረድ ቢያስቸግርም ፖለቲካዊ ሒደቱን ተቋቁሞ በሐዋርያዊ መንገድ ችግሩን ለመወጣት የተደረገ ጥረት ግን ጎልቶ አይሰማም፡፡ እንዲያውም የፖለቲከኞችን ተንኮል ካለመገንዘብም ይሁን ከሰብአዊ ድካም በመነጨ በማይታወቅበት መንገድ ባይብራራም ተወቃሽ ተደርገው ሲቀርቡም ይስተዋላል፡፡
የደርግ ዘመን አብቅቶ ኢሕአዴግ ሲገባም ግቡ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ግን በመንበሩ ላይ በነበሩት አባት የወደፊት ሁኔታ ላይ ግን ለየት ያለ ድርጊት ተፈጸመ፡፡ በቀደመው ዘመን በአቡነ ቴዎፍሎስ የነበረውም ድርጊት ተወገዘ፡፡ ሆኖም የቀደመውን ድርጊት አውጋዦቹ ሌላ ተመሳሳይ ድርጊት ላለመፈጸማቸው ዋስትና ከመሆን ይልቅ የሚያወግዙትን ድርጊት አሻሽለው ከመፈጸም አልተመለሱም፡፡ በዚህ ወቅት የነበሩት አባቶችም አሁንም ከሐሜት መትረፍ አልቻሉም፡፡ ሐሜታውም በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉትን የሚያጠቃልል ነው፡፡
ታሪኩን በዚህ መጠን ለማስታወስ ያህል የሞከርነውም የችግሩ ተጠያቂነት በሁሉም ላይ ያረፈ መሆኑን ለመጠቆም ያህል እንጂ በታሪኩ ላይ ለመነታረክ አይደለም፡፡ ይልቁንም በተጠያቂነት ከመጠየቅ አልፈን ታሪካችንን ለሚያድስና ያለፈውን ለትምህርት ብቻ እንድንተወው የሚያደርግ አዲስ ወርቃማ ዕድል በእጃችን መኖሩን አስተውለን ሁላችንም በኅብረተ መንፈስ ቅዱስ አንድ እንድንሆን የምንጸልለውን ጸሎት በተግባር እንድናውለው ለመጠየቅ ያህል ብቻ ነው፡፡
በዚህ መልእክታችንም በቅዳሴያችንና በዘወትር ጸሎታችን የምንጸልያቸውን መነሻ አድርገን ልናደርጋቸው የሚገቡንን በማስታወስ መልእክታችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡
ሀበነ እግዚኦ አእይንተ አእምሮ
አባቶቻቸን አርእስተ መናብርቱ፣ በሁሉም በኩል ያሉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ካህናት በሙሉ ቅዳሴ እግዚእን በሚቀድሱበት ጊዜ ሓዳፌ ነፍስ ወይም ነፍስን የሚያጸዳ የሚወለውል ተብሎ በሚጠራው የመጨረሻው ጸሎት ላይ “ኀበነ እግዚኦ አእይንተ አእምሮ ወትረ ኪያከ ይርአያ ወአእዛንነሂ ቃለ ዘባሕቲትከ ይስምዐ” ‘አቤቱ ጆሮዎቻችን የአንተን ቃል ብቻ ይሰሙ ዘንድ ዐይኖቻችንም አንተን ብቻ ያዩ ዘንድ የዕውቀትን የማስተዋልን ዐይኖች ስጠን’ እያሉ ስለራሳቸውም ስለ እኛም ይጸልያሉ፡፡እኛም ልጆቻችሁ ዛሬ ሌላ መልእክት የለንም፡፡ እንደምትጸልዩልን እንደምትለምኑልን ልክ እንደዚያው የሌሎችን ቃል ትታችሁ የጌታችንን ቃል ሰምታችሁ አስታውሳችሁ አንድ ሁኑልን ብቻ ነው የምንለው፡፡የእርሱን ቃል ደግሞ ልትዘነጉት አትችሉም፡፡የጌታችን ቃሉ ደግሞ ትናንት በተፈጠረው በታሪኩ ላይ እንድንነታረክና እንድንከራከር አይፈቅድልንም፡፡ ይልቁንም “ወንድምህን እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት ይቅር በለው” እያለ የትላንቱን እንድንተወው ግዴታ ይጥልብናል እንጂ፡፡ እራሱም ጌታችን አስቀድሞ ሰይጣን ይህን ሊያደርገው ደጋግሞ የሚሞክረው መሆኑን “ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና” (ሉቃ 22 ፥31-32)ሲል እንደገለጸልን ይህ የመለያየት ነገር የሰይጣን ነው፡፡ በመከራ ጊዜ ደግሞ እንደተጻፈው ብዙ ሰው ይፈተናል፡፡ በወቅቱ የድርጊቱ ተሳታፊዎች ባለመሆናችን የምንተቸው ሰዎች ሁሉ በቦታውና በጊዜው ብንኖር ኖሮ ከዚህ የከፋ ልናደርግ እንደምንችል ገምቶ ራስንም በእነርሱ አስገብቶ ይቅር ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ እነ እገሌ ናቸው ተጠያቂ በሚል መንገድ መተቸት ነገሩን ከማባባስ ያለፈ የሚፈጥረው ፋይዳ የለም፡፡ በርግጥም እንዲህ ያለው ልዩነት ምእመናን በክርስትናቸው የሚበጠሩበት ነው፡፡ ጌታችን ግን በአንጻረ ቅዱስ ጴጥሮስ “እምነትህ እንዳይጠፋ አማለድሁ” ብሎ በሥጋዌው ቤዛ ሆኖ ያቀረበልንን የጸሎት መሥዋዕት ምልጃ ብሎ በመጥራት ነግሮናል፡፡ ይኸውም “ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው”(ዮሐ17፥11) የሚለው ነው። ስለዚህ በቅዳሴያችን ላይ ጆሮቻችን የአንተን ቃል ብቻ ይሰሙ ዘንድ ካላችሁ አይቀር ቃሉ አንድ ይሁኑ የሚል ስለሆነ አንድ ትሆኑልን ዘንድ በታላቅ ትሕትና እንጠይቃለን፡፡
በርግጥም ልንሰማውና ልንከተለው የሚገባን የእርሱ ቃል ብቻ መሆን አለበት፡፡ በቤተ መቅደስ በቅዳሴ ጊዜ “ባርክ ላዕለ አባግዐ መርኤትከ፤ ወአብዝኀ ለዛቲ አጸደ ወይን እንተ ተከልካ በየማንከ ቅዱስ” እያላችሁ ምእመናንን ለማብዛትና ለመጠበቅ ፈቃዳችሁ ጸሎታችሁ መሆናችሁን ሁልጊዜ ትገልጻላችሁ፡፡”ባርኮ ለዘንቱ ኅብስት … ወሚጦ ለዝንቱ ጽዋዕ … ” እያላችሁ ቅዱስ ምስጢርን እንዲፈጸምላችሁ ትማጸኑታላችሁ፡፡ ያለ እርሱ ሊሆን ሊፈጸም የሚችል አይደለምና፡፡ ታዲያ ለምሥጢራት የምንጠራውን ጌታ ምሥጢራቱን ለሚፈጽሙት አበው አለመግባባት እንዴት ልንዘነጋው እንችላለን? በዚያ ጊዜ ብቻ ይህን አድርግ ብለን ለምነነው ይህን ጉዳይ ግን ብቻችንን ወይም ደግሞ ፖለቲከኞችንና ሌሎች የልዩነት ተጠቃሚዎችን ይዘን እንፈታዋለን ልንልምአንችልም፡፡እንግዲያው ጆሮዎቻችን እንደምንጸልየው የእርሱን ቃል ብቻ የሚሰሙበት፤ዐይኖቻችንም እንደ ምልጃ ጸሎታችን እርሱንም ብቻ ሊያዩበት እና ሌሎች ጊዜያዊ ነገሮችንና ፐሮፓጋንዳዎችን ቸል ሊሉበት የሚገባው እውነተኛው ጊዜ ዛሬ መሆን አለበት፡፡ ለወጡት ሚጠት (መመለስ)፣ለባዘኑት ዕረፍት፣ ለሚጨነቁት መረጋጋት፣ በግጭትና በዕልህም ውስጥ ላሉት ሰላምና አንድነት፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት እና ለምእመናን ኅብረት ይሆን ዘንድ በእውነት ሌሎችንን ተጽእኖዎች ሁሉ ተቋቁመን መገኘት ይገባናል፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆንን ግን”በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ”(ሐዋ፳ ፥፳፰) በሚለው ቃለ ሐዋርያ መወቀሳችን የማይቀር ይሆናል።
አድኅን እግዚኦ ዛተኒ ሀገረ
የአባቶች አንድነት ለሀገር አንድነትና ሰላም ያለውም አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ የማይጠረጠር ነው፡፡የጥላቻ፣ የወቀሳና የከሰሳ ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያውያን ልብ ዘልቆ ከገባበት ከላፉት ስድሳ ዓመታት ወዲህ ጥላቻና መለያየት፤መሰዳደብና መወጋገዝ፣ በቀልና ግድያ፣ ተንኮልና ሴራ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡ ብሔራዊ መግባባት በተወሰነ ደረጃ በሚቀነቀንበት በአሁኑ ሰዓት እንኳ በሰላም አልባሳት የተደበቁ የበቀል ድምፆች ከአንዳንዶች የሚሰሙ መሆኑን ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ታዲያ እንደዚህ ባለጊዜ ዐለምን በሙሉ ወደ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማቅረብ አደራውን ለተቀበሉ አባቶች ሓላፊነቱ ግልጽ ነው፡፡ ” … ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላመከ ኀበነ ወአጽንዕ ለነ ሰላመከ” ብለን በየቅዳሴያችን እየለመንነው ሰላም አጣን ብንል ሁሉም ይታዘበናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ካልገፋናት በስተቀር የእርሱን ሰላም ከእኛ ማንም ሊወስዳት አይችልምና፡፡
ይልቁንም እኛ ፍጹም ሰላም ሆነን ሀገራችንም ከየትኛውም ችግር እንድትወጣ በእውነት መጣር ይኖርብናል፡፡ በዐርብ የሊጦን ጸሎታችን “አድኅን እግዚኦ ዛተኒ ሀገረ ወካልኣተኒ አኅጉረ ወበሐውርተ እለ በሃይማኖተ ዚአከ የኀድሩ” ‘አቤቱ ይህች ሀገር እና አንተን በማመን የሚኖሩ ያሉባቸውን በዐለም ላይ ያሉ ሌሎችን ሀገሮችም ሁሉ አድን’ እያልን የምንማልድ ሰዎች በእኛ ልዩነት ምክንያት ሕዝበ ክርስቲያኑን ለያይተን፣በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ አስገብተን ፣ በአንድ ቤት ሳይቀር ባልና ሚስት፤ ታላቅና ታናሽ ተለያይተው ጸሎቱ ምልጃው እንዴት ስሙር ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በልዩነቱ ምክንያት ሰብሳቢ አጥተው ባዝነው ከመንጋው እየተለዩ ወደሌሎቹ በረቶች ምንያህል ነፍሳት እንደሔዱ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እንኳን ከምእመናን መምህራንና አገልጋይ ከሚባሉት አንኳ ምን ያህሉ በነፍስ ተጨነቁ፤ ስንቶቹስ ባዘኑ፡፡ ስለዚህም ጸሎታችንን በተግባር እንግለጠው፡፡ያ ካልሆነ አቤቱ ሀገራችን አድን ስንለው ልዩነቱንና መለያየቱን እናንተ በተግባር አገዛችሁት እንጂ መች ተጸየፋችሁት የሚያስበለን ይመስላል፡፡ ስለዚህም ስለሀገራችንም፣ ስለሕዝበ ክርስቲያንም አንድነት ስንል አንድነቱን ያለ ቅድመ ሁኔታ በይቅርታ እና በዕርቅ ልንዘጋው ይገባናል፡፡ በዘመናችን የሀገራችን ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ፖለቲከኞች ለሚሔዱበት የዕርቅና የሰላም ጉዞ አርአያ መሆን እንኳ ባይቻለን ፍኖተ ሣህሉን ለመከተል እንኳ ካልቻልን ጌታችን አይሁድን በዚህ ትውልድ ንግሥተ አዜብ ትፈርድበታለች እንዳለ በእኛም ላይ በመጨረሻው ዘመን የሚያስፈርድብን በእኛው ፖለቲከኞች መሆኑ የማይጠረጠር ነው፡፡ እነርሱ ከእኛ በብዙ መንገድ ተሽለው ተገኝተዋልና፡፡
በኵሉ ልብ ናስተብቊዖ ለእግዚአብሔር አምላክነ
ይህ ይሆን ይፈጸም ዘንድ ጸሎት እንደሚደርግ የታመነ ነው፡፡ይልቁንም አሁን ደግሞ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት”አመንኩ በዘነበብኩ”‘በተናገርሁት(በጸለይኩት) አመንኩ’ የአመንኩትንም ጸለይኩ፤ መሰከርኩ (መዝ115፥1)እንዳለው የምንጸልየውን የበለጠ አስተውሎ መፈጸም ሳይጠይቅ አይቀርም፡፡ይህን የምናስታውሰው አይደረግም ለማለት ሳይሆን አሁንም በምንቀድሰው ቅዳሴ ዲያቆኑ አስቀድሞ “ያማረ በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጸም አንድነትን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችን በፍጹም ልብ እንለምነው” ሲል የታወቀውን በአዋጅ እንደሚያነቃን እንደሚያስታውሰው ያለ የልጅነት ማስታወሻ ብቻ ነው፡፡ እናንተም “ኀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ” ‘የአንተ በሆነ መንፈስ ቅዱስ አንድ መሆንን ስጠን’ የምትሉትን በተግባር ማየት የማይመኝ የለም፡፡ይልቁንም በዐርብ ሊጦን ጸሎታችን “ሀበነ ከመ በአሐዱ ልብ ወበአሐዱ አፍ ንሰብሕ ለአብ ወወልድ መንፈስ ቅዱስ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም” ስትሉ እንደምትማልዱት በአንድ ልብ እና በአንድ አፍ በአንድ መቅደስና በአንድ ቅዳሴ አንድ ላይ ሆናችሁ ለፈጣሪ ምስጋና ስታቀርቡ ለማየት አብዝተን የምንመኝና የምንጸልይ እርሱንም “በፍጹም ልብ”ይሁን የምንል መሆናችንን ለሁላችሁም በታላቅ ትሕትና እናቀርባለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፤ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቊጥር 2፤ሰኔ2010 ዓ.ም