“ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” (ዮሐ.፲፫፥፴፬)
ግንቦት ፫፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
መውደድ በሰዎች መካከል የሚኖር ስሜት ነው፤ ያለ መዋደድም በዚህ ምድር ላይ መኖር አይቻለንም፤ መጠኑ ይብዛም ይነስ በሰው ልብ ውስጥ የመዋደድ ስሜት ይፈጠራል፡፡ ሰዎች ተቻችለንና ተሳስብን እንዲሁም ተዛዝነን የምንኖረው ስንዋደድ ነው፡፡ ግን ይህ ስሜት ከምንም ተነሥቶ በውስጣችን ሊፈጠር አይችልምና መውደድ መነሻው ምንድነው? የሚለውን ነገር ብንመረምር መልካም ነው፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረ በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት” ብሎ ባዘዘው መሠረት የሰው ዘር የአብሮነትን ኑሮ ይኖር ዘንድ የፈጣሪው መልካም ፈቃድ ነው፡፡ (ዘፍ.፱፥፪) ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ነው፡፡ (ገላ.፭፥፲፬) ሰው ባልንጀራውን እንደ ራሱ እንዲወድ ሲታዘዝ በምን መልኩ ይህን የእግዚአብሔር ቃል መተግበር እንደሚችል ማሰቡ አይቀሬ ነው፤ ስለዚህም ትርጉሙን አስቀድሞ ማወቁ ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ ያገኘዋል ማለት ነው፡፡ መውደድ ወይም ፍቅር የሚገለጸው በአርአያና በአምሳል ለሚመስለን ሰውን ከልባችን ማሰብ፣ ማዘን፣ መታገሥ እንዲሁም ለራሳችን ያደረግነውን ማንኛውም በጎ ነገር ለባልንጀራችን ማድረግ ነው፡፡ ደስታንም ሆነ ኀዘንን መካፈል ደግሞ ከሁሉ የሚቀድም ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም ሰውን እንደራሳችን የምንወድ ከሆነ ችግሩ ችግራችን ደስታው ደስታችን ይሆናልና ኀዘኔታችንም ይሁን ደስታችን ከልብ የመነጨ ይሆናል፡፡
በዚህ የአብሮነትና የአንድነት ኑሮ ውስጥም ሰብአዊነታችን የሚገለጽ በመሆኑ የአምላካችንን ቅዱስ ቃልን በመተግበር በክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ጸንተን እስከመጨረሻ እንጓዛለን፡፡ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” እንዲል (ዮሐ.፲፫፥፴፬-፴፭) መከራና ችግር እንኳን ቢፈራረቅብንም እርስ በርሳችን በመተጋዝ ሁሉ ነገር በኅብረት ይታለፋል፡፡
ዓለማችን መላ ቅጧ ጠፍቶ ባለችበት በዚህ ጊዜ በቤተ ሰባችን፣ በማኅበረሰባችን እንዲሁም በሀገራችን በየጊዜው የሚከሰቱት ችግሮች የተፈጠሩት ሰው ለሰው ፍቅር አጥቶ አብሮ መኖር ስላዳገተው ነው፡፡ ከመዋደድ ይልቅ በጥላቻ መንፈስ መኖራችን እንዲሁም ከሰዎች ጋር የምንኖረው ሕይወት የይምሰል በመሆኑ ለረጅም ዓመታት የተጓዝንበት የጥፋት ጎዳና አዘቅት ውስጥ ከቶናል፡፡ ከቤተ ሰቦቻችን፣ ከዘመዶቻችን፣ ከባልንጀሮቻችን እንዲሁም ከመምህራኖቻችን ጋር ተስማምተን መኖርም አቅቶናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ከራሳችን ጋርም መስማማት አቅቶን፣ ኅሊናችን ሸጠን፣ እውነትን ክደንና በከንቱ ሐሳብ እየዋዠቅን መኖር ከጀመርንና ውስጣችን ሰላም ካጣ ብዙ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ማናችንም ቢሆን ይህ ጊዜ የማይሰጠውና በፍጥነት ሊፈታ የሚገባ ችግር መሆኑን ማሰብም ሆነ አምኖ መቀበል የምንፈልግ አይመስልም፡፡ የዕለት ጉርሻችንን ሟሟላትና ነገሮችን እንዳመጣጣቸው መቀበልንም ልምድ አደረግነው፡፡ በዚህ ከንቱ ሕይወት ውስጥ ያጣነው የእግዚአብሔር ውድ ስጦታ መኖሩን ማወቅም ሆነ ማስተዋል ተስኖን በዘፈቀደ መኖራችን ለከፍተኛ ጥፋት ስለዳረገን በአሁን ጊዜ ልንፈታቸው የማንችላቸው ችግሮቻችን በዝተዋል፡፡
እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዙፋኑ ወርዶ ለሰው ልጅ ሲል በመልዕልተ መስቀል ላይ እንዲሰቀል ያደረገው ፍቅር በመሆኑ “እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” ሲል አስተማረን፤ ምክንያቱም ያለ ፍቅር ሰዎች መኖር አይቻለንም፡፡ ፍቅር ለሚወዱት መከራና ሥቃይ መበቀል እንደሆነም ጌታችን አስተምሮናልና ለሰዎች ስንል መቸገር፣ ማዘንና ማሰብ ይገባል እንጂ ነገ ለሚጠፋ ሀብትና ለሚሻር ሥልጣን ስንል በሰዎች ላይ ክፋት ማድረግ፣ ኑሮአቸውን ማቃወስ፣ ማሳደድ፣ ማራቆት እንዲሁም መግደል ግፍና በደል ነው፡፡
አብዛኞው የዚህ ዘመን ትውልድ ሰው ከፍቅር ይልቅ ጥቅምን፣ ከዕውቀት የበለጠ ገንዘብን እንዲሁም የሥጋን ድሎት የሚወድ በመሆኑ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለማፍረስና ሕጉን ለመተላለፍ ተዳርጓል፡፡ ኃጢአታችንም ስለበዛ ቁጣው በእኛ ላይ በረታና በሽታው፣ ረኃቡ፣ ጦርነቱ እንዲሁም ማኅበራዊ ቀውሱ በሀገራችን ብቻም ሳይሆን በዓለም ደረጃ ተበራከተ፡፡ አንዱ ችግር በሌላው እየተተካና እየተደራረበ በመብዛቱም የቱን አስበንና ተወጥተን እንደምንችል ግራ እስክንጋባ ድረስ ጭንቀት ውስጥ ገብተናል፡፡ በድፍረትና በሥጋዊ ሐሳብ የጀመርነው የተሳሳተ ኑሮ የማንወጣበት ውስብስብና የተደራረበ ችግር ውስጥ ሲከተንና መፍትሔም ስናጣ ግን ወደ እግዚአብሔር መጮህ ጀመርን፡፡ ይህ ቢሆን እንኳን ቢያንስ ለሠራነው ኃጢአት ይቅርታና ምሕረት መለመን እንጂ እርሱን ማማረር ተገቢ አልነበርም፡፡ ምክንያቱም ችግሩን የፈጠርነው ራሳችን በመሆናችን መፍትሔውም ከራሳችን የሚመጣ ነው፡፡
ሰው ከሕገ እግዚአብሔር የወጣ ከሆነና ሕጉን ከተላለፈ የሚኖረው ኑሮ ከንቱ እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን እንደተናገረው “ከንቱ፣ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ፤ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፡፡” (መክ.፩፥፪) የዚህ ዓለም ነገር አሳሳችና እጅግ ፈታኝ ቢሆንም ግን ሥጋዊ ምኞታችንን አሸንፈን፣ ለነፍሳችን ትኩረት ሰጥተንና የነፍስን ሥራ መሥራት ይገባል እንጂ ለሥጋ መሸነፍ የሞት ሞትን ያስከትላል፡፡ የኋላ ኋላ መዘዙ ብዙ ቅጣቱም ከባድ ነውና፡፡ በሕገ እግዚአብሔር እንድንኖር የተገባን በመሆናችንም “ፍቅር የሕግ መፈጸሚያ ነው” እንደተባለውም በአምሳልና በሰብእና ከሚመስለን ፍጥረት ሁሉ ጋር ተዋደድን መኖር ያስፈልጋል፡፡ (ሮሜ ፲፫፥፲)
አምላካችን እግዚአብሔር በፍቅር እንድንኖር ይርዳን፤ አሜን!