ታቦት

ትምህርት ሃይማኖት (የሃይማኖት ትምህርት) በሁለት ይከፈላል፡፡ ይኸውም፦
1ኛ፡- ዶግማ   2ኛ፡- ቀኖና በሚል ነው፡፡
ዶግማ፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ፍችውም እምነት ማለት ነው፡፡

ቀኖና፡- ደግሞ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ ከሁለቱ ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፤ አይቀነስበትም፤ አይሻሻልም፤ ችግርና ፈተናም ቢመጣ እስከ ሞት ድረስ አጥብቀን የምንይዘው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ፤ ቢመረምር እንጂ የማይመረመር ሁሉን ቻይ አምላክ፤ የሚሳነው ነገር የሌለ ፈጣሪ፤ የሰማይና የምድር ባለቤት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔር ነው፡፡

እግዚአብሔር (ፈጣሪ) የአካል ሦስትነት አለው፡፡ በመለኮት፣ በመፍጠር፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ ግን አንድ ነው፡፡ በሦስትነቱ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ ሲባል በአንድነቱ አንድ መለኮት አንድ እግዚአብሔር ይባላል፡፡ በአዳም ምክንያት ከመጣው የዘለዓለም ሞትና ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣነው ከሦስቱ አካላት በአንደኛው አካል ማለትም በወልድ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህ ዶግማ ወይም እምነት ይባላል፡፡

ቀኖና ግን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ያደጉ ክርስቲያኖች የሚመሩበት ሥርዓት ስለሆነ፤ በሃይማኖት አባቶች ወይም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት እንደጊዜው ሁኔታ የሚሻሻል በመሆኑ የሚጨመርበት፤ የሚቀነስለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል እኛ ኦርቶዶክሳውያን የምንጠመቀው ሴት በሰማንያ ወንድ በአርባ ቀናችን ነው፡፡ የተወለዱ ሕጻናት ሴቷ ሰማንያ ወንዱም አርባ ቀን ሳይሞላቸው ቢታመሙና በሽታው አስጊ ከሆነ በ10፣ በ20፣ በ30…ቀናቸው መጠመቅ ይችላሉ ቀኖና ነውና፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የቀዳስያን ብዛት መነሻው አምስት ነው፡፡ ምናልባት ከአምስቱ አንዱ፤ ሁለቱ፤ ሦስቱ ቢታጡና ሌላም ተፈልጎ እስከ መጨረሻ የማይገኝ ከሆነ ከአቅም በላይም የሆነ ችግር ከገጠመ ሁለቱ ወይም አንዱ ብቻ ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ፡፡ ቀኖና ነውና፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ታቦት ሲከብር ቤተ ክርስቲያኑን የሚዞረው ሦስት ጊዜ ነው ችግር ካለ አንድ ጊዜ ብቻ ዑደት ተፈጽሞ ሊገባ ይችላል። ቀኖና ነውና፤ ስለቀኖና (ስለሥርዐት) ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ ሲል ጽፏል።

1. ‹‹ነገር ግን ሁሉን በአግባብና በሥርዐት አድርጉ፡፡›› 1ኛ ቆሮ. 14፥40፡፡
2. ‹‹ወንድሞች ሆይ በሠራንላቸው ሥርዐት ሳይሆን በተንኮል ከሚሄዱት ወንድሞች ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዝዛችኋለን፡፡ እኛን ልትመስሉ እንደሚገባችሁ እኛም በእናንተ መካከል ያለ ሥራ እንዳልኖርን ራሳችሁ ታውቃላችሁ›› 2ኛተሰ. 3፥6-7›› ቀኖና (ሥርዐት) የሚወሰነው በሃይማኖት አባቶች እንደሆነና ወንጌልን የሚስተምር ሰው ለሚያስተምራቸው ክርስቲያኖች በሃይማኖት አባቶች የተወሰነ ቀኖና ማስተማርና መሰጠት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስረዳል፡፡

በየከተማውም ሲሄዱ፥ ሐዋርያትና ቀሳውስት በኢየሩሳሌም ያዘዙትን /የወሰኑትን/ ሥርዐት አስተማሯቸው፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ጸኑ ዕለት ዕለትም ቁጥራቸው ይበዛ ነበር፡፡›› ይላል የሐዋ. 16፥4-5፡፡ በዚህ የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ቅዱስ ጳውሎስ ደርቤንና ልስጥራን በተባሉ ቦታዎች ለነበሩ ክርስቲያኖች ወንጌልን ከሰበከ በኋላ ሐዋርያት የወሰኑትን ቀኖና (ሥርዐት) እነደሰጣቸው እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ቀኖና ወይም ሥርዐት ቤተክርስቲያንን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡ በመሆኑም ዶግማንና ቀኖናን ወይም እምነትንና ሥርዓትን ጎን ለጎን ይዞ መጓዝ ሐዋርያትን መከተል እንጂ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሁድን መከተል አይደለም፡፡ እንግዲህ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የሚቃወሙ ሰዎች ሁሉ፤ የሚቃወሙት በቀኖና (በሥርዐት) የሚመሩትን ክርስቲያኖች ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል የሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በመሆኑ እንዳይሳሳቱ አደራ እንላለን፡፡

አሁን እንግዲህ የዶግማንና የቀኖናን ልዩነት ከተረዳን በቀጥታ ወደ ታቦቱ ጥያቄ እንሄዳለን፡፡

ጥያቄ፡-1 ዛሬ በእኛ ቤተክርስቲያን ያለው ታቦት ነው? ወይስ ጽላት በታቦትና በጽላት መካከል ልዩነት አለና፡፡

መልስ፡- ታቦት የጽላት ማደሪያ ነው፡፡ ዘዳ 40፥20፡፡ ጽላት ደግሞ ቅዱስ ቃሉ የተጻፈበት ሰሌዳ ማለት ነው፡፡ ዘዳ 34፥27-28፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ነገሮች ዛሬም በሐዲስ ኪዳን አሉ። ሆኖም ግን አሠራሩ ሙሉ በሙሉ በዘጸ 25፥10-18 ያለውን የሙሴን ሕግ የተከተለ አይደለም፡፡ ምክንያቱም፤

1ኛ፡- ታቦት እንደሙሴ ሕግ የሚዘጋጀው ከግራር እንጨት ሆኖ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ቁመቱም አንድ ተኩል ይሁን ይልና በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት ይላል፡፡ ደግሞም ታቦቱን የሚሸከሙት ከወርቅ በተሠሩ መሎጊያዎች አራት ሰዎች እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ በአጠቃላይ የብሉይ ኪዳን የታቦት አሠራር እጅግ ከባድ በመሆኑ በሁሉም ዘንድ አይቻልም ነበር፡፡ ምናልባት አንዳንድ የቤተክርስቲያን ፍቅር የነበራቸው ነገሥታትና ዛሬም ፍቅረ ቤተክርስቲያን ያላቸው አንዳንድ ምዕመናን ይችሉት እንደሆነ ነው እንጂ፡፡

2ኛ፡- ጽላት፤ ጽላትም እንደሙሴ ሕግ ከሆነ መዘጋጀትና መጠረብ ያለበት ከከበረ ድንጋይ ነው፡፡ በአንድ ታቦት ውስጥም መቀመጥ ያለባቸው ሁለት ጽላቶች ናቸው፡፡ ዘዳ 34፥1፡፡ በአጠቃላይ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ሕግና ሥርዐት ከባድ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳኑ ሥርዐትም ለሐዲስ ኪዳኑ ሥርዓት ጥላ ሆኖ አልፏል፡፡ 2ኛ ቆሮ 3፥7-11 ፤ ቆላ 2፥17፤ ዕብ 10፥1፡፡

እንግዲህ እዚህ ላይ የሐዲስ ኪዳኑ ታቦትና ጽላት የብሉይ ኪዳኑን የታቦት አሰራርና ሥርዐት ጠንቅቆና ተከትሎ የማይሄድ ከሆነ፤ ይህ የብሉይ ኪዳኑን የታቦትና የጽላት አቀራረጽ ሥርዐት ጠንቅቆ ያልሄደ የሐዲስ ኪዳን ታቦትና ጽላት ከየት መጣ የሚል ጥያቄም ሳይነሳ አይቀርም፡፡

አንባብያን ሆይ በቀጥታ ወደ ጥያቄው ከመግባታችን በፊት በዚህ ጽሑፍ ዶግማ ላይ ስለዶግማና ቀኖና ማብራሪያ የሰጠነው ይህን ለመሰለው ጥያቄ እንዲጠቅም ነው፡፡ አሁን ወደ ሐዲስ ኪዳን ታቦትና ጽላት ስንሄድ ቁም ነገሩ እንደሚከተለው ነው፡፡

የሐዲስ ኪዳን የታቦትና የጽላት አቀራረጽም ሆነ አጠቃቀሙ የተወሰነውና የሚወሰነው በቀኖና ነው፡፡ ቀኖና ደግሞ እንደ ሁኔታው የሚሻሻል ነው፡፡ ሲቻል ይጨመርበታል ሳይቻል ደግሞ ይቀነስለታል፡፡ እንግዲህ በቤተክርስቲያናችን ቀኖና ካበረከታቸው ነገሮች አንዱ የሐዲስ ኪዳን የታቦትና የጽላት አቀራረጽንና አጠቃቀምን ነው፡፡

ስለዚህ በሐዲስ ኪዳን ታቦትን ለመቅረጽ የግራር እንጨት ባይገኝ በዘፍ 1፥31 ላይ ‹‹ እግዚአብሔርም የፈጠረውን (ያደረገውን) ሁሉ እጅግ መልካም እንደሆነ አየ›› ስለሚልና እግዚአብሔር የፈጠረውን ስለማይንቅ ከግራር ሌላ ከማይነቅዝ እንጨት መቅረጽ እንችላለን፡፡ ቁመቱ ወርዱና ዙሪያውም እንደችሎታችን ይሆናል፡፡ በውስጥና በውጭ ስለሚሆነው የወርቅ ክብርም እንደችሎታችን ይወሰናል፡፡ ከሌለንም ወርቁ ይቀራል ቀኖና ነውና፡፡

ስለጽላቱም እንደዚሁ ነው ከቻልን ከከበረ ድንጋይ፣ ከዕብነ በረድ መቅረጽ እንችላለን፤ ካልቻልን ጽላቱን ከማይነቅዝ እንጨት መቅረጽ እንችላለን፡፡ በሌላ በኩልም ከቻልን እንደ ብሉይ ኪዳኑ በአንድ ታቦት ሁለት ጽላት ማስቀመጥ እንችላለን፤ ካልቻን በአንድ ታቦት አንድ ጽላት ብቻ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የጽላቱን ማስቀመጫ ታቦት ባይኖረን ጽላቱን ታቦት ብለን በመጥራት በጽላቱ ብቻ መጠቀም እችላለን ቀኖና ነውና፡፡

በተጨማሪም በኤር 31፥31፤ 2ኛ ቆሮ 3፥1-3፤ በዕብ 8፥8-13፡፡ የእኛ አካልና ልቡና የእርሱ ታቦትና ጽላት አልሆነም ወይ? በሐዲስ ኪዳን ለምን ታቦትና ጽላት አስፈለገ? ለምንስ ይህ ሁሉ ተፈጠረ የሚሉ አሉ፡፡ የክርስቲያኖች  አካልና ልቡና በክርስቶስ ደም ታቦት፤ ጽላት፤ ቤተ መቅደስ መሆኑን እናምናለን፡፡ ቢሆንም በሐዲስ ኪዳን ታቦትና ጽላት ያስፈለገበት ምክንያት ስለአምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና ክብር ሲባል ነው፡፡ ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ክብሩን የገለጠበት፤ ቃሉን ያሰማበት፣ ሙሴን እንደባልጀራ ያነጋገረበት፣ የክብሩ ዙፋን ሆኖ ጽላቱ በውስጡ ለታቦቱ ማደሪያ በመሆኑ፤ በሐዲስ ኪዳንም የሥጋውና የደሙ የክብር ዙፋን እንዲሆን ሲሆን ስለእኛ በዚህ ዓለም መከራ የተቀበለውን መድኅኔዓለም ክርስቶስን ለማክበር ሲባል ነው፡፡

ጥያቄ2፡- በዘዳ 31፣18፣32፣15፣134፣1-5፡፡2ኛዜና 5፣10 ያሉትን ጥቅሶች በመጥቀስ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ሁለት ጽላቶችን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እነዚህን እልፍ አእላፋት ጽላቶች ከየት አመጣቻቸው? አራብታችሁ ቅረጹ የሚል አለ ወይ?

መልስ፡- በዘዳ 32፥19፡፡ ስንመለከት እግዚአብሔር ራሱ አዘጋጅቶ ለሙሴ የሰጠውን ሁለቱን ጽላቶች እሥራኤል ጣዖት ሲያመልኩ ስላገኛቸው ሙሴ ተበሳጭቶ ሰብሯቸዋል፡፡ነገር ግን ቸርነቱ ለዘለዓለም የሆነ እግዚአብሔር አምላክ  ለሙሴ የመጀመሪያዎቹን አስመስሎ እንዲሰራ ነገረው፤ ሙሴም አስመስሎ ሠራ፡፡ ዘዳ 34፥1-5 መሥራት ብቻ ሳይሆን ዐሥሩን የቃል ኪዳን ቃላትም በጽላቶቹ ላይ እንዲጽፍ ሙሉ ሥልጣን ከእግዚአብሔር ተሰጠው፡፡ ሙሴም ተፈቅዶለታልና አሥሩን ቃላት በጽላቶቹ ላይ ጻፈ፡፡ ዘዳ 34፥27-28 ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጽላትንም ሆነ ታቦትን እያስመሰሉ ለመሥራት ሙሉ ሥልጣንን አግኝተናል፡፡ ይህን በተመለከተ አንዳንድ አባቶች እንዲህ ይላሉ፤

‹‹አዳም እንኳን በደለ አዳም ባይበድል ኖሮ አምላክ ሰው ሆኖ በቀራንዮ ስለእኛ የመሰቀሉን፤ ስለኛ የመሞቱን የፍቅር ምስጢር አናውቀውም ነበር፡፡››

እስራኤልም በጥጃ ምስል ጣኦት አምልከው እንኳን በደሉ እሥራኤል ባይበድሉ ሙሴ በእግዚአብሔር የተዘጋጁት ሁለቱ ጽላቶች’ የሰው ልጅም እግዚአብሔር የሠራቸውን የፊተኞቹን አስመስሎ ለመሥራት ስልጣን ባልኖረውም ቢሠራም ለምን ሠራህ ለሚለው መረጃ ባላቀረበም ነበር›› ይላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ጽላትን አስመስለን፤ አባዝተን፤ አራብተን ለመሥራት መሠረታችን ሥልጣኑ ለኛ ለልጆቹ የተላለፈልን ከአባታችን ከሙሴ ነው፡፡››

ሙሴ የተሰበሩትን አስመስለህ ሁለት ጽላቶች ቅረጽ ከሚል በቀር ጽላቶችን አብዝታችሁ፤ አራብታችሁ ተጠቀሙ የሚል ቀጥተኛ ቃል አምጡ ለሚለው ግን ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የጽላትም ሆነ የቤተ መቅደስ ሥርዐት፤ የመስዋዕቱ የዕጣኑ አገልግሎት፤ በኢየሩሳሌም ብቻ ስለነበረና፤ የሌላውም አገር ሕዝብ የሚከተለው የጣዖትን ሥርዓት እንጂ የሙሴን ሥርዐት ባለመሆኑ ጽላቱ ተባዝቶ ተራብቶ ለሌላው አገር ሕዝብ አልተሰጠም፡፡ እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ውጭ አልፈቀደም የተቀደሰውን ጣዖታውያኑ አሕዛብ ያረክሱታልና ስለዚህ ስግደቱም የቤተመቅደስ ሥርዐቱም በኢየሩሰሳሌም ብቻ ነበር። /ዮሐ 4፥18-24/

በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ አሕዝቦችም ሠሎሞን ያሠራው ታላቁ ቤተ መቅደስና ሁለቱ ጽላቶች አንሰውናል፤ በርቀት የምንገኝ እኛ የመንገድ ድካም በዝቶብናልና፡፡ ስለዚህ በያለንበት ቤተ መቅደስ ሠርተን ጽላቱን አክብረን መገልገል እንፈልጋለንና ይፈቀድልን ብለው ሙሴም ከሁለቱ ጽላቶች በቀር ሌላ አልተፈቀደም ብሎ መልስ የሰጠበት ቦታ የለም፡፡

ያም ሆነ ይህ በሐዲስ ኪዳንም በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በአብ፤ በወልድ፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀው ፤ሁለተኛ የድኅነት ልደት ተወልደው የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣን ሰጣቸው። ለክርስቲያኖችም ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ እንደሚበዙና በአዲስ ኪዳን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ንጹሕ የሆነውን ቁርባን ከኢየሩሳሌም ውጭ በየቦታው ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡፡

1. ‹‹ ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ይከበራልና፤ በየስፍራው ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፤ ንጹሕንም ቁርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር›› ሚል 1፥11፡፡
2. ‹‹ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎ የለምን? እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ አስተማራቸው›› ማር11፥17፤ ኢሳ 56 ፥ 7፤ ኤር 7፥11 ፡፡

ይህ ትንቢት በቀጥታ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሆኑ ግልጥ ነው፡፡ ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስም ሆነ የዕጣን፤ የቁርባን አገልግሎት እንኳን ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ላሉ አሕዛብ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በቀር ለእስራኤል ጎረቤት አገሮች እንኳ አልተፈቀደምና፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ንጹሕ ዕጣን ያለው በማቴ 2፥11፡፡ ወንጌል እንደተናገረው ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰብአ ሰገል በቤተልሔም ዋሻ ለክርስቶስ ካቀረቡት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም ያለን ክርስቲያኖች በክርስቶስ ስም ለክርስቶስ የምናቀርበው ቅዱስ ዕጣን ነው፡፡

ንጹሕ ቁርባን የሚለውንም በማቴ 26፥26፤ ጌታ ኅብስቱን አንሥቶ ነገ የሚቆረሰው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ወይኑንም አንሥቶ ነገ ስለብዙዎች ሀጢአት የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው ብሎ ለሐዋርያት የሰጣቸው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፡፡ ንጹሕ የተባለው እርሱ በባሕርዩ ንጹሕ ሆኖ የእኛን የኃጢአት እድፍ ስለሚያነጻ ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን በኢየሩሳሌም ብቻ መሆን የሚገባቸው ቤተ መቅደሱ፤ ዕጣኑ፣ ቁርባኑ፣ በክርስቶስ ደም በአዲስ ሕይወት፣ በአዲስ ተፈጥሮ፤ በአዲስ ሥርዓት፣ ክርስቲያኖች ለሆንን ለዓለም ሕዝቦች በየሥፍራው (በያለንበት) እንድንጠቀምባቸው ከተፈቀዱልን በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት ሁለቱ ጽላቶች ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ተባዝተው በዓለም ያለን ክርስቲያኖች በያለንበት በየቤተ መቅደሳችን ለሥጋውና ለደሙ የክብር ዙፋንነት ብንገለገልባቸውና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ብናከብርባቸው ምን የሚጎዳ ነገር ተገኘ? የሚያስደነግጠውስ ምኑ ነው? ስህተቱስ የቱ ላይ ነው?
   
እንዲሁም ዐሠርቱ ትእዛዛት የተጻፉባቸው ሁለቱ ጽላቶች መባዛት መራባት የለባቸውም ከተባለ በጽላቶቹ ላይ የተጻፉት ዐሠርቱ ትእዛዛት መባዛት የለባቸውም፡፡ ከኢየሩሳሌምም መውጣት የለባቸውም ማለት አይደለም? ትእዛዛቱም ተከለከሉ ማለት ነውና፡፡

በጽላቶች ላይ የተጻፉት ትእዛዛት በእግዚአብሔር ፈቃድ በፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ በሚገኙ ክርስቲያኖች እጅ ገብተዋል፡፡ ይህም ያስደስታል እንጂ አያሳዝንም፡፡ ይህ ከሆነ ለሥጋውና ለደሙ (ለክርስቶስ) ክብር ሲባል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ጽላቶች ምን በደል አስከተሉ፥ እግዚአብሔር ለቀደሙ አባቶቻችን በታቦቱ አድሮ የሠራላቸውን ድንቅ ሥራ እያስታወስን እግዚአብሔርን ከማመስገን ውጭ ደግሞም ጌታ ስለ ጸሎት ሲያስተምረን ‹‹አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎት ውስጥ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን›› በሉ ብሏል፡፡ በዚህ መሠረት በዮሐንስ ራዕይ 11፥19 ላይ ታቦቱን በሰማይ አሳይቶናል፡፡ ስለዚህ የሙሴ የቃል ኪዳኑ ታቦት በሰማይ እንዲገኝ፤ በሰማይ እንዲሆን፤ በሰማይ እንዲታይ ፈቃዱ ከሆነ፤ በምድርም እንዲሆን ፈቃድህ ይሁን ብለን ብንጠቀምበት ስህተቱ ምን ይሆን?

ጥያቄ3፡- የሰሎሞን ቤተ መቅደስ እስኪሠራ ድረስ በእርግጥ ታቦቱ ከቦታ ወደ ቦታ ይዘዋወር ነበር፤ ቤተ መቅደሱ ተሠርቶ ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደሱ ከገባ በኋላ ግን ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው ስለመውጣታቸው መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም፡፡ ታዲያ ዛሬ ክርስቶስ ደሙን ካፈሰሰ በኋላ፤ በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መመሪያ ሳይኖር፤ ከየት አምጥታችሁ ነው ታቦትን በየጊዜው በማውጣት የክርስቲያኖች ህሊና ሁሉ ወደተሰቀለው ክርስቶስ መሆኑ ቀርቶ ወደ ታቦቱ የሆነው?

መልስ፡- በብሉይ ኪዳን እንኳን አይወጣም ነበር ማለት አንችልም ምክንያቱም በችግራቸው ጊዜ ለችግራቸው መፍትሔ ያገኙ ዘንድ ከነበረበት ከድንኳኑም ቢሆን ያወጡት ነበርና ለምሳሌ፦

1. በሙሴ ምትክ  የተመረጠ ኢያሱ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ወደ ምድረ ርስት ሲሄድ ድንገት የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ባገኘው ጊዜ ወንዙን ከፍሎ አሕዛብን ለማሻገር ከእግዚአብሔር በተነገረው መሠረት ካህናቱ ታቦቱን ከነበረበት ቦታ ተሸክመው ወደ ወንዙ በመሄድ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት እግር ወንዙን ሲረግጥ ወንዙ ተከፍሎ ሕዝቡ ሁሉ በሰላም መሻገራቸውን እናገኛለን፡፡ ኢያሱ 3፥1-17፡፡
 
2. እስራኤል ምድረ ርስት በደረሱ ጊዜ ምድረ ርስት (ኢያሪካ) በጠላት እጅ በጽኑዕ ግንብ ታጥራ አገኟት፡፡ በዚህም ጊዜ ይህን የጠላት የግንብ አጥር ለማፍረስና ርስታቸውን በእጃቸው ለማድረግ እግዚአብሔር የገለጠላቸው ጥበብ ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው ሕዝቡም እየተከተሉ ሰባት ጊዜ ግንቡን እንዲዞሩት ነው፡፡ የታዘዙትን አደረጉ ግንቡም ፈረሰላቸው፡፡ ኢያሱ 6፥1-17፡፡

3. እስራኤል ጠላት በበረታባቸው ጊዜ ጠላትን ለማሸነፍ ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው ይወጡ ነበር፡፡ 1ሳሙ 5፥1-ፍ፡፡ ስለዚህ በብሉይ ኪዳን ካህናቱ ታቦቱን ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ካልሆነ በቀር ለሚፈልጉት ዓላማ ታቦቱን ካለት ቦታ ተሸክመው አያወጡትም ነበር ማለት አንችልም፡፡ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ካስገባው በኋላ ቢሆንም ካህናቱ ታቦቱን ተሸክመው እንዳያወጡ የሚል ሕግም የለም፡፡ እግዚአብሔር የሠራው ሥራ በብሉይ ኪዳን የተፈጸመው አገልግሎት ሁሉ ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አልተጻፈም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ያልተጻፈ ብዙ ነገር እንዳለ እናምናለን ከዚህ በመነሳት ነው እኛ በሐዲስ ኪዳን ታቦትን ተሸክመን የምናወጣው፤

በብሉይ ኪዳን በእግዚአብሔር ቸርነት (ትእዛዝ) ካህናቱ ታቦታቱን ተሸክመው እንዲወጡ ተደርጎ ካህናቱም ታቦታቱን ተሸክመው በመውጣት በታቦቱ ያደረ ኃይለ እግዚአብሔር ለሕዝበ እስራኤል ያደረገው ድንቅ ሥራ ለማሰብና እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው፡፡ዛሬም ለሥጋና ለደሙ የክብር ዙፋን የሆነውን ቅዱስ ስሙም የተጻፈበትን ቅዱስ ታቦት በምናወጣበት ጊዜ በደሙ የባረከን መድኅነ ዓለም ክርስቶስ አሁንም የሥጋውና የደሙ ዙፋን በሆነው በታቦቱ ረቂቅ ኃይሎች በማስተላለፍ በረከቱን ያበዛልናል ብለን በማመን ነው፡፡

የተሰቀለው አምላክ መክበሩና መንገሡ ቀርቶ በየጊዜው ታቦት ወጣ እየተባለ ታቦቱ ብቻ ነገሠ ከበረ ሕዝቡም ወደ አምልኮ ባዕድ ኮበለለ ስለሚለው ግን አንድ ሕዝብ የንጉሡን ዙፋን ሲያከብርና ሲፈራ ንጉሡን ማክበሩና መፍራቱ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡

እኛ የምናምነው ቅዱስ ስሙ የተጻፈበትን የክርስቶስ ሥጋና ደም የክብር ዙፋን የሆነውን ታቦት ማክበራችን በኪሩቤል ዙፋን የሚቀመጥ መድኅነ ዓለም ክርስቶስን ማክበራችን መሆኑን ነው፡፡ በታቦቱ ፊት መስገዳችንም በታቦቱ ለተጻፈው ለቅዱስ ስሙ ነው፡፡ በታቦት ፊት ለእግዚአብሔር ስም ይሰግዱ የነበሩ ኢያሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች በረከት አገኙበት እንጂ አልተጎዱበትምና ነው፡፡ ኢያ 7፥6፣ ዘዳ 33፥10፡፡

በሐዲስ ኪዳንም ‹‹ድል ለነሣው ስውር መናን እሰጠዋለሁ፤ የብርሃን መጽሐፍንም እሰጠዋለሁ፤ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ ላይ ከተቀበለው በቀር ማንም የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎበታል›› ራእ 217፡፡ ለዚህ ስም ደግሞ ጉልበት ሁሉ መንበርከክ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤

‹‹ይህም በሰማይና በምድር በቀላያትና ከምድርም በታች ያለ ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰግድ ዘንድ ነው። አንደበትም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር አብ ክብር ጌታ እንደሆነ ያምን ዘንድ ነው›› ፊልጵ 2፥10-11፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱስ ስሙ በተጻፈበት ከነጭ ድንጋይ (ከዕምነ በረድ፣ከእንጨት) በተሠራው በጽላቱ ፊት ለቅዱስ ስሙ መስገድ ታላቅ የመንፈስ ጥበብ እንጂ ሞኝነት አይደለም፡፡ ምናልባት ስለታቦት፣ ስለጽላት ባለማወቅ ባጠቃቀሙ በኩል የሚሳሳቱ አባቶችን፤ እናቶችን ወንድሞችንና እህቶችን በተገቢው መንገድ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡

ከዚህ በላይ ስለ ታቦት ከቤተ መቅደስ መውጣትና አለመውጣት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ከመሆኑም በተጨማሪ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

ብዙዎች በሐዲስ ኪዳን ታቦትን ለመቃወም በኤር 3፥16፡፡ የተጻፈውን ጠቅሰው “በዚያ ዘመን ፦የ እስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት እነኋት እያሉም በአፋቸውም አይጠሯትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሿትም።” ተብሏልና ታቦት አያስፈልግም በማለት ያስተምራሉ፡፡

እንደተባለው ታቦት ብሎ መጥራት ካላስፈለገ በኤርምያስ 31፥34፤ ደግሞ “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፣ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን ዕወቅ ብሎ አያስተምርም” ተብሎ ስለተጻፈ እንግዲህ ሰው ሁሉ በየዘመኑ እግዚአብሔርን እንዲያውቅ ማስተማር አያስፈልግም ማለት ነዋ! ደግሞም ጌታችን በማቴ 28፥19 “እንግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ” ብሎ መናገሩ ስህተት መሆኑ ነዋ! በአጠቃላይ እንዲህ ነው ብሎ ከመናገር አስቀድሞ በመጽሐፍ የተጻፈው ነገር ለምንና እንዴት ባለ ሁኔታና ጊዜ መጻፉን ማጥናትና መልእክቱን (ምስጢሩን) መመርመር ይገባል እንላለን፡፡

በመጨረሻ ግን በኢትዮጵያ ኦርቶኮክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማርያም፣ የቅዱሳን፣የሰማዕታት፣ የመላዕክት ወዘተ…. ታቦት እየተባለ የተሰየመበት ምክንያቱና የዚህ ስያሜ ከየት ነው የመጣው ምንድን ነው የሚሉ ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እርግጥ ነው፡፡

እንዲህ ተብሎ መሠየሙ በትንቢተ ኢሳይያስ 56፥46 በተገለጸው መሠረት የእግዚአብሔርን ሰንበቱን ለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘውንም ለሚመርጡ ቃል ኪዳኑንም ለሚይዙ ጃንደረቦች (ስለእግዚአብሔር መንግሥት ራሳቸውን ጃንደረባ ያደረጉ ቅዱሳን) ማቴ 19፥12 በእግዚአብሔር ቤትና በቅጥሩ የዘለዓለም መታሰቢያ እንደሚደረግላቸው የተገለጠ በመሆኑ ይህን አብነት በማድረግ ጌታ ሥጋው፣ ደሙ የሚከብርበት ሆኖ ለቅዱሳኑም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፡፡ /መዝ 111፥7/ እንዲሁም የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነውና ምሳ 10፥7፡፡ በዚህ ምክንያት እንጂ በታቦታቱ የሚከብረው መድኃኒተ ዓለም ክርስቶስ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡

እግዚአብሔር አስተዋይ ልቡና ይስጠን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን።

/ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ሚያዝያ 1985 ዓ.ም/