‹‹ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ›› (የዘወትር ጸሎት)
ዲያቆን ታደሰ ተስፌ
ሚያዚያ፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
እግዚአብሔር ሰውን ከፍጥረት ሁሉ ለይቶ በአርአያውና በአምሳሉ ለዘለዓለማዊ ዓላማ ነባቢ አድርጎ ፈጥሮታል። (ዘፍ.፩፥፳፮) ይኸውም ዘለዓለማዊ ዓላማ እግዚአብሔርን መስሎ የጸጋ አምላክ የባሕርዩ ተካፋይ እንዲሆን በጸጋ ወደ አምላክነት እንዲያድግ አድርጎ ቢፈጥረውም የሰው ልጅ ግን ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ጉዞውን ወደ አምላክነት እግዚአብሔርን ወደ መመሰል ሳይሆን በኃጢአት ምክንያት ከደጋ የተራቆተ ሆነ። (፪ኛጴጥ.፩፥፬)
በዚህም አለመታዘዝ ወደ ባሕርይው ዘልቀው የገቡት ኃጢአት፣ ሞት፣ መበስበስ፣ ባርነት፣ ከመለኮታዊ ብርሃን መራቆት፣ ሰውን እንዲኖር ከተፈጠረበት ዓላማ ውጥቶ በባርነት መኖር ጀመረ። ምክንያቱም ህልውና ዘለዓለማዊና ሕያው ከሆነ ከእግዚአብሔር ጋር ያለ ሱታፌ ነውና። ሕያው የነበረ ሰው ሞት ነገሠበት፤ ነጻ የነበረው ሰው ወደ ድቅድቅ የባርነት ጨለማ ውስጥ ወደቀ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ የነበረ የሰው ልጅ የአጋንንት መጫወቻ ሆነ ይህን የሰው ልጅ ውድቀት ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፤ ‹‹በዚያም የምድረ በዳ አራዊት ያርፋሉ፥ ጕጕቶችም በቤቶቻቸው ይሞላሉ፤ ሰጎኖችም በዚያ ይኖራሉ፥ በዚያም አጋንንት ይዘፍናሉ።›› (ኢሳ.፲፫፥፳፩)
ይህ የሰው ልጅ ውድቀት ባሕርይው መልካም የሆነውን እግዚአብሔር አሳዝኗል፤ እርሱ ቸር፣ ምሕረትና ቸርነት ባሕርይው ነውና የሰውን ጥፋት እያየ መተው አልቻለም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን ከዚህ በአለመታዘዝ ከመጣበት ሁለትናዊ ውድቀት ያድነው ዘንድ ቀጠሮ ያዘ። በነቢያቱ በመንፈስ ቅዱስ ስለምጽአቱ፣ ስለ ሕማሙ፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ለሰው ስለሚያደርገው ዘለዓለማዊ ድኅነት አስቀድሞ ነገረን፤ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግረ፡፡›› (ዕብ.፩፥፩) ዘመኑ ሲደርስም ለቃሉ የታመነው አምላክ እንደተናገረው አደረገ፤ ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ›› እንዲል፤ (ገላ.፬፥፬) ጌታ ሰው በመሆኑም የሰውን ልጅ ከኃጢአት፣ ከሞት እና ከሰይጣን ባርነት ነጻ አወጣው።
እነዚህ ድል የተነሡትም ፍጹም እስከ መስቀል ሞት በደረሰ መታዘዝ፣ ቅዱስ በሆነ ሕማሙ፣ አዳኝ በሆነ ሞቱና፣ በትንሣኤው ኃይል ነበር። ስለዚህም መከራ መስቀልን እና የመስቀል ላይ ሞትን ይቀበል ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፤ ጌታችን ራሱ ‹‹እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ›› እንዳለ የተበተኑት የሚሰበሰቡት በእርሱ ሞት ነውና ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም በድርሰቱ ‹‹እጆቹን በመስቀል ላይ በዘረጋ ጊዜ የምድርን ጫፎች አቀፈ ሁሉንም ወደ እቅፉ ሰበሰበ›› በማለት እንደተናገረው ነፍሱን ስለብዙዎች አሳልፎ የሚሰጥበት ጊዜ በደረሰ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። (ዮሐ.፲፪፥፴፪፣ Saint Cyril of Jerusalem: Catech. Lect. 13:28, ክፍል ትምህርት ፲፭፥፳፰)
ድኅነታችንንም ይፈጽም ዘንድ በአይሁድ ተያዘ፤ የነፍሳችንን ቁስል ይፈውስ ዘንድ ቆሰለ፤ የእርሱ ቁስል የእኛ ድኅነት ነውና፤ ‹‹በቁስልህ ቁስሌን ፈውስ›› እንዳለው አረጋዊ መንፈሳዊ የእሾህ አክሊልን ደፋ፤ በዚህም የብርሃንን አክሊል ደፋልን፤ ተሠቃየ፤ አፉን ግን አልከፈተም፤ የእግዚአብሔር የፋሲካው በግዕ ነውና፡፡ (ኢሳ.፶፫፥፯) ንጹሕ መሥዋዕት ‹‹ኃይል ያላት መሥዋዕት፣ በእግዚአብሔር ፊት ሥልጣን ያላት መሥዋዕት፣ በእግዚአብሔር የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ራሱን አቀረበ፤ ስለዚህም ‹‹በዚህ ቅዱስ መሥዋዕት ተቀደስን›› እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ (ድርሳን ፲፯፥፴፯)፤ በደሙ ያጸድቀን ዘንድ እርሱ ወደ መስቀል ወጣ፤ ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ ‹‹ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን›› ብሎናል፡፡ (ሮሜ ፭፥፱:) ራሱ ሊቀ ካህን፣ ራሱ መሥዋዕት ራሱ መሥዋዕት፣ ተቀባይ በመሆን ድኅነታችንን ፈጽሟልና።
መስቀል ጌታችን የከበረበት ቦታ እንጂ እንደ አንድ ወንጀለኛ የተቀጣበት አይደለም፤ መስቀል ክርስቶስ ጠላታችንን ያሸነፈበት የድል አደባባይ ነው፤ ስለዚህ መስቀል የድል ዓርማ ነው፤ ጠላት የተቀጠቀጠበት ጽኑ የአድማስ ድንጋይ ነው። ‹‹በዚያም ቀን እግዚአብሔር ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን ጠማማውንም እባብ ሌዋታንን በጠንካራ በታላቅም በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፤ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል›› እንዲል። (ኢሳ.፳፯፥፩) ይህ ቀን ዲያብሎስ የሞተበት ቀን ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዳለን የቀደመው እባብ በመለኮታዊ ሰይፍ የተቆረጠበት በባሕር ውስጥ ያለው የተጣለው ዘንዶ የተገደለበት ቀን ነው፤ (ራእይ ፲፪፥፱) የሰው ልጅ ዘለዓለማዊ ጠላት ራስ የተቀጠቀጠበት፣ የተነገረው ትንቢት የተፈጸመበት ነው፡፡ ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ›› እንዲል። (ዘፍ.፫፥፲፭) አዎ! ጎልያድ (ሰይጣን) በራሱ ሰይፍ አንገቱ የተቆረጠበት ቀን ነው፤ ሰይጣን ባመጣው ሞት እርሱ ራሱ ሞቷልና፤ አማናዊው ዳዊት (ክርስቶስ) እስራኤል ዘነፍስን ከጎልያድ (ዲያብሎስ) ያዳነበት ቀን ነው፤ ጌታችን በሥጋ ቢሞትም በመንፈስ ግን ሕያው ነው፤ የማይሞት መለኮታዊ ባሕርይ ነውና ‹‹ሞትን ይሽረው ዘንድ የማይሞተው ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ›› እንዲል፡፡ (ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈወርቅ)
ይህም የእግዚአብሔር ልጅ ሞት እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳየበት ነው፤ ይህንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ እያለ ያደንቃል፤ ‹‹ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳን የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል፤ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና፤ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።›› (ሮሜ ፭፥፯-፰)
ጌታችንም ሞቱ የፍቅሩ ፍጻሜ መሆኑን በወንጌል ‹‹ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም›› ይለናል፡፡ (ዮሐ.፲፭፥፲፫) ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው›› የሚለውን ቃል ሲተረጉም ስለ ክርስቶስ ፍቅር እንዲህ ይላል፤ ‹‹ከገሃነም በላይ እነዚህን ቃላት እንፍራቸው፤ ቃላቱ የሚገልጹትን ከመንግሥተ ሰማይ በላይ እናወድሳቸው ስለዚህም ቅጣትን አንፍራ ኃጢአትን እንጂ፡፡›› (፪ኛቆሮ. ፭፥፳፩) ስለዚህ ፍቅር ብለን ክርስቶስን እንውደደው! ስለዚህ ፍቅር ሕግጋቱን እናፍቅር! ይህንን ፍቅር ማሳዘንን ለዘለዓለም በገሃነም ከመቃጠል በላይ እንፍራ! ይህን ፍቅርም ከሰማይ መንግሥት በላይ እንጠማው! ይህ ፍቅር የቅዱሳን ምግብ፣ የመላእክት ደስታ ሕይወት ነው፤ ለዚህ ፍቅር እንጠንቀቅ! ‹‹እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ ደግሞ እንወደዋለን።›› (፩ኛዮሐ.፬፥፲፱)
ጌታ ከሞተ በኋላ የተሰቀለበት ቀኑ ዓርብ ስለሆነና ቀጥሎ የሚመጣው ቀን ሰንበት በመሆኑ አይሁድ ደግሞ በሰንበት ከዘረጉ የማያጥፉ ከተቀመጡ የማይነሡ ስለሆነ ሥጋቸው በመስቀል ተሰቅሎ ከመስቀል ሳይወርድ ሰንበት እንዳይገባ ጭናቸውን ሰብረው ከመስቀል እንዲያወርዷቸው አዘው ነበር፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፴፩) ወደ ጌታ ሲመጡ ግን ሞቶ ስላገኙት አብረውት የተሰቀሉትን ጭኖቻቸውን ሲሰብሩ ከእርሱ ግን ጭኑን አልሰበሩም። ይኸውም ‹‹አጥንቱን አትስበሩ›› የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። (ዮሐ.፲፱፥፴፮) ይህም አጥንቱ የመለኮቱ፣ ሥጋው የትስብእት ምሳሌ ነው። ጌታ በሥጋው ቢሞትም በመለኮቱ ግን ሕያው መሆኑን በነቢያት የተገለጸ ትንቢት ነው። ጌታ የሞተው የሥጋን ሞት ነውና ሞቱ የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፤ ለመለኮት ግን ሞት አይነገርም፤ አይስማማም፤ አይታሰብምም፤ እርሱ ዘለዓለማዊ ሕይወት ነውና። ሕይወት ሊሞት አይችልም፤ ነገር ግን በሥጋ ሞተ። ‹‹ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ።
ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት። በተሰቀለበትም ስፍራ አትክልት ነበረ፤ በአትክልቱም ማንም ገና ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበረ። ስለዚህ መቃብሩ ቅርብ ነበረና ስለ አይሁድ ማዘጋጀት ቀን ኢየሱስን በዚያ አኖሩት።›› (ዮሐ.፲፱፥፴፰-፵፪)
በመጽሐፈ ኪዳን እንደተገለጸው ጌታችን ከሞተ በኋላ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሲገንዙት ተገልጾ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት፤ ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት፤ ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ድበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል የማይሞት፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ አቤቱ ይቅር በለን፤ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል የማይሞት፤ በዮርዳኖስ የተጠመቀ በዕፀ መስቀል የተሰቀለ አቤቱ ይቅር በለን›› እያሉ እንዲገንዙት አዟቸዋል፤ በዚህም እርሱ ሕያው የማይሞት የሕይወት አስገኝ መሆኑን ገለጸ፤ ወደ መቃብር ስለመውረዱ ቅዱስ ኤራቅሊስ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹ሰማይን እንደ ድንኳን የዘረጋው በመቃብር አደረ፤ ከሙታንም ጋር ተቆጠረ፤ በሞቱም ሲኦልን በዘበዛት፡›› (ሃይማኖተ አበው ፵፰፥፭) ጌታ ወደ መቃብር ሲወርድ የመቃብርን ኃይል አደከመ፤ ሞትም ኃይሉን አጣ፤ መበስበስ መፍረስ ድል ተነሣ፤ ብዙ ሙታንንም ሰጠ። ይኸውም በዓለም ፍጻሜ ሙታንን ሁሉ በጌታችን የትንሣኤ ኃይል እንደሚያወጡ ምልክት ነው፤ እርሱ የትንሣኤያችን በኩር ነውና።
በመቃብር ያደረው እርሱ ግዕዛን ያላቸው ፍትረታት ሁሉ ሕያው ዘለዓለማዊ ዕረፍታቸው ነውና ክርስቶስ ያረፈባት ይህች ቦታ ምን ዓይነት ቅድስት ቦታ ናት። መለኮታዊ ሥጋን ለመሸከም የተመረጠች ቦታ በእውነትም ቅድስት ናት፤ ኑ እርሷን እንምሰላት! ቅዱስ አግናጥዮስ እንዳለው የሞት መድኃኒት የሆነውን የክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል በዚያ ዮሴፍና ኒቆድሞስ አሉ፤ በዚያ የካህናት አለቃ የሚቀደስባቸው የሐዲስ ኪዳን ካህናት አሉ፤ (medicine of immortality, ኤፌሶን ፳፥፪) ኑ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት የነፍስን ምግብ እንብላ! የነፍስን ጥም ለዘለዓለም የሚቆርጥ “መስቴ መኮንን” ፈራጅ መጠጥ እንጠጣ፤ ኑ ከዚህ ዕፀ ሕይወት ፍሬን ቀጥፈን እንብላ! ይህ በገነት እንዳለችው የዕውቀት ዕፅ በልተን ወደ ሲኦል የሚያወርድ አይደልም፡፡ ከሕይወት ወንዝ የበቀለ ዘወትር የሚያፈራ የሕይወት ዕፅ ነው እንጂ፡፡ (ራእይ ፳፪፥፪)
ከዚህ ዕፅ ያልበላ ሕይወት የለውም፤ እርሱ “የሞት መድኃኒት” ነውና ቅዱስ ዮሐንስ እንዳለው በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነጻነትን ሰበከላቸው፤ ሲኦልም ምርኮዋን ሰጠች። ጨለማው በብርሃን ተዋጠ፤ ‹‹ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም።›› (ዮሐ.፩፥፭) መድኃኔዓለም ጎርፍ የሲኦልን ነፍሳት ወደ ገነት መለሰ፤ ገነትን ከፈተ፤ የሚገለባበጠውን ሰይፍ ሰበረ። የክብር ንጉሥ መጥቷልና መኳንንቶች በሮቻቸውን ከፈቱ፤ ያን ጊዜ ሞት በሕይወት ተዋጠ። ነፍሳት ሁሉ እንዲህ እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ ‹‹በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ፤ ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፤መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው፤ አመሰግነውማለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው፤ ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡›› (ዘጸ.፲፭፥፩-፫)
በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በወንጌል ተጽፎ እንደምናገኘው፣ አባቶቻችንም እንደነገሩን ክርስቶስ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ነው፤ እንደ ፍጹም ሰውነቱ በመስቀል ላይ ሞተ፤ እርሱ ግን ሕይወት የሕይወት ራስ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው ‹‹የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፡፡›› (የሐዋ.ሥራ ፫፥፲፭) ሞት ይይዘው ዘንድ አይችልምና አዎ እርሱ ሰማያትን የፈጠረ ኃይል ነው። አዎ እርሱ ለፍጥረት የመኖርን የሰጠ ዘለዓማዊ ትንሣኤ ነው። ‹‹ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፤ ይኸውም መለኮቱ ነው፤ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፡፡›› (ቅዱስ ሄሬኒዎስ)
የክርስቶስ ትንሣኤ ሞት የተሸነፈበት የመጨረሻው ድል ነው፤ የክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትናችን ሕይወት ነው፤ የክርስቶስ ትንሣኤ ለዓለም የዘለዓለማዊነት ተስፋ የፈነጠቀ የተስፋ ፀሐይ ነው፤ የክርስቶስ ትንሣኤ የመጨረሻው ጠላት የተሻረበት፣ ባሕርያችን የክብር አክሊል የደፋበት የድል ቀን ነው። አዎ! ጌታችን በትንሣኤው የጨለማ ገዢዎችን ኃይል ሽሯል፡። (መዝ.፸፯፥፷፭) ከትንሣኤው ዲያብሎስ ሊቋቋመው የማይችል መለኮታዊ ብርሃን ወጥቷል፤ ይህ ብርሃን የትንሣኤው ብርሃን ነው፤ ይህ ብርሃን የጨለማ ገዢዎችን ራስ የቀጠቀጠ መለኮታዊ መዶሻ ነው፤ ይህ ብርሃን የእባቡን ልብ የወጋ መለኮታዊ ጦር ነው፡፡
ነቢዩ ዕንባቆም ስለዚህ የትንሣኤው ኃይል እንድህ ይለናል፤ ‹‹ፍላፆችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ፥ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሣ፥ ፀሐይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ።›› (ዕን.፫፥፲፩) በትንሣኤው ለዓለም ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ሰበከ፤ ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያንን በትንሣኤው ገሠፃቸው፤ እንስሳዊ ሕይወት ይኖር ለነበረው ዓለም የዘለዓለማዊነትን ወንጌል በትንሣኤው ሰበከ፤ ትንሣኤ ወንጌል ነው። ክርስትናን ልዩ የሚያደርገው ትንሣኤ ነው፤ ትንሣኤ ከሌለ እምነት የለም። በመንፈስ የሚናገር የትንሣኤው ምስክር ቅዱስ ጳውሎስ ያለ ትንሣኤ ክርስትና አለመኖሩን እንዲህ ይነግረናል፤ ‹‹ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ?፤ ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው፤ እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ደግሞም ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን፤ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም። ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። በዚህች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል፡፡›› (፩ኛቆሮ.፲፭፥፲፪-፲፱) ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትና መሠረት ነው። ድኅነታችን የተፈጸመው በእርሱ ትንሣኤ ነውና!
ወስ ብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን!!!