ታላቁ አባ መቃርስ
ነሐሴ ፲፰፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም
ከ፹ ዓመት በላይ በበረሃ የተጋደሉ፣ በአስቄጥስ ገዳም ፭፼ መነኮሳትን በመመገብ የመሩ፣ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ወደሙን ተቀብለው ስለ ሥጋ ወደሙ ክብር ሲሉ ለ፷ ዓመት ምራቃቸውን ሳይተፉ የኖሩት ታላቁ አባት አባ መቃርስ በነሐሴ ፲፱ ፍልሰተ አጽማቸው ሳስዊር ከሚባል ሀገር ወደ አስቄጥስ የተፈጸመበት የከበረ በዓል ነው፡፡
ታላቁ አባ መቃርስ ከዕረፍታቸው በኋላ ከሀገሩ ከሳስዊር ሰዎች መጥተው ሥጋቸውን በድብቅ ወስደው ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ከዚያ አኑረዋቸዋል፡፡ ሆኖም በዚያን ጊዜ እስላሞች በመንገሣቸው ክርስቲያኖች ለመሰደድ ተገደዱ፡፡ በዚህም የተነሣ የአባ መቃርስን ሥጋ ወስደው በድጋሚ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በዚያ አኖሩት፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የአባ መቃርስን ሥጋ እንዲሰጠው እያለቀሰ ወደ እግዚአብሔርን ልመና ካቀረበ በኋላ የአስቄጥስ ገዳም አረጋዊ መነኮሳትንም አስከትሎ የአባ መቃርስ አጽም ወዳለበት ሄደ፡፡
ሕዝበ ሳስዊር ግን በመከንኑ መሪነት ሰይፋቸውን ይዘው የአባ መቃርስን አጽም ከለከሏቸው፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱና መነኮሳቱም እጅግ አዝነው ተመለሱ፡፡ ይህን ጊዜ አባ መቃርስ በዚያች ሌሊት ለመኮንኑ በራእይ ተገለጠለትና ‹‹ከልጆቼ ጋር መሄድን ለምን ትከለክለኛለህ? እንግዲህስ ከልጆቼ ጋር ወደ ቦታዬ ልሄድ›› አለው፡፡ መኮንኑም በጠዋት ተነሥቶ እየፈራና እየተንቀጠቀጠ አረጋውያን መነኮሳቱን ጠርቶ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደስ ተሰኝተው የአባ መቃርስን ሥጋ ይዘው በመርከብ በመሳፈር ተርኑጥ የምትባል ሀገር ሲደርሱ ስለመሸባቸው በዚያው አደሩ፡፡ በማግሥቱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ለመድረስ በረሃውን ሲያቋርጡ ጥቂት ድካም ስለተሰማቸው ሊያርፉ ቢወዱም አባ ሚካኤል ግን ‹‹የቅዱስ አባታችንን ሥጋ የምናሳርፍብን ቦታ እግዚአብሔር ካልገለጠልን በቀር አናርፍም›› በሚል ሐሳብ አቀረቡ፡፡ ከመቅጽበትም የአባ መቃርስን ሥጋ የተሸከመው ግመል ወደ አንድ ቦታ ደርሶ በዚያ በርከክ በማለት የአባ መቃርስ ሥጋ ያለበትን ሣጥን ራሱ ይጥል ዘንድ ወዲያና ወዲህ ሲዟዟር ተመለከቱ፡፡ መነኮሳቱም እግዚአብሔር የፈቀደው ቦታ መሆኑን አውቀው ድስ ተሰኙ፡፡ ያም ቦታ እስከዛሬም ድረስ እንደታወቀ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ መነኮሳቱ የአባ መቃርስን ሥጋ ይዘው ወደ አስቄጥስ ገዳም በደረሱ ጊዜ የገዳሙ መነኮሳት ሁሉም ወጥተው ወንጌልና መስቀሎችን ይዘው እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገቡት፡፡ ከአባ መቃርስም ሥጋ ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተገልጠዋል፡፡
ታላቁ አባ መቃርስ እጅግ ሩህሩህ አባት ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት አንዲት ዘመሚት ነክሳቸው ገደሏት፡፡ ነገር ግን ወዲያው ተጸጽተው ስለ ትንኟ ነፍስ ወደ በረሃ ወንዝ ወርደው ሥጋቸውን ለዘመሚቶች ሰጥተው ዘመሚቶቹ እየነከሷቸው ስድስት ወር ኖረዋል፡፡ ከስድስት ወር በኋላም ወደ ገዳማቸው ሲመለሱ ምን እንደሆኑና የት እንደነበሩ ማንም አላወቀም ነበር፡፡
አንድ ቀንም በበዓታቸው ሳሉ አንዲት ሴት ጅብ መጥታ የአባታችንን ቀሚስ ይዛ እየጎተተች ወስዳ ዋሻዋ ውስጥ አደረሰቻቸው፡፡ ሦስት ልጆቿንም አወጣችላቸው፡፡ እርሳቸውም ቀርበው ቢመለከቷቸው ዕውሮች ናቸው፡፡ እናቲቱንም ጅብ እያደነቁ ግልገሎቿን ይዘው በዐይኖቻቸው ውስጥ ምራቃቸውን ተፍተው አዳኝ በሆነ በክርስቶስ መስቀል ምልክት አማተቡባቸው፡፡ ወዲያውም ድነው ይፈነድቁ ከእናታቸውም ጋር ይጫወቱ ጀመር፡፡ መቃርስም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ በዓታቸው ተመለሱ፡፡ እናቲቱ ጅብም የበግ አጎዛ አምጥታ ሰጣቻቸውና አባ መቃርስም አጎዛውን የመኝታቸው ምንጣፍ አደረጉት፡፡
በግብፅ ሀገር ታላቅ ረኃሀብ ተከሥቶ ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ጢሞቴዎስ መልእክተኛ ወደ እርሳቸው በመላክ አብረው ጸሎት እንዲያደርጉ ጠየቋቸው፡፡ አባ መቃርስም ሄደው በጋራ ቢጸልዩ ዕለቱን ሕዝቡ ‹‹በቃን በጎርፍ እንዳናልቅ…›› እስኪል ድረስ ዝናብን አዝንበውላቸዋል፡፡ አባ መቃርስ የጌታችን ሥጋ ወደሙን ተቀብለው ስለ ሥጋ ወደሙ ክብር ሲሉ ፷ ዓመት ምራቃቸውን ሳይተፉ ኖረዋል፡፡
ታላቁ አባ መቃርስ ከእስክንድርያው መቃርስ ጋር ያሳለፉት ታሪክም እንዳለ ቅድሳት መጻሕፍት ይጠቅሳሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ለሁለቱም በአካል ተገልጦላቸው ታቦቱንና ንዋየ ቅዱሳቱን አክብሮታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስም በአካል ተገልጠውላቸው በቅዳሴ ጊዜ ተራድተዋቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ዮሐንስም የየራሳቸውን መልእክት አንብበውላቸዋል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም መዝሙሩን ዘምሮላቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶላቸዋል፡፡
ቅዱሳን መላእክትም ይራዱአቸው ነበር፡፡ አባ መቃርስና የእስክንድርያው መቃርስ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቀድሰው ለሕዝቡ ሥጋ ወደሙን አቀበሉ፡፡ ጌታችንም ለአባ መቃርስና ለእስክንድርያው መቃርዮስ ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ለዚያች ደሴት ሕዝቦች ሌላ ጳጳስ ከሾሙላቸው በኋላ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ባሰቡ ጊዜ መልአክ መጥቶ ነጥቆ ወስዶ የእስክንድርያ ጳጳስ አባ ጢሞቴዎስ ፊት አቆማቸው፡፡ እርሱም ሁለቱን ባያቸው ጊዜ እጅግ ተደሰተ፤ ከዚያም መልአኩ ወደ ገዳመ ሲሐት ወሰዳቸው፡፡ በመጨረሻም ግንቦት ስድስት በሽምግልና ሆነው በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡
የታላቁ አባት የአባ መቃርስ ተራዳኢነት አይለየን፤ በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን፡፡
ምንጭ፡– የግንቦትና የነሐሴ ወራት መጽሐፈ ስንክሳር