ተዝካሩን አውጥቶ ክርስቶስን የተከተለ ሐዋርያ
በዲያቆን ዘክርስቶስ ጸጋዬ
ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
አንድ ሰው ከቅፍርናሆም ገበያ ወደ ገሊላ ባሕረ ወደብ በሚወስደው ዐቢይ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ ነጋዴዎችን ቀረጥ ያስከፍል ነበር፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ሲያስተምር ቀረጥ ከሚሰብስብበት ቦታ ጠርቶ ‹‹ተከተለኝ›› አለው፡፡ እርሱም ሥራውን ርግፍ አድርጎ ትቶ ተከተለው፡፡ ለሐዋርያነት በተጠራ ጊዜ በቤቱ ድግስ አዘጋጅቶ ለጌታችን ግብዣ አቅርቦ፣ ለድሆች መጽውቶ፣ የቁም ተዝካሩን አውጥቶ ክርስቶስን ተከተለው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. ፱፥፲-፲፫)፡፡
ማቴዎስ ማለት ‹የእግዚአብሔር ስጦታ፣ ኅሩይ እመጸብሓን (ከቀራጮች መካከል የተመረጠ)› ማለት ነው፡፡ አባቱ ዲቁ እናቱ ደግሞ ክሩትያስ ይባላሉ፡፡ አባቱ (ዲቁ) በሌላ ስም ‹እልፍዮስ› (Aliphaeus) እየተባለ ይጠራል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ብሔረ ሙላዱ (የተወለደበት አገር) ናዝሬት፤ ነገዱም ከነገደ ይሳኮር ነው፡፡ የቀድሞ ስሙ ‹ሌዊ› ነበር (ማር. ፪፥፲፬)፡፡ በዕብራውያን ዘንድ በሁለት ስሞች መጠራት የተለመደ ሲኾን ሌዊ ከቀድሞ ጀምሮ ይጠራበት የነበረ፤ ማቴዎስ ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከተከተለ በኋላ የተጠራበት ስሙ እንደ ኾነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡
የቅዱስ ማቴዎስ ለሐዋርያነት መጠራት
ቅዱስ ማቴዎስ በቅዱሳን ሐዋርያት የስም ዝርዝር ላይ በራሱ ወንጌል በስምንተኛ፤ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌል ደግሞ በሰባተኛ ቍጥር ተጠቅሷል (ማቴ. ፲፥፫)፡፡ በቀድሞ ሥራው ቀራጭ (የሮማውያን ግብር ሰብሳቢ) ነበር፡፡ የቀራጭነት ሥራውን ይሠራ የነበረውም በገሊላው ገዥ በሄሮድስ አንቲጳስ ሥር የነበረ ሲኾን ቦታውም በገሊላ ባህር አጠገብ በምትገኘው ደማቋ ከተማ ቅፍርናሆም ነበር፡፡ ዛሬ ይኼ ቦታ በእሾኽ ታጥሮ የጥንቱን የገበያ ምልክት ይዞ ይገኛል፡፡ የእልፍዮስ ልጅ ሌዊ በዚህ የመቅረጫ ቦታ ተቀምጦ የዓሣ እና የሌላም ነገር ንግድን እየተቆጣጠረ የቀራጭነት ሥራውን ይሠራ ነበር፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚቀርጥበት ቦታ ጠጋ ብሎ ‹‹ተከተለኝ›› አለው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ሲጠራ ቤት፣ ንብረት የነበረው ታዋቂ ባለ ሥልጣን ነበር፡፡ ጌታችን ‹‹ተከተለኝ›› ሲለው ድሆችን በነጻ የሚያበላ፣ ድውያንን በነጻ የሚፈውስ አምላክ መኾኑን ተረድቶ ሥራውን ርግፍ አድርጎ ትቶ ተከተለው፡፡ የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መኾኑን በቤቱ ለጌታችንና ለተከታዮቹ ግብዣ በማድረግ ግልጥ አደረገ (ሉቃ. ፭፥፳፱)፡፡ ለጌታችና ለተከታዮቹ ግብዣ ያቀረበበት ቤቱም በቅፍርናሆም የሚገኝ ሲኾን ዛሬ ላቲኖች ቤተ ክርስቲያን ሠርተውበታል፡፡
የሐዋርያው አገልግሎት
ተዝካሩን ያወጣው ሐዋርያ ከክርስቶስ ጋር በነበረበት ጊዜ ከዋለበት እያዋለ፣ ካደረበት እያደረ፣ እንዲሁም በትንሣኤና በዕርገቱ ጊዜ በበዓለ ኀምሳ ደግሞ ለደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ አብሮ ነበር (ማቴ. ፲፥፩-፭፤ ሉቃ. ፲፰፥፴፩)፡፡ ከዚያም ሰባቱ ዲያቆናት እስከ ተመረጡበትና እስጢፋኖስም እስከ ተገደለበት ቀን ድረስ ከዚያም በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት ጋር አብሮ ነበር፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ ሲከፋፈሉም ለእርሱ በደረሰው ሀገረ ስብከት በምድረ ፍልስጥኤም ገብቶ ጌታ ከፅንስ ጀምሮ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርት፣ የሠራውን ትሩፋት ቢነግራቸው ብዙዎች ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመለሰው፣ በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል፡፡
በካህናት አገር ወንጌልን መስበኩ
ቅዱስ ማቴዎስ በደመና ተጭኖ በጌታችን ትእዛዝ ወደ ሀገረ ካህናት እንደ ተወሰደ በገድለ ሐዋርያት እና በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ በዚያም ወደ ከተማው መግቢያ ደጅ በደረሰ ጊዜ አንደ ወጣት ብላቴና አገኘ፡፡ ወደ ከተማው ለመግባት እንዴት እንደሚችል ቢጠየቀው ወጣቱ ብላቴናም ‹‹እራስኽንና ጺምኽን ካልተላጨኽ፣ በእጅህም ዘንባባ ካልያዝኽ መግባት እትችልም›› ሲል መለሰለት፡፡ ይህም ነገር ለሐዋርያው ማቴዎስ አስጨንቆት ሲያዝን አስቀድሞ ያነጋገረው ያ ወጣት ብላቴና ዳግም በስሙ ጠራው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹ወዴት ታውቀኛለህ?›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እኔ ጌታህ ኢየሱስ ነኝ፤ አሁንም እንደ ነገርኹኽ አድርግ፡፡ እኔም ካንተ ጋር አለሁ፡፡ ካንተም አልርቅም›› አለው፡፡
ከዚያን በኋላ ጌታችን እንዳዘዘው አድርጎ ወደ ካህናት አገር ገባ፡፡ በዚያም ከጣዖቱ ካህናት አለቃ ከአርሚስ ጋር ተገናኘ፡፡ ከእርሱም ጋር ስለ አማልክቶቻቸው ተነጋገረና ‹‹ራሳቸውን ማዳን የልቻሉ ሌላውን እንዴት ያድናሉ?›› ብሎ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ጣዖቶቻቸውን አቃጠላቸው፡፡ በዚያን ጊዜም ከአርሚስ ጋር ብዙዎች ሰዎች አመኑ፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አጠመቃቸው፡፡ ከሰማይ ምግብ አውርዶም መገባቸው፡፡
የአገሩም ንጉሥ የሐዋርያውን ድንቅ ስራ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ከአርሚስ ጋር ሐዋርያውን ወደ እሳት በጨመረው ጊዜ ጌታችን ከእሳቱ አዳናቸው፡፡ ከዚያን በኋላ በሚያሰቃያቸው ነገር ሲያስብ ንጉሡ ልጁ መሞቱን ሰማ፡፡ በዚህም እያዘነ ሳለ ሐዋርያው ማቴዎስ ‹‹ልጅህን እንዲያስነሡት ወደ አማልክትህ ለምን አትለምንም?›› አለው፡፡ ንጉሡም ‹‹አማልክት የሞተ ማንሣት እንዴት ይችላሉ?›› ብሎ መለሰ፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም ‹‹ብታምንስ የእኛ አምላክ ልጅኽን ከሞት ማስነሣት ይችላል›› አለው፡፡ ንጉሡም ‹‹ልጄ ከሞት ከተነሣ እኔ አምናሁ›› አለው፡፡ በዚያን ጊዜ ሐዋርያው ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየና የንጉሡንም ልጅ ከሞት አስነሣው፡፡ ንጉሡም በጌታችን አመነ፡፡ የአገሩ ሰዎችም ዂሉ አመኑ፡፡ የቀናች ሃይማኖትንም አስተምሮ ክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው፡፡ የጣዖቱ ካህን የነበረው አርሚስንም ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾመላቸው፡፡
የማቴዎስ ወንጌል
ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቀኖና በጠቀሰበት ጽሑፉ ቅዱስ ማቴዎስ ከአይሁድ ወደ ክርስትና ለተመለሱ ዕብራውያን ወንጌሉን እንደ ጻፈው ሲገልጽ ‹‹ማቴዎስ ለዕብራውያን ተአምራተ ኢየሱስን ጻፈ›› በማለት ተናግሯል፡፡ በመቅድመ ወንጌል ትርጓሜ ላይም እንዲህ ይላል፤ ‹‹ምድረ ፍልስጥኤም ለማቴዎስ በዕጣ ደረሰችው፡፡ ከዚያ ገብቶ ጌታ ከፅንስ ጀምሮ ያደረገውን ተአምር፣ ያስተማረውን ትምህርት፣ የሠራውን ትሩፋት ቢነግራቸው እስራኤል ናቸውና ከኦሪት ወደ ወንጌል፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመለሱ፤ አመኑ፤ ተጠመቁ፡፡ ትምህርት ካልደሰበት ለማዳረስ ወጥቶ በሚሔድበት ጊዜም ‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል› ብለውት ጽፎላቸዋል››፡፡
የሐዋርያው አገልግሎት በኢትዮጵያ
አውሳብዮስ ዘቂሣርያ እና ሩፊኖስ የጻፏቸው ማስረጃዎች እንደሚያስረዱት ቅዱስ ማቴዎስ በእስራኤል፣ በኢትዮጵያ፣ በፋርስ፣ በባቢሎን፣ በዓረቢያ፣ በግሪክ፣ በፍልስጥኤም እና በብሔረ ብፁዓን ወንጌልን አስተምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ቅዱስ ማቴዎስ በአገራችን ኢትዮጵያ በትግራይ አካባቢ ከዓድዋ አውራጃ በስተምዕራብ ልዩ ስሙ ናዕይር በተባለው ቦታ ወንጌልን አስተምሯል፡፡
ሐዋርያው በብሔረ ብፁዓን
ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ብሔረ ብፁዓን በደመና ተጭኖ ሔዶ ማስተማሩን ገድለ ዞሲማስ (ዘሲማስ) ያስረዳል፡፡ ከቅዱስ ማቴዎስ በኋላ በብሔረ ብፁዓን ስለሚኖሩ ወገኖች አኗኗር በጥልቀት በቀሲስ ዞሲማስ የተዘረዘረ ሲኾን ለእነዚህ ወገኖች ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱስ ማቴዎስም ወንጌልን እንዳስተማሯቸው በመጽሐፈ ገድሉ ተጠቅሷል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዂልጊዜ በየበዓላቸው ወደ ብሔረ ብፁዓን መሔዱ፣ ቅዱስ ማቴዎስም ከቅዱሳን መላእክት እና ሄሮድስ ካስገደላቸው አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናት ጋር እግዚአብሔርን ማመስገኑ ተገልጿል፡፡
የሐዋርያው ተጋድሎና የምስክርነቱ ፍጻሜ
የቅዱስ ማቴዎስ ተጋድሎውና የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲቃረብ ወደ አንዲት ከተማ ገብቶ አስተማረ፡፡ በዚያም ብዙዎችንም አሳመነ፡፡ አገረ ገዢውም ይዞ ከወኅኒ ቤት ጨመረው፡፡ በወኅኒ ቤቱም አንድ እጅግ የሚያዝን እስረኛ አገኘና ስለ ሐዘኑ ጠየቀው፡፡ እርሱም ብዙ የጌታው ገንዘብ ከባሕር እንደ ሰጠመበት ነገረው፡፡ ሐዋርያው ማቴዎስም እስረኛው የጠፋበትን ገንዘብ የሚያገኝበትን የባሕር ዳርቻ ጠቆመው፡፡ እስረኛውም ሐዋርያው በነገረው መሠረት የጠፋውን ገንዘብ አግኝቶ ለጌታውም ሰጠው፡፡ ጌታውም ከየት እንዳገኘው ቢጠይቀው ከወኅኒ ቤት ባገኘው በሐዋርያው ማቴዎስ ጥቆማ የጠፋውን ገንዘብ ሊያገኘው መቻሉን ነገረው፡፡ ጌታው ግን ሊያምነው አልቻለም ነበር፡፡
ይልቁንም እጅግ ተቆጥቶ ሐዋርያውን ከእስር ቤት አስወጥቶ ወደ ንጉሡ ወሰደው፡፡ ንጉሡም ተዝካሩን አውጥቶ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተለውን ሐዋርያ ቅዱስ ማቴዎስን ወዲያው በሰይፍ ራሱን እንዲቆርጡት፣ ሥጋውንም ለሰማይ ወፎች እንዲጥሉት አዘዘ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም በታዘዙት መሠረት ጥቅምት ፲፪ ቀን በ፷ ዓ.ም የሐዋርያውን አንገት በሰይፍ ቆርጠው ራሱን ለብቻ፣ ሰውነቱን ለብቻ አድርገው አሞሮች እንዲበሉት ጥለውት ሔዱ፡፡ ምእመናንም ራሱንና ቀሪው ሰውነቱን በአንድ አድርገው ካባቶቹ መቃብር እንዲቀበር አደረጉ፡፡ ያ ሐዘንተኛ እስረኛም የቅዱስ ማቴዎስን መገደል ሲሰማ ለሦስት ቀናት እያዘነ አለቀሰ፡፡ ከቅዱስ ማቴዎስ ሞት በኋላ አምስት ቀናት ቆይቶ እርሱም ዐረፈ፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን! እኛንም ተዝካሩን አውጥቶ፣ ሥልጣኑንና ሥራውን ትቶ፣ የሚበልጠውን ሰማያዊ መንግሥት ሽቶ ክርስቶስን በተከተለው ሐዋርያ በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ምንጭ፡- የጥቅምት ፲፪ ቀን ስንክሳር እና ገድለ ሐዋርያት፡፡