ተአምረኛዋ ሥዕል
መስከረም ፰፤፳፻፲፰ ዓ.ም.
እጅጉን የሚያስደንቀው የአምላክ ሥራ የተገለጠበት፣ ለሰው ልጆች ተስፋ፣ ፈውስ ሥጋ እንዲሁም ፈውስ ነፍስን ሊሰጠን በፈቀደ እርሱ ድንቅ ተአምራትን በምድር አደረገ፤ ጌታ በትስብእቱ በዓለም ተገልጦ ካደገጋቸው ተአምራትም በተጨማሪ እርሱ ካረገ በኋላም በሰዎች አድሮ ላይ አድሮም ይሁን በተለያዩ መንገዶች ዕጹብ ሥራውን አሳይቶናል፡፡
ከዚሀ ሁሉም በበለጠ መልኩ በክብርት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም የተደረገው ምሥጢር እጅግ ይልቃል፤ ነገረ ድኅነቱን የፈጸመባት እመቤታችን ለአዳም ዘር በሙሉ ተስፋ በመሆኗ ጌታ ከእርሷ በለበሰው ሥጋ ተገልጦ ያደረገልንን ለመግለጽ ቃላት ባይኖርም ምስጋና ግን ማቅረብ የሁላችንም ፈንታ ነው፡፡ አልፎ ተርፎም እርሷም እንደ ልጇ ተነሥታ ካረገች በኋላ ድንቅ ተአምርም በእርሷ ተደርጓል፡፡ ቅዱሳት መጽሐፍት በተለያዩ ጊዜ እመቤታችን ያደረገችውን ተአምር ገልጸው ጽፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመጽሐፈ ስንክሳር መስከረም ፲ ቀን ተመዝግቦ የምናገኘው አንድ ተአምረኛ ሥዕል እንዳለ ነው፤ ታሪኩም እንዲህም ይነበባል፡፡
አንዲት ማርታ የምትባል ሴት እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምትወድና በሚቻላትም ሁሉ የምታገለግላት፣ ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቴዎድሮስ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ መነኰስ ከእርሷ ዘንድ በእንግድነት አድረው በማግሥቱ ከቤቷ ሲወጡ ማርታ የሚሔዱበትን አገር በጠየቀቻቸው ጊዜ እርሳቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ቅዱሳት መካናትን እንደሚሳለሙ ነገሯት፡፡ ማርታም ከእርሷ ገንዘብ ወስደው የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተው ይዘውላት እንዲመጡ ለመነቻቸው፡፡ መነኵሴውም በራሳቸው ገንዘብ ሥዕሉን ገዝተው እንደሚያመጡላት ቃል ገቡላት፡፡
አባ ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም ደርሰው ቅዱሳት መካናትን ከተሳለሙ በኋላ ሥዕሏን ሳይገዙ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ?›› የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰምተው ተመልሰው መልኳ ያማረና የተወደደ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ገዝተው በሐርና በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ይዘው እየተጓዙ ሳሉ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ሲደርሱ ወንበዴዎች ተነሱባቸው፡፡ ሊሸሹ ሲሉም ‹‹መንገድህን ሒድ›› የሚል ቃል ከሥዕሏ ወጣ መነኵሴውም መንገዳቸውን በሰላም ተጓዙ፡፡ ሁለተኛም አንበሳ ሊበላቸው በተነሣባቸው ጊዜ ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረላቸው፡፡
አባ ቴዎድሮስ ይህን ኹሉ ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜም ያቺን ሥዕል ለማርታ ከመስጠት ይልቅ ወደ አገራቸው ሊወስዷት ወደዱ፡፡ በመርከብ ተሳፍረው በሌላ አቅጣጫ ሲሔዱም ታላቅ ነፋስ ተነሥቶ ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያ ወሰዳቸው፡፡ ከመርከብም ወርደው ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ደረሱ፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን ለማርታ አልገለጡላትም ፤ እርሷም አላወቀቻቸውም ነበር፡፡
በማግሥቱም ተሠውረው ወደ አገራቸው ሊሔዱ ሲሉ የቅፅሩ ደጃፍ ጠፍቶባቸው ሲፈልጉ ዋሉ፤ በመሸባቸው ጊዜም ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ፡፡ ማታ ማታ በሩን ያዩታል፤ ነግቶ መሔድን ሲሹ ግን የበሩ መንገድ ይሠወርባቸዋል፡፡ እንዲህም ኾነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቆዩ፡፡ ማርታም ‹‹አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን? ስትቅበዘበዝ አይሃለሁና ምን ሆነህ ነው?›› ስትል ጠየቀቻችው፡፡ እርሳቸውም ከእመቤታችን ሥዕል የተደረገውን ተአምር ሁሉ ነገሯት፤ ራሳቸውንም ገለጡላትና ሥዕሏን ሰጧት፡፡ እርሷም የእመቤታችንን ሥዕል ተቀብላ የተጠቀለለችበትን ልብስ በፈታችው ጊዜ ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋ ብዛት የተነሣም የአባ ቴዎድሮስን እጃቸውንና እግራቸውን ሳመች፡፡ ሥዕሏም ቅዱስ ሉቃስ የሳላት ነበረች፡፡
አንኳን ለበዓለ ጼዴንያ ማርያም አደረሳችሁ!