ተቀጸል ጽጌ
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
መስከረም ፱፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
‹‹ተቀጸል ጽጌ›› ማለት ‹‹አበባን ተቀዳጅ›› ማለት ሲሆን በዘመነ አክሱም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበሩት በዐፄ ገብረ መስቀል የተጀመረ በዓል ነው፡፡ ይህ የተቀጸል ጽጌ በዓል የክረምቱን መውጣት መሠረት አድርጎ መስከረም ፳፭ ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን ሕዝቡ በክረምቱ ምክንያት፣ በዝናቡ ብዛት፣ በወንዙ ሙላት ተለያይቶ ይከርም ነበርና ለንጉሠ ነገሥቱ የአበባ አክሊል/ጉንጉን/ ሠርቶ በማምጣት የሚያበረክትበት በዓል ስለነበረ ‹‹ተቀጸል ጽጌ ገብረ መስቀል ሐፄጌ፤….ዐፄ ገብረ መስቀል አበባን ተቀዳጅ›› እየተባለ ይዘመር ነበር፡፡
ምንም እንኳን በታሪክ ደምቆ የሚታወቀው በዚህ መልኩ ቢሆንም ቀደም ያለ የታሪክና የትውፊት ውርርስ ያለው በዓል ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕዝበ እስራኤልን በሰባተኛው ወር (ኤታኒም/መስከረም የመጀመሪያው ቀን ከሚከበረው በዓል መጥቅዕ /የመለከት በዓል/ በኋላ በዐሥረኛው ቀን የሥርየት በዓል አድርገው እንዲያከብሩት አዝዟቸው ነበር፡፡ (ዘሌ. ፳፫፥፳፭)
ይህ የመስከረም ወር ዐሥረኛው ቀን የእስራኤላውያን የንስሐ መግቢያ የጾም ቀን አድርገው ሲያከብሩት የነበረና በሕገ ኦሪት ተወርሶ በኢትዮጵያም የሚከበር እንደነበረና በኋላ ግን በዘመነ ሐዲስ የዐፄ መስቀል በዓል እንደተተካበት መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ የዐፄ መስቀል በዓል ሕዝቡ ሁሉ ነገሥታቱን ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ለማለት ወደ ነጉሥ ከተማ የሚወጣበትና መሪውን የሚያገኝበት በሀገር ላይ ስላለው ሁኔታም የሚወያይበት ቀን ሆኖ ይከበር ነበር፤ በዓሉም የሚከበረው መስከረም ፳፭ ቀን ነበር፡፡ (ክብረ በዓላት ገጽ ፶፬)
ቆይቶ ግን በዐሥረኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጌታችን ግማደ መስቀል በዐፄ ዳዊት አማካኝነት ከአሌክሳንደርያ ወደ ኢትዮጵያ የገባው መስከረም ዐሥር ቀን ስለነበር የተቀጸል ጽጌ በዓል የዐፄ መስቀል በዓል እየተባለ ቀኑ ከመስከረም ፳፭ ወደ መስከረም ፲ ተዛውሮ ሲከበር ኖሯል፡፡
ምክንያቱም ንጉሡ መስቀሉን መስከረም ፲ ቀን ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ሲገቡ በኢትዮጵያና በአውራጃዎቿ ሁሉ ብርሃን ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቱም ወንዱም፣ ትንሹም ትልቁም፣ ሕዝቡም አሕዛቡም በፍጹም ደስታ በዓል አደረጉ፤ ዐፄ ዳዊትም መስከረም ፲ ቀን ከሠራዊታቸው ጋር ደስ እያላቸው በዓሉን አከበሩ፤ በእጃቸው እያጨበጨቡ በእግራቸው እየረገጡ በሆታ ካህናቱ በዝማሬ ‹‹መስቀል ኃይልነ፣ መስቀል ጽንዕነ›› እያሉ ከፍ ባለ ደስታ በዓሉን አከበሩ፡፡ ይህንንም ልማድ አድርገው በኢትዮጵያ የነገሡ ነገሥታት ሁሉ በዓልን ሲያከብሩት ኖረዋል፡፡ ስሙንም ‹‹ዐፄ መስቀል በዓል›› ብለው ሰይመውታል፡፡ (መጽሐፈ ጤፉት ገጽ ፶-፶፩፣ የመስከረም ፲ ስንክሳር አርኬ)
ስለዚህ ጉዳይ ድርሳነ መስቀልም እንዲህ ይላል፤ ‹‹መስከረም ዐሥር ቀንም በንጉሥ ከተማ መካከል በመስቀል ምልክት ሰንደቅ ዓላማ ተተከለ ስለዚህም ያቺ ዕለት የዐፄ መስቀል ተባለች›› ይላል፡፡ (ድርሳነ መስቀል ገጽ ፪፻፺፬)
ይህ ታላቅ በዓል እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ በቤተ መንግሥት ሲከበር የቆየ ሲሆን በደርግ መንግሥት ምክንያት በዓሉ ተቋርጦ እስከ ፲፱፻፹፫ ዓ.ም ሳይከበር ቆይቷል፡፡ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ በዓሉ በቤተ መንግሥትና በነገሥታት ፊት ባይከበርም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በፓትርያሪኩ ፊት በዓሉ ለመታሰቢያ ያክል እየተከበረ ይገኛል፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር!