ተስፋ

ሰኔ ፳፫፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ሕይወታችን ያለ ተስፋ ባዶ ነው፤ ያለ ተስፋ መኖር አንችልም፤ ተስፋ ከሌለን ማንኛውንም ዓይነት የኑሮ ገጠመኝና ችግር ማሳለፍ አይቻለንም፡፡ የሰው ልጆች ዋነኛው ብርታት ተስፋ ማግኘትና በተስፋ መኖር ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰው አዳም የአምላካችን የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፎ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ ከበላ በኋላ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በምድር ላይ ሲኖር በኀዘንና በጭንቅ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ፈጣሪ የልቡን ጭንቀትና ኀዘን ተመልክቶ ሊምረው ስለወደደ ከልጅ ልጁ ተወልደ እንደሚያድነው ቃል ገባለት፡፡ ይህም ለአዳም ትልቅ ተስፋ ስለነበረ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ በተስፋ ጠብቋል፡፡

ሰዎች በምድር ላይ ልንኖር የምንችለው ተስፋ የምናደርግበት ነገር ሲኖረን ነው፡፡ አዳም ማጥፋቱን አውቆና አምኖ ምሕረትን ስለለመነ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንደቻለ እኛም ተስፋ ማድረግ ያለብን ተስፋ (ርስተ) መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ይህም የምድር ሕይወታችንን በመልካሙና በእውነተኛው መንገድ እንድንኖር ይረዳናል፡፡ ለዚህም ምሳሌዎች የሆኑት የጻድቃን የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ታሪኮች ምስክሮች ናቸው፡፡

ጻድቁ ኢዮብ ሀብቱንና ንብረቱን እንዲሁም ልጆቹን በሙሉ አጥቶ በዚያ ሕመምና በሽታ በተፈራረቀበት ጊዜ እንኳን በእግዚአብሔር ተስፋ ሳይቆርጥ ‹‹ብርሃንን ተስፋ አደረግሁ›› በማለት ተናገረ እንጂ አምላክን እንዳላማረረ ቅዱሱ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ (ኢዮ.፴፥፳፮) ይህ በእውነት ለእኛ ትልቅ ትምህርት የሚሆነን ነው፡፡ በእርግጥም እንደ ኢዮብ ያለ መከራ እና ችግር ሳይደረስብን በራሳችን ችግር ተውጠን ባለንበት በዚህ ጊዜ ተስፋ ማድረግ የምንችለው አምላካችንን ሊሆን ይገባል እንጂ በሆነው ባልሆነው ነገር እግዚአብሔርን ማማረር እራስን ለባሰ ችግር ማጋለጥ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በሕይወቱ ውስጥ የሌለ ሰው ተስፋ ሊኖረው እንደማይችል በቅዱሳን ታሪክ ብቻም ሳይሆን በራሳችን ተሞክሮም የተመለከትነውና ያወቅነው ነገር ነው፡፡ ብዙዎቻችን ሳናውቅም ሆነ አውቀን ከገባንበት ችግር ለመውጣት አቅቶን ስንባዝን የከረምንና ግራ በመጋባት መፍትሔ መስሎን ወዳልሆነ ነገር የገባን ልንኖር እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ሰዎች ችግራቸውን ለመፍታትና ከገቡበት ዕዳ ለመላቀቅ ሲሉ ወደ ባዕድ አምልኮት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህ ግን የባሰ ችግር እንደሚያመጣ በወቅቱ ላያውቁና ላያገናዝቡ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ሰው ለምድራዊ ሕይወት ሲል ፈጣሪውን ክዶ ለጠላት መገዛት ከጀመረ ለጊዜው ችግሩ የተፈታለትና የሥጋ ድሎት ያገኘ ቢመስለውም ወደደም ጠላ የእርጅናው ዘመን በደረሰ ጊዜና ወደ ሞት ሲቃረብ በፍርሃት መኖር ይጀምራል፤ ከዚህም በባሰ መልኩ ሲያመልከው የነበረው ዲያብሎስ ሞቱ በቀረበ ጊዜ ተስፋ አሳጥቶ ነፍሱን ወደ ገሃነም ሊያወርዳት ይፋጠናል፤ በዚህ ጊዜ የመዳን ተስፋው ተሟጦ ንስሓ እንዳይገባ ዲያብሎስ የማያደርገው ጥረት የለም፡፡

ሰው ሲተማመንበት የነበረው ሀብቱም ሆነ ውበቱ ወይም ሥልጣኑ ከገሃነም ሊያድነው አይችልም፤ ይህ ሁሉ አላፊ ጠፊ ነው፤ የሥጋ ነገር ሁሉ ጠፊ ነውና፤ ‹‹ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ሁኩ ከንቱ ነው›› እንዲል፤ (መክ.፩፥፪) ይህንን ግን በጊዜው ተረድቶ ለነፍሱ መኖር የሚችል ሰው በአሁኑ ጊዜ ጥቂት ነው፤ አብዛኛው ሰው በምድራዊ ችግሮቹ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚኖር ነው፡፡ ስለሆነም ከአቅማችን በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥመንና መፍትሔ ስናጣ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ያዳግተናል፡፡ ይቅር እንደሚለንና ምሕረትን መለመን እንደምንችልም ማመን ስለሚከብደን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡

ሕይወት በውጣ ውረድ የተሞላች እንደመሆኗ የሚያሳዝን ነገር በኑሮአችን ሲያጋጥመን በመከፋት ተስፋ መቁረጥ የለብንም፤ ዛሬ ቢጨልምብን ብርሃን ይሆናልና፡፡ ጻድቁ ኢዮብ ‹‹…በጎ ነገርን በተጠባበቅኋት ጊዜ እነሆ ክፉ ቀኖች መጡብኝ፤ ብርሃንን ተስፋ አደረግሁ›› በማለት እንደተናገረው ምንም እንኳን መከራና ችግራችን የተደራረበበት ወቅት ላይ ብንሆንም እነዚህ ክፉ ቀናት አልፈው በጎ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ማድረግ ይገባል፡፡ አባቶቻችን ‘ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም’ ይላሉ፤ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን በሙሉ የትኛውም ዓይነት ችግር ቢገጥመንም ሆነ መከራችን በዝቶ በሥቃይ ላይ ብንሆን አምላካችን እንደማይተወን ማመን አለብን፡፡ እግዚአብሔርን ተስፋ ያደረገ ሰው ወድቆ አይወድቅም፤ ከወደቀበትም ይነሣል፤ ፈጣሪ ሰውን አይረሳምና፤ እንደማያይና እንደማይሰማ ሆኖ ዝም የሚለን ለሁሉም ነገር ጊዜ ስላለው ነው፡፡ በትዕግሥት እርሱን ተስፋ አድርጎ ለሚጠብቀው ሰው ችግሩን ይፈታለታል፤ ከመከራና ከሥቃይም ያወጣዋል፡፡ ‹‹እንደማይሰጥ ይዘገያል›› እንደታበለውም ለሁላችንም የሚያስፈልገንን ከእኛ የበለጠ ለራሳችን የሚያውቅ አምላክ ስለሆነ በጊዜው የወደደውንና የፈቀደውን ያደርግልናል፡፡ (ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት)

አምላካችን እግዚአብሔር ተስፋችን ነው፤ ፈጣሪያችን መመኪያችን ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ እርሱን ያመነ ሰው ማንኛውንም የመከራ ጊዜ ማለፍ እንደሚቻለው ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ በተለይም በዚህ ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን በስደትና መከራ ላይ በሆነችበት ወቅት መለስ ብለን ታሪካችንን ልንመረምር እንደሚገባ እንወቅ!

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ እንደምናነበው ከሆነ ቅድስት የሆነችው የእግዚአብሔር ማደሪያና የክርስቲያኖች ቤት ቤተ ክርስቲያን በዘመናቱ በተነሡ አሕዛብ ነገሥታት ስትፈርስና ስትቃጠል  ኖራለች፡፡ በካህናትና ምእመናን ላይም ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል፤ በግፍ የተገደሉ፣ ቤት ንብረታቸው በቃጠሎ አልያም በዝርፊያ ያጡ ቁጥራቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ በዚህ ጊዜ የተመለከትነውና የታዘብነው እንዲሁም የመሰከርነው እውነት ነው፡፡ ሰዎች ያለ ጥፋታቸው ወንጀለኛ ተብለው ሲታደኑ፣ ሲታሠሩና በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ በዓይናችን አይተናል፤ ‘የፍርድ ያለህ’ እስክንል ድረስም ግፍ ተፈጽሞብናል፡፡ “ይህ ሁሉ ለምንድን ነው በእኛ ያለ የደረሰብን?’’ ብለን መጠየቅ ግን ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ፈተና ከብዙ አቅጣጫ የሚመጣ ነውና፤ አምላካችን ለጽድቅ ሲፈትነን ጠላት ደግሞ ቀንቶ ሊያጠፋን በመሆኑ ይህንን ተገንዝበን በሕጉ በመመራትና ለሥርዓቱ ተገዢ ሆነን እንኑር! ካልሆነ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በማይመለሱ ኃጢአተኞች የሚበረታ ስለሆነ ለተቃጣ መቅሠፍትና ቅጣት እንዳረጋለን፡፡

ተስፋ ከሚያሳጡን ዋነኛ ነገሮች ኃጢአት ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፤ በጎውን ትተን ክፋት ስናስብና ስንበድል ከአምላካችን ስለምንርቅ ለመዳንም ተስፋ አይኖረንም፤ ኃጢአት በሠራን ቁጥር ደግሞ እግዚአብሔርን እንደበደልን ስለምናውቅ ይቅርታንና ምሕረትን ማግኘት እንደማንችል ማሰብ እንጀምርና ከአምላካችን እየራቀን እንዲሁም የመዳን ተስፋችን እየመነመነ ይሄዳል፡፡ ኑሯችንም በጭንቅ የተዋጠና ሰላምና ዕረፍትን ያጣን እንሆናለን፡፡ ስለዚህም መልካሙን ሕይወት ለመኖርና በጎ ቀኖችን ለማየት ተስፋችን እግዚአብሔርን በመፍራትና ለእርሱ በመገዛት መኖር ያስፈልጋል፡፡

በእርግጥ የክርስትና ሕይወት መንገዷ ጠባብ መተላለፊያዋም ውስን እንደሆነ ይታወቃል፤ በመሆኑም “ሥርዓቱን መጠበቅ ይከብደናል” በሚል ሰበብ በተሳሳተ መንገድ መጓዝና በተጣመመ ጎዳና መራመድ መጨረሻው ገደል መግባት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ ‹‹ወደ ጠባቡ በር ትገቡ ዘንድ በርቱ›› በማለት እንደተናገረው ይህን እውነት ለተረዳ ሰው የመኖር ትርጉሙን ማወቅ ይቻለዋል፤ (ሉቃ.፲፫፥፳፬) ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ››  በማለት አምላካችን ተናግሯልና፤ (ዮሐ.፲፬፥፮) ትክክለኛው መንገድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረተው፣ መከራ መስቀሉን የምንቀበልበት፣ ለእርሱ ፍቅር ስንል ሥጋችንን የምናራቁትበት ከፍ ሲልም ሰማዕት የምንሆንበት የክርስትና ሕይወት ነውና፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ቸርነቱንና ምሕረቱን ያብዛልን፤ አሜን!