ተስእሎተ ቂሣርያ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፱ .

በየዓመቱ ነሐሴ ፯ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ የጌታችን በዓላት መካከል የተስእሎተ ቂሣርያ በዓል አንደኛው ነው፡፡ ‹ተስእሎተ ቂሣርያ›፣ የቃሉ (ሐረጉ) ትርጕም ‹በቂሣርያ አገር የቀረበ ጥያቄ› ማለት ሲኾን፣ ይኸውም ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል?›› ብሎ ደቀ መዛሙርቱን መጠየቁን ያስረዳል፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታችን በቂሣርያ አውራጃ ሐዋርያቱን ሰብስቦ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስን) ማን ይሉታል?›› ብሎ ሲጠይቃቸው እነርሱም ‹‹ዮሐንስ፣ ኤልያስ፣ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ባቀረበላቸው ጊዜ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፤ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዳ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽም ሰዎች ስለ ክርስቶስ ማንነት ከሚሰጡት ግምትና ከሐዋርያት ዕውቀት በላይ በመኾኑ ጌታችን ‹‹የእኔን አምላክነት ሰማያዊ አባቴ ገለጸልህ እንጂ ሥጋዊ ደማዊ አእምሮ አልገለጸልህም›› በማለት በአንክሮ ተቀብሎታል፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ስለ እርሱ የሚናገሩትንም፣ የሚያስቡትንም የሚያውቅ አምላክ ሲኾን በቂሣርያ ሐዋርያቱን ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል›› ብሎ መጠየቁ በአንድ በኩል አላዋቂ ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ፤ በሌላ ምሥጢር ደግሞ አምላክነቱን ለመግለጥ፣ እንደዚሁም መዓርገ ክህነትን ለሐዋርያትና ለተከታዮቻቸው (ለጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት) ለመስጠት ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽና ጌታችን በሰጠው ሥልጣን ይታወቃል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ልጅነትና የባሕርይ አምላክነት ከመሰከረ በኋላ ጌታችን፣ ‹‹አንተ ዓለት (መሠረት) ነህ፤ በአንተ መሠረትነት ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፡፡ የገሃነም ደጆች (አጋንንት) አይችሏትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ፡፡ በምድር ያሠርኸው በሰማይም የታሠረ፤ በምድር የፈታኸው በሰማይም የተፈታ ይኾናል›› በማለት ለአብያተ ክርስቲያናት መስፋፋት፣ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎትና ለምእመናን ድኅነት ምክንያት የኾነውን መዓርገ ክህነት ሰጥቶታል (ማቴ. ፲፮፥፲፫-፲፱)፡፡

ይህ ሥልጣነ ክህነት በቅዱስ ጴጥሮስ አንጻር ከሐዋርያት ጀምሮ ለሚነሡ አባቶች ካህናት የተሰጠ ሰማያዊ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ምእመናን በኃጢአት ስንወድቅ ከካህናት ፊት ቀርበን የምንናዘዘውና ንስሐ የምንቀበለው፤ በመስቀሉ እየተባረክን ‹‹ይፍቱን›› የምንለው ጌታችን ለሐዋርያት የሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አባቶች ካህናትም ‹‹ይኅድግ ይፍታሕ ያንጽሕ ወይቀድስ …›› እያሉ በመናዘዝ ‹‹እግዚአብሔር ይፍታ›› የሚሉን ከባለቤቱ የማሠርና የመፍታት ሥልጣን ስለ ተሰጣቸው ነው፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው እንደሚያስረዱት ጌታችን ሐዋርያቱን ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› ብሎ ከጠየቃቸው በኋላ ምላሻቸውን ተከትሎ ሥልጣነ ክህነትን መስጠቱ በብሉይ ኪዳን (እግዚአብሔር አምላክ በሥጋ ከመገለጡ በፊት) አዳም የት እንዳለ እያወቀ ‹‹አዳም ሆይ ወዴት ነህ?›› (ዘፍ. ፫፥፲) ብሎ ከጠየቀውና ያለበትን እንዲናገር ካደረገው በኋላ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚል የድኅንት ቃል ኪዳን መግባቱን ያስታውሰናል፡፡ እግዚአብሔር በሦስትነቱ ከአብርሃም ቤት በገባ ጊዜ ሣራ ያለችበትን ቦታ እያወቀ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል አብርሃምን ያለችበትን ቦታ እንዲናገር ካደረገው በኋላ ‹‹ሣራ ልጅን ታገኛለች›› የሚል ቃል መናገሩም ከዚህ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ቃሉም በአንድ በኩል የይስሐቅን መወለድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት የሚያጠይቅ ነው (ዘፍ. ፲፰፥፱-፲፭)፡፡

በሐዲስ ኪዳንም አልዓዛር በሞተ ጊዜ ጌታችን የተቀበረበትን ቦታ እያወቀ ‹‹አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት›› ብሎ መካነ መቃብሩን ከጠየቀ በኋላ በሥልጣኑ ከሞት እንዲነሣ ማድረጉም ከተስእሎተ ቂሣርያ እና ከላይ ከጠቀስናቸው ምሳሌዎች ጋር የሚወራረስ ምሥጢር አለው (ዮሐ. ፲፩፥፴፯)፡፡ ይኼ ዅሉ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ሐሳባቸውን ያላወቀ መስሎ እየጠየቀ ሰዎች ስሜታቸውን እንዲገልጡ እንደሚያደርግ፤ የልባቸውን መሻትና እምነት መሠረት አድርጎም ሥልጣንን፣ በረከትን፣ ጸጋንና ፈውስን እንደሚያድላቸው የሚያስረዳ ትምህርት ነው፡፡ ለዚህም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው በአካለ ሥጋ ሲመላለስ መዳን እንደሚፈልጉ እያወቀ ‹‹ልትድን ትወዳለህን? ልትድኚ ትወጃለሽን? ልትድኑ ትወዳላችሁን?›› ብሎ እየጠየቀ የልባቸውን መሻት እንዲናገሩ ካደረገ በኋላ የእምነታቸውን ጽናት አይቶ በአምላካዊ ቃሉ ‹‹ፈቀድኩ ንጻሕ፤ ፈቀድኩ ንጽሒ፤ ፈቀድኩ ንጽሑ = ፈቅጃለሁ ተፈወስ፤ ፈቅጃለሁ ተፈወሺ፤ ፈቅጃለሁ ተፈወሱ፤›› እያለ ለሕሙማነ ሥጋ ወነፍስ ፈውስን ማደሉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡

ትምህርቱን ወደ እኛ ሕይወት ስናመጣው ዛሬ ዓለም ክርስቶስን ማን ትለዋች? እኛስ ማን ብለን እንጠራዋለን? ምላሹ እንደየሰዉ የመረዳት ዓቅም ሊለያይ ይችላል፡፡ እውነታው ግን አንድ ብቻ ነው፤ በእርግጥ እግዚአብሔር አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሕዝቡን እንዳዳነ ያልገባት ዓለም ክርስቶስን ከፍጡራን ተርታ ትመድበዋለች፡፡ የእርሷ የፍልስፍና ሐሳብ አራማጆች መናፍቃንም አምላክነቱን ክደው ‹‹አማላጅ ነው›› ይሉታል (ሎቱ ስብሐት)፡፡ ሌሎችም እንደየዓቅማቸው ለክብሩ በማይመጥን ልዩ ልዩ ስም ይጠሩታል፡፡ በሐሰተኛ ትምህርታቸውም ብዙ የዋሃንን አሰናክለዋል፡፡ እርሱ ባወቀ ወደ ቤቱ ይመልሳቸው እንጂ፡፡ እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን እርሱ ባለቤቱ፣ ቅዱሳን ሐዋርያትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ አካላት አንዱ፤ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር (አምላክ ወልደ አምላክ)፤ በቈረሰው ሥጋ፣ ባፈሰሰው ደሙ ከዘለዓለማዊ ሞት ያዳነን የዅላችን ቤዛ እንደ ኾነ እናምናለን፤ እንታመናለን፡፡ ይህን ሃይማኖታችንንም ለዓለም በግልጽ እንመሰክራለን፡፡ እርሱም በምድር እንደየእምነታችን መጠን መንፈሳዊ ጸጋን፣ በረከትን፣ ፈውስን ያድለናል፡፡ በሰማይም እንደየሥራችን ዋጋ ይከፍለናል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን እንደ እኛ ድክመት ሳይኾን እንደ ቸርነቱ ብዛት ስሙን ለመቀደስ፤ መንግሥቱንም ለመውረስ ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡