የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ፳፻፲፯ ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት ዐዋጅ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተላለፈ የምህላ ሱባኤ፡-

‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ አስተጋብኡ ሕዝበ ሊቃውንተ ሕዝብ፤ ጾምን ቀድሱ፣ ጉባኤውንም ዐውጁ፤ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ።›› (ኢዩ.፩÷፲፬)

ሁላችንም እንደምናውቀው ያለንበት ዓለም የመከራ ዓለም ነው፣ መከራው በኛ ስሕተትና ክፋት የመጣና እየሆነ ያለ መሆኑም ይታወቃል፤ እኛ የምንፈጽመው ጥቃቅንና ትላልቅ ግብረ ኃጢአት እግዚአብሔርን እንደሚያስቈጣ በቅዱስ መጽሐፍ ተረጋግጦ ያደረ ነው፤ ለዚህም ከነነዌ ነዋሪ ሕዝብ የበለጠ ማስረጃ የለንም፤ የነነዌ ከተማ ነዋሪዎች በፈጸሙት ግብረ ኃጢአት እግዚአብሔርን አስቈጥተዋል፤ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ ቢሆንም እሱ ምሕረቱን ማስቀደም ስለፈለገ በዮናስ በኩል አስጠንቅቆአቸዋል፤ የነነዌ ነዋሪዎችም በዮናስ በኩል የደረሳቸውን የንስሓ ጥሪ ወዲያውኑ ተቀብለው በምህላ፣ በጾም፣ በጸሎት ንስሓ ስለገቡ እግዚአብሔር ፍጹም ይቅርታ አድርጎላቸዋል፤

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን!

እኛ ሰዎች ዛሬም በየሰዓቱ ብቻ ሳይሆን በየደቂቃው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ አበሳ እንደምንፈጽም ማወቅ ኣለብን፣

አበሳውና ኃጢኣቱ ሲበዛ እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ ነውና ወደ ዳኝነት ተግባሩ ይገባል፤ይህ ደግሞ በሰብአ ትካት በሰዶምና በጎሞራ ያስተላለፈውን ዳኝነት ያስታውሰናል፤ አሁን ያለንበት ዘመን ዓመተ ምሕረት በመሆኑ እግዚአብሔር ለጊዜው ቢታገሠንም በኃጢኣታችን የምንጠየቅበት ጊዜ አዘጋጅቶአል፤ ዛሬም ቢሆን የማናስተውለው ሆነን ካልሆነ በስተቀር እግዚአብሔር ተግሣጹን ማስተላለፍ አላቆምም፤ በምድራችን ላይ በምናደርሰው የተዛባ ተግባር በጐርፍ፣ በድርቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በአየር መዛባት እየገሠጸን እንደሆነ ማስተዋል አለብን።

እግዚአብሔር ከጥንቱ ከጠዋቱ ጀምሮ ምድርን እንድንከባከባት፤ እንድናበጃት፣ እንድናጠብቃትና እንድናለማት አዞናል፤ ሆኖም ይህን ትእዛዙን ገሸሽ አድርገን በኬሜካልና በመርዛም ጋዝ ምድርን በመበከል፣ደንዋን በመመጠርና ራቁቷን በማስቀረት በምናደርገው ድርጊት አበሳ እየፈጸምን እንደሆነ ያወቅነው አይመስልም፤ በዚህም ምክንያት በጐርፍ፣ በድርቅ ለሰው ልጆች በማይመች የኣየር ፀባይ ወዘተ . . . ስጋት ውስጥ እየወደቅን ነው፤

በሌላም በኩል በምናወሳስበው የአስተዳደር ርእዮትና መሳሳብ የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጋጭና ያላስፈላጊ አደጋ ላይ እንድወድቅ እያደረግን ነው፤ በዚህም ጠንቅ ሰላም እየደፈረሰ፣ ፍቅርና አንድነት እየላላ የሃይማኖት ክብርና ልዕልና እየተነካ ራሳችንንም እየጐዳን ነው፤በዚህ ሁሉ ተግባራችን እግዚአብሔርን እያሳዘንን ነው፤ ይህ ሊገባንና ሊቈረቁረን ይገባል፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ አላቸው፤ መፍትሔውም የሚገኘው ከእግዚአብሔርና ከእኛ ነው፤ ከእኛ በንስሓ ተመልሰን ከልብ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅና ከክፉ ተግባራችን በእውነት መጸጸት ይጠበቃል፤ እግዚአብሔር ደግሞ ይህንን ዓይነቱ ንስሓ ከኛ መኖሩ ሲመለከት ምሕረትና ይቅርታን ይለግሰናል፤በዚህም መፍትሔና ፈውስ ይገኛል፤ ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ ለሀገራችንና ለዓለማችን ስጋት የሆኑ የጦርነት ክሥተቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የአየር መዛባት፣የድርቅ መከሠት፣የጎርፍ መጥለቅለቅ የሰላም መደፍረስ፣ የሰላማውያን ወገኖች መጎዳት፣ የፍቅርና የአንድነት መላላት ወዘተ. . . . ከምድራችን ተወግደው ፍጹም ምሕረትና ሰላም እናገኝ ዘንድ በኃጢኣታችን ተጸጽተን በምህላ ንስሓ መግባት አለብን፤ ከዚህ አኳያ ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ የሚጾመው ጾመ ነነዌ ለዚህ አመቺ ጊዜ ስለሆነ ከየካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ለሦስት ቀናት ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ሁላችንም ጠዋትና ማታ በየቤተክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት እየተገኘን በንስሓ በዕንባ በጸሎት በምህላ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ እንድንጠይቅ፤ እንደዚሁም በሀገራችንና በውጭ ያላችሁ ሊቃውንተ ሕዝብ ቀኖናውን ጠብቃችሁ ይህንን በማስፈጸም ምህላውን በቀኖናው መሠረት እንድታከናውኑ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤

እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረቱን ይቅርታውንና ሰላሙን ለሀገራችንና ለዓለማችን ይስጠን፤ ምህላችንንም ይቀበልልን፤

“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስምወዕጨጌ
ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ጥር ፳፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ