ብፁዕ አቡነ አብርሃም እየተዳከመ የመጣው የብራና መጽሐፍ ዝግጅት ዳግም ማንሠራራቱን ገለጹ
ሐመረ ብርሃን የብራና መጻሕፍት ሥራ ድርጅት በኅዳር ፲፭፤ ፳፻፲፯ ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት በአካሄደው የምስጋና መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ባስተላለፉት መልእክት የብራና መጽሐፍት ዝግጅት ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ እየተዳከመ የመጣ ቢሆንም ዛሬ ላይ በዚህ መልክ እያደገ መምጣቱ የሚያስደስት መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው “አባቶቻችን በድካም ያቆዩልንን ትውፊትና ታሪክ አንዱም ሳይዛባ እንዲቀጥል አጥብቃችሁ ያዙ” ሲሉም አባታዊ ምክርና መመሪያ ሰጥተዋል።
የቀደመ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጥበብና ዕውቀት ለማስፋፋት እየሠራ የሚገኘው የብራና መጻሕፍት ሥራ ድርጅት ሐመረ ብርሃን ለዚህ ውጤት ጉልህ ሚና እንዳለው በምስጋና መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት አባላት እማኖች እንደሆኑም ተነግሯል፡፡
በተጓዳኝ ድርጅቱ የብራና መጽሐፍት ዝግጅቶችን አጠናክሮ ውጤታማ ለማድረግ የቻለው ለስኬታማ ጉዞው ጉልህ ሚና በነበራቸው ባለ ድርሻ አካላት እንደሆነ ባዘጋጀው የምስጋና መርሐ ግብር ላይ አስታውቋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የተገኙትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ አቡነ እንድርያስ ፣ የዴንቨርና ኮሎራዶ አካባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ነበሩ።
በዕለቱ የመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የጓንቻ ገዳም አቡነ ተጠምቀ መድኅን ገዳም፣ ደብረ ድማኅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ ማኅበረ ቅዱሳን እና ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ተቋማት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እጅ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።