ቤተ ክርስቲያናችን ይቅርታ ልትጠየቅ እንደሚገባ ተገለጸ
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዐድዋ ጦርነት ጊዜ በአገሩ ላይ የደረሰውን ሽንፈት ለመበቀል ሲል የኢጣልያ ፋሽስት መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ላይ ላደረሰው ቃጠሎ፤ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአባቶች ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና መነኮሳት እንደዚሁም በምእመናን ላይ በግፍ ለፈጸመው ጭፍጨፋ የጣልያን መንግሥት እና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን (ቫቲካን) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እና ኢትዮጵያን ይቅርታ መጠየቅ፤ የኢጣልያ ፋሽስት መንግሥት ከየገዳማቱና አድባራቱ የዘረፋቸውን ንዋያተ ቅድሳት፣ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን እና አገራዊ ቅርሶቻችንንም መመለስ እንደሚገባቸው ተገለጸ፡፡
ይህ ሐሳብ የተገለጸው በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል አዘጋጅነት የማኅበሩ አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በአጠቃላይ በርከት ያሉ ምእመናንና ምእመናት በታደሙበት በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አዳራሽ የካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በተካሔደው የጥናት መርሐ ግብር ላይ ሲኾን ፣ በዕለቱ ‹‹በኢትዮጵያ ላይ የፋሽስት ኢጣልያ ወረራ እና የሮሙ ፖፕ ፒዮስ ፲፩ኛ አቋም›› እና ‹‹ቅኔ ዘዝክረ ዐድዋ›› በሚሉ አርእስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፤ በጥናቶቹ ዙሪያ ከታዳሚዎች ለተነሡ ጥያቄዎችም በጥናት አቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ላይ የፋሽስት ኢጣልያ ወረራ እና የሮሙ ፖፕ ፒዮስ ፲፩ኛ አቋም›› የሚለው ርእሰ ጉዳይ አቅራቢ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ፋሽስት ኢጣልያ አገራችን ኢትዮጵያን በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም በወረረበት ወቅት የጊዜው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ወረራውን እና በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን ግፍ በዝምታ መመልከታቸው ተገቢ አለመኾኑን አስታውሰው ፖፑ ወረራውን ሊያወግዙ ያልቻሉበት ምክንያትም፡- በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በኢጣልያ መንግሥት መካከል ጥላቻ እንዳይፈጠር በመስጋታቸው፤ በዘመኑ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በካህናቱ መካከል ከባድ ተቃውሞ ስለነበር በመካከላቸው ግጭት እንዳይፈጠር በማሰባቸው እንደኾነና ዋነኛው ምክንያት ግን የኢጣልያ ኢትዮጵያን መውረር የካቶሊክ ሃይማኖትን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት መልካም ዕድል ይፈጥራል ብለው በማመናቸው እንደኾነ በጥናታቸው አትተዋል፡፡
ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ አያይዘውም ፖፑ የወቅቱ የኢጣልያ ፋሽስት መንግሥት ‹‹በእግዚአብሔር ፈቃድ የተነሣ፣ በሊበራሊዝም አስተሳሰብ ያልተሞኘ መንግሥት ነው›› ብለው ያምኑ እንደነበር፤ በወቅቱ ስለወረራው ሲጠየቁ ለሚድያዎች የሰጡት ምላሽም ፖፑ ለጦርነቱ የነበራቸውን ጥሩ አቋም እንደሚያመለክት፣ ለአብነትም በአንድ ወቅት ‹‹ራስን የመከላከል ጦርነት ነው›› ሲሉ ስለ ወረራው አስፈላጊነት እንደተናገሩ፤ የአገሪቱ መንግሥት ኢትዮጵያን ሊወርር ሲዘጋጅ ሙሶሎኒ በሮም ከተማ ንግግር በሚያደርግበት ጊዜ መላው የሮም ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ደወሎች ለረጅም ሰዓት ሲደወሉ እንደነበር፤ ይህም የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ በኢጣልያ እንድትወረር የነበራትን ፍላጎት እንደሚያመለክት ባለጥናቱ ጠቁመዋል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወረራውን በገንዘብ ደግፋለች ተብላ ቤተ ክርስቲያኗ ተከሳ እንደነበር ያወሱት ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ፣ ፋሽስት ኢጣልያ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላም ‹‹እጅግ የሚያስደስት ድል›› በማለት ፖፕ ፒዮስ ፲፩ኛ ጦርነቱን ማድነቃቸው ፖፑ የፋሽስት መንግሥት እና የወረራው ደጋፊ እንደነበሩ አንዱ ማሳያ መኾኑን ልዩ ልዩ ምንጮችን ዋቢ አድርገው የፖፑን አቋም ለጉባኤው አስረድተዋል፡፡
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለፋሽስቱ ሠራዊት በስውር የሞራል ድጋፍ ከማድረጓ ባሻገር የኢጣልያ ፋሽስት መንግሥት በየጊዜው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አድባራትና ገዳማት ላይ ቃጠሎና የቅርስ ዘረፋ ሲያካሒድ፤ እንደዚሁም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን እና ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን በግፍ ሲረሽን፤ በአባቶች ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ምእመናን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጽም በዝምታ መመልከቷ (ድርጊቱን አለማውገዟ) የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የወረራው ደጋፊ እንደነበረች የሚያስገነዝብ ሌላኛው ነጥብ መኾኑን በመጥቀስ ለዚህ ዅሉ በደልም የጣልያን መንግሥት እና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን (ቫቲካን) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ፤ ለጥፋታቸውም ተመጣጣኝ ካሣ መክፈል፤ ከየገዳማቱና አድባራቱ የተዘረፉ ንዋያተ ቅድሳትን፣ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን እና አገራዊ ቅርሶቻችንንም ለአገራችን መመለስ እንደሚገባቸው ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ሐሳብ መሳካትም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍ እንዲያደርጉ በማሳሰብ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አጠቃለዋል፡፡
‹‹ቅኔ ዘዝክረ ዐድዋ›› የሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ቀሲስ ኃይለ ኢየሱስ አለባቸው ደግሞ ከአድዋ ጦርነት በፊት፣ በጦርነቱ ወቅት እና ከድሉ በኋላ የተደረጉ አንዳንድ ጥንታውያን የግእዝ ቅኔያትን ትርጕምና ምሥጢር ከታሪክ መጻሕፍት ጋር አነጻጽረው በማቅረብ በቅኔአቸው ንጉሡንና ሠራዊቱን በማበረታታት ለአገራችን ድል ማግኘት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽዖ በጥናታቸው አተተዋል፡፡
አባቶቻችን በዐድዋው ጦርነት ኢጣልያን ድል ማድረግ የተቻላቸው በወታደር እና በጦር መሣሪያ ብዛት ሳይኾን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳዒነት መኾኑን ያስታወሱት ቀሲስ ኃይለ ኢየሱስ ‹‹አዲስ ቅኔ መቀኘት ባንችልም እንኳን አባቶቻችን የፈጸሙትን የዐርበኝነትና የድል አድራጊነት ታሪክ እያነበብን የመወያያ አጀንዳችን ልናደርገው ይገባል›› ሲሉ ትውልዱ የአባቶቹን ውለታ መርሳት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡
በመጨረሻም በጥናታዊ ጽሑፎቹ ላይ ውይይት ከተደረገ እና ከመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ለተነሡ ጥያቄዎች በጥናት አቅራቢዎቹ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ መርሐ ግብሩ በአባቶች ጸሎት ተፈጽሟል፡፡