በጸሎትህ ጠብቅ!
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ታኅሣሥ፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ከቅዱሳን አበው የሆነ ውልደትህ
የጸሎታቸው መልስ ለእናት ለአባትህ
ክብርህ እጅግ በዛ ተወደደ ሥራህ
ፍጥረት ያስደሰተ የውልደትህ ዜና
ገና ሕፃን ሳለህ የጀመርክ ምሥጋና፡፡
ጽድቅን ተጎናጽፈህ ወንጌል ተጫምተሃል
በጉብዝናህ ወራት መስቀሉን ሽተሃል፡፡
እንደ ጠዋት ጤዛ በምትረግፈው ዓለም
ልብህ ሳይሸነፍ ለምቾት ሳትደክም
ከትዳርህ ይልቅ ምንኩስናን መርጠህ
ከጫጉላ ቤት ወጥተህ በረኃ ተገኘህ፡፡
እንጦንስ አባትህን አርገህ አርአያ
የመላእክት አስኬማን የለበስህ ሐዋርያ
እልፍ አእላፍ ያፈራህ የጽድቅ ዘንባባ
ቃል ኪዳንህ ጽኑ መጠለያ አንባ
ከሰይጣን ተጋድለህ ያሸነፍክ አርበኛ
ዐቃቤ ሃይማኖት የሥርዓት ዳኛ፡፡
አራቱን ወንጌላት ዞረህ አስተምረሃል
በመብረቅ ጸሎትህ አጋንንት ጠፍተዋል
ትዕግሥት ጽንአትህ በአምላክህ ተደንቋል፡፡
መምህረ ሰላም፣ ፍቅር፣ ወአንድነት ለአንተ ይገባሃል፡፡
ስለ አምላክህ ክብር የተጋደልክ ጸንተህ
እንደ ተወደደ የዘይት ዕንጨት ነህ፡፡
የተጋድሎህ ፍሬ መዓዛው ያውዳል
እልፍ አእላፍ አምነው ባንተ ተጠምቀዋል፡፡
የብርሃን ደመና ጠቅሰህ ተጉዘሃል
በጸሎትህ ኃይል ሙት አስነስተኻል፡፡
ገድል ተአምርህን የወንጌሉን ሥራ
አቡነ ዜና ማርቆስ ሆይ…
መካነ ጸሎትህ ደብረ ብሥራት ታውራ፡፡
የሚታዘዙልህ ንስርና አሞራ
በአሕዛብ ሁሉ ፊት ብርሃንህ በራ፡፡
በኪደተ እግርህ ኢትዮጵያን ቀደስካት
ለእግዚአብሔር መንግሥት ሙሽራ አረካት፡፡
አጋንንት ከፊትህ እንደ ጢስ በ’ነዋል
ኃይል ጽንዐቱን ክርስቶስ ሰጥቶሃል፡፡
ቅዱስ ቃል የዘራህ ትጉሁ ገበሬ
ማደሪያህ የሆነች …ኢትዮጵያ ሀገሬ
ዛሬም በጸሎትህ ታፍራ መቶ ፍሬ፡፡
የጸጋህ ብርሃን ጨለማዬን ትግፈፍ
በረከት ጸሎትህ ለትውልዱ ትትረፍ
ጣፋጩ መዓዛህ ዘወትር ይሽተተኝ
ረደረኤት በረከትህ ሁሌም ትጠብቀኝ፡፡
ሕግና ሥርዓትን ያስተማርክ ጻድቅ
አቡነ ዜና ማርቆስ…
የመንፈሴን ዝለት በጸሎትህ ጠብቅ!