‹‹በጠበበው ደጅ ግቡ›› (ማቴ.፯፥፲፫)
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
ግንቦት ፳፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ወዳጄ ሆይ! የምትጓዝበትን መንገድ የማታውቅ ከሆነ ትጠፋለህና በየትኛው መንገድ ላይ ልትራመድ እንደሚገባህ ልታገናዝብ ያስፈልግሃል። በፊትህ ሰፊ፣ አታላይና ጠባብ መንገዶች አሉና፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋቸዋል። ‹‹በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጁ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፤…፡፡›› (ማቴ.፯፥፲፫)
ሰዎች በተመሳቀለ መንገድ ላይ እንደደረሱ በመጀመሪያ ሊያሳቡ የሚችሉት እንዲህ ባለው ሰፊ መንገድ ነው። በዚህ መንገድ ላይ ለሚራመድ ሰው የመንገዱ ስፋትና ቅለት ለእርሱ አመቺ ይሆናል። ይህን መንገድ የሚመርጡ ሰዎች እጅግ ብዙዎች ናቸው!
አንድ ሰው ሰፊውን መንገድ ወደ መብት እና ወደ ነጻነት ወደ ደስታ እንዲሁም ገደብ እና ወሰን ወደ ሌለበት ሕይወት የሚመራ መንገድ ነው ብሎ ሊያስብ ይችላል። በእርግጥም እነዚህ ሁሉ ነገሮች በሰፊው መንገድ በስፋት ይገኛሉ። በሰፊው መንገድ ውስጥ፦ እስከ አረመኔነት ድረስ የሚያደርስ ወሰን ያጣ ነጻነት አለ፤ ወደ ዋልጌነት የሚለውጥ ወሰን የለሽ መብት አለ። ለኃጢአት ባርነት ሊዳርጉ የሚችሉ ድርጊቶችንም በውስጡ ይዟል። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ።
አጸያፊ አነጋገሮችና ቀልዶች፣ የሚያሰክር የወይን ጠጅ
ለዝሙት የሚዳርጉ ተግባራት
የቁማር ገበታዎችና ምግባር የለሽ ቧልቶች
ነውረኛና ኀፍረት የሌለባቸው የምንዝር ጌጥ መዋቢያዎች
ሴሰኝነትና ዝሙት እንዲሁም ማንኛውም ዓይነት የሥነ ምግባር ጉድለቶች
ሕገ ወጥነትና በዓመፅ የተሞላ ራስ ወዳድነት
በዚህ ሰፊ መንገድ ላይ የሚጓዙ ሰዎች ከኅሊና ወቀሳ ለማምለጥ ኃጢአትን የሚሠሩት ዓለማዊ በሆኑ አስተሳሰቦች ነው፤ የእነርሱን እምነት የማይጋሩትን ደግሞ ኋላ ቀር እና ጤናማ እንዳልሆነ በማሰብ ዝቅ አድርገው ይመለከቷቸዋል።
በመንገዱ ላይ ከመጓዝህ በፊት በጥንቃቄ መርምር፤ ስለ ስፋቱ ስትል እንዳትታል ተጠንቀቅ። ከጊዜያዊ ደስታና ከአካላዊ ሴሰኝነት በስተጀርባ ተሸሽገው ያሉትንና በግልጽ የሚታዩትን ነውሮች ልትመረምር ግድ ነው። ይህን መንገድ የሚመርጡ ሰዎች የሚሸከሙት መከራ እጅግ የበዛ ነውና። ከእነዚህም መካከል ሰላም ማጣት፣ ግራ መጋባትና ድንጋጤ ይገኙበታል።
ወዳጄ ሆይ! እንዲህ ያለው ሰፊ መንገድ እንዴት ወዳለው መጨረሻ እንደሚያደርስህ ተገነዘብህ? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምን በማለት እንደ ተናገረ አድምጥ! ‹‹ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጁ ሰፊ መንገዱም ጥልቅ ነው፡፡›› የዚህ መጨረሻ አስቀያሚና የማያስደስት ነው፤ በዚያ ያሉት የማያንቀላፉ ትሎች እና የማይጠፋ እሳት ናቸውና። በዚያ ያለው በእሳትና በዲን የተሞላ ባሕር ነውና። በዚያ ያለው ድቅድቅ ጨለማ እጅግ ያስፈራልና። ይህ ሁሉ በኃጢአተኞች ላይ የሚደርሰው ሥቃይ ዘለዓለማዊ ነውና።
ለሁለተኛው ሕይወት ለጥቂት ጊዜ ያህል እንኳን ዕድል እንዲኖራቸው ከሚመኙ ምን ያህሉ ምስኪኖችና ጎስቋሎች በሆኑ ነበር! እነርሱ ለዚህ ዕድል ቢኖራቸው ይህን አስፈሪ ሥቃይ ከነ ሽብሩ ለማምለጥ በዕንባ ንስሓ በገቡ ነበርና።
አንቺ ጎስቋላ ነፍሴ ሆይ፦ ኃጢአት ዓይኖችሽን ጋርዶ ወደዚያ ደስታ ወደሌለበት መጨረሻ እንዳይመራሽ እጅግ እፈራለሁ! የሚያነሆልለው የዚህ ዓለም ሙዚቃ ልብሽን ምርኮኛ አድርጎ ጥፋትሽን እንዳያመጣብሽም እጅግ እፈራለሁ! ሣሩን አይቶ ገደሉን ሳያይ ጭልጥ ካለው ገደል ውስጥ ገብቶ እንደተንኮታኮተው በሬ ዓይነት ማለት ነው። እነዚህ ሰዎች ወደ ራሳቸው ሲመለሱ ራሳቸውን በዚያ አስፈሪ ባሕር ውስጥ ያገኙታል ማለት ነው።
ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው›› በማለት እንደተናገረው ከሰፊው መንገድ የበለጠ እጅግ በጣም አደገኛ መንገድም አለ፤ (ምሳ.፲፬፥፲፪) መንገዱ እንደ አታላይ ባልንጀራ አደገኛ ነው። የዚህ መንገድ አደገኛነት የሚገለጸው በሥውርነቱና በአታላይነቱ ነው። ብዙ ሰዎች ታዳኝ ሆነው የሚያዙት በአታላዩ መንገድ ወጥመድ ውስጥ ነው። የዋሁንም ጭምር የማሳት ኃይል ሊኖረው ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ ጥፋት የሚዳረጉት ሰዎች በጽኑ እምነት፣ በሃይማኖትና በክርስቲያናዊ ምግባር መኖር ያልቻሉት ናቸው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጠባይ ኮንኖታል፤ እንዲህ በማለት፦ ‹‹በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ፤ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።›› (ራእ.፫፥፲፭-፲፮) እኔ ደግሞ ለራስህ ታማኝና ጽኑ እንድትሆን እመኝልሃለሁ፤ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ካለው ጎጂ መንገድ ማታለያዎች ነጻ ያወጣህ ዘንድ ለምነው!
ወዳጄ ሆይ! መስቀለኛ መንገድ ላይ ስትደርስ ደጁ የጠበበ የቀጠነ መንገድ ታገኛለህና ተመልከት። ይህ መንገድ እጅግ ጠባብ ይሁን እንጂ ቀጥተኛና መልካም መንገድ ነው። በመንገዱ መጓዝ ከባድ ቢሆንም እውነተኛ ነውና አትፍራ! ከዓለማዊና ሐሰተኛ ከሆነው ደስታ የተለየ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ጌታችን በመስቀሉ ቤዛነት የመሠረተው መንገድ በመሆኑም ራሱ በቃሉ ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› በማለት አረጋግጦልናል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፮)
በዚህ መንገድ ላይ ሊራመዱ የሚችሉ መንፈሳውያን የሆኑ ወይም መንፈሳዊያን ለመሆን በጎ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ሥጋዊው ወይም ዓለማዊው ሰው በዚህ መንገድ ላይ ሊራመድ አይችልም። ስለዚህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት አማካኝነት ዓለማዊውን ሰው ከመንፈሳዊው ሰው መለየት ግድ እንደሆነ ተምረናል፤ ‹‹ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው›› እንዲል፡፡(ዮሐ.፫፥፮)
መልካሙ መንገድ ጠባብ የሚሆነው ለሥጋውያን ሰዎች ነው። ምክንያቱም እነርሱ በመንገዱ ውስጥ ለሥጋዊ ድሎታቸው፣ ለሴሰኝነታቸው፣ ለመዳራታቸውና ለአመንዝነታቸው የሚሆን ቦታ አያገኙም። የክብር አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እነርሱ ሲናገር ‹‹ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጁ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና፤ የሚያገኙም ጥቂቶች ናቸው›› ብሏል፡፡ (ማቴ.፯፥፲፬)
በዚህ መንገድ መጓዝ የሚችሉ ጥቂት መሆናችውን፣ ብዙ ሰዎች የሚመርጡትም ሰፊውን መንገድ መሆኑን ጌታችን በቃሉ ነግሮናል፤ መንፈሳውያን ሰዎች ይህን መንገድ የሚመለከቱት መልካም እንደሆነ አድርገው ነው፤ በውስጡ የደስታቸው ምንጭ እና የርካታቸው ምሥጢር ስለሆነ ማለት ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንዲህ በማለት አዞናል፡፤ ‹‹የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ … በእርስዋም ላይ ሂዱ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፡፡›› (ኤር.፮፥፲፮)
ለመንፈሳዊው ሰው ይህ በፈተናና በመከራ የተሞላ መንገድ ወደ ዕረፍት የሚያወጣ ነው፤ መጥበቡ ወደ ስፋት፣ ኀዘኑም ወደ ደስታና ሐሴት ይለወጥለታል፤ ይህ ሥጋ የሚታረምበትና ነፍስ አርነት የምትወጣበት መንገድ ነው፤ በዚህም ዋጋችንን እናገኝበታለን፡፡
በመጨረሻም መንገዱ ወደ አምላካችን እግዚአብሔር፣ ዘወትር ወደ ምታበራው፣ ፀሐይዋ እስከ መቼም ድረስ ወደ የማይጠልቅባት፣ የአዕላፋት መላእክት ኅብረት ወደ ሚታይባት፣ ወደ አጠቃላዩ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ያደርሳል። ስለዚህ በመልካሙ መንገድ ልንጓዝ እንደሚገባ ቤተ ክርስቲያን ያስተማረችንን ቃል በማሰብ ልንኖር ይገባል!
“ነፍሴ ሆይ! በሐሴት ዕረፍት ታደርጊ ዘንድ መልካም በሆነው መንገድ ላይ ተጓዢ! እግዚአብሔር አምላክም እርምጃዎችሽን ወደ ሰላም ማደሪያ ይምራልሽ!‘’ አሜን!
ምንጭ፦ መንፈሳዊው መንገድ፣ የንስሓ ሕይወት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባት ዘካርያስ ቡትሮስ እንደጻፉት።