በጎ መካሪ
ዲያቆን ዘኪዩስ አደሙ
ጳጉሜ ፫፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
የሰውን ልጅ የውድቀት ታሪክ ስንመለከት፣ የመጀመሪያው መንሥኤ የክፉ ምክር ውጤት እንደሆነ እንረዳለን። አባታችን አዳም የእግዚአብሔርን ሕግ ጠብቆ ለሰባት ዓመታት ያህል በገነት ቢኖርም፣ በሰይጣን ክፉ ምክር ተታሎ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን የመሰለ ቦታ አጥቷል። ይህ የሆነው በክፉ ምክር ምክንያት ነው። ዛሬም በዚህች ምድር፣ እንደ ጥንቱ ሁሉ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በክፉ ምክር የሚያታልሉና ላልተገባ ነገር የሚዳርጉ ክፉ አማካሪዎች አይጠፉም።
በተቃራኒው ደግሞ ለበጎ ነገር የሚያነሣሱ፣ ትክክለኛውን መንገድ የሚያሳዩ፣ መርተው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ እንደ ሐዋርያው ፊልጶስ ያሉ መልካም አማካሪዎችና የልብ ወዳጆችም ብዙ ናቸው። (ዮሐ ፩፥፵፮-፶፩)
ኦርቶዶክሳዊ ሰው ከማን ጋር እንደሚውልና እንደሚያመሽ ማወቅና መገንዘብ አለበት፤ ምክንያቱም ክፉ ባልንጀራ መልካሙን ጠባይ ያጠፋል። አንድ ሰው “ማን ወዴት ያደርሰኛል?” የሚለውን ካላወቀ፣ የተጠጋውና ወዳጄ ብሎ የገመተው ሰው ወደማይጠቅም የሕይወት ጎዳና ሊመራው ይችላል፤ በመጨረሻም ከአምላኩ ሊያርቀው አልፎ ተርፎም ሊለየው ይችላል። እናታችን ሔዋን ይህንን ብታውቅ ኖሮ፣ በእባብ አካል ተሰውሮ ከመጣው አሳሳች ጠላት ጋር ባላወራችና ፈጣሪዋ በአዳም በኩል የነገራትን የፈጣሪነትና የፍጡርነትን ሕግ ገልጣ ባልተናገረች፣ እርሱም በክፉ ምክሩ ባልተተናኮላትና ከገነት ባላስወጣቸው ነበር። “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” እንዲል፡፡ (፩ኛ ቆሮ ፲፭ ፥፴፫)
ጥሩ ወዳጅን የሚፈልግ ሰው በመጀመሪያ መገንዘብ ያለበት የሰውን ክብር ነው። እኛ ሰዎች በአርአያ ሥላሴ የተፈጠርን በመሆናችን፣ ከተፈጠሩት ፍጥረታት ሁሉ ክብራችን ታላቅ ነው። የማይገባውን ያደረጉ፣ ከክብራቸው ዝቅ ብለው የወደቁ፣ ከጸጋ የተለዩት ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጅ ቢሆኑም ቅሉ አባታችን አዳም ከበደለ በኋላ በመበደል ከሚቀደሙት መላእክት ቀድሞ ንስሐ ገብቷል፤ ይህም የሰው ልጅ ያጣውን ጸጋ ዳግም እንዲያገኝ ረድቶታል። ጥፋቱን በማመን የበደለውን አምላኩን ይቅርታ በመጠየቁ ምክንያት የልቦናው መሻትና አምላክ የመሆን ፍላጎቱ ሥጋ በለበሰው አካላዊ ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጻሜውን አግኝቷል። ሥጋ ለብሶ መገለጡም የክብራችን አንዱ ማሳያ ነው።
ከፍጥረታት መካከል በሁለት ዓለም የሚኖር (በምድርና በሰማይ)፣ ሁለት ልጅነት ያለው፣ የአምላኩን ሥጋና ደም በልቶና ጠጥቶ ለዘለዓለም የሚኖር፣ የማሠርና የመፍታት ሥልጣን የተሰጠው፣ በአጠቃላይ የምሥጢራት ሁሉ ተካፋይ ከሰው ልጅ በቀር ማን አለ? እነዚህ ሁሉ የሚነግሩን የሰው ልጅን ክብርና ታላቅነት ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ ክብሩን ተገንዝቦ፣ ቦታውን አውቆ ለእርሱ የሚመጥነውን በጎ አማካሪ መምረጥና መወዳጀት ይገባዋል። ክብርን አለማወቅ የሚያመጣው የነፍስና የሥጋ ውድቀት ቀላል አይደለም። ይህንንም ለማወቅ የመጀመሪያውን የሰው ልጅ ታሪክ መመልከት ብቻ በቂ ነው።
መልካም አማካሪ የሌለው ሰው መሪ እንደሌለው መኪና ነው። መኪና መሪ ከሌለው መንገዱን ጠብቆ ወደ ትክክለኛው ቦታ መሄድ አይችልም። የሰው ልጅም ከልቡ የሚያማክረው ወዳጅ ከሌለው የሕይወትን መንገድ ሊስት፣ ባልተገባ ውሳኔ ሊጠለፍ ይችላል። በጎ መካሪ ካለ ግን በነፍስና በሥጋ የሚጠቀምበትን ምግባር ትሩፋት መሥራት ይችላል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የቅድስት ኢየሉጣና የቅዱስ ቂርቆስ ታሪክ ነው። እናትና ልጅ ሰማዕትነት ለመቀበል በሚዘጋጁበት ጊዜ፣ ቅድስት ኢየሉጣ የንጉሡ ዛቻና የውኃው ፍላት ልቧን ባሸበረ ጊዜ “እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ ከፈላ ውኃ ያድነናል” በማለት እናቱን ያጸና ለሰማዕትነትም ያበቃት እንደ በጎ አማካሪዋም እንደ አባትም እንደ ልጅም የሆነው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ነው።
ፈጣሪን ለማምለክ የሚተጉ፣ በእምነት የሚያጸኑ፣ ለበጎ ነገር የሚያነሣሱ፣ ለሊት ለማኅሌትና ለሰዓታት የሚቀሰቅሱ፣ ለኪዳን የሚያፈጥኑ፣ ለቅዳሴ የሚያነቁ፣ ገዳማቱንና አድባራቱን ለመሳለምና ታሪካቸውን ለማወቅ ከበረከታቸው ለመሳተፍ የሚያተጉ ወንድሞችንና እኅቶችን ለሕይወታችን መምረጥና መወዳጀት ይገባናል።
ሳንለምነው የሚያስፈልገንን የሚያውቅና የሚሰጥ አምላክ ለሁላችንም በጎ አማካሪና የልብ ወዳጅ ይስጠን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!