በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ”!
- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን፤
- በጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት እና
- በወልዳ ዳንዲ አቦቲ (ፍኖተ አበው ማኅበር) መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም በጃን ሜዳ የሚደረገውን ሕዝባዊ ጉባኤ አስመልክቶ በጋራ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአገራችን አንድነት ፤ ነፃነት፤ ዕድገትና ሰላም ምክንያት የሆነች፣ አገራችን በመላው ዓለም ለምትታወቅበት አገራዊ ዕሴት መሠረት የጣለች መሆኗ በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በውጭ አገር ተመራማሪዎችና ታሪክ ጸሐፊዎች የተረጋገጠ እውነታ ነው። ይሁንና አንዳንድ አካላት ማንም የማይዘነጋውና በደማቅ ቀለም የተጻፈውን ይህን ሐቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲደበዝዝ ብሎም በአዲስ እንዲተካ ዕንቅልፍ አጥተው ታሪክን የማጠልሸት፣ የነበረውን አፍርሶ ደብዛውን የማጥፋት እኵይ ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።
በተለይም በአገራችን የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ምክንያት አድርጎ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስ እና ማቃጠል፣ ንዋያተ ቅድሳትን ማቃጠል እና መዝረፍ፤ የእምነቱ ተከታይ ምእመናንን መግደል፣ መደብደብና አካል ጉዳት ማድረስ፣ ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች በማሳደድ ማፈናቀል፣ ንብረታቸውን መዝረፍ እና ማቃጠል በየጊዜው የምንሰማው የየዕለት ክሥተት እየሆነ በመምጣቱ የሚመለከታቸው የመንግሥት አከላት እና ብዙኃን መገናኛዎችም በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ዓይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ በዝምታ የሚያልፉት ሆኗል።
በአገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በክርስቲያኖች እና በንብረታቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ አጥንቶ ማቅረብ ባይቻልም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ታልፎ በተሰበሰበ መረጃ የመኖሪያ ቤታቸው እና የንግድ ድርጅቶቻቸው የወደመባቸው ፣ ከሥራ የተፈናቀሉ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ፣ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች፣ ቤተሰቦቻቸው አላግባብ ታስረውባቸው ደጋፊ የሌላቸው፣ ተገደው ሃይማኖታቸውን የቀየሩ እና በጥቃቱ ምክንያት ከአካባያቸው የተፈናቀሉትን በሺዎች የሚቈጠሩ ክርስቲያኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ተግባር መፈጸም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው።
ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋምና ወደ ነበሩት የቀደመ ኑሮ ለመመለስ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንደሚስፈልግ በባለሙያ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም በክርስቲያኖች ላይ የደረሰውን ጉዳት ሰብአዊነት የሚሰማቸው ወገኖች ሁሉ እንዲያውቁት የሚያደርግና ጥቃት የደረሰባቸውን ለማጽናናትና መልሶ ለማቋቋሚያ የሚሆን ድጋፍ ለማሰባሰብ ከላይ የተጠቀሱ ሦስት አካላት መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ ከ30ሺ በላይ ሰዎች ይታደሙበታል ተብሎ ዕቅድ የተያዘለት ሕዝባዊ ጉባኤ በጃን ሜዳ አዘጋጅተዋል።
በዕለቱ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ልዩ ልዩ ከተሞች ተመሳሳይ መርሐ ግብራት ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁንም ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
በመርሐ ግብሩ በሚሰበሰብ ድጋፍ ሊከናወኑ የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት፡
- በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች አጽራረ ቤተክርስቲያን በፈጸሙሟቸው ጥቃቶች ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ፣ ቤቶቻቸው የተቃጠለባቸው፣ ከኖሩበት ቀዬቻቸው የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ ማቋቋም፣
- ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሕይወት እንዲጠናከር ለማገዝ እና አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናትን በመመደብ የምሥጢራት ተካፋይ እንዲሆኑ፣ ስብከተ ወንጌልን እንዲጠናከር ለማድረግ እና
- ክርስቲያኖች አፍ በፈቱበት ቋንቋ የሚያገለግሏቸውን ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ሰባኪያንን ለማፍራት የሚያስችል ተግባር መፈጸም ናቸው፤
የዝግጅቱ መሪ ቃል
ምሥራቀ ፀሐይ ክርስቶስ በጥንተ ስቅለቱ መጋቢት ሃያ ሰባት በሞት በተገለጠ ፍቅር የሰውን ልጅ ሁሉ ባዳነበት ዕለት ስለሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን የተቀበሉ ክርስቲያኖችን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎት ለማሰብ፣ ክርስቲያናዊና ሰብአዊ ግዴታችንን ለመወጣት ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ የሚል ነው።
መጋቢት 04 ቀን 2012 ዓ.ም.