«በደብረ ዘይት ተቀምጦ አስተማረ» (ማር.፲፫፥፫)

ዲያቆን ደረሰ ተሾመ
መጋቢት ፲፩፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

በመዋዕለ ስብከቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሥነ ሕንፃ በትኩረት እያንዳንዱን ነገር በመመልከት ሲያደንቁ እርሱ ግን ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ፣ ከሞት በኋላ ተነሥቶ እንደሚያርግና ነገር ግን ዓለምን ለማሳለፍ ዳግም እንደሚመጣ ነገራቸው። ምሥጢሩ ቢረቅባቸው በሰፊው እንዲገልጽላቸው ጠየቁት። ጥያቄውም «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድን ነው?» የሚል ነው። (ማቴ.፳፬፥፫) ጥያቄያቸው በዋናነት ስለ ዕለትና ስለ ምልክት ነው። ይህም «መቼ» እና «ምን» የሚል ነው። «የቤተ መቅደሱ መፍረስ መቼ ይሆናል? የዓለም መጨረሻና የመምጣትህስ ምልክቱ ምንድን ነው?» አሉት።

«መቼ ይሆናል?» ላሉት «ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም» (ማቴ.፳፬፥፴፮) አላቸው። ስለ ምልክቱም እንዲህ አላቸው፤

፩. ሐሰተኞች ክርስቶሶች ይመጣሉ

በዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ ፲፫ “አውሬ” ተብሎ የተጠቀሰውና በቅዱስ ጳውሎስ «የዐመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ» የተባለው የጨለማ አበጋዝ የሆኑ ሐሰተኞ ክርስቶሶች ተነሥተዋል። በእውነተኛው ንጉሥ ክርስቶስ ዳግም መምጣት የሚደመሰሰው ሐሳዊ መሲሕ የመጨረሻው ቤተ ክርስቲያንን የሚዋጋ የታላቁ መከራ ፈጻሚና አስፈጻሚ ይሆናል። ለዚህ ነው መድኃኒታችን እስኪመጣ ድረስ እንዳንሰናከል አስቀድሞ «ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ … በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ» ሲል ያስጠነቀቀን። (ቁጥ. ፭ እና ፳፫)

በሀገራችንም በኢትዮጵያ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት “እኔ ክርስቶስ ነኝ” የሚል ሐሳዊ/ሐሰተኛ ክርስቶስ ተነሥቶ እንደነበር በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመዝግቧል። ይህ በሀገራችን ተንሥቶ የነበረው ሐሳዊ ክርስቶስ ልክ እንደ እውነተኛው ክርስቶስ ፲፪ ሐዋርያት፣ ፸፪ አርድእትና ፴፮ ቅዱሳት አንስት አስከትሎ “እኔ ክርስቶስ ነኝ” እያለ ሲንቀሳቀስ ንጉሡ አስቀርበው “አንተ ማን ነህ?” ቢሉት በድፍረት “እኔ ክርስቶስ ነኝ” አላቸው። ንጉሡም “ክርስቶስማ ከድንግል ማርያም ተወልዶ አስተምሮ፣ ተሰቅሎ፣ ዓለምን አድኖ ከሞት ተንሥቶ ዐርጓል፤ ዳግም ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል፤ አንተ ግን ማነህ?” ቢሉት “አዎ ትክክል ነው። ከዚህ ቀደም ከቤተ እስራኤል ከምትሆን ከድንግል ማርያም ተወልጀ፣ አስተምሬ፣ ተሰቅየ፣ ሙቼ፣ ተነሥቼ ዐርጌ ነበር፤ አሁን ደግሞ ጥቁሮች አፍሪካውያን ባይተዋር አደረገን እንዳይሉኝ ለጥቁሮቹ ዳግም ተወልጄ ነው” አላቸው። ንጉሡም “ሰይጣን በሰው እያደረ እንዴት ይጫወታል” ብለው በሰይፍ አስቀጡት፤ ተከታዮቹም ተበተኑ፡፡ ዛሬም በዓለም ላይ በስሙ የሚነግዱ፣ባላቸው ሥልጣን፣ ባገኙት ሹመት፣ ባፈሩት ንብረት በመመካት ራሳቸውን ከፈጣሪ ያስተካከሉ ኃይሉን የካዱ ብዙዎች ናቸው።

፪. የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ

ይህንንም ጌታችን የዳግም ምጽአቱን ምልክት ለጠየቁት ደቀ መዛሙርቱ ሁለተኛ ምልክት አድርጎ «ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና» ሲል ተናግሯታል። (ማቴ.፮-፯) ዛሬም ዓለም የሰላም አየር አጥሯታል፣መንግሥታት በመንግሥታት ላይ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ የጦርነት ወሬን ያወራል። ዳሩ ግን ቀናችን የንስሐ ጊዜ ስለሆነ አትሸበሩ፣ በምክረ ካህን በፈቃደ እግዚአብሔር ሕጉን የጠበቀ የተስፋውን ምድር እንዲወርስ አለውና።

፫. ረኃብ ይሆናል

ረኃብ የምጽአት ሦስተኛ ምልክት ሆኖ በጌታችን ለደቀ መዛሙርት ተነግሯል፤ «ረኃብም ቸነፈርም በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል» አላቸው። (ማቴ.፳፬፥፯) በዘመናችንም ሰው የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ አጥቶ መከራ የሚቀበልበት ዘመን ሆኗል።

፬. የምድር መንቀጥቀጥ ይሆናል

የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት ዓመታት በርካታ ጉዳት በተለያዩ ሀገሮች እንዳደረሰ የሚዘነጋ አይደለም። በተለያዩ ሀገሮች የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ፣ አያሌዎችን ቤት ንብረት አልባ ያደረገ የመሬት መቀጥቀጥ ተከሥቷል። በሄይቲ፣ በታይዋን፣ በቱርክ፣ በፊልፒንስ፣ ወዘተ ተከሥቷል። በተለይ በዚህ ዓመት በሀገራችን ኢትዮጵያም እንዲሁ ከቤት ንብረታቸው፣ ከርስት ጉልታቸው ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ ብዙዎች ናቸው። ይህም ለደቀ መዛሙርቱ «የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል» ተብሎ በጌታ የዓለም ፍጻሜ ምልክት ተደርጎ የተነገረው ቃል አይቀርምና እየተፈጸመ ነው። (ማቴ.፳፬፥፯)

፭. የክርስቲያኖች መከራ ይሆናል

«በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ» እንዳለ ሃይማኖተኛነት እንደ ኋላ ቀርነት፣ ከሐዲነት እንደተራማጅነትና ሥልጡንነት የሚታይበት ዘመን ላይ እንዳለን ግልጽ ነው። (ማቴ.፳፬፥፱) ይህም አመለካከት ክርስቲያኖችን ወደ ማግለልና ወደ መወንጀል ያደርሳል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በጊዜውም ያለጊዜውም ጽና›› እንዳለ በጽናት መቆም ይጠይቃል፡፡ (፪ኛ ጢሞ.፬፥፪)

በእንዲህ ዓይነት የመከራ ዘመን የክርስቶስ ተቃዋሚዎች በክርስቲያኖች ላይ ከሚያመጡት መከራ የበለጠ የክርስቲያኖች እርስ በርስ መከዳዳት ጭንቁን ያከፋዋል፤ መከራውን መራራ ያደርገዋል፡፡ «በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ» ተብሎ በጌታ እንደተነገረ የክርስቶስ ጠላቶች ሆን ብለው በዓላማ በክርስቲያኖች መካከል መከዳዳትን፣ ጸብ ክርክርን፣ ጦርነትን በመፍጠር ክርስቲያኖችን ለመከራ እና ለግፍ እየዳረጉ ይገኛሉ። (ማቴ.፳፬፥፲)

፮. ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ

በዲያብሎስ መንፈስ ምትሐታዊ ምልክትን እያሳዩ አይቻላቸውም እንጂ ቢቻላቸው የተመረጡትን ሳይቀር የሚያስቱ “ነቢያት ነን” የሚሉ ብዙዎች ደፋሮች እንዲነሡ ጌታችን ስድስተኛ የምጽአቱ ምልክት አድርጎ ነገራቸው። በአሁኑ ዘመን በሀገራችንም ነቢያት ነን የሚሉ አጭበርባሪዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። ለጊዜ እያታለሉ ክህደትን እያሠራጨ ቢሆንም ቅሉ፣እንደ ጉም ተነው እንደ አመድ በነው መጥፋታቸው አይቀርምና ክርስቲያኖች ከሐሰተኞች ነቢያት የሐሰት ትምህርት መጠበቅ አለባቸው።

በነቢዩ ኤልያስ፣ በነቢዩ ኤልሳዕ ስም እያጭበረበሩና እየዋሹ በምትሐታዊ አሠርራር የሚያስቱ ሐሰተኞች እንደሚነሡ ሌላው የዳግም ምጽአቱ ምልክት ሆኖ «ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ …ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ … እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ ተብሎ በጥብቅ ተነግሯል። (ማቴ ፳፬ ቁጥ.፲፩፥ ፳፬ እና ፳፮) እንግዲህ በዘመናችን በሀገራችን ሆነ በሌላው ዓለም በነቢይነትና በሰባኪነት ስም የሚደረገውን የንግድና የርኩሰት እንቅስቃሴ በማስተዋል መከታተልና ከከሕደታቸው መጠበቅ ያስፈልጋል።

፯. ፍቅር ትቀዘቅዛለች

ሌላውና አሳዛኙ ጉዳይ በሰው መካከል የፍቅር መቀዝቀዝ ነው። «ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው» ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው። ፍቅር የመልካምና በጎ ነገር ሁሉ መገኛና ምንጭ ነው፡፡ የሰው ልጅ ፍቅርን ማጥፋት እና ማጣት የሌለበት ሀብቱ ነው። አሁንም «ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች» በማለት እንደተናገረው በሰው ልጆች መካከል ፍቅር ጠፍቷል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፲፪)

፰. ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል

የወንጌል ለዓለም መዳረስ ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱ ምልክቶች ሆነው ከተሰጡት አንዱ ነው። በፍርድ ቀን (በመጫረሻው ጊዜ) በክርስቶስ አምኖ እና እምነቱን በሥራ ግልጾ ስለመኖር ሲጠየቅ አልሰማሁም አላየሁም አላወቅኩም በማለት አያመልጥም «ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል» እንዳለ። (ማቴ. ፳፬፥ ፲፬) ወንጌል በሁሉም ቤት ይሰበካል። መስማትን ከተግባር አስተባብሮ ወንጌልን መፈጸም ርስት እንዲያሰጥ፣ሰምቶ መተግበር ዋጋ አለው። የምጽአት ነገር እንደምንድን ነው ቢሉ እንደመብረቅ እንደ ሌባ አላቸው።

ፍጥነቱ፦ ፍጥነቱ እንደ መብረቅ ነው። «መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል» ተብሏልና። (ማቴ.፳፬፥፳፯)

የቀኑ መምጣት፦ (መድረስ) እንደ ሌባ ነው። ያን ግን ዕወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፣ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር፤ … የሰው ልጅም በማታስቡበት ሰዓት ይመጣል፡፡ (ቁጥ. ፵፫-፵፬)
የኖኅ ዘመንም እንደዚሁ ባልታሰበ ሰዓት እንደሚመጣ ማስገንዚያ ሆኖ በጌታችን ቀርቧል። (ከቁጥ. ፴፯-፴፱)።

“እንዴት እንጠብቀው? እንዴት እንዘጋጅ?” ቢሉት ተጠንቀቁ፦ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ!” (ቁጥ.፬)። “ንቁ፦ጌታችሁ በምን ሰዓት እንደመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ (ቁጥ. ፵፪)። ተማሩ ዕወቁ፦ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ” (ቁጥ. ፴፫)። አትደንግጡ፦ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ። ትጉና ጸልዩ፦ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ። ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፦ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና (፵፬)። ጽኑ፦ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል (ቁጥ.፲፫) አላቸው። “ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” የሚለው የጌታችን ትእዛዝ የቤተ ክርስቲያን የሁልጊዜም መልእክት ነው!
• በጽኑ እምነት መኖር “እግዚአብሔርን ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም” (ዕብ.፲፮፥፮) ተብሎ በቅዱሱ መጽሐፍ እንደጻፈ።
• በንስሐ ሕይወት መመላለስ
• ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን በመቀበል
• በፍቅር ሕይወት በመመላለስ
• በተስፋ በመኖር ተዘጋጅተን ልንጠብቀው ያስፈልጋል።

የአብ ልጅ የድንግል ማርያም ልጅ የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስም በታላቅና እጅግ አስፈሪ በሆነ መለኮታዊ ግርማ የብዙ ብዙ በሚሆኑ እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት ታጅቦ ይመጣል፡፡ (ዘካ. ፲፬፥ ፮፤ ማቴ. ፳፭፥ ፴፩፤ ፩ኛ ተሰ. ፬፥ ፲፮)

በዚያን ጊዜ በፊቱ ችሎ የሚቆም ማን ይሆን? (ኢዩ. ፪፥ ፲፩) አመጣጡም እንደቀደመው ከሐና ወደ ቀያፋ ከዚያም ወደ ጲላጦስ አደባባይ እያንገላቱ ሲወስዱት ዝም እንዳለ በዚህ ዓይነት አመጣጥ አይደለም፡፡ የሚመጣው በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ መለኮታዊ ግርማና ክብር ነው፡፡ (መዝ. ፵፱፥ ፪) መጥቶም ዝም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል፤ ኃጥአንን ከፊቱ ጠራርጎ ወደ ገሃነመ እሳት የሚጨምር ጥቅል አውሎ ነፋስም አለ፡፡ (ማቴ. ፳፬፥ ፴፤ ራእይ ፩፥ ፯)
እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥአንን በግራው ለይቶ ያቆማቸዋል፡፡ በቀኙ ያሉትን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ ወደ አባታችሁ መንግሥተ ሰማያት ግቡ፡፡” ብሎ ለዘለዓለም ሕይወት ይጠራቸዋል፡፡ በግራው ያሉትን ደግሞ እጅግ በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ የቁጣ ቃል “እናንተ ርጉማን ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” ይላቸዋል፡፡

ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ትወርዳለች ማለትም ለምእመናን ትሰጣለች፡፡ ምእመናንም ርስት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፣ ብርሃንን ተጎናጽፈው ለዘለዓለም በደስታ ይኖራሉ፡፡ (ማቴ. ፳፭፥ ፴፩-፵፮፤ ራእይ ፳፩፥ ፩-፪)፡፡

ኦርቶዶክሳውያን! ነቢዩ ኤርምያስ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- በመንገድ ላይ ቁሙ፤ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች ዕወቁ፤ በእርስዋም ላይ ሂዱ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” በማለት እንደተናገረው በቀደመችው በመልካሚቱ የሕይወትና የጽድቅ መንገድ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነታችን እስከ መጨረሻው ድረስ ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡ (ት.ኤር. ፮፥ ፲፮)

እንግዲህ እኛን በቀኙ ያቆመን ዘንድ የአባቴ ቡሩካን ኑ! ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ የሚለውን የሕይወት ቃል ያሰማን ዘንድ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ጾመ ድጓ)

እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ፡፡ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ፡፡ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን:: ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር፡፡ ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ፡፡ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእምኅበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚአ ለሰንበት፡፡

ትርጉም፡ ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ ብዙዎች “እኔ ክርስቶስ ነኝ” እያሉ በስሜ ይመጣሉ ፤ እስከ መጨረሻ የጸና እርሱ ይድናል፡፡ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማያትና የምድር ኃይላት ሁሉ ይናወጣሉ፡፡ ያን ጊዜ በምድር ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለቅሳሉ አላችው፡፡ ጌታችንም ራሱ እንደተናገረ በትእዛዝ፣ በመላእክትም አለቃ ድምፅና በመለከት ድምፅ ከሰማይ ወደ ምድር ይመጣል፡፡ እርሱ የሕይወት መገኛ ነውና ያን ጊዜ በኃጢአት ከመሞት ይራራልን፡፡

መልእክታት

ምንባብ አንድ (፩ኛ ተሰሎንቄ ፬ ቊ. ፲፫-ፍጻሜ)
ምንባብ ሁለት (፪ኛ ጴጥ. ፫ ቊ. ፯-፲፭)
ምንባብ ሦስት (ሐዋ. ፳፬ ቊ. ፩-፳፪)
ወንጌል (ማቴ. ፳፬ ቊ. ፩-፴፮)
ቅዳሴ: ዘአትናቴዎስ

ምስባክ (መዝ.፵፱ ቊ. ፪-፫)

«እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ
ወአምላክነሂ ኢያረምም፤
እሳት ይነድድ ቅድሜሁ።»

ትርጒም፤ «እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፡፡
አምላካችን ዝም አይልም፡፡
እሳት በፊቱ ይነዳል፡፡»

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !